Saturday, 21 July 2018 13:22

የኔልሰን ማንዴላ 100ኛ ዓመት ልደት ተከበረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የጸረ-አፓርታይድ ታጋዩና የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ 100ኛ ዓመት የልደት በአል ባለፈው ረቡዕ በደቡብ አፍሪካና በሌሎች አገራት በተለያዩ ዝግጅቶች መከበሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ደቡብ አፍሪካውያን ከአምስት አመታት በፊት ከዚህ አለም በሞት የተለዩትን ኔልሰን ማንዴላን መልካም ስራዎችና አፓርታይድን በመታገል ያበረከቱትን ታሪካዊ አስተዋጽኦ በመዘከርና የበጎ አድራጎት ስራዎችን በማከናወን የ100ኛ ዓመት የልደት በአላቸውን ማክበራቸው ተነግሯል፡፡
ያም ሆኖ ግን፣ ጥቂት ደቡብ አፍሪካውያን ማንዴላ የታገሉለት የቀለም ልዩነትና ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል ለዘመናት ተሻግሮ አሁንም ድረስ ስር ሰድዷል በሚል የማንዴላን ስኬት ጥያቄ ውስጥ መክተታቸውንና የልደት በአሉ በመከበሩ ደስተኞች አለመሆናቸውን ሲገልጹ መደመጣቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤የማንዴላን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ከ44 የተለያዩ አገራት ለተውጣጡና በኦባማ ፋውንዴሽን የአፍሪካ ሊደርሺፕ ፕሮግራም ለታቀፉ 200 ወጣት አፍሪካውያን መሪዎች በጆሃንስበርግ አነቃቂና የማንዴላን ታላቅነት የሚዘክር ንግግር ማድረጋቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 1677 times