Print this page
Saturday, 28 July 2018 15:33

ኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ጀግናዋን አጣች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(30 votes)

 የቀብር ስነ-ስርአታቸው ነገ በ7 ሰዓት ይፈፀማል

    ግንባታው መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የተጀመረውን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላለፉት 6 ዓመታት በሥራ አስኪያጅነት የመሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ፤ በተሽከርካሪያቸው ውስጥ ሞተው መገኘት ዜጎችን በእጅጉ አስቆጥቷል፡፡  ብዙዎችን በእልህና በቁጭት አስለቅሷል፡፡ ጥቂቶችን ደግሞ ተስፋ ያስቆረጠ ይመስላል- የጀግናው የኢትዮጵያ ልጅ ድንገተኛ ህልፈት፡፡
ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ማለዳ 2፡30 ገደማ መስቀል አደባባይ አካባቢ በላንድክሩዘር ቪ8 ተሽከርካሪ ውስጥ በጥይት ተመተው ሞተው የተገኙት ኢንጂነር ስመኘው፤ በእለቱ 3 ሠዓት ላይ ፍላሚንጎ አካባቢ በሚገኘው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ወደ ግድቡ ለጉብኝት ለሚያቀኑ ጋዜጠኞች ቅድመ-ማብራሪያ ለመስጠት ቀጠሮ እንደነበራቸው ታውቋል፡፡ በበነጋው አርብ እለትም ወደ ግድቡ በማቅናት ጋዜጠኞቹን ለማስጎብኘት እቅድ እንደነበራቸው በጉብኝቱ እንዲሣተፉ የተጋበዙ ጋዜጠኞች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ሞተው የመገኘታቸው ዜና በተሠማበት ቅፅበት ወደ አካባቢው ያመሩ ጋዜጠኞች፤ ኢንጂነሩ ኮፍያ አድርገው፣ ቀይ ጃኬት ለብሠው፣ በሹፌሩ መቀመጫ ላይ እንደተቀመጡ አንገታቸው ወደ ጎን አዘንብሎ ከጆሮአቸው ደም እየፈሰሰ ማየታቸውን ጠቁመዋል፡፡ በቀኝ እጃቸው በኩል ሽጉጥ መገኘቱንም ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በሥፍራው የደረሡ የፖሊስ ባልደረቦችም በአካባቢው ተሠብስበው የነበሩ ሰዎችን ከአደጋው ቦታ በማራቅ የፎረንሲክና የተለያዩ ምርመራዎችን ሲያካሂዱ ቆይተው ከረፋዱ 5፡30 ሲሆን አስከሬኑን ከመኪናው በማውረድ ቤተሠብ እንዲመለከተው ከአደረጉ በኋላ ለምርመራ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ልከዋል፡፡
አስክሬኑ ወደ ሆስፒታል መላኩን ተከትሎም በአደባባዩ ሂደቱን ሲከታተሉና በዋይታና ኡኡታ ሲያነቡ የነበሩ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ተሠባስበው ወደ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ዋና ፅ/ቤት በማምራት ከፍተኛ ተቃውሞና ቁጣ አሰምተዋል፡፡ ተቃውሞው እስከ ምሽት ድረስ በሆስፒታሉ አካባቢም ቀጥሎ ነበር፡፡
“ፍትህ ለኢንጂነር ስመኘው”፣ “የኢንጂነር ስመኘው ደም ፈሶ አይቀርም”፤ “ኢትዮጵያ ነፃ ትውጣ…” የሚል መፈክር ሲያሠሙና በእልህ ሲያለቅሱ ተስተውሏል፡፡ “ገዳዮች ለፍርድ ይቅረቡ” ሲሉም የድንገተኛ ሠልፉ ተሣታፊዎች ጠይቀዋል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ መለሳለስ ትቶ ወንጀለኞች ላይ እርምጃ እንዲወስድም አበክረው አሳስበዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሠራተኞችም የኢንጂነሩን ድንገተኛ ህልፈት ሲሠሙ በለቅሶና ዋይታ ተቃውሞና ቁጣ ማሰማታቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በጎንደር የኢንጀነሩ ህልፈት ያስደነገጣቸውና ያስቆጣቸው ወጣቶች ተቃውሟቸውን በእልህና በቁጭት መግለፃቸውን የጠቆሙ ምንጮች፤ ሰላም አውቶብሶችንም እንዳቃጠሉ ተናግረዋል፡፡ በትናንትናው ዕለትም ተቃውሞው በጎንደር ቀጥሎ መዋሉ ታውቋል፡፡
ኢንጅነር ስመኘው ከህልፈታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ስለ ፕሮጀክቱ ተጠይቀው፤ ስራው በተገቢው መንገድ እየተሠራ ነው የሚል ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል፡፡
የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የክልል መስተዳደሮች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የመንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሠማቸውን ሃዘን የገለፁ ሲሆን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፤ “ኢ/ር ስመኘው በህይወት ዘመኑ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ጥሎት ያለፈው ታላቅ ሙያዊ አበርክቶ በትውልዱ ህሊና ውስጥ በደማቁ ታትሞ የሚዘልቅ ይሆናል” ሲሉ የተሠማቸውን ሃዘን ገልፀዋል፡፡
በአሜሪካ የሚገኙት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ በኢንጂነር ስመኘው ህልፈት ማዘናቸውንና ቅስማቸው መሰበሩን ገልፀው፤ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡ መንግስት የኢንጂነሩን አሟሟት በአፋጣኝ አጣርቶ እውነቱን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግም ጠ/ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
ኢንጅነር ስመኘው በቀለ የተወለዱት በ1957 ጎንደር ማክሰኝት ሲሆን የመጀመሪያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ አካባቢያቸው ተከታትለዋል፡፡ ከዚያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምህንድስና የተመረቁ ሲሆን፡፡ ላለፉት 38 አመታትም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ውስጥ ባለሙያዎች ከማሠልጠንና ማስተማር ጀምረው የታላላቅ ፕሮጀክቶች ስራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ከ1997-2003 ዓ.ም የግልገል ጊቤ ሁለት ሃይል ማመንጫ ሥራ አስኪያጅ ነበሩ፡፡ ጊቤ ሁለት ከተጠናቀቀ በኋላም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅና አስተባባሪ በመሆን እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ፕሮጀክቱን መርተዋል፡፡
ኢንጀነሩ የሁለት ወንድ እና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ሲሆኑ ባለቤታቸውም በካናዳ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደነበሩ ታውቋል፡፡
የሟች ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የቀብር ስነ ስርአት ነገ እሁድ ከቀኑ 7 ሠዓት በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል የሚፈፀም ሲሆን ስነ ስርአቱም ለአንድ የልማት አርበኛ በሚመጥን መልኩ ይሆናል ተብሏል፡፡
በቀብር ስነ ስርአቱ ላይ ወላጅ አባታቸውን ጨምሮ ቤተሠቦቻቸው፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የስራ ባልደረቦቻቸውና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲስ አድማስ ጋዜጣ ለኢንጅነር ስመኘው በቀለ ቤተሰቦችና ለመላው ኢትዮጵያውያን መፅናናትን ይመኛል፡፡


Read 9126 times