Saturday, 28 July 2018 15:31

ቤተ ክርስቲያኒቱ ሲኖዶሳዊ አንድነቷ መመለሱን አበሠረች

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 በልዩነቱ ያዘኑ ምእመናንን ይቅርታ ለመጠየቅ ተወስኗል
          “ዋነኛው የጥላቻ ምሶሶ በይፋ ተናደ”/ጠቅላይ ሚኒስትሩ/


    ላለፉት 26 ዓመታት በተፈጠረ አለመግባባት ለሁለት ተከፍሎ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ አንድነቱ እንዲመለስ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱ በሁለት ፓትርያርኮች እንድትመራ ከስምምነት ተደረሰ፡፡
ካለፈው ሳምንት እሑድ ጀምሮ በአሜሪካን ዋሽንግተን ዲሲ የተካሔደው የኢትዮጵያውና የአሜሪካኑ ሲኖዶሶች የሰላም ጉባኤ በዕርቅ መቋጨቱን ተከትሎ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት አንድነቷን ከትላንት በስቲያ ሐምሌ 19 ቀን ዐውጃለች፡፡
4ኛው ፓትርርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በ1984 ዓ.ም. በፖለቲካዊ ግፊትና ጫና መንበራቸውን ለቀው ከተወሰኑ ብፁዓን አባቶች ጋራ መሰደዳቸውን ተከትሎ፣ የአሜሪካው የስደት ሲኖዶስ እና የኢትዮጵያው የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ በሚል በተፈጠረ መከፋፈል ቀኖና እንደተጣሰና አስተዳደራዊ ልዩነት እንደተከሠተ ተገልጿል፡፡
ከሁለቱ ሲኖዶሶች የተወከሉ ስድስት ልኡካን አባቶች፣ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 16 ቀን ያለአደራዳሪ በቀጥታ ባካሔዱት የአጭር ጊዜ ውይይት፣ መከፋፈሉ እንዲያበቃ ከስምምነት መድረሳቸው ተበሥሯል፡፡ ላለፉት 26 ዓመታት የዘለቀው ልዩነት አብቅቶ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እየተቀበለች እንደምትመራ ከትላንት በስቲያ ሐምሌ 19 ቀን፣ በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በዚሁ ባለ6 ነጥቦች መግለጫ መሠረት፣ ላለፉት 26 ዓመታት በስደት በአሜሪካ የኖሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በፓትርያርክ ማዕርግ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በመንበረ ፓትርያርኩ በሚዘጋጅላቸው ለክብራቸው የሚመጥን ማረፊያ ይቀመጣሉ፡፡ሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያርኮች የሥራ ድርሻ እንደሚኖራቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በጸሎትና በቡራኬ መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጣሉ፤ 6ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱ አቡነ ማትያስ ደግሞ፣ የአስተዳደሩን (የቢሮውን) ሥራ እያከናወኑ አጠቃላይ አመራር ይሰጣሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሁለቱም ፓትርያርኮች እኩል የአባትነት ክብር የምትሰጥ ሲሆን፤ አገልግሎቷን በምታከናውንባቸው የዓለም ክፍሎች ሁሉ የሁለቱንም ስም በቅደም ተከተል ትጠራለች፡፡
በሁለቱም ሲኖዶሶች በኩል ቀኖናዊ ጥሰት እንደተፈጸመና ሁለተኛው ፓትርያርክ ሰማዕተ ጽድቅ አቡነ ቴዎፍሎስ ለሞት ተላልፈው ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ መሰል ስሕተቶች በተደጋጋሚ መታየታቸውን መግለጫው አውስቷል፡፡ ይህም፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ከጊዜው ጋራ አብሮ ለመሔድ በሚል የቤተ ክርስቲያኒቱን መብት የማስጠበቅ ሓላፊነቱን ባለመወጣቱ የተከሠተ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ ጥፋቱና የዓመታት ልዩነቱ የምእመናኑን ልብ በሐዘን እንደሰበረው ጠቅሶ፣ ያለፉትንም ኾነ በሕይወት ያሉትን በጋራ ይቅርታ ለመጠየቅ ልኡካኑ በጋራ መወሰናቸውን አስታውቋል፡፡ ከሁለቱ ሲኖዶስ መዋሐድ በኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከዳግም ክፍፍል ለመጠበቅና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ቅዱስ ሲኖዶሱ ሕጉንና ሥርዐቱን ያገናዘበ ደንብ እንዲወጣ ልኡካኑ መስማማታቸውን ጠቁሟል፡፡
ከሁለቱም በኩል የተላለፈው ቃለ ውግዘት፣በአንድነት በሚካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲፈታ በሰላም ልኡካኑ በአንድ ድምፅ የወሰነ ሲሆን፣ ከልዩነቱ በፊት የተሾሙ ነባር ሊቃነ ጳጳሳት፣ ስማቸውና ክብራቸው ተጠብቆ በውጭ ሀገርም ኾነ በሀገር ቤት እንዲመደቡና እንዲያገለግሉ፤ ከልዩነቱ በኋላ የተሾሙት ኤጲስ ቆጶሳት፣ ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት ደግሞ ስማቸውን እንደያዙ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀበላቸው፣ በውጭም ኾነ በሀገር ቤት አህጉረ ስብከት ተመድበው እንዲያገለግሉ ልኡካኑ ተስማምተዋል። የስም ተመሳስሎ ያላቸው አባቶች፣ እንደቅደም ተከተላቸው ቀዳማይ፣ ካልዓይ፣ ሣልሳይ…ወዘተ በሚል እንዲለዩ ተወስኗል፡፡
ለዕርቅ ሰላሙ ከአዲስ አበባ የተወከሉት ልኡካንና የአስተባባሪው ኮሚቴ አባላት ሰሞኑን የሚመለሱ ሲሆን፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስና አብረዋቸው ያሉት አባቶች፣ ምእመናኑን ተሰናብተው ከነሐሴ አጋማሽ በኋላ እንደሚመለሱ ተጠቁሟል፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሚመራና በዘጠኝ ንኡሳን ክፍሎች የተዋቀረ የአቀባበል ዐቢይ ኮሚቴ መቋቋሙ ታውቋል፡፡
በይፋዊ መግለጫው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ለዕርቀ ሰላሙ በተደጋጋሚ የተደረጉ ጥረቶች ሳይሳኩ ሲኖዶሳዊ አንድነቱ መዘግየቱን፣መንግሥትም የድርሻውን አለመወጣቱን ጠቅሰው ይቅርታ ጠይቀዋል። “ዋነኛው የጥላቻ ምሶሶ በይፋ ተናደ” በማለት ስምምነቱን ያሞገሱት ዶ/ር ዐቢይ፣ የሁላችን ኩራት የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሁለት መከፈሏ ብቻ ሳይሆን በሁለቱም ወገን ውግዘትና ነቀፋ ሲዘራ አያገባኝም ብሎ የቆመ ኃይል ሁሉ ዛሬ ሊጸጸት ይገባዋል፤ ሲሉ ወቅሰዋል። አንድነቱ ቀድሞ ቢመለስ ኖሮ የኢትዮ ኤርትራ ችግር አይዘገይም ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አንድነቱ ከተመለሰ ዘንድ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ ችግሮቿን በራሷ ከመፍታት በሻገር ለሀገር ለላምና ልማት የመጸለይ፣ የመገሠጽና የማስታረቅ ተግባሯን እንድትፈጽም አሳስበዋል፡፡
የአንድነቱን መመለስ በሀገር ቤት ለማብሠር ብዙ ሺሕ ምእመናን በተገኙበት በሚሌኒየም አዳራሽና በተለያዩ ከተሞች የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር እንደሚደረግም ዶ/ር ዐቢይ አስታውቀዋል፡፡

Read 6474 times