Saturday, 04 August 2018 09:36

የ21ኛው ዓለም ዋንጫ ልዩ ማስታወሻ ‹‹እኔ ከኢትዮጵያ ነኝ››

Written by  ግሩም ሠይፉ (ከሞስኮ)
Rate this item
(1 Vote)


    በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንና በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር አማካኝነት 21ኛው የዓለም ዋንጫን በራሽያ ተገኝቶ ለመዘገብ ከተመረጡት ሶስት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች አንዱ የሆንኩት ከብዙ አወዛጋቢ አጀንዳዎች በኋላ ነበር፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ለዚህ ዓይነቱ እድል በተለይ በህትመት ኢንዱስትሪው የሚገኙ ጋዜጠኞችን ተመራጭ ያደርግ ነበር፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ የብሮድካስት ሚዲያው ከደረሰበት የአቅም ደረጃ አንፃር ዓለም ዋንጫው ለኢትዮጵያ ይዞ በመጣው እድል ብዙ እሰጥ አገባ ተፈጥሯል፡፡ አንዳንድ የስፖርት ጋዜጠኞች እንደውም በተሰጠው እድል ዙርያ በግልፅ ተቃውሞ ነበራቸው፡፡ የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርን የሚፈታተን ውሳኔም ላይ ደርሰዋል፡፡ እድሉ የሚሰጣቸው ጋዜጠኞች ስፖንሰርሺፕ የማግኘት አቅም አይኖራቸውም፤ በዓለም ዋንጫው እንኳን 1 ወር 3 ቀናትም መቆየት አይችሉም እያሉም አጣጥለዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት ዓለም ዋንጫን የመዘገብ እድሉ የተሰጣቸው አንጋፋ ጋዜጠኞች ከተቃዋሚዎቹ ዋንኞቹ መሆናቸው የሚያስገርም ነበር። ለኢትዮጵያ የተገኘውን እድል እኔ ካልሆንኩ ሌላውን ላሳር በሚል ስሜት እንደሚመለከቱ አልጠበቅኳቸውም። እንደውም ዓለም አቀፉን መድረክ ለመዘገብ በተገኘው እድል ተባብረን እንሰራለን የሚሉ ነበር የመሰለኝ፡፡
ስለዚህም በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ የመዘገቡ እድል ከጅምሩም የሚያበረታታ ድጋፍ አለማግኘቱ የሚያሳስብ ነበር፡፡ በተለይ ከሚመለከታቸው የስፖርት ጋዜጠኞችና እና ሚዲያዎች አዎንታዊ ትብብር በማድረግ መስራት ለምንችልበት እድል አንድም ፍንጭ አለመታየቱም ግራ ያጋባል፡፡ በእግር ኳስ ውድድሮች የቀጥታ ስርጭት የሚሰሩ የኤፍኤም ሞገዶች፤ የስፖርት ቶክሾዎች…የመዝናኛ ፕሮግራሞች እና ሌሎች ህትመቶች ዓለም ዋንጫውን በልዩ ሁኔታ ሽፋን ለመስጠት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ሲያስተዋውቁም ከፊፋ ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንዳላቸው አስመስለው ነበር፡፡  በፊፋ እድል ከተሰጠን ጋዜጠኞች ጋር በተለያዩ ትብብሮች ለመስራትም ያደረጉት አንዳችም ሙከራ የለም፡፡ ይህን በመሰለ ሁኔታ ውስጥ  ለዓለም ዋንጫ ማለፉን ብቻ ማሰብ  ያስጨንቅ ነበር። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ለኢትዮጵያ ካቀረበው የሶስት ጋዜጠኞች ኮታ ለእኔ የተሰጠው የፍሪላንስ ፎቶግራፈር ምድብ መሆኑንም አደናግሮኝ ነበር። ስላሳሰበኝ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የምፅፍ ከፍተኛ ሪፖርተር እና የስፖርት አምድ አዘጋጅ መሆኔን በመግለፅ ደብዳቤ ለፊፋ ፃፍኩ፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር የስፖርት ጋዜጠኛ እንደሆንኩ የምሰራበትን አዲስ አድማስ ጋዜጣም እንደሚያውቅ በምላሹ ካረጋገጠልኝ በኋላ ለ21ኛው የዓለም ዋንጫ ወደ ራሽያ ለመጓዝ  ወሰንኩ፡፡ በ2013 እኤአ ለ14ኛው  የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሞስኮ ስለነበርኩ ወደ ራሽያ ስጓዝ በስፖርት ጋዜጠኝነት ለሁለተኛ ጊዜ ሆነ ማለት ነው፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊትበተካሄደው የዓለም ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ ተሳታፊ ሆና 3 የወርቅ፤ 3 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎች ማግኘቷ የሚታወስ ነው፡፡  በስፖርት ጋዜጠኝነት ሰፊ ልምድ ነበረኝ፡፡ ከተለያዩ የራሽያ የህትመት እና የብሮድካስት ሚዲያዎች ጋር ልዩ ቃለምልልሶች በማድረግ የኢትዮጵያን አትሌቶች በሚመለከት አስተያየቶችን ሰጥቻለሁ፡፡ ከቢቢሲ ራድዮ ስፖርት ጋር በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር የቀጥታ ስርጭቶች በፊት በተደረጉ ውይይቶች ተሳታፊ ነበርኩ፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ካነጋገሩኝ መካከል  የደቡብ ኮርያ ጋዜጣ፤ የቱርክ አትሌቲክስ መፅሄት፤ ሁለት የተለያዩ የስዊድን ጋዜጣዎች፤ ከጃማይካ የማህበራዊ ገፅ ጋዜጠኞች እና የአትሌቲክስ ድረገፆች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከውድድሮች በኋላ በሚዘጋጁ ጋዜጣዊ መግለጫዎችም ላይ ንቁ ተሳታፊ ነበርኩ፡፡ ከጥሩነሽ ዲባባ ጋር በሉዚሂንኪ ስታድዬም ደጃፍ ልዩ ቃለምልልስ ከመስራቴም በላይ በመግለጫዎች ላይ ለመሀመድ አማን፤ ለመሰረት ደፋር፤ ለሶፊያ አሰፋ ፤ኢብራሂም ጄይላን፤ ለሌሊሳ ዴሲሳ እና ሌሎችም የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርቤ ምላሾቹን ዘግቢያለሁ፡፡ ከሌሎችአገራት አትሌቶች ደግሞ እንግሊዛዊው ሞፋራህ፤ ኡጋንዳዊው ሮበርት ኪፕሮቲች እና ከአሜሪካው በርናንድ ላጋት ጋር አጭር ቃለምልልሶችም ነበሩኝ፡፡ በታላቅ ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ ከላይ የተዘረዘሩትን ስራዎች ማከናወን ከፍተኛ ውጤት ነበረው። ስለሆነም ወደ ራሽያ በመመለስ በዓለም ዋንጫ ይህን ስኬትና ልምድ ለማግኘት መጓጓቴ አልቀረም፡፡
***
በዓለማችን ታላቅ የስፖርት መድረክ ‹‹የዓለም ዋንጫ›› ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የመዘገብ እድሉ ብዙ ሽኩቻዎችን ፈጥሮ ካለ በኋላ ሌላው ፈተና ሙሉ ወጭን ሸፍኖ ጉዞውን ማሳካት ነበር፡፡ ለካንስ የኢትዮጵያን ሚዲያ በመወከል ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ብቻውን በቂ አልነበረም። ዋናው ነገር ሙሉ የጉዞ ወጭዎችን መሸፈን ነው፡፡ ወደ 21ኛው የዓለም ዋንጫው ለማቅናት የቪዛ፤ የጉዞ እና የተለያዩ ዝግጅቶች ሳከናውንና  ወጪዬን የሚሸፍኑ ስፖንሰሮች ሳፈላልግ  ከ4 ወራት በኋላ በላይ ጊዜ ወስዶብኛል፡፡  በዓለም ዋንጫው  አገርን እንደወከለ ብሄራዊ ቡድን ነበር ራሴን የቆጠርኩት፡፡ ሙሉ ትኩረት ሰጥቼ ለመንቀሳቀስ ከምሰራበት የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ቢሮዬ ባሻገር ልዩ ካምፕ መፍጠር ነበረብኝ፡፡ ስለዚህም ካሳንቺስ 28 ሜዳ አካባቢ የሚገኘውን የሰዓሊና ዲዛይነር ዳዊት ሙሉነህ የስነጥበብ ማዕከል አይከን ስቱድዮ እንደካምፕ ልገለገልበት ወሰንኩ። ዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያን በጎበኘችበት ወቅት ከኮካ ኮላ የተሰጠችኝን የኳስ ስጦታ ለዚሁ ስቱድዬ አበርክቻት ነበር። በአይከን ስቱድዮ የሚሰባሰቡት በርካታ ወጣት ምሁራንና ባለሙያዎች ይሰባሰባሉ፡፡  ዶክተር፤ ኢንጅነር፤ ሰዓሊ፤ ቀራፂ፤ አንትሮሎጂስት፤ የቱሪዝም ባለሙያ፤ ፊልም ሰሪ፤ የኮምፒውተር ኢንጅነር፤ ባንከኛ፤ ሙዚቀኛ….  ይገኙበታል። እነዚህ የአይከን ስቱድዮ አባላት ዓለም ዋንጫን ለመዘገብ  በፊፋ  ከኢትዮጵያ ከተጋበዙት የስፖርት ጋዜጠኞች አንዱ መሆኔን ካወቁ በኋላ የሞራል ደጋፊዎቼ መሆን ጀመሩ፡፡  የስቱድዮው አባላት በየሙያ ዘርፋቸው እና ልምዳቸው ኢትዮጵያን ማገልገልና ማስጠራት የሚወዱ ናቸው፡፡ እንዲሁም ስቱድዬው በሚገኝበት ግቢ የነበሩ ቤተሰቦችም ያው ናቸው፡፡ በዓለም ዋንጫ የአዲስ አበባ ጉብኝት ወቅት ያገኛኋትን የኮካ ኮላ የዓለም ዋንጫ ኳስ ለስቱድዬው ካበረከትኩት በኋላ ይህን ልዩ ድጋፋቸውን በተግባር አረጋገጡልኝ፡፡ የራሽያው ጉዞዬ እንዲሳካልኝ መልካም ምኞታቸውን በመግለፅ  በኳሷ ላይ ፊርማቸውን አኑረውባታል፡፡ ይህችን ኳስ በየቀኑ በስቱድዮው እየተመለከትኩ ከፊፋ ጋር የተለያዩ ደብዳቤዎችን እፃፃፍ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ወደ የሚገኘው ራሽያ ኤምባሲ በመንቀሳቀስ የቪዛ ጉዳዮቼን ያስጨረስኩትም ከዚያ ስቱድዮ እየተነሳሁ ነበር፡፡
አስፈላጊውን የዓለም ዋንጫ የሚዲያ ግብዣ እና የፍቃድ ደብዳቤ ከፊፋ እንዲሁም በራሽያ ለ56 ቀናት የምቆይበትን ቪዛ በኢትዮጵያ ከሚገኘው የራሽያ ኤምባሲ አግኝቼ በአይከን ስቱድዮ መስራቴን ቀጥያለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ የእለት እለት ጭንቀቴ ወጭዬን የሚሸፍኑልኝ ስፖንሰሮች ማፈላለግ ነበር፡፡ በስቱድዮው ካከናወንኳቸው ተግባራት ብዙም ያልተሳካልኝ ማለት ነው፡፡ ድጋፍ ሰጭ ስፖንሰሮችን ያፈላለግኩባቸው እልህ አስጨራሽ ጥረቶች ናቸው፡፡ የመጀመርያው የየስፖንሰርሺፕ ጥያቄዬ የጥበብ ሞገድ በሚል ስያሜ ከምሰራበት የሬድዮ ጣቢያ ጋር ለመስራት ቢሆንም እንደጠበቅኩት በቂ ምላሽ ሳይሰጡኝ ቀሩ፡፡ ከዚያም የሚመለከታቸውን ታላላቅ ኩባንያዎች ከ5 በላይ ይሆናሉ ከፍተኛ ደጅ ጥናት በማድረግ የስፖንሰርሺፕ ደብዳቤዎች እያስገባሁ ድጋፋቸውን ጠየቅኩ፡፡
በአይከን ስቱድዬ ሆኜ ለጠየቅኳቸው የስፖንሰርሺፕ ድጋፎች  ምላሽ አለማግኘቴ በመጀመርያ በጣም ያበሳጨኝ ነበር፡፡  በአይከን ስቱድዮ የነበረው የስነጥበብ ድባብ እና መንፈስ ግን የመንፈስ ጥንካሬ ነበር የፈጠረልኝ፡፡ ሰዓሊና ዲዛይነር ዳዊት ሙሉነህ፤ኢንጅነር ሳምሶን ጌታቸው፤ የሻማ አርቲስት ቀራፂ አስናቀ ክፍሌ እና ሌሎችም በአይከን ስቱድዮ በእነዚህ አስጨናቂ ስፖንሰርሺፕ የጠፋባቸው ቀናት ሲያበረታቱኝ እና ሲያጽናኑኝ ነበር፡፡ በዓለም ዋንጫው ኢትዮጵያን በመወከል የምትጓዝበት እድል በማግኘትህ ብቻ ልትኮራ ይገባል፡፡ ያለህን አቅም አሰባስበህ በእግርህም ቢሆን መሄድህ አይቀርም ይሉኝም ነበር፡፡ ከሄድክ ደግሞ ያለጥርጥር የኢትዮጵያ አምባሳደር በምትሆንበት ሚና ልትሰራ ይገባል በማለትም በየቀኑ ይመክሩኛል፡፡
ወደ ሞስኮ የደርሶ መልስ ትኬት የቆረጥኩት ዓለም ዋንጫው 1 ሳምንት ሲቀረው ነበር፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በስፖርቱ ያሳለፍኩትን ልምድ እና አስተዋፅኦ ግምት ውስጥ በማስገባታቸው ይህን ወሳኝና ልዩ ድጋፍ አድርገውልኛል፡፡ የ21ኛው የዓለም ዋንጫ   ጉዞው  እውነት እየመሰለ የመጣው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሙሉ ስፖንሰርሺፕ  ባይሆንም ኃይሌ ገብረስላሴ እና ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም የተወሰነ ድጋፍ አደረጉልኝ፡፡ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ጉዞዬም የትኛውም ትልቅ ኩባንያ የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ ባይሰጠኝም ከላይ በተገለፀው ሁኔታ የግለሰቦች ድጋፍ ዓለም ዋንጫውን እንደምሳተፍ አረጋገጠልኝ፡፡
ከዚህ በኋላ ዓለም ዋንጫው 1 ሰሞን ሲቀረው የአይከን ስቱድዮ ባለቤት ሰዓሊና ዲዛይነር ዳዊት ሙሉነህ ልዩ ሃሳብ አቀረበ፡፡ ራሽያ ስትጓዝ በተለየ መንገድ ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ ይኖርብሃል፡፡ ለዚህም ደግሞ ቀለል ያለ የቲሸርት ዲዛይን እንስራ ነው ያለው፡፡ ሃሳቡን ስለወደድኩት በሶስት ልሙጥ ቲሸርቶች ላይ ‹‹እኔ ከኢትዮጵያ ነኝ›› እንዲሁም ‹‹ይ ዚ ኢፍዮፒ›› የሚል ፅሁፍ በአማርኛ እና በራሽያ ፊደላት እንፃፍ ፤የራሽያ ባንዲራ ቀለማትም የቲሸርቱ ዲዛይን ኣካል ይሁን ብለን ተነጋገርን፡፡ ሰዓሊና ዲዛይነር ዳዊት ሙሉነህ በሚገርም ንቃት እና በጎ ፈቃደኝነት ቲሸርቱን ሰራልኝ። ኢትዮጵያን በቀላሉ ለማስተዋወቅ ያገዘኝ፤ አስቀድመን እንደገመትነውም የዓለም ዋንጫው እንግዶች እና አስተናጋጅ ራሽያውያን ከየት እንደሆንኩ ለሚያቀርቡልኝ ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ልዩ ቲሸርቶች ነበሩ፡፡
ከአይከን ስቱድዮ የተሰራልኝ ቲሸርት አስቀድመን እንዳቀድነው ከፍተኛ አገር የማስተዋወቅ ስራ እንዳከናወንኩበት በምሳሌ ላስረዳ እችላለሁ፡፡ በሩብ ፍፃሜው ከሚደረጉ 4 ጨዋታዎች መካከል በፊፋ እንድዘግብ የተፈቀደልኝ  ራሽያ ከክሮሽያ በሶቺ ከተማ የተገናኙበት ነበር፡፡ ሶቺ ከሞስኮ ከተማ 1634 ኪሜትር ርቃ የምትገኝ ናት፡፡ በባቡር የማደርገው ጉዞ ደርሶ መልስ 78 ሰዓታት የሚወስድ ነበር፡፡ በጥቁር ባህር ወደ ተከበበችው ሶቺ  ለመድረስ የ38 ሰዓታት  የባቡር ጉዞ አድርጌ ከተማዋ የገባሁት ከአይከን ስቱድዮ የተሰራልኝን ‹‹ እኔ ኢትዮጵያ ነኝ›› የሚለውን ቲሸርት ለብሼ ነበር፡፡ በከተማዋ የፕሬስ ማዕከል ይህን ቲሸርት ለብሼ ስገባ እንግዶችን የሚቀበሉት የከተማ ሰዎች፤ የሚዲያ ባለሙያዎች እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች በከፍተኛ አድናቆት እና ክብር አቀባበል አድርገውልኛል፡፡
የለበስኩት ቲሸርት ላይ በአማርኛ እና ራሽያኛ የፃፍኩት መልዕክት የራሽያን የባንዲራ ቀለማት መቀባቴን ሲመለከቱ ራሳቸው ለአቀባበል ካዘጋጁት ስነስርዓት ጋር መመሳሰሉ በጣም ነው ያስደሰታቸው፡፡ በመጀመርያ በሚዲያ ማዕከሉ እነሱ እንዳሰቡት ከሶቺ ባህር በወጣ ጥቁር ድንጋይ ላይ የራሽያን ባንዲራ ቀለማት እንድስል አደረጉ፡፡ ይህን ስሰራ አብረውኝ ሁለት የራሽያ አዛውንቶች የነበሩ ሲሆብ ለቴሌቭዥን ፕሮግራምም እየተቀረፀ ነበር። ሁለት የሶቺ የቲቪ ጣቢያዎች እና ሌሎች ሚዲያዎች ቃለምምልስ አደረጉልኝ፡፡ ቲሸርቱን የት አሰርቼ ለምን ራሽያ ለብሼ እንደገባሁ፤ ወደ ሶቺ ከተማ ወደፊት ለጉብኝት ከተጋበዝኩ እድሉን እንዴት መጠቀም እንደምችል፤ ስለራሽያ እና የኢትዮጵያ ወዳጅነት ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች በልበሙሉነት መልሻላቸዋለሁ፡፡
***
ባለፈው ሳምንት እንደገለፅኩት እስከ 15 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን በቀጥታ በስፍራው ተገኝቶ መከታተል ከፍተኛ እውቀትና ልምድ የሚገኝበት ነው፡፡ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፉ መድረክ በመወከል ስኬታማ አድርገውኛል የምላቸው ሁኔታዎች እዚህ ጋር በዝርዝር መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ የፊፋ ቴክኒካል ኮሚቴ፤ የራሽያ ዓለም ዋንጫ አዘጋጆች፤ የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በሰጧቸው መግለጫዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረጌ የመጀመርያው ነው። ለራሽያ ብሄራዊ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ ሃላፊዎች እና ለፊፋ ሰዎች፤ ለፊፋ የቴክኒካል ኮሚቴ አባላት ለእነ ፔሬራ፤ ቫንባስተንና አሞካቺ፤ ለፊፋ የግብ ጠባቂዎች ኤክስፐርት፤ ለፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በቀጥታ ያቀረብኳቸው ጥያቄዎች ነበሩ፡፡  ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሳቡትን እነዚህን ጥያቄዎች ከኢትዮጵያ መሆኔን በመጥቀስ አቅርቢያለሁ፡፡ ከሆላንዱ ምርጥ ቫንባስተን፤ ከብራዚሉ ባለታሪክ ሮናልዶ ሊውስ ናዛርዮ ዴሊማ፤ ከጀርመኑ እውቅ አምበል ማቴያስ ዛመር፤ ከናይጄርያው ዳንኤል አሞካቺ፤ ከኡራጋዩ ዲያጎ ፎርላን… በተገናኘሁባቸው አጋጣሚዎች አድናቆቴን ከመግለፅ ባሻገር ማወቅ የፈለግኳቸውን ነገሮች በመጠየቅ ምላሽ አግኝቻለሁ፡፡
በቀጥታ ካደረግኳቸው ቃለምልልሶች ዋንኛው ተጠቃሽ ፕሮስቱፕሮስስፖርትስ ከተባለ የድረገፅ ቲቪ ጋር ያደረግኩት ነበር፡፡ ቃለምልልሱን ጥንታዊቷን የራሽያ መዲና ኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ እያስጎበኘኝ የሰራው አርቲዬም የተባለ የራሽያ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ በአገር አቋራጭ ባቡር ከሞስኮ ወደ ኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ ከ480 ኪሜትር በላይ ስንጓዝ የተጀመረው የቪድዮ ቃለምልልስ ያበቃ በኖቭጎሮድ ከተማ አውራ ጎዳናዎች እና በጎርኪ አደባባይ ነበር፡፡ በቃለምልልሱ ከራሽያዊው ጋዜጠኛ ስለዓለም ዋንጫው ካደረግነው ውይይት የበለጠ ትኩረት ሰጥተን ያወራነው ስለ ኢትዮጵያ እና የራሽያ ህዝቦች የጋራ ባህልና ሃይማኖት፤ ስለ ሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች፤ ስለቀድሞዋ ሲቪዬት እና ኢትዮጵያ ወዳጅነት፤ በራሽያ ተምረው በስነጥበብ እና በስነፅሁፍ የላቁ ስራዎች ስላበረከቱ ኢትዮጵያውያን፤ በኢትዮጵያውያን ስለሚታወቁት የራሽያ የጥበብ ሰዎች ፑሽኪን፤ ጎርኪ፤ ዶስቶቭስኪ እና ሌሎችም በማንሳት ቃለምልልሱ ተሰርቷል፡፡ ከባንግላዴሽ፤ ከህንድ፤ ከናይጄርያ ከሱዳን፤ ከኡራጋይ ከአርጀንቲና እና ከአሜሪካ… ከበርካታ አገራት ጋዜጠኞችም ጋር የተለያዩ ውይይቶችን አድርገናል፡፡ ለጋዜጣ፤ ለመፅሄት፤ ለድረገፅ  እና ሌሎች የብሮድካስት እና የሚዲያ አውታሮች የሚሆኑ መረጃዎችን የተቀባበልንባቸው ግንኙነቶች ነበሩ፡፡
***
በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ስኬታማ የሚዲያ ተግባራትን ለማከናወን እንደ እኔ ሁሉ በፊፋ ፍቃድ ካላቸው የሙያ ባልደረቦቼ የሊግ ስፖርቱ አለምሰገድ ሰይፉ እና የሪፖርተሩ ዳዊት ቶሎሳ ጋር ሰርተናል፡፡ የኢትዮጵያን የስፖርት ጋዜጠኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ ለማድረግና ለማጣጣም በልዩ ሞራል እንቀሳቀስ ነበር፡፡ በተለያዩ የራሽያ ከተሞች በነበረን ቆይታ  በየስታድዬሙ የሚድያ ማዕከሎች ከመላው ዓለም ከተውጣጡ የስፖርት ጋዜጠኞች በተለያዩ አጀንዳዎች በየጊዜው እንወያይ ነበር።  የራሽያ፤ የባንግላዴሽ፤ የህንድ፤ የጣሊያን፤  የአርጀንቲና፤ የሜክሲኮ፤ የስፔን፤ የእንግሊዝ… የበርካታ አገራት ጋዜጠኞች ለሚሰሩባቸው የተለያዩ የሚዲያ አውታሮች የሚጠቀሙባቸውን መረጃዎች በኢትዮጵያ ስላለው የስፖርት እንቅስቃሴ  በቃለምልልስና በውይይት መልክ ሰጥተናቸዋል፡፡ ከደቡብ አሜሪካ የመጡ ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ  የእግር ኳስ ስፖርት መኖሩን ሁሉ በመጠራጠር ይጠይቁን ነበር፡፡
ላቲኖች ከእግር ኳሳችን ይልቅ ስለኢትዮጵያ የሚያውቁት ንጉስ ኃይለስላሴን እንደሆነ የአርጀንቲና፤ የፔሩ እና የቦሊቪያ ጋዜጠኞች ያወጉኝ ይታወሰኛል፡፡ የሚገርመው ግን በሁሉም ዓለም ክፍል ያሉ ጋዜጠኞች ስለ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ እና ውጤታማ ታላላቅ አትሌቶች የሚያውቁት ነበራቸው፡፡ አንዳንዶቹ የሚዲያ ባለሙያዎች እንደውም ስለነ ኃይሌ፤ ቀነኒሳ፤ ጥሩነሽ እና ሌሎች እውቅ አትሌቶች አድናቆታቸውን ይገልፁልን ነበር፡፡ ከበርካታ አፍሪካውያን ጋዜጠኞች ጋርም እንገናኝ ነበር፡፡ በተለይ ከምዕራብ አፍሪካ ከመጡት ጋር በተደጋጋሚ የምናወጋው በአፍሪካ የእግር ኳስ አስተዳደር ስለተንሰራፋው ሙስና የነበረ ሲሆን አንድ ታዋቂ የካሜሮን ካሜሮናዊ ጋዜጠኛ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ሲሰጥ በአፍሪካ እግር ኳስ በአስተዳደር ደረጃ የአቶ አብነት ገብረመስቀል ብቃት እና ስብዕና እንደሚያስፈልግ በኩራት ያብራራበትን መንገድ የምረሳው አይሆንም፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ ጋዜጠኞች ጋር ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከአንድም ሁለት ሶስቴ ውይይት አድርገናል፡፡  
ከሊግ ስፖርቱ አለምሰገድ ሰይፉ እና ከሪፖርተሩ ዳዊት ቶሎሳ ጋር  ከስታድዬሞች የሚዲያ ማዕከሎች ውጭ በምናደርጋቸው ጉዞዎች ለጋዜጠኝነቱ የሚጠቅሙ መረጃዎችን ከመሰብሰብ ባሻገር ኢትዮጵያንም በተለያየ መንገድ እናስተዋውቅም ነበር፡፡ በልዩ ልዩ የባቡር ጉዞዎች  እና ጉብኝቶቻችን ላይ የሚያጋጥሙን የተለያዩ የዓለም ህዝቦች ከየት እንደሆንን ጠይቀው በመቀጠል ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ የሆነ መረጃ ይጠይቁንና በተለያየ መንገድ እንመልስላቸዋለን፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ማልያ ሶስታን ለብሰን በራሽያ ስንዘዋወር በርካታ የዓለም ህዝቦች በተለይም ራሽያያን ከእኛ ጋር ፎቶዎችን በድካም እስክንዝል ነበር የሚነሱት፡፡ የአርጀንቲና ደጋፊዎች ይህን ማልያ በራሳቸው ቀይረው የወሰዱበት አጋጣሚ ነበር፤ የአርጀንቲና፤ የሜክሲኮ ደጋፊዎች በሜትሮ የባቡር ጣቢያዎች እና ባቡር ውስጥ፤ በየአደባባዩ እና በየጎዳናው በዝማሬያቸው ላይ ኢትዮጵያን በመጥራት ሁሉ በተደጋጋሚ ይዘምሩልን ነበር፡፡
21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ በፊፋ ኦፊሴላዊ ፈቃድ ተሰጥቶን በራሽያ የተገኘነው ጋዜጠኞች በውድድሩ የኢትዮጵያ ሚዲያ የተሳትፎ ታሪክ ከፍ ያለውን ልምድ ያገኘን ይመስለኛል፡፡
***
ለስንብት  ሁለት ገጠመኞችን ላካፍላችሁ፡፡ 21ኛውን የዓለም ዋንጫን የምንግዜም ምርጥ ብለው ባደነቁበት መግለጫ ላይ የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ቦብ ማርሌይ ብለው መጥራታቸው ከገረሙኝ አጋጣሚዎች ዋንኛው ነው፡፡ በመግለጫው ለኢንፋንቲኖ ጥያቄዬን ከማቅረቤ በፊት ስሜን ተናግሬ ከኢትዮጵያ መሆኔን ስገልፅላቸው በመጀመርያህ የት አለህ በማለት ከዓለም ሚዲያ መካከል ሲያፈላልጉኝ ቆዩና ያደረግኩትን አረንጓዴ ቢጫቀይ ኮፍያ ሲመለከቱ  ቦብ ማርሌይ፤ ቦብ ማርሌይ ነህ ወይ እያሉ ለጨዋታ ሲናገሩ፡፡ ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትኩረትን ፈጥረውብኛል፡፡ 21ኛውን የዓለም ዋንጫ የምንግዜም ምርጥ ብለው ስለማድነቃቸው ኢንፋንቲኖ  ከእኔ ጥያቄ በመነሳት በዝርዝርም በመግለጫው ላይ አብራርተውታል፡፡ በነገራችን ላይ ከጋዜጣዊ መግለጫው በኋላ ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ቦብ ማርሌይ ብለው ስላናገሩህ ተከፍተሃል ወይ ብለው የትልልቅ ሚዲያዎች በርካታ ታዋቂ ጋዜጠኞች ጠይቀውኝ ነበር፡፡ አረ ምንም ችግር የለውም፡፡ በራሽያ ቆይታዬ ያገኘኝ ሁሉ ቦብ ማርሌይ ሲለኝ ነበር፡፡ የኢንፋንቲኖ አጠራር ለጨዋታ ነው፡፡ እንደውም ደስ ብሎኛል ብየ መልሸላቸዋለሁ፡፡
በሌላ በኩል የምጠቅሰው አስገራሚ አጋጣሚ የዓለም ዋንጫ በተፈፀመበት እለት የተከሰተው ነው። ከዋንጫ ፍልሚያው ቀደም ብሎ በሚዲያ ማዕከል የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ከ9 የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ከ12 በላይ አፍሪካዊ ደም ያላቸውን ተጨዋቾች በስብስቡ መያዙን አስመልክቶ እንወያይ ነበር፡፡ ኪሊያን ምባፔ (ካሜሮን/አልጄርያ)፤ ፖል ፖግባ (ጊኒ)፤ ስቲቭ ማንዳና (ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ)፤ ብሌስ ማቱዲ (አንጎላ/ኮንጎ)፤ ኒጎሎ ካንቴ (ማሊ)፤ ኦስማን ዴምቤሌ (ሴኔጋል ፤ ማሊና ሞሪታኒያ)፤ናቢል ፌኪር (አልጄርያ)፤ ሳሙኤል ኡምቲቲ (ካሜሮን)፤ አዲል ራሚ(ሞሮኮ)፤ ቤንጃሚን ሜንዲ (ሴኔጋል)፤ ኮረንቲን ቶሊሶ (ቶጎ)፤ ጂብሪል ሲዴቤ (ሴኔጋል) እና ፕሬንሴል ኪምፔቤ (ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ) መሆናቸውን በመጥቀስ ሁላችንም አፍሪካውያን ነን በማለት ሌሎች የዓለም ሚዲያዎችን እነግራቸው ነበር። አንዳንዶቹ የሚዲያ ባለሙያዎች ይህ ሁኔታ የፈረንሳይ መድብለ ባህል የሚያሳይ መሆኑን ሲገልፁ፤ አፍሪካን የወከሉ 5 ቡድኖች በምድብ ማጣርያው በመሰናበታቸው  የፈረንሳይ ቡድን ብቸኛው የአፍሪካ ተወካይ እያሉ ያሾፉም ነበሩ፡፡ የተባበረችው አፍሪካ United states of Africa ለፍፃሜ አለፈች እየተባለም ነበር፡፡
በእኔ እምነት አፍሪካውያን ደም ያላቸው ተጨዋቾች በስደት ለሌላ አገር ብሄራዊ ቡድን በመሰለፋቸው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽንና አባል ፌደሬሽኖቹን ሊያሳስብ ይገባል ነው፡፡ በተለይ የየአገራቱ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች በሙስና የዘቀጠ እና በፕሮፌሽናል መንገድ የማይመራ አስተዳደር ለውድ አፍሪካውያን ኮከቦች ፍልሰት ምክንያት ሆኗል ብዬ ላስረዳም ሞክርያለሁ፡፡ ሳሙኤል ኡምቲቲ ለካሜሮን እንዲጫወት ሮጀር ሚላ ጥረት አድርጎ አልተሳካለትም፡፡ ኮረንቲን ቶሊሶ ለአፍሪካዊ ቡድን እንዲጫወት በክላውድ ዲ ለሮይ ጥረት ተደርጎ እምቢ በማለቱ አልሆነም፡፡ ንጎሎ ካንቴ ለማሊ እንዲጫወት በተደጋጋሚ ጥሪ ቀርቦለት አሻፈረኝ ብሏል፡፡ ስቴቨን ኖቮኒ ለኮንጎ እንዲጫወት ሁለቴ ቨተጠይቆ በመጀመርያ ለእንግሊዝ ከዚያም ለፈረንሳይ በሚጫወትበት እድል ላይ አተኩሯል፡፡ ናቢል ፍኪር ለአልጄርያ ቡድን ተመረጦ የነበረ ቢሆንም ለፈረንሳይ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታዎች ተሰለፎ እድሉን ገሸሽ አድርጎታል በማለትም ምሳሌዎችን አቅርቤላቸዋለሁ፡፡
በአጠቃላይ በፍልሰቱ ላይ የአፍሪካ እግር ኳስ አመራሮች መምከር ይኖርባቸዋል የሚል አቋሜን በማንፀባረቅ ስሞግታቸው የነበሩ የዓለም ሚዲያዎች…. ራስታ ማን …ቦብ ማርሌይ በማለት በፍፃሜው እንገናኝ እያሉ ስንሰነባበት የአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ኮፍያዬ ተነሳና ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት ባንዲራቸውን ከኢትዮጵያ ሰንደቅ መውሰዳቸውን ነግርያቸው ተለያየን፡፡
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ኮፍያዬ በዓለም ዋንጫው አዘጋጅ ከተሞች እና ስታድዬሞች፤ የሚዲያ ማዕከሎች እንዲሁም ግዙፍ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የነበረኝ ተሳትፎ ያደመቀች ነበረች፡፡  በሉዚሂንኪ ስታድዬም በጎ ፈቃደኞችን ለማመስገን በተከናወነው የስንብት ዝግጅት ላይ ዓለም ዋንጫውን ያሸነፉት የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች በዚህ ኮፍያዬ ከበጎ ፈቃደኞቹ ጋር ጨፍርውባታል፡፡ በተለይ ኡምቲቲ እና ሜንዲ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ኮፍያዬን እየተፈራረቁ በማድረግ ደስታቸውን ሲገልፁ ነበር፡፡
ራሽያ በተሳካ ሁኔታ ባዘጋጀችው 21ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት የነበረኝ ልምድ እና ተመክሮ ይህን ይመስላል፡፡ በቀጣይ ሳምንታት በራሽያ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር የተደረጉ ቃለምልልሶች ፤ በአራቱ የራሽያ ከተሞች ሞስኮ፤ ስፓርታክ፤ ሴንትፒተስበርግ እና ሶቺ ከተሞች ያደረግኳቸውን አስገራሚ ጉብኝቶች፤ ልዩ አጋጣሚዎች፤ መልካም ተመክሮዎች በልዩ ማስታወሻው ማካፈሌን ቀጥላለሁ፡፡ ይቀጥላል…

Read 1239 times