Print this page
Saturday, 28 July 2018 15:30

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቃዋሚዎች እና በምሁራን አንደበት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ባለፈው እሁድና ሰኞ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ጋር ተወያይተዋል፡፡ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የፓርቲ አመራሮችና ምሁራን ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት መደነቃቸውን ይገልጻሉ፡፡  በተለይ የተቃዋሚ አመራሮች ከውይይቱ በኋላ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ተቋምን መጎብኘት መቻላቸውን እንደ ትልቅ የለውጥ እርምጃና ትሩፋት ይጠቅሱታል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ በውይይቶቹ ላይ የተሳተፉ ምሁራንና የፓርቲዎች አመራሮች ስለ ጠ/ሚኒስትሩ ያላቸውን አስተያየት አሰባስቦ እንደሚከተለው አጠናክሮታል፡፡


              “ጠ/ሚኒስትሩ ለለውጥ የተዘጋጁ፣ ለለውጥ የሚጋብዙ ናቸው”
                 አቶ አበበ አካሉ (የሰማያዊ ፓርቲ አመራር)

     እንደ አንድ ፖለቲከኛና እንደ አንድ ጥሩ ዜጋ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሩ ሰብዕና እንዳላቸው ነው የተረዳሁት፡፡ ሌሎች ማህበረሰቦችን ሲያናግሩበት የነበረው ሰብዕና፣ እኛን ባነጋገሩበት ወቅትም አልተጓደለም፤እንደውም እንደ አንድ ገዥ ፓርቲ መሪ ሳይሆን እንደኛ ሆነው ነበር ስንመካከር የነበረው፡፡ ኢህአዴግን ለመገዳደር ተጠናከሩ በማለት ነበር ሲመክሩን የነበረው። ተበጣጥሳችሁ የትም አትደርሡም፣ አንድ ሁኑ፣ ተሰባሰቡ እያሉ ከልባቸው ነግረውናል፡፡ ተቃዋሚዎች እግር ሲያወጡ እየጠበቅን እንቆርጣለን ከሚል መሪ፣ ወደ ተጠናከሩና ግጠሙን የሚል መሪ መሸጋገር ለኔ አስደንቆኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንዳንድ ፓርቲዎች የወረደ ሃሣብ እንኳ እየቀረበላቸው በትዕግስት ሲያዳምጡ ነበር፡፡ ይሄ ትልቅ ብቃት ነው፡፡ ከተቋማት ገለልተኝነት ጋር በተያያዘ የተሄደበት መንገድም በአብዛኛው የሚያስማማን ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ከፌደራል ስርአቱ መዋቅር፣ የባንዲራ ጉዳይ፣ የህገ መንግስት ማሻሻል ጉዳይን በተመለከተ በርካታ ሃሣቦች ተነስተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ማሻሻያዎች በማምጣት ረገድ ተቃዋሚዎችም ጥናት እንዲያቀርቡ ጋብዘዋል፡፡ ይሄ ትልቅ ነገር ነው፡፡
አፅንኦት ሰጥተው ከተናገሩትና እኔ ውስጥ ከቀሩት ጉዳዮች “አሁን የሚታለል ትውልድ አይደለም፤ ያለን ምርጫ አንድና አንድ ነው- ዲሞክራሲያዊ ምርጫ፡፡ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣን ሲያዝ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ ከእንግዲህ ሊያምነው የሚችለው” ብለዋል፡፡ ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ እንደሚሠሩም ነው ቃል የገቡት፡፡ እናንተ ተጠናከሩ ብለውም አበክረው ተናግረዋል፡፡ እንደውም በምሳሌነት የኦሮሞ ፓርቲዎች 11 ያህል መሆናቸውን በመጥቀስ፣ 11 ፓርቲዎች ለኦሮሞ ህዝብ ምን ያደርጋል፣ ወደ አንድ ወይም ወደ ሁለት ተደራጁ ብለዋል፡፡ የተሟላ ስራ አስፈፃሚ የሌለው ፓርቲ ባለበት ሁኔታ፣ ይሄን ማለታቸው ተገቢ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጠቃላይ በቃላቸው የሚናገሩትን ለውጥ በተግባር ለመተርጎም የቆረጡ ሰው ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡ ፕ/ር መስፍን በእለቱ ያደረጉት ንግግርም ልብን የሚነካ ነበር፤ጠ/ሚኒስትሩም በቅርበት አክብረው አነጋግረዋቸዋል፡፡ “አቶ ለማና ዶ/ር ዐቢይ ከእግዚአብሔር የተሰጡ ፀጋዎች ናቸው፤ እባካችሁ እንርዳቸው ለውጡ ወደ ላቀ ደረጃ መድረስ አለበት” ብለዋል፤ፕ/ር መስፍን፡፡ እኔም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሳያቸው ለለውጥ የተዘጋጁ፣ ለለውጥ የሚጋብዙ ናቸው፡፡ ብዙዎቻችሁ አሁን አርጅታችኋል ስልጣን የመያዣ ዕድሜያችሁ አይደለም፤ አሁን ሃሳብ ነው ማዋጣት ያለባችሁ ብለዋል፡፡ ይሄ ትልቅ ቁም ነገር ያለው መልዕክት ነው፡፡ ጠመንጃ የሚተኩሱት ሃሳብ ያለቀባቸው ሰዎች ናቸውም ብለዋል፡፡ ሃሳብ አዋጡና ወደ አንድ ብሄራዊ መግባባት እንሂድ ሲሉ ነው የጠየቁን፡፡ ይሄ ትልቅ ነገር ነው፡፡ እኔ በጣም ተደስቼበታለሁ፡፡
እኔ የደህንነት ተቋሙ ከደረሰብኝ በደልና ጠባሣ የተነሳ ስሙ ሲጠራ ያስጨንቀኛል፡፡ ሌላ ጉዳይ ስለነበረብኝ እኔ ባልጎበኘውም፣ በተቃዋሚዎች እንዲጎበኝ በመደረጉ ተደስቻለሁ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ገለልተኛ ይሆናል ያሉት ጉዳይ ወደ ተግባር መሸጋገሩ እውን እየሆነ እንደሆነ ተስፋ እንዲያድርብን አድርጎናል።


----------


          “ሞትን የማይፈሩ ደፋር ፖለቲከኛ ናቸው”
            አቶ ተሻለ ሠብሮ (የኢራፓ ፕሬዚዳንት)


    ክቡር ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፤ የቃል እና የተግባር ሰው ናቸው፡፡ ቃል የገቡትን ወይም የህዝብ ጥያቄ ነው ብለው ያመኑበትን ለመመለስ እየተንቀሣቀሱ ነው፡፡ ለዚህ ነው የቃልም የተግባርም ሰው ናቸው  ያልኩት፡፡ እሣቸውን ልዩ የሚያደርገው የኢህአዴግ ልጅ ሆነው፣ ከዚያው ከፓርቲው ፕሮግራም ሳይወጡ፣ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ህዝብ ተቀባይነትን ባጣበት ሁኔታ እሳቸውና ጥቂት ተከታዮቻቸው በህዝብ ተቀባይነት ማግኘታቸው ነው፡፡ ተራማጅነታቸውንም ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የሚወዱና ለዚህም የሚታገሉ መሆናቸውንም መረዳት ይቻላል፡፡ ሞትን የማይፈሩ ደፋር ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ እኔ ብሞት ሚሊዮኖች አሉ ብለው ያምናሉ፡፡ እንዲህ ያለ ቆራጥና ቅን ሰው ናቸው፤ በኔ ምልከታ፡፡
በዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሩ አዳማጭ መሆናቸውንም ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ ሰዓት ሳይገድቡ ነበር ፖለቲከኞችን በትዕግስትና በጥሞና ሲያዳምጡ የነበረው፡፡ በተለይ ቀጣዩን ምርጫ ዲሞክራሲያዊና ተአማኒ ለማድረግ እንደሚሠሩ፣ ተቃዋሚዎችም በዚህ ምርጫ የሚካሱበት እድል ከፊታቸው እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ኢህአዴግ ለምርጫው ጠንክሮ ይዘጋጃል፤እናንተም ጠንክሩ ተሰባሰቡና ታገሉ ማለታቸው በእለቱ ከነበሩ የውይይት ሃሳቦች በውስጤ የቀረ ጉዳይ ነው፡፡ እርግጥ ነው ተቃዋሚዎች ባለፉት ጊዜያት የደረሰባቸው ሁለንተናዊ ጉዳት በምንም የሚካካስ አይደለም፡፡ የቁም እስረኞች ሆነን ነው የቆየነው፡፡
የደህንነት ተቋሙን በተመለከተ በእጅጉ ነው የረካሁት፡፡ በኖርኩበት አሜሪካን ሃገር ሲአይኤ ምን እንደሚመስል አነባለሁ፡፡ የሌሎችንም እንዲሁ፡፡ የኛን በተመለከተ ግን ድብቅብቅ ያለ እና ለዜጎቹ አስፈሪ እንደነበር ሳስብ፣ በእነ ሲአይኤ እቀና ነበር፡፡ አሁን  የኛን የደህንነት ተቋም ስንጎበኝ ግን ትልቅ ጥቁር መጋረጃ የተቀደደ ያህል ነው የተሠማኝ፡፡ እያንዳንዱን ቢሮ በትዕግስት ነው ያስጎበኙን፡፡ እኔ ይሄ ይሆናል ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ አሁን ተቋሙ የኔ ነው እንድል አድርገውኛል፡፡ ለወደፊት ከእናንተ ጋር አብረን እንሠራለን፤ ቢሮአችን ለእናንተ ክፍት ነው ብለውናል፡፡ ከዚህ በላይ ለኛ ትርጉም ያለው ነገር የለም፡፡ ይሄ ወደ ህዝባዊነትና ዲሞክራሲያዊነት የሚደረግ ጉዞ  እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ፡፡ አሁን ለዚህ ተቋም ቁጥር አንድ ተቆርቋሪ እንደምሆን ጥርጥር የለውም፡፡


----------------


              “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመርህ ሰው መሆናቸውን ተገንዝቤያለሁ”
                ዶ/ር ጫኔ ከበደ (የኢዴፓ ፕሬዚዳንት)

     ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመርህ ሰው መሆናቸውን መገንዘብ ችያለሁ፡፡ ዲሞክራሲው ከምንም በላይ ማደግ እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተው ሲናገሩም ከልባቸው እንደሆነ መረዳት ችያለሁ፡፡ ኢህአዴግ ከወትሮም በበለጠ የተጠናከረበት ወቅት ነው፣ እናንተም መጠናከር ይኖርባችኋል ብለው ከልባቸው ምክር ለመስጠትም ሞክረዋል፡፡ ብትችሉ ሶስት እና አራት ቦታ ተሰባስባችሁ ብትደራጁ መልካም ነው ብለውናል። ተጠናክራችሁ ማሸነፍ የምትችሉ ከሆነ ኢህአዴግ በእርግጠኝነት ስልጣኑ ያስረክባል ነው ያሉን፡፡  
በውይይት መድረኩ ላይ ምሁራዊ አስተያየቶች ከፓርቲ አመራሮች የቀረቡትን ያህል አባሎቻችን ታሰሩብን የሚሉ አቤቱታዎችም ሲቀርቡ ነበር፡፡ እኔ በዋናነት ያቀረብኩት ጥያቄ፤ ዲሞክራሲውን ለማሳደግ ፓርቲዎች ምን ማድረግ አለባቸው? የት ድረስ ነው መሄድ ያለብን የሚል ነበር፡፡ እሳቸውም ይሄን ጥያቄ አዘል አስተያየት መሰረት አድርገው፣ ችግሮች አሏቸው የምትሏቸውን አካሄዶች ህገ መንግስቱን፣ የብሄራዊ መግባባት ጉዳይ፣ የፌደራሊዝም ጉዳይ ላይ ፓርቲዎች ጥናት አድርጋችሁ ብታቀርቡና ብንወያይበት መልካም ነው ብለውናል፡፡ ከዚህ በመነሳት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቀናነትና ለወደፊት ዲሞክራሲውን የማሳደግ ፍላጎቱ እንዳላቸው መረዳት ይቻላል፡፡ አቀራረባቸው የአንድ ሃገር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓይነት ሳይሆን የወንድማዊ ዓይነት ነበር፡፡ በሻይ ሰአት ራሱ ከኛው ጋር ቁጭ ብለው ሲወያዩ ነበር፡፡ ይህ በጣም ያስደሰተኝ አቀራረብ ነው፡፡
ከውይይታችን በኋላ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ተቋምን ጎብኝተናል፡፡ እንድንጎበኝ ያመቻቹልን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ በእውነቱ በጣም በሚያስገርም ሁኔታ ጀነራል አደም መሃመድ በር ላይ ቆመው ነው ሁላችንንም በክብር እየጨበጡ ወደ ውስጥ ያስገቡን። ይህ ታይቶ የማይታወቅ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የራሳችሁ ቤት ነው፤ ለእናንተ ክፍት ነው ብለውናል፡፡ የደህንነት ህጉም እየተሻሻለ ነው፤ በዚህ ላይም የእናንተ ግብአት ይፈለጋል ብለውናል ጀነራሉ፡፡ ተቋሙን የህዝብ እናደርገዋለን ብለዋል፡፡ ይሄ ለኛ ትልቅ መሻሻልና ለውጥ ነው፡፡ ተቋሙ በሙያና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑንም ነው ጀነራሉ የነገሩን።
ገለልተኛነቱም ከዚህ በኋላ ለድርድር የማይቀርብ እንደሚሆንም አበክረው ነግረውናል። አለማቀፍ ተቋም ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸውልናል፡፡ እውነቱን ለመናገር እጅግ ረክተን የወጣንበት ጉብኝት ነበር።


-------------


             “ጠ/ሚኒስትሩ ፖለቲካዊ ንቃተ ህሊናቸው ከፍተኛ መሆኑን ተረድቻለሁ”
                ዶ/ር በዛብህ ደምሴ (የመኢአድ ፕሬዚዳንት)


     ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሳያቸው አንደበተ ርቱዕና የፖለቲካ ንቃታቸው ከፍተኛ የሆኑ ሰው ናቸው፡፡ እኛ ጠቅላይ ሚኒስትሩን መወሰድ ያለብን ከሚያደርጉት የፖለቲካ አካሄድ አንፃር ነው፡፡ ካለፉት ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የሚለዩበት ዋናው ነገር፣ ኢትዮጵያንና አንድነትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያንፀባርቁ ሰው መሆናቸው ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ላለፉት 27 ዓመታት ኢህአዴግ ሲያራምደው የነበረው ፖለቲካ፣ በአንድነትና በኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በጎሳና ቋንቋ ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን ለሚወደው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ይሄ አካሄድ ተቀባይነት ያልነበረው ነበር፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ኢትዮጵያዊነትና አንድነትን በማራመድ የሚንቀሳቀሱ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡
እኔ በውይይታቸው ወቅት በእጅጉ የማረከኝ ጉዳይ ስለ ተቃዋሚዎች መከፋፈል ያነሡት ጉዳይ ነው፤ ተሰባሰቡ ብለው የመከሩት ነገር ሁላችንም ልናስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች መሰባሰብ አለብን የሚለው ሃሳብ የሁላችንም መሆን አለበት፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ይሄን መናገራቸው ትልቅ ቁም ነገር ነው፡፡
ከውይይታችን በኋላ እንግዲህ የደህንነት ተቋሙን ነው የጎበኘነው፡፡ እኔ በፍልውሃ መስመር ሳልፍ፣ በትልቅ ውብ የግንብ አጥር የተከለለ ግቢ የማን ነው እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር፡፡ ከውይይታችን በኋላ ደህንነቱን ብትጎበኙ ብለውን ወደ ግቢ ስናመራ ግን የደህንነት ተቋም መሆኑን አውቄ ተገርሜያለሁ። ተቋሙ እዚሁ አዲስ አበባ ሆኖ፣ ከኛም ከህዝብም የተሠወረ ነበር፡፡
ጀነራል አደም መሃመድም፤ በክብር ተቀብለው ነበር ያስተናገዱን፡፡ ደህንነቱን በተመለከተ ዋና ዋና ጉዳዮችን አንስተው አስረድተውናል፡፡ ተቋሙ የማንም ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ መሆኑን ነግረውናል። ይሄ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ብዙ መጥፎ ነገር የተሠራበትና የኢህአዴግ መሳሪያ እንደነበር የሚነገርለትን ተቋም፤ በዚህ መንገድ አስጎብኝተውን ገለፃ ማድረጋቸው፣ ተቋሙን ገለልተኛ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ከፍተኛ መሆኑን አመላክቶናል፡፡ ተቃዋሚዎች ሃሳብ በማዋጣትም አግዙን ነው ያሉት የተቋሙ መሪ፤ ይሄ ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ ሁሉንም የተቋሙን ክፍሎች አይተናል፡፡ ሰፊ ማብራሪያ ነው የተደረገልን፡፡ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ደህንነቱ በሩ ክፍት እንደሆነ ነው የነገሩን፡፡ ይሄ ከዚህ በፊት ያላየነው ነገር ስለሆነ፣ ጥሩ ጅማሮ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡


--------------



            “ለሃገሬ ጉዳይ ሃሣብ ማዋጣት አለብኝ ብዬ እንዳምን አድርገውኛል”
              አስማማው አዲስ (የዩኒቨርሲቲ መምህር)


    ዶ/ር ዐቢይ፤ በጣም ስነ ስርአት ያላቸው፣ ሃይማኖተኛ፣ የተረጋጉ፣ ነገሮችን ማስተናገድና ማዳመጥ የሚችሉ ሰው እንደሆኑ ነው የተረዳሁት። ማንኛውንም ሃሳብና አስተያየት በሠከነ መንገድ ሲያደምጡ ተመልክቼአለሁ፡፡ ለኔ ይሄ ሰብዕናቸው አስደንቆኛል፡፡ በጣም ትዕግስተኛ ናቸው፡፡ ለኔ ይሄ በጣም አስገርሞኛል፡፡ እስከዛሬ እንደዚህ የሚያዳምጥ መሪ ነበር ያጣነው፡፡
እኔ በግሌ አሁን የፖለቲካ ለውጥ መጥቷል ብዬ አላምንም፡፡ ዜጎች የመረጡት መንግስት አይደለም ስልጣን ላይ ያለው፤ ግን የፖለቲካ ሽግግር ላይ ነን ብዬ አምናለሁ፡፡ ወደ ዲሞክራሲ በሚወስደው መንገድ ላይ ነን ብዬ ነው የማስበው፡፡ በዚህ ሂደት  ውስጥ ህገ መንግስታዊ እና ተቋማዊ ለውጦች ይካሄዳሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ በዚሁ መድረክ ላይ ህገ መንግስቱ ይሻሻል ይሆን ተብለው ለተጠየቁት ጠ/ሚ ሲመልሱ፣ ህገ መንግስት ለምን አይሻሻልም ሠንደቅ አላማውም ህዝብ በፈለገው መንገድ ይሻሻላል ነው ያሉት።
ተቃዋሚዎችን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ነግረውናል፡፡ ይሄ ለኛ ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ የትምህርት ጥራት እንደሚያስፈልግ አምነውበት እንዲሻሻል መፈለጋቸው በራሱ ለኔ በበጎ ያየሁት ነው፡፡
ከዚህ ስብሰባ በኋላ ተስፋ አግኝተናል፡፡ ለለውጡ ሃሳብ እንድናዋጣ ገፋፍቶናል፡፡ እኔ በግሌ ምን ሚና መጫወት አለብኝ የሚለውን ራሴን እንድጠይቅ አድርገውኛል፡፡
በማንኛውም ጉዳይ ሃሳብ ማዋጣት እንዳለብኝ እንዳምን አደርገውኛል፡፡ ለብዙዎቻችን ከዳር ቆመን መመልከታችንን እንድንተው ያነቃቃን ይመስለኛል። እኔ በማስተምረው የጋዜጠኝነት ትምህርት፣ በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለብኝ በጥልቀት እንዳስብ አነቃቅተውኛል፡፡

Read 2109 times