Saturday, 04 August 2018 10:21

“ኦነግ” ትጥቁን እንዲፈታ የኤርትራ መንግስት አሳሰበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

 ላለፉት 26 ዓመታት የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የቆየው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ትጥቁን ፈትቶ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ የኤርትራ መንግስት አሳሰበ፡፡
ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ፣ የኦነግ ሊቀ መንበር የሆኑትን አቶ ዳውድ ኢብሣን በፅ/ቤታቸው ማነጋገራቸውን የጠቆሙት የዜና ምንጮች፤ ኦነግ የትግል አማራጩን እንዲያስተካክል ፕሬዚዳንቱ ማሳሰባቸውን አመልክተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ለኦነግ አመራሮች ያቀረቡት ምርጫ፣ ድርጅቱ ትጥቁን ፈትቶ ኤርትራ ውስጥ በጥገኝነት እንዲቀመጥ አሊያም ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በሠላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀስ ነው ተብሏል፡፡ የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሣ በበኩላቸውም፤ ወደ ኢትዮጵያ  ገብተው በሰላማዊ መንገድ መታገሉን እንደመረጡ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ኦነግ በቅርቡ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ማድረጉን አስታውቆ የነበረ ሲሆን የተኩስ አቁም ስምምነቱ በኢትዮጵያ መንግስት እየተጣሰ ነው ሲል መውቀሱም አይዘነጋም፡፡
በሌላ በኩል ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በኤርትራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከኦነግ አመራሮች ጋር መወያየታቸውን ሰሞኑን በአሜሪካ ሚኒሶታ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ጠቅሰው፤ ኦነግ ወደ ሃገር ቤት ገብቶ በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀስ ማግባባታቸውንም አስረድተዋል፡፡
በቀጣዩ ሣምንትም የኦነግ አመራሮችን የሚያግባባ ቡድን ወደ አስመራ እንደሚልኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

Read 12237 times