Print this page
Saturday, 04 August 2018 10:17

በጣሊያን ኤምባሲ የሚገኙት ሁለቱ የደርግ ባለሥልጣናት የምህረት አዋጁ አይመለከታቸውም ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

 ላለፉት 27 ዓመታት በጣሊያን ኤምባሲ ተጠልለው የሚገኙት ሁለቱ የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህ እና ሌተናል ጀነራል አዲስ ተድላ ምህረት እንደማይደረግላቸው ተገለፀ፡፡
የሁለቱን የደርግ ባለሥልጣናት ጉዳይ የሚከታተሉ ምንጮች ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ባለስልጣናቱ በዘር ማጥፋት ወንጀል የተከሰሱ በመሆናቸው ሰሞኑን በወጣውና ለ6 ወራት ብቻ በሚቆየው የምህረት አዋጅ ተጠቃሚ አይሆኑም ተብለዋል፡፡
በዘር ማጥፋት ወንጀል የተጠየቁ ምህረት አይደረግላቸውም በሚለው የአዋጁ አንቀፅ 28 ምክንያት ባለስልጣናቱ የምህረቱ ተጠቃሚ መሆን አይችሉም መባሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአዛውንትነት ዕድሜ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ባለስልጣናት፣ በእርጅናና በጤና መታወክ እየተሰቃዩ  መሆኑንም ምንጮች ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ በተመሳሳይ በዘር ማጥፋት ወንጀል የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ኮሎኔል መንግስቱ ሃ/ማርያም እና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ ከሠሞኑ በዚምባቡዌ-ሃረሬ ተገናኝተው መወያየታቸው የታወቀ ሲሆን ፎቶግራፋቸው በማህበራዊ ድረ ገፆች መለቀቁን ተከትሎም አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱ ተነግሯል፡፡  
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ክስ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው የነበሩ የደርግ ባለሥልጣናት ከ6 ዓመት በፊት በይቅርታ መፈታታቸው ይታወሳል፡፡   

Read 9741 times