Saturday, 28 July 2018 15:58

ዳቦው

Written by  ቮልፍጋንግ ብሮሸርት ትርጉም፡- ዮናስ ታረቀኝ
Rate this item
(6 votes)

 ቮልፍጋንግ ብሮሸርት (እ.ኤ.አ 1921-1947) ጀርመናዊ ደራሲና ጸሐፌ ተውኔት ነው፡፡ ሥራዎቹ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በነበረው አምባገነን መንግሥትና ራሱም እዚያ ውስጥ በነበረው አገልግሎት ተፅዕኖ ስር የወደቁ ናቸው። ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ የጻፈው “እውጭ በሩ ላይ” የሚለው ቴአትሩ ዝናን አትርፎለታል። የሰብዊነት ጥቄዎችን በፍፁም ለድርድር የማያቀርብ ደራሲ መሆኑን በአብዛኛዎቹ ሥራዎቹ ላይ ያሳየ ደራሲ ነው፡፡ ይህ “ዳቦው” ተብሎ ወደ አማርኛ የተመለሰ ሥራው Das Brot በሚል ርዕስ እ.አ.አ በ1946 የተጻፈ ነው፡፡
. . .
ድንገት ከእንቅልፏ ነቃች፡፡ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ተኩል ነው፡፡ “ምንድን ነው ያባነነኝ” ስትል ራሷን ጠየቀች፡፡ ምግብ ማብሰያ ክፍል ውስጥ የሆነ ሰው ከወንበሩ ጋር ተጋጨ፡፡ ጆሮዋን ወደ ምግብ ቤቱ አቅጣጫ ቀሰረች፡፡ ምንም ድምጽ አይሰማም፡፡ ፍፁም ፀጥ ያለ ነው፡፡ በጎን በኩል አልጋውን ብትዳብስ ባዶ ነው፡፡ ይበልጥ ፀጥታ እንዲሰፍን ያደረገው  ነው፡፡ ትንፋሹ የለም፡፡ ከአልጋዋ ወርዳ ቀስ ብላ ጨለማ በዋጠው ሳሎን በኩል ወደ ኩሽናው አመራች፡፡ ኩሽናው ውስጥ ተገናኙ፡፡ ሰዓቱ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ተኩል ነው፡፡ ኮሞዲኖው አጠገብ የቆመ የሆነች ነገር ተመለከተች፡፡ መብራቱን አበራችው፡፡ ሁለቱም ቢጃማ ለብሰው ቆመዋል፡፡ ሌሊት፣ በስምንት ሰዓት ተኩል፤ ኩሽናው ውስጥ፡፡
ኩሽና ውስጥ ባለ ጠረጴዛ ላይ ዳቦ የሚቀመጥበት ሳህን አለ ከዳቦ ላይ እንደተቆረሰለት ተመለከተች። ቢላዋው ሳህኑ አጠገብ ተቀምጧል። የጠረጴዛው ልብስ ላይ የዳቦ ፍርፋሪ ይታያል። ማታ ማታ ወደ መኝታ ከመሄዳቸው በፊት በእያንዳንዱ ምሽት፡፡ ሁልጊዜም ጠረጴዛውን  ታፀዳለች፡፡ አሁን ግን ጠረጴዛው ላይ ፍርፋሪ አለ፤ ቢላዋውም አጠገቡ አለ፡፡ ብርዱ ወለሉ ላይ ካለው የሴራሚክ ንጣፍ ተነስቶ ቀስ እያለ ወደ እሷ ሲሳብ ተሰማት፡፡ እይታዋን ከሳህኑ ላይ አነሳች፡፡
“የሆነ ነገር የሰማሁ መስሎኝ ወደ እዚህ መጣሁ!” አለና፣ የምግብ ማብሰያ ክፍሉን ዙሪያ መመልከት ጀመረ፡፡ “እኔም ሰምቻለሁ!” ብላ መለሰችለት፡፡
በሌሊት በፒጃማ ስታየው እውነትም የዕድሜውን ያህል እንዳረጀ ተገነዘበች፣ ስድሳ ሶስት ዓመት፡፡ አንዳንዴ በቀን ሲታይ ገፅታው ገና ወጣት ይመስላል፡፡ እሷም፣ “በፒጃማ ስትታይ ያረጀች ትመስላለች” ሲል አሰበ፡፡ ምናልባት በፀጉሯ ምክንያት ይሆናል፡፡ ሴቶችን ሌሊት ላይ በድንገት ያረጁ የሚያስመስላቸው ፀጉራቸው ነው፡፡
“ጫማ ማድረግ ነበረብሽ፤ በባዶ እግርሽ የሴራሚኩ ቅዝቃዜ ብርድ ያስመታሻል፡፡”
ከሰላሳ ዘጠኝ የጋብቻ ዓመታት በኋላ መዋሸቱን መቋቋም ስላልቻለ አልተመለከተችውም፡፡
“የሆነ ነገር የሰማሁ መስሎኝ እኮ ነው! ከዚያ ምግብ ማብሰያ ክፍል ውስጥ ነው ብዬ አሰብኩ” አለና በድጋሚ ዝም ብሎ፣ ከአንዱ ጥግ ወደ ሌላው ጥግ መመልከት ያዘ፡፡
“እኔም የሆነ ነገር ሰምቻለሁ፤ ግን ምንም ነገር የለም!” ብላ ዳቦ ያለበትን ሳህን አንስታ፣ ፍርፋሪውን ከጠረጴዛው ላይ አራገፈችው፡፡
“ምንም የለም!” ሲል እርግጠኛ ባልሆነ ስሜት አባባሉን ደገመው፡፡
“ና! ወደ አልጋችን እንሂድ፡፡ እውጭ ይሆናል። የሴራሚኩ ቅዝቃዜ ብርድ ያስመታሃል” አለችው ክንዱን ይዛ፡፡
“እውነትሽን ነው፤ ከውጭ የመጣ ድምጽ ሳይሆን አይቀርም… እዚህ ውስጥ መስሎ እኮ ነው” በመስኮቱ አሻግሮ ተመለከተ፡፡
እጇን ወደ ማብሪያና ማጥፊያው ዘረጋች። “መብራቱን ማጥፋት ይኖርብኛል፡፡ ካለዚያ በድጋሚ ሳህኑን ለመመልከት እገደዳለሁ፡፡ ሳህኑን መመልከት ደግሞ የለብኝም” ስትል አሰበች፡፡ ከዚያም “ና! እውጭ ነው፡፡ ንፋስ ሲኖር የጣራው ክፈፍ ሁሌም ከግድግዳው ጋር እንደተጋጨ ነው” ብላ መብራቱን አጠፋችው፡፡
“ልክ ነሽ፡፡ ንፋስ ሲኖር ክፈፉ ሁልግዜ እንደተርገበገበ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ኩሽና ውስጥ መስሎኝ”
ሁለቱም ቀስ እያሉ በጨለማ ውስጥ በኮሪደሩ አልፈው ወደ መኝታ ክፍል ገቡ፡፡ ባዶ እግሮቻቸው ወለሉ ላይ “ጣ! ጣ የሚል ድምጽ ያሰማ ነበር፡፡
“ንፋሱ ነው፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ሲነፍስ ነበር” አለ፡፡
አልጋው ላይ ጋደም እንዳሉ፣ “ልክ ነው፤ ሌሊቱን ሙሉ ሲነፍስ ነበር፡፡ የጣሪያው ክፈፍ ነው የተንቋቋ” አለች፡፡
“አዎን! እኔ ደግሞ ኩሽና ውስጥ መስሎኝ ነበር። ለካስ የጣሪያው ክፈፍ ነው፡፡” በግማሽ እንቅልፍ ላይ  በሚመስል ሁኔታ ተናገረ፡፡ ይሁን እንጂ ሲዋሽ ድምጹ ምን ያህል እውነተኛ እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡
 “ይበርዳል፣ ውስጥ ልግባ፡፡ ደህና እደር!” ብላው በስሱ አዘጋች፡፡
“ደህና እደሪ በጣም ይበርዳል!” አላት፡፡
ከዚያ በኋላ ፀጥታ ሰፈነ፡፡ ብዙ ደቂቃዎች ካለፉ በኋላ ቀስ ብሎ በጥንቃቄ ሲያኝክ ሰማችው። እንቅልፍ ሊወሰዳት መሆኑን እንዳያውቅባት ሆን ብላ ያላመቋረጥ በጥልቀት መተንፈስ ጀመረች። ማኘኩ ግን ተከታታይነት ስለነበረው ቀስ በቀስ እንቅልፍ ወሰዳት፡፡
በበነጋታው ምሽት ላይ ወደ ቤት ሲመጣ አራት ቁርጥ ዳቦ አቀረበችለት፡፡ ሌላ ጊዜ የሚባላው ሦስት ቁርጥ ዳቦ ነበር፡፡
“አራቱንም ብላ፡፡ እኔ ከዚያ በላይ መብላት አልቻልኩም፡፡ አንዱን ጨምረህ ብላ!” ብላው ከጠረጴዛ መብራቱ አጠገብ ዞር አለች፡፡ ሳህኑ ላይ እንዴት እንዳቀረቀረ ተመለከተችው፡፡ ቀና አላለም። በዚህ ጊዜ በጣም አሳዘናት
“ሁለት ቁርጥ ዳቦ ብቻማ ልትበዬ አይገባም” አለ እንዳረቀረ፡፡
“በእውነት በቃኝ፡፡ አልበላልሽ እያለኝ ነው፤ ግዴለም አንተ ብላ!...ብላ!” አለችው፡፡ ጠረጴዛው መብራት ስር መጥታ የተቀመጠችው ለተወሰነ ጊዜ ከእሱ እርቃ ከቆየች በኋላ ነበር፡፡

Read 2492 times