Sunday, 22 July 2018 00:00

ሰሜን ኮርያና ኤርትራ በዘመናዊ ባርነት አለምን ይመራሉ ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 - 9 ሚሊዮን አፍሪካውያን በከፋ ባርነት ውስጥ ይኖራሉ
  - በአለማችን ባለፉት 19 ወራት 40ሚ. ሰዎች የባርነት ሰለባ ሆነዋል

    ሰሜን ኮርያና ኤርትራ በርካታ ዜጎች ለዘመናዊ ባርነት ተዳርገው የሚኖሩባቸው ቀዳሚዎቹ የአለማችን አገራት መሆናቸውንና ባለፉት 2 አመታት በመላው አለም ከ40 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎች የዘመናዊ ባርነት ሰለባዎች መሆናቸውን ዎክ ፍሪ ፋውንዴሽን የተባለው አለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገው የ2018 የፈረንጆች አመት አለማቀፍ የባርነት ደረጃ ሁኔታ አመላካች ሪፖርት፣ ሰሜን ኮርያ በቀዳሚነት የተቀመጠች ሲሆን ከአገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 10 በመቶ የሚሆነው የዘመናዊ ባርነት ሰለባ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በአመቱ የተቋሙ ሪፖርት ከአለማችን አገራት ሁለተኛ ደረጃን በያዘቺው ኤርትራም፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በብሔራዊ ውትድርና ግዳጅና በሌሎች የጉልበት ብዝበዛዎች ለአስርት አመታት የከፋ የባርነት ኑሮን ሲገፉ ኖረዋል መባሉን የዘገበው ሮይተርስ፤ በሪፖርቱ ሶስተኛ ደረጃን የያዘቺው ብሩንዲ መሆኗንም ጠቁሟል፡፡
በሶስቱም አገራት መንግስታት ዜጎቻቸውን ለጉልበት ብዝበዛና ለሌሎች የዘመናዊ ባርነት ጭቆናዎችና ድርጊቶች እየዳረጉ እንደሚገኙ የጠቆመው የሮይተርስ ዘገባ፤ በመላው አፍሪካ ከ9 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን አስከፊ የባርነት ኑሮን በመግፋት ላይ እንደሚገኙም በሪፖርቱ መጠቀሱንም አመልክቷል፡፡
በተለያዩ አለማችን አገራት የሚከሰቱ ግጭቶችና የአገራት መንግስታት የሚያሳድሩት ጭቆና በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዜጎች ለከፋ ዘመናዊ ባርነት መዳረጋቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ዘመናዊ ባርነት ተስፋፍቶባቸዋል በሚል ከጠቀሳቸው ሌሎች አገራትም ውስጥ መካከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ አፍጋኒስታን፣ ደቡብ ሱዳንና ፓኪስታን ይገኙበታል፡፡
እ.ኤ.አ ከ2016 አንስቶ ባለው ጊዜ ውስጥ በመላው አለም ከ40 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎች የዘመናዊ ባርነት ሰለባዎች ሆነዋል ሲሉ ዎክ ፍሪ ፋውንዴሽንና አለማቀፉ የስራ ድርጅት ማስታወቃቸውን የዘገበው ሮይተርስ፤ ተቋሙ እ.ኤ.አ በ2016 ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ከአለማችን አገራት መካከል በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች የዘመናዊ ባርነት ሰለባዎች የሆኑባት ቀዳሚዋ አገር ህንድ እንደነበረችና በአመቱ 18.4 ሚሊዮን ያህል ህንዳውያን የዘመናዊ ባርነት ሰለቦች እንደነበሩም አስታውሷል፡፡

Read 3157 times