Saturday, 21 July 2018 13:11

የኮምፒዩተር ሳይንስ ተመራቂዎች የቴክኖሎጂ ፈጠራ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 በቅርቡ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት 5ኛው ዙር ICT ኤክስፖ በሚሊኒየም አዳራሽ መቅረቡ የሚታወስ ሲሆን 67
በመቶ ክፍሏ በኢትዮጵያውያን የተሰራችውን “ሶፊያ” የተሰኘች ሮቦት ጨምሮ በርካታ የፈጠራ ስራዎች ለእይታ ቀርበዋል፡፡ ከነዚህ ፈጠራዎች መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዩተር ሳይንስ ዲፓርትመንት ተመራቂዎች፣ ለመመረቂያ የሰሩት የቴክኖሎጂ ውጤት
ይጠቀሳል፡፡ ለመሆኑ ተመራቂዎቹ የሰሩት ቴክኖሎጂ ምንድነው? ለምንስ ነው የሚያገለግለው? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣
ከተመራቂዎቹ ተወካይ ሚኪያስ ጌታቸው ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች፡፡


    እስቲ በ5ኛው የICT ኤክስፖ ላይ ስላቀረባችሁት የፈጠራ አይነት አስረዳኝ …
እኛ በዩኒቨርሲቲው የቆየን የኮምፒዩተር ሳይንስ ተመራቂዎች፣ፕሮጀክቱን የሰራነው ለመመረቂያችን ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ተመርጦ ለICT ኤክስፖ ቀርቧል። የሰራነው ፕሮጀክት “ካርአውቶሜሽን” ይባላል፡፡ ይህ ስራ በዋናነት በቁልፍ ልትከውኛቸው የምትችያቸውን ስራዎች በስማርት የስልክ ቀፎም ይሁን በታብሌት ካልሆነም በዴስክቶፕ ያለ ምንም ዳታና ካርድ መሙላት ሳያስፈልግ መቆጣጠር ትችያለሽ ማለት ነው፡፡
መቆጣጠር ሲባል ምን ምን ክዋኔዎችን ያካትታል?
ለምሳሌ መኪና መክፈት ወይም መዝጋት፣ መኪና ማስነሳት ኤሲ ማብራት፣ መብራቶቹን ማብራት ማጥፋትና ሌሎችንም ስራዎች ከመኪናሽ ውጭ ሆነሽ እንድትሰሪ ያስችልሻል፡፡ ይህ አፕሊኬሽን፤ ዩዘርኔም እና ፓስወርድ ካለሽ፣ ያልኩሽን ስራዎች ከመኪና ውጭ ሆነሽ መከወን ትችያለሽ፡፡
ስንት ሆናችሁ ነው የሰራችሁት? ሀሳቡስ እንዴት መጣላችሁ? አጠቃላይ ሂደቱስ ምን ይመስላል?
የሰራነው ሦስት ሆነን ነው፡፡ እኔ ናሆም ኪዳነማሪያምና መላኩ ሀብቱ ሆነን ማለት ነው። መጀመሪያ በአድቫይዘር ሶስት ፕሮጀክት እንድታቀርቢ ትጠየቂያለሽ፣ ከሦስቱ አንዱ ተመርጦ ነው የምትሰሪው። የሚገርምሽ እኛ እንደውም ይሄ ፕሮጀክት ይመረጣል ብለን አላሰብንም፡፡ ሌሎች ርዕሶች ላይ ነበር ያተኮርነው እናም በሦስተኛ ደረጃ ነበር ያቀረብነው፡፡ ነገር ግን በአጋጣሚ ተመርጦ በኤክስፖ ቀርቦ እስከመታየት ደርሷል፡፡ እንዴት ሀሳቡ መጣላችሁ ላልሺው፣ ያው የመኪና ደህንነትና ቁጥጥር ሥራ ብዙም ስለማንጠቀም መኪኖች ይሰረቃሉ። በተለይ አሁን አሁን የሚሰሩት ዘመናዊ መኪኖች ካልሆኑ የቀድሞዎቹ ብዙ ነገር ስለሚጎድላቸው ያንን ክፍተት ለመሙላት ነው ሀሳቡን ያመነጨነው፡፡
በጣም ቴክኒካል ቢሆንም ስለ አሰራሩና ቴክኖሎጂውን ለመስራት ምን ምን ነገሮች እንደተጠቀማችሁ ብትነግረን …
ለምሳሌ ስለ ኢንትሩደር ዲቴክሽን ልንገርሽ። መጀመሪያ 270 ዲግሪ የምታሳይ ካሜራ ውስጥ ኢንስቶል እናደርግና፣ ካሜራው ቀንም ማታም ላይ ማየት ይችላል፡፡ ካሜራው ሌባ መጥቶ ስፖኪዮም ይሁን ከመኪና ውስጥ እቃ ሊሰርቅ ቢሞክር፣ “ሞሽን ዲቴክሽን” የሚባል ሲስተም ስላለው፣ ይህ ሲስተም የሌባውን እንቅስቃሴ ዲቴክት አድርጎ፣ ጥቆማ (ኖቲፊኬሽን) ወደ ስልካችን ይልክልናል፡፡ መኪናው ያለበት አካባቢ ከሆንን፣ ወደ መኪናው በመሄድ መኪናችንን ከሌባ ማስጣል እንችላለን፡፡ በርቀት ላይም ብንሆን፣ ቢያንስ በማን እንዴት እንደተሰረቀ መረጃ ያስቀምጥልናል ማለት ነው፡፡ ያንን ሪከርድ የተደረገ ማስረጃ ከሲስተሙ ላይ በሜሞሪ ካርድ ወስዶ፣ ለሚመለከተው የህግ አካል ማስረከብ ይቻላል፡፡
እኛ አገር በዋናነት ችግር የሆነው የመኪና የውጭ አካልና ከውስጥ ላፕቶፕን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶች ላይ የሚፈጸም ስርቆት ነው፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ  ይህን ችግር የሚያስቀር ይመስላልና ምን ያህል ልትገፉበት አስባችኋል?
በአይሲቲ ኤክስፖም ብዙ ሰዎች ስራችንን እያዩ ባዘጋጀነው ፎርም ላይ አድራሻቸውን እንዲያሰፍሩና ሄደን ባሉበት እንደምንገጥም ነግረናቸው ነበር። የእኛንም አድራሻ ወስደው፣ በርካታ ሰዎች ሲደውሉልን ነበር፡፡ ይሄ የችግሩ ስፋት ምን ያህል እንደሆነ ያሳያል፡፡ ብዙ ሰዎችም ስፖኪዮና መሰል እቃዎች እየተሰረቁባቸው መቸገራቸውን በስፋት ገልፀውልናል፡፡ የእኛም ዋናው አላማችን፣ “አውቶሜሽን እና ሴኪዩሪቲ” ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን የመኪና ቁልፍ ይቀረፃል፡፡ RF ሲግናል የምትባል ናት ቁልፏ። በዚህ ሲግናል ማንኛውም ሰው በቀላሉ መኪናሽን ከፍቶም ሆነ የውጭ ስፖኪዮሽን ሰርቆ ይሄዳል፡፡ የእኛ ቴክኖሎጂ ግን ከምንጠቀመው ቴክኖሎጂ በተጨማሪ ዩዘር ኔምሽንና ፓስወርድሽን ሌላ ሰው ካላወቀ በፍፁም አይከፍተውም፡፡
የእናንተ ቴክኖሎጂ ምን ያህል ርቀት ድረስ ይሰራል?
ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ለጊዜው የእኛ ሲስተም በዋይፋይ በ300 ሜትር ርቀት ድረስ ነው የሚሰራው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ወደ ውጭ ስለምሄድ፣ ሲስተሙን መጠቀም የምፈልገው በኢንተርኔት ነው ካለ በቀላሉ የምትጫን ተጨማሪ ሞጁል ስላለችን፣ እሷን ሞጁል ስንጭንለት፣አገልግሎቱን ማግኘት ይችላል፡፡ ሰውየው አሜሪካም ሆነ ካናዳ፣ ብቻ ኢንተርኔት ያለበት ሆኖ አጠቃላይ የመኪናውን ሁኔታ መቆጣጠር ይችላል፡፡ የኛን ሲስተም ልዩ የሚያደርገው ካሉን አገልግሎቶች የመረጥሽውን መጠቀም የሚያስችል ነው፡፡ ይሄ ማለት የደህንነት ሲስተሙን ተጠቅሜ፣ መኪናዬን መጠበቅ ብቻ እፈልጋለሁ ካልሽ፤ የደህንነቱን፣ አውቶሜሽኑን ካልሽም አውቶሜሽኑን፤ ሁለቱንም እፈልጋለሁ ካልሽም፣ ሁሉንም አገልግሎት መጠቀም የሚያስችል የተለየ አሰራር ነው ያለን፡፡ አንዳንድ በጣም ዘመናዊ መኪኖች የኋላ ማርሽ ሲያስገቡና ወደ ኋላ ሲሄዱ፣ የግራና የቀኙን ካልኩሌት አድርጎ ምን ያህል እንደተጠጋ ይገልፅላቸዋል፡፡ ይሄ ሰው የእኛን የፓርኪንግ ኤይድ አይፈልግም ማለት ነው፤ የሚፈልገው የደህንነቱን ሲስተም ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ያንን የሚፈልገውን ብቻ እንሰራለታለን እንጂ ያለንን አገልግሎት ሁሉ ደንበኞች እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ አሰራር የለንም፡፡ እኛ ግን በመኪናቸው ይሄ አገልግሎት ለሌላቸው፣ ፓርኪንግ ኤይድ ፕሮክሲሚቲ ሴንሰር እና IR ሴንሰር አለን፡፡ እነሱን ከኋላ በመጫን ምን ያህል ርቀት እንደተጠጋ ይነግረዋል ማለት ነው፡፡
“አውቶሜትድ ቴምፕሬቸር ሬጉሌሽን” የተባለው ሲስተማችንም ሌላው ፈጠራችን ነው፡፡ ይህ ሲስተም ለምሳሌ ኤሲውን ከፍተን ረስተነው ልንሄድ እንችላለን ወይም ስንከፍተው በጣም ሙቅ አሊያም በጣም ቀዝቃዛ አድርገን ሊሆን ይችላል፡፡ በጣም አዳዲሶቹ መኪኖች ካልሆኑ በስተቀር የቆዩት ቴምፕሬቸሩን በምትፈልጊው መጠን አያመጣጥኑም፡፡ የእኛ ፈጠራ ግን የምትፈልጊውን የሙቀትና የቅዝቃዜ መጠን በዲግሪ ሴልሺየስ ታስገቢያለሽ፡፡ ለምሳሌ የምትፈልጊው 25 ወይም 27 ዲግሪ ሴልሺየስ ከሆነ፣ ቁጥሩን ስታስገቢለት ሴንስ እያደረገ፣ ሙቀትና ቅዝቃዜውን አስተካክሎ ያስቀምጥልሻል፡፡ በዚህ መሰረት ቀኑን ሙሉ ኤሲው አይከፈትም፣ ነዳጅም አይጨርስም፡፡ የመኪናውም ቴምፕሬቸር ከፍና ዝቅ እያለ አያስቸግርሽም ማለት ነው፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፣ “አውቶሜትድ ካር ስታርት” የተባለም ሲስተም አለን፡፡ አንድ ሰው መኪናውን አቁሞ ከአዲስ አበባ ሊወጣ ይችላል፡፡ ሲወጣ ታዲያ የመኪናውን ቁልፍ ለሌላ ሰው ይሰጥና የመኪናዬ ባትሪ እንዳይሞት እየከፈትክ አስነሳልኝ ብሎ ይሄዳል፡፡ ሰው ከሌለው ባትሪውን ነቅሎ አውጥቶ ነው የሚያስቀምጠው፤ ይሄ ለመኪና ብልሽት ይዳርጋል። የእኛ ሲስተም ግን በየቀኑ ለምን ያህል ጊዜ፣ ለስንት ደቂቃ ልነሳ የሚለው ላይ በቀን ሁለት ጊዜ ለአምስት ደቂቃ እየተነሳ ራሱን አሙቆ ይጠፋል፤ መኪናሽ ወርም ቆየሽ ሁለት ወር ጤናማ ሆኖ ይጠብቅሻል። ባትሪውም ጤነኛ ሆኖ ይቆያል ማለት ነው፡፡ “ዩዘር ማናጀር” የሚባል አለን፡፡ ይህ ሲስተም ደግሞ አንቺ መኪናሽን በዩዘርኔም እና በፓስወርድ ስትቆጣጠሪ፣ ካንቺ ውጭ ያለ አንድ ሰው እንዲያንቀሳቅሰው ወይም እንዲጠቀመው ብትፈልጊ፣ ስልክሽን ለዛ ሰው መስጠት አይጠበቅብሽም፡፡ ለምሳሌ ልጅሽ መኪናውን እንዲጠቀመው ከፈለግሽ፣ የልጅሽን ዩዘርኔም እና ፓስወርድ ታስመዘግቢያለሽ፡፡ ይህም ሆኖ ለልጅሽ የፈቀድሽው የመኪናውን በር እንዲከፍትና እንዲዘጋ ብቻ ይሆናል፡፡ እስከ መንዳት ፈቃድ ልትሰጪውም ትችያለሽ፡፡ ልጅሽ በተሰጠው ዩዘርኔም እና ፓስወርድ በራሱ ስልክ ገብቶ የተፈቀደለትን ብቻ በመኪናው ላይ ይከውናል፡፡ ለምሳሌ የመኪናውን በር መዝጋትና መክፈት ብቻ ፈቅደሽለት ከፍቶ ገብቶ ልንዳው ቢል ግን አይችልም፤ አልፈቀድሽማ!! የዩዘር ማናጀሩ ዋና ስራም ይህንን ይመስላል፡፡
ለምሳሌ መኪናዬን የምቆጣጠርበትን ቴክኖሎጂ የያዘው ስልኬ ቢሰበር ወይም ቢጠፋ ምን ሊገጥመኝ ይችላል?
ይህ ቴክኖሎጂ በዘመነ መንገድ መኪናን ከዝርፊያ ለመጠበቅ በተሻለ ቴክኖሎጂ አውቶሜትድ ለማድረግ የሚረዳ ቢሆንም የመኪና ቁልፍ ቀረ ማለት አይደለም፡፡ ስለሆነም ስልክሽ እክል ሲገጥመው ወዲያው ቁልፍሽን ትጠቀሚያለሽ፡፡ ይሄኛውን ቴክኖሎጂ እየተጠቀምሽ በመሆኑ ቁልፍ ይዘሽ ባትወጪ በቀላሉ አጠገብሽ ባገኘሽው ሰው ስማርት ስልክ ዩዘርኔምና ፓስዎርድሽን አስገብተሸ መኪናሽን ማስነሳት ትችያለሽ፡፡
በአይሲቲ ኤክስፖ ላይ ይህን ቴክኖሎጂ ይዛችሁ ስትቀርቡ፣ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም ሆነ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ያገኛችሁት የማበረታቻ ሽልማት ወይም ሌሎች ዕድሎች አሉ ?…
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮምፒዩተር ሳይንስ ዲፓርትመንት የእውቅና ሰርተፍኬት አግኝተናል፡፡ ከዛ ባለፈ አብረውን ለመስራት ፍላጎት ያሳዩ የተለያዩ አካላት አግኝተን፣ ከየትኛው ጋር እንስራ በሚለው ላይ ለመወሰን ገና እየተወያየን ነው፡፡ ብዙ ሰው ጎብኝቶናል። ይሄ ለእኛ ትልቅ ነገር ነው፡፡
የፈጠራ መብት ባለቤትነት  አግኝታችኋል?
እኛ ለአዕምሮአዊ ንብረት ጽ/ቤት አመልክተን እስኪመዘገብልን እየጠበቅን ነው፡፡ ጽ/ቤቱም ይህ ፈጠራ ከዚህ በፊት በአገራችን ተሰርቷል ወይስ የመጀመሪያው ነው የሚለውን አጣርቶ ይመዘግበናል ብለን እናምናለን፡፡
ይህንን ጅምራችሁን የት ለማድረስ ነው ህልማችሁ?
በአሁን ሰዓት ከጓደኞቼ ጋር “ኢትዮ አውቶሜሽንስ” የተሰኘ አዲስ ኩባንያ መስርተናል፡፡ ለጊዜው በመኪና ደህንነት አውቶሜሽን ብንጀምርም በቀጣይ በመኖሪያ ቤቶችና በኢንዱስትሪዎች ላይ ለመስራት እቅድ አለን። በአሁኑ ወቅት በቤታቸውና በኢንዱስትሪያቸው ላይ የእኛ አገልግሎት እንዲገጠምላቸው ፍላጎት ያደረባቸው የተወሰኑ ሰዎች አግኝተናል፡፡ በተጨማሪም ፋይናንስ አውጥተው አብረውን መስራት ለሚፈልጉም በራችን ክፍት ነው፡፡
እስኪ ስለ ራስህ ደግሞ ትንሽ ንገረኝ --- ወደ ቴክኖሎጂው እንዴት ተሳብክ?
የተማርኩት “ኢትዮፓረንትስ” የተባለ ሃይስኩል ነው፡፡ ከዚያ ጨርሼ ስወጣ አባቴ የፈለጋችሁትን መርጣችሁ መማር ትችላላችሁ አለ፤እናቴ ግን ሜዲስን እንድማር ነበር የምትፈልገው፡፡ እኔም የመጀመሪያ ምርጫዬ ሜዲስን መማር ነበር፡፡ ያም ሆኖ ኮምፒዩተር ሳይንስ ላይ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ከዚያ በኮምፒዩተር ሳይንስ ከአዲስ አበባ አራት ኪሎ ካምፓስ ለመጨረስ በቅቻለሁ ማለት ነው፡፡ ለቤቴ የመጀመሪያ ልጅ ስሆን አንድ ታናሽ ወንድም አለኝ፤ ወደ 12ኛ ክፍል አልፏል፤ ሜካኒካል ኢንጂነር ነው መሆን የሚፈልገው። አባታችንም ሜካኒካል ኢንጂነር ነው፡፡ የአባቴ ተፅዕኖ በወንድሜ ላይ ያረፈ ይመስለኛል፡፡

Read 2000 times