Print this page
Saturday, 04 August 2018 10:32

ከአቡነ መርቆርዮስ የፕሮቶኮል ሹም ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

  - “በግፍ በመከራ ወጥተን፤ በክብር በሞገስ ወደ አገራችን ተመልሰናል”
     - “ፓትርያርኩን ለማባረር የቤተ ክርስቲያኒቱ በጀት ለ3 ወራት ታግዶ ነበር”
     - “ጠ/ሚኒስትሩ ለቤተ ክርስቲያኒቱ በጣም ባለውለታ ናቸው”

    ከሃያ ስድስት ዓመታት በፊት በስደት ከአገራቸው ወጥተው በኬኒያ በኩል ወደሰሜን አሜሪካ የተጓዙትና ላለፉት 17 ዓመታት በሰሜን አሜሪካ የተቋቋመውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሲመሩ የቆዩት ብፁህ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ አገራቸውና ወደ መንበረ ፕትርክናቸው ተመልሰዋል፡፡ እኚህ ቅዱስ አባት በወቅቱ በነበረው መንግስት በተደረገባቸው ተደጋጋሚ ጫናና የቤተክርስቲያኒቱን በጀት ለ3 ወራት በማገድ ሠራኛውን ለከፍተኛ ችግር እንዲዳረግ በመደረጉ ምክንያት መንበራቸውን ለቀው በስደት ከአገር ለመውጣት ተገደዋል፡፡
ፓትርያርኩ ከመንበራቸው እንዲለቁ የተደረገበትን ምክንያት፣ በስደት ከአገራቸው ከመውጣታቸው በፊት የሣለፉትን ችግርና መከራ፣ በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ ለመግባት ባደረጉት ጥረት የገጠማቸውን ፈተና፣ የስደት ዘመን ሕይወታቸውንና ቆይታቸውን አስመልክቶ ከ26 ዓመታት በፊት ከፍተኛ መስዋዕትነትን ከፍለው ከአገር ያወጧቸውን የፓትርያርኩን የቅርብ ረዳትና የወቅቱ የፕሮቶኮል ሹማቸው የነበሩትን መልአከ መዊህ ልሳነወርቅ ውቤን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሣዬ አነጋግራቸዋለች፡፡


     ከሃያ ስድስት ዓመታት በፊት ፓትርያርኩ ከአገር ለመውጣት የተገደዱበት ዋነኛ ምክንያት ምን ነበር?
ሁሉንም ነገር እግዚአብሔር በሰላምና በጥሩ ነገር ስለቋጨው ብዙ ነገር ማለት አልፈልግም፡፡ ነገር ግን ብፁህ አቡነ መርቆርዮስ በቤተክርስቲያናችን ህግና ሥርዓት መሰረት በፓትርያርክነት ተመርጠው ለ3 ዓመታት ያህል በመንበረ ፓትርያርክ ውስጥ አገልግለዋል፡፡.. የመንግስት ለውጥ ሲደረግ አዲሱ መንግስት ከእኚህ ፓትርያርክ ጋር አብሮ ለመስራት የማይፈልግ መሆኑን በተደጋጋሚ በተለያዩ መንገዶች ሲያሳይና መንበራቸውን ለቀው እንዲወጡ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እሳቸው ስለታመሙ እየባረኩ ይረፉ፤ ሥራውን ግን  ሲኖዶሱ ተረክቦ ይምራው በሚል በአቡነ ዜና ማርቆስ የሚመራና አምስት ሊቃነጳጳሳት በአባልነት ያሉበት ኮሚቴ በነሐሴ 28 ቀን 1983 ዓ.ም ተቋቋመ፡፡ በመቀጠልም ፓትርያርኩ መንበሩን ለቀው እንዲወጡ በደብዳቤ ተጠየቁ፡፡ የቤተ/ክርስቲያኒቱ ቀኖና በዚህ መንገድ ጥሎ መሄድን የማይፈቅድ በመሆኑ ሁሉን ነገር በመታገስና በፀሎት ለጥቂት ጊዜ በመንበራቸው ላይ ለመቆየት ጥረት አደረጉ፡፡ በመጨረሻ ግን የቤተ/ክርስቲያኒቱ በጀት እንዲታገድ በመደረጉና ለ3 ወራት ያህል ለሠራተኛው የሚከፈለው ደሞዝ ሁሉ ጠፍቶ ከፍተኛ ችግር በመፈጠሩ ምክንያት ፓትርያርኩ መንበራቸውን ጥለው ለመውጣት ተገደዱ፡፡ እሳቸው ከወጡ በኋላ በጀቱ እንዲለቀቅ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በአቶ ታምራት ላይኔ ፊርማ ትዕዛዝ የተሰጠበት ወረቀት በእጄ ይገኛል፡፡
ከመንበራቸው ከለቀቁ በኋላ በቀጥታ ወደ ውጪ አገር ነው የሄዱት?
አልሄዱም፡፡ በመስከረም ወር ከመንበራቸው ከለቀቁ በኋላ እሳቸውን ደብቆና ሰውሮ ማቆየቱ እጅግ በጣም ፈታኝ ነገር ነበር፡፡ ያንን ክፉና አስቸጋሪ ዘመን ያለፍነው ሰዋራ በሆነ ሥፍራ ላይ በሚገኝ በአንድ የእስልምና እምነት ተከታይ በሆኑ ሼክ ቤት ውስጥ ነበር፡፡፡ በዚህ ቤት ውስጥ ለአንድ ዓመት ከአራት ወራት ያህል ስንቆይ የፓትርያርኩን በዚያ ሥፍራ መኖር እጅግ በጣም ጥቂት ከሆኑና በጣት ከሚቆጠሩ ሰዎች በስተቀር የሚያውቅ ሰው አልነበረም፡፡ በዚህ ቤት እስከ መስከረም 30 ቀን 1985 ዓ.ም ማለትም አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ሆነው እስከ ተሾሙበት ጊዜ ድረስ ቆይተናል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በአገር ውስጥ መቆየቱን ለፓትርያርኩ ህይወት አደገኛ ሆኖ በመገኘቱ ከአገር ለመውጣት ተገደድን፡፡
ከአገር የወጣችሁትስ በምን መንገድ ነው? ፓትርያርኩስ ከአገር የመውጣቱን ሃሳብ እንዴት ተቀበሉት?
ትልቁ ፈተና ይህንን ለሳቸው ማሳመኑ ነበር፡፡ እዚህ አገሬ ላይ እሞታለሁ እንጂ የትም አልሄድም ብለው በጣም አስቸግረው ነበር፡፡ የስደታችን ዋነኛ ዓላማ የአንድን ሰው ሕይወት ከሞት ለማትረፍ አልነበረም። የቤተክርስቲያኒቱን ቀኖና የመጠበቅ ጉዳይ ነበር፡፡  ብፁህ አቡነ ቴዎፍሎስን ደርግ ይዞ ገደላቸው፡፡ ስለሞቱ ቀኖናው መጣሱን ብዙ ሰው አያውቅም ነበር፡፡ ጠያቂም አልነበረም፡፡ ያኔ ጠያቂ ቢኖር ኖሮ፣ ይህ አሁን በአቡነ መርቆርዮስና በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የተፈፀመው የህግ ጥሰት አይፈፀምም ነበር፡፡ አሁን እኚህ አባት ተርፈው በስደት ከአገራቸው መውጣት በመቻላቸው ሣቢያ የቀኖናውን መጣስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያውቀው ችሏል፡፡ ፓትርያርክ በህይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ ሊሾም አይገባም፡፡ እናም ዋነኛ ዓላማችን ይኸው ነበር፡፡ ከአገር ለመውጣት ስናስብ አስቀድሜ እኔ ሁኔታዎችን ማጥናትና ነገሮችን ማመቻቸት ጀመርኩ። ወደ ሞያሌ እየተመላለስኩ ነገሮችን አጠናሁ፡፡ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ወቅት ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ሞያሌ ድረስ 14 ያህል ከፍተኛ ፍተሻ የሚደረግባቸው ኬላዎች ነበሩ። እናም ለእሳቸው፣ ለእኔና ለሾፌራችን የይለፍ ወረቀቶችን አዘጋጀሁ፡፡ ፓትርኩን እንደ አንድ የአብነት መምህር አለባበሰ አለበስኩና፣ ትልቅ ሻሽ እንዲጠመጥሙና ራሳቸውን በተወሰነ መልኩ እንዲቀይሩ አድርጌ፣ በቀድሞ ስማቸው መታወቂያ ተዘጋጅቶላቸው ፈታሾቹ እንዳያውቁን ሆነን ነው የፍተሻ ጣቢያዎቹን ያለፍነው፡፡ መቼም በየፍተሻ ጣቢያው የነበረውን ጭንቀትና ፀሎት አሁን ሲናገሩት ቀላል ይመስላል፡፡ ግን በጣም ከባድ ነበር፡፡ በተለይም እኔ እሳቸውን ከአገር ለማስወጣት ኃላፊነቱን ወስጄና “ተው ይቅርብኝ” ሲሉን በግድ አሳምኜ ይዤ ስለመጣሁ ጭንቀቴ ከባድ ነበር። አስራ አራቱን የፍተሻ ጣቢያ በፀሎት አልፈን 10 ሰዓት ላይ ሞያሌ ደረስን። ማታ ሲጨላልም በጫካ በኩል በእግራችን እኔና እሳቸው ብቻ ኢትዮጵያ ሞያሌን ተሻግረን ኬኒያ ሞያሌ ገባን። ከዛም ሁሉንም ነገር አዘጋጅቼ ስለነበር ከቦረና ወደ ኬኒያ ለእርድ ከሚሄዱ ከብቶች ጋር እሳቸውን ገቢና እሳፍረን እኛ ከከብቶቹ ጋር ከኋላ ተጭነን ኬኒያ ኢሲኦል የሚባል ከተማ ገባን፡፡ ከዛ በመኪና ተሳፍረን ናይሮቢ ገባንና ከሁለት ቀን በኋላ ለኬኒያ መንግስትና ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስደተኞ ከፍል እጃችንን ሰጠን፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከእኛ ቀደም ብሎ የገቡትን ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ያሣረፉበት ሴንት ጁሊያን የሚባል ከናይሮቢ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በጫካ ውስጥ የሚገኝ ገዳም ውስጥ አስገባን፡፡ ለበርካታ ዓመታትም በዚያው ቆየን፡፡
በወቅቱ ወደ አሜሪካና ሌሎች አገራት ለመሄድ አስቸጋሪ ጉዳይ ስለነበር ማለትም የኢትዮጵያ መንግሰት ከየአገራቱ ጋር በነበረው ወዳጅነት ሳቢያ ሁኔታዎች ጥሩ ስላልነበሩ እዛው ኬኒያ ውስጥ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ቆይተናል፡፡ በመጨረሻም በቅድሚያ እሳቸው ደህንነቱ ወደተረጋገጠበት ስፍራ መሄድ የግድ ስለነበረባቸው ብቻቸውን ወደ አሜሪካ እንዲሄዱ ከፍተኛ ጥረት አደረግን፡፡ ምክንያቱም ቁጥራችን ከበዛ ሊፈቀድ አይችልም በሚል ስጋት ማለት ነው፡፡ እናም እግዚአብሔር ረድቶን እሳቸው ወደ አሜሪካ አንዲገቡ ፍቃድ አገኙ፡፡
ብቻቸውን ወደዚያ ሲልኩአቸው ስጋት አላደረብዎትም?
ሥጋቱ ነበረኝ፡፡ ግን እዚያም ቀደም ሲል በአገር ውስጥ ሣሉ የሚያውቋቸውና በእሳቸውም ሆነ በቤተክርስቲያኒቱም ላይ የተፈፀመውን በደል አጥብቀው የሚቃወሙ አባቶች ስለነበሩ እነሱ እንደእኔ ሆነው እንደሚጠብቋቸው አምን ነበር፡፡ እውነትም በጥሩ ሁኔታ ተቀብለው፣ በጥሩ ሁኔታ ሲንከባከቧቸው ቆይተዋል፡፡
ከዓመታት በኋላ የገጠማቸውን ህመም በማስታመም በመንከባከብና ከጎናቸው በመሆን ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉ በርካታ አባቶች ነበሩን፡፡ በዚህ መንገድ አሜሪካ ከገቡ በኋላ በዚያ የተቋቋመውን ቅዱስ ሲኖዶስ በመምራት እስከ አሁን ድረስ ቆይተዋል። አሁን ያው ዕድሜውም የጤንነቱ ሁኔታም ትንሽ አደካከሟቸዋል፡፡
ያን ጊዜ በዚህ መንገድ ከአገር ወጥታችሁ አሁን ደግሞ እንደዚህ ወደ አገራችሁ ስትመለሱ ምን ተሰማችሁ? የፓትርያርኩስ ስሜት እንዴት ነው?
ለእኔ ከአዕምሮ በላይ ነው፡፡ ይህንን ለመናገር ቃላትም የለኝም፡፡ ያኔ የነበረውን ፈተናና መከራ ሳስታውስ፣ አሁን ደግሞ ያለሁበትን ሁኔታ ሳስብ፣ ያኔ በሞያሌ በኩል ከአገር ለመውጣት ድንበሩን ለመሻገር ያየነውን…መከራ አሁን ደግሞ ይህን በመሰለ ክብር በዚህ ደስታ ወደ አገራችን ለመመለስ መቻላችንን… ሳይ ለእኔ የተአምር ያህል ነው፡፡ በግፍ በመከራ ወጥተን እንደገና በክብር በሞገስ ወደ አገር መመለስ መቻል፣ ለእኔ የህልም ያህል ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አንግቦ በሚምዘገዘግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጋር አብረን በክብር ወደ አገራችን መመለስ መቻላችን፣ ከመጣን በኋላ ደግሞ በቅድስት ስላሴና በመንበረ ፓትርያርክ ያለው ያቀባበል ስነስርአት ሳይና ከቀድሞ ጋር ሣነፃፅር ለእኔ የተአምር ያህል ነው፡፡ የእሣቸውም ስሜት ይኸው ነው፡፡ እጅግ ተደንቀዋል፡፡ ለሃያስድስት ዓመታት ቤተክርስቲናችን ለሁለት ተከፍላ አባቶች ሲወገዙ ምዕመኑ ለሁለት ተከፍሎ እርስ በርስ ሲነቋቆር ማየቱ ውርደት ነው፡፡ ሃዘን ነው፡፡ አሁን ያ ሃዘናችን ሻረ፡፡ ቤተክርስቲያናችን ወደቀደመው ክብሯ ተመልሳለች፡፡ አንድ ሆናለች፡፡ ይህንን ሳይሞቱ በህይወት ማየት ትልቅ ፀጋና ክብር ነው፡፡ በዚህች ምድር ላይ ከዚህ በላይ የሚያስደስት ነገር ምን አለ?
እዚህ ከመጡ በኋላ ያዩት ነገር ምን ይመስላል? አንድነቱ ምን ያህል ተቀባይነት አግኝቷል ብለው ያስባሉ?
ደስ የሚል ነገር ነው ያለው፡፡ አቡነ ማቲያስ ሲናገሩ ከፓትርያርኩ አቡነ መርቆሪዮስ ጋር በቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን አብረው ሲያገለግሉ እንደነበርና የሚግባቡ ጓደኛሞች እንደነበሩ፣ ሁሉቱም በብፁህ ወቅዱስ አቡነተክለሃይማኖት በአንድ ቀን ጵጵስና እንደተሾሙ ሲናገሩ ነበር። ከአባቴ፣ ከጓደኛዬና ከወንድሜ ጋር በዚህ መንገድ ስለተገናኘሁ ደስታዬ ወሰን የለውም፣ አብረን በፍቅር እንኖራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በእርግጥም ይህ ለሳቸውም ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በአቡነ ጳውሎስም ተሞክሮ ነበር፡፡ ግን አልሆነም። እድለኛ ሆነው በእሳቸው ዘመን ተሳካ። በዚህ በጣም እድለኛ ናቸው፡፡
አሁን ወደ አገር ቤት የመጡት ጳጳሣት ምን ያህል ናቸው?
ብፁዕ ፓትርያርኩን ተከትለው 16 ሊቃነጳጳሳትና የቤትርክስቲያን ሊቃውንት፣ መምህራንና የሽምግልና ኮሚቴዎች በአጠቃላይ 42 ሰዎች ናቸው የመጡት፡፡
ለዚህ እርቅ መሳካት ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ናቸው፡፡ እንደው ስለእሳቸው ምን የሚሉት ነገር አለ?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ መድሃኒት አድርጎ የላካቸው ይመስለኛል፡፡ እስራኤላውያን ለ400 ዓመታት በግብፅ ባርነት ሲሰቃዩና ብዙ ግፍ ሲፈፀምባቸው እግዚአብሄር ለእስራኤላውያን መድሃኒት አድርጎ የላከላቸው ሙሴን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድም እንደዚሁ ይመስሉኛል፡፡
የኢትዮጵያን ህዝብ ለማዳን የላካቸው መልእክተኛ ማለቴ ነው፡፡ በዘር፣ በሃይማኖትና በጎሣ ተከፋፍለን ብዙ መከራዎችን አይተናል። ብኩርናችን ተነስቶ ተመሰቃቅለናል፡፡ እኚህ ሰው ከመጡ በኋላ የምንሰማው ነገር ግን የተለየ ሆኖብናል፡፡ የእግዚአብሔር ስም በመሪ ሲነሳ መስማት ችለናል፡፡ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያላቸውን አክብሮትም እጅግ በጣም አስደስቶናል፡፡ ለቤተክርስቲያኒቱ በጣም ባለውለታ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር አገራችንን ይባርክ። የቤተክርስቲያናችንን አንድነት ይጠብቅ።

Read 1609 times