Saturday, 04 August 2018 10:39

“ለውጡን በሰከነ መንገድ መምራት ይገባናል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 - ለውጥ ያስፈልጋል ካልን፣ የተለሳለሰ ለውጥ የሚባል ነገር የለም
 - ህዝቡ ከእንግዲህ በፀረ-ዲሞክራሲያዊ መንገድ አልገዛም ብሏል
 - የመንግስት ሚዲያዎች ትልቅ ስካር ውስጥ ነው ያሉት
 - ለውጥ አንፈልግም የሚሉትም ቢሆኑ ሃሳባቸው መሰማት አለበት
 - በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ጭቆና እንደ ዶ/ር ዐቢይ የገለፀ መሪ አላውቅም
 - የትግራይ ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል

    የህወኃት አንጋፋ ታጋይና የቀድሞው የአየር ሃይል አዛዥ ሜጀር ጀነራል አበበ ተክለሃይማኖት፤ የኢትዮጵያን ህዝብ የትግል እንቅስቃሴ በመደገፍ ይታወቃሉ፡፡ ኢህአዴግ ራሱ ያፀደቀውን ህገ መንግስት እየጣሰ መሆኑን በመግለፅም ህገመንግስቱ እንዲከበር አበክረው ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡ ትክክለኛው ለውጥ የሚመጣው በወጣቱ ሃይል ነው የሚል ፅኑ አቋምና እምነት ያላቸው የፖለቲካ ምሁርና ተንታኝም ናቸው፡፡  ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በታዩ የለውጥ ጅማሬዎችና በአጠቃላይ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታው ላይ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ጥልቅ ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ እነሆ፡-

     ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ እየታዩ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን እንዴት ይመለከቷቸዋል?
የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ ይፈልግ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ፀረ- ዲሞክራሲያዊ የሆነ ሁኔታ በጣም ነበር የሠፋው፤ ፍትህ የታጣበት፣ ሙስና የሰፋበት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ መብት የታፈነበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ ስለዚህ ለውጥ ያስፈልግ ነበር፡፡ ለውጥ ሁልጊዜ በተለያዩ ሃገሮች በተለያየ መንገድ ነው የሚመጣው፡፡ በሃገራችን በተለይ በእነዚህ 3 አመታት የነበረውን ሁኔታ ስናየው፣ ከሞላ ጎደል በህዝቡ ተነሣሽነት የመጣ ለውጥ ነው። እንዲህ ያለውን ለውጥ መሪ አልባ ለውጥ ወይም ማህበረሠብ- መር ለውጥ ልንለው እንችላለን። ከ2008 ጀምሮ ነው ትግሉ የተጠናከረው፡፡ እርግጥ ነው ከ2008 በፊት በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች፣ የትግራይን ክልላዊ መንግስት በመቃወም የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ ከዚያ በኋላ በኦሮሚያ፣ በአማራና በተለያዩ ቦታዎች ሠፍቶ ታይቷል፡፡
የለውጡ እንቅስቃሴ በከተማ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በገጠርም ጭምር ነው፡፡ ያካለለውም ከከተማ እስከ ገጠር ነው፡፡ ለውጥ ያስፈልግ ነበር፤ አሁን የለውጥ ጅማሮ አለ፡፡ ዋናው ለውጥ ግን ገና ነው፡፡
የለውጥ ጅማሮ ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
የለውጥ ጅማሮ ሲባል አግላይ የነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ቢያንስ በከፍተኛ ደረጃ ሲታይ አካታች መሆን ጀምሯል፡፡ ሙሉ ለሙሉ አካታች ባይሆንም ጅምሩ ጥሩ ነው፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች እንዲሣተፉ ጥሪ ተደርጎላቸው እየመጡ ነው፡፡ እስረኞች በብዛት ተፈትተዋል። መከላከያ ገለልተኛ እንዲሆን አዲስ መመሪያ ተሰጥቶታል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፈፃሚው ጋር የኮንትራት ግንኙነት እንዲኖረው ተወስኗል፡፡ ግን ይሄ ገና ከላይ ያለ ነገር ነው፤ ብዙ ብዥታዎች ያለበትም ነው፡፡ ወደ ታች መውረድ ይቀረዋል። የአካታችነቱም ጉዳይ ቢሆን አካታች መሆን ጀምሯል እንጂ ገና ሙሉ ለሙሉ አካታች አልሆነም፡፡ አሁንም የለውጥ ስካር፣ የለውጥ ሙቀት አለ፡፡ በሌላ መንገድ ዶ/ር ዐቢይ የሚሉትን ብቻ የሚያስተናግድ ሚዲያ አለ፡፡ ሌላ አመለካከት ያለው ሁሉ እንደ ሃጢያት፣ ፀረ ለውጥ አድርጎ የማየት ሁኔታ አለ፡፡ ድሮ ዶ/ር ዐቢይ ከመምጣታቸው በፊት ትምክህተኛ፣ ጠባብ፣ ኪራይ ሰብሳቢ እየተባለ የሚገለፀው አሁንም በሌላ መልክ እየተፈጠረ ነው፡፡ ፍቅር እያሉ ጥላቻን የሚነዙ፣ የለውጥ አርበኞች ነን እያሉ፣ ፀረ ለውጥ አግላይ እንቅስቃሴዎች የሚያደርጉ አሉ፡፡ ስለዚህ አሁንም ልንል የምንችለው የለውጥ መንፈስ አለ ነው፤ ለውጡ በተወሠነ ደረጃም የተጀመረ ነገር አለው፤ ነገር ግን እንደ ማንኛውም ለውጥ የሚቀረው ብዙ ጉዳይ አለ፡፡ ከፀጥታ አኳያ አንዳንድ ቦታ ችግር አለ፤ ዘር ተኮር ጥቃት አለ፣ ህግን መጣስ አለ፡፡ በእርግጥ ቄሮ መንግስትን ለማፍረስ ነው የተቋቋመው፤ አሁን ደግሞ በቀላሉ ተመለስ ቢባል የሚቻል አይሆንም፡፡ ሰፊ ሥራና ውይይት ይጠይቃል። በዚያው ልክ ለቄሮ ትግል መነሻ የሆኑ ጥያቄዎችም ገና አልተመለሱም። የስራ አጥነት፣ የፍትህ ማጣት ጥያቄዎችም ገና አልተመለሱም፡፡ ስለዚህ የተለያዩ ተግዳሮቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡
ይህ የለውጥ ጀማሮ በቀጣይ ወዴት የሚያመራ ይመስልዎታል?
አሁን ወደ ዋናው ለውጥ እየተሸጋገርን ስለሆነ የተለያዩ የሚዘበራረቁ ነገሮች ይኖሩታል። መጀመሪያ መመለስ ያለብን ነገር፣ ለውጡ ያስፈልጋል አያስፈልግም የሚለውን ነው፤ ለውጥ ያስፈልጋል ካልን፣ የተለሣለሠ ለውጥ የሚባል ነገር የለም፡፡ አጠቃላይ ሂደቱ ግን ሲታይ አሁን ጥሩ ጅማሮ ላይ ነን፤ ህዝቡ ከእንግዲህ በፀረ ዲሞክራሲዊ መንገድ አልገዛም ብሏል፡፡ ሁለተኛ፤ አሁን ከተስፋ መቁረጥ ወደ ተስፈኝነት የመሸጋገር ነገር ይታያል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ እንደኛው ሰው ናቸው፤ ጉድለቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ጉድለቶቹ ላይ አይደለም አተኩረን እሣቸውን ለመመዘን መሞከር ያለብን፤ ያለውን አጠቃላይ መንፈስ እያየን ነው ወደፊት መጓዝ ያለብን፡፡ አሁን እየተፈጠረ ያለው የህግ የበላይነት ያለመከበር ችግር መቀረፍ መቻል አለበት፡፡ የመንግስት ባለስልጣናትም ህዝቡም የህግ የበላይነት እየተከበረ እንዲሄድ ማድረግ አለባቸው፡፡ አካታች ፖለቲካን እስከተከተልን ድረስ የለውጡ ጅማሮ ተስፋ የሚሰጥ ነው፤ አግላይ ከሆነ ግን የባሠ ችግር ነው የሚፈጥረው፡፡ በአጠቃላይ ለውጥ በአንድ ጊዜ የሚመጣ አይደለም፤ በትንሽ ተጀምሮ እያበበ እየፈካ የሚሄድ ነው፡፡
አሁን ባለው የለውጥ እንቅስቃሴ የተገለለ ቡድን አለ ብለው ያምናሉ?
ለውጥ አለ የሚል ሃይል በአንድ ወገን አለ። ለውጥ የለም የሚል በሌላ በኩል አለ፡፡ ለውጡ በዚህ መንገድ መሄድ የለበትም የሚል ደግሞ በሌላ ወገን አለ፡፡ አሁን እነዚህን ሁሉ አመለካከቶች የሚያካትት፣ ለሃሳብ ብዝሃነት ቦታ የሚሰጥና የሚያከብር ለውጥ መኖር አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ነው አግላይ አይደለም አካታች ነው ልንል የምንችለው፡፡ በተለይ በሚዲያዎች በኩል እነዚህን የተለያዩ ሃሳቦች ያለማስተናገድ ዝንባሌ እየተመለከትን ነው፡፡ የለውጡ ደጋፊዎች ነን የሚሉት ሌላውን በሙሉ እንደ ሃጢያት የመኮነን እንቅስቃሴ ነው የሚያደርጉት፤ ሌላውን ሃሳብ የጥፋት መንገድ አድርገው ነው የሚያዩት። በተለይ ሚዲያ አካባቢ ትልቅ ችግር ነው ያለው። የመንግስት ሚዲያዎች ሰክረዋል፤ ትልቅ ስካር ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ለውጥ አንፈልግም የሚሉትም ቢሆኑ መድረክ አግኝተው ሃሣባቸው መሰማት አለበት፡፡ ሃሳባቸው ተሠምቶ ገዢ ካልሆነ ህዝቡ ራሱ ውድቅ ያደርገዋል፡፡ በተለይ ሚዲያ አካባቢ ያለው የስካር መንፈስና የአግላይነት ዝንባሌ አደገኛ ነው፡፡ በጊዜ መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው። ካልተስተካከለ የቀድሞ አግላይነት መልኩን ቀይሮ ይመጣል ማለት ነው፡፡ ለውጥ በአግባቡ ካልተመራ ለውጡ ራሱ ይሠክርና ፀረ ለውጥ ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው የትኛውም ለውጥ ሲጀመር ይሠክራል፤ ቀስ እያለ ነው የሚሠክነው። አሁን የኛም ለውጥ እየሠከነ፣ ከስካሩ እየተላቀቀ መሄድ አለበት፡፡
ኢህአዴግ ውስጥ በራሱ ለውጥ ደጋፊና ለውጥ የማይፈልጉ ቡድኖች መፈጠራቸውን እንዴት ይመለከቱታል? በቀጣይስ ምን ሊፈጠር ይችላል?
ይሄን ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር ማየት ነው ጥሩ፡፡ አሁን  የፖለቲካ አሠላለፍ ለውጥ አጠቃላይ በሃገሪቱ እየመጣ ነው። ይሄን ለኔ እንደ አንድ በጎ ነገር ነው የማየው። በፌደራል ደረጃ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች ከውጭ ወደ ሃገር ቤት ገብተዋል፣ ለመግባትም ያኮበኮቡ አሉ። ለምሳሌ ኦሮሚያ ውስጥ የተለያዩ ሃይሎች፤ የተለያዩ አመለካከቶች ይዘው ገብተዋል፡፡ ትግራይም፣ አማራ ክልልም በተመሳሳይ፡፡ በአንድ በኩል በስልጣን ላይ የቆዩትም በመድረኩ አሉ። ስለዚህ በሃገሪቱ አሁን የሃይል አሠላለፍ እየተቀየረ ነው። ብአዴን ከአብን (የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ) ጋር በምን ላይ የጋራ መግባባት አላቸው? በምን ላይ አብረው ሊሠሩ ይችላሉ? የሚለው ገና አልለየም፡፡ በትግራይም ህወኃት ከአረና ወይም ትዲት (የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር) በተመሳሳይ፡፡ ብአዴን እና አብን አንድ ላይ ሊዋሃዱ ወይም ሊተባበሩ ይችላሉ፡፡ ኦህዴድ እና ኦነግ ሊዋሃዱ ወይም ሊተባበሩ ይችላሉ። አሠላለፉ ገና ባይለይለትም አዲስ አይነት አሠላለፍ ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ኢህአዴግ አሁን የሚለካው ባቀረበው ፕሮፖዛል ነው፡፡ እሡ ስፖንሰር ያደረገው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አለ፡፡ ከዚህ አንፃር ስለካው አሁን ኢህአዴግ የሚል በፎርም (ቅርፅ) ሊኖር ይችላል፡፡ በተግባር (በቁም ነገር ደረጃ) ግን የለም፡፡ ምክንያቱም ህገ መንግስቱን የሚያከብር ኢህአዴግ አሁን የለም፡፡ ህወኃትም፣ ኦህዴድም፣ ብአዴንም፣ ደኢህዴንም ህገ መንግስቱን እየጣሱ ነው፡፡
በዚህ አካሄድ ኢህአዴግ ወዴት የሚያመራ ይመስልዎታል?
ኢህአዴግ የሚታወቅበት የራሱ ፕሮግራም አለ፡፡ በሌላ በኩል ህገ መንግስቱ አለ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ከመምጣታቸው በፊት ኢህአዴግ ህገ መንግስቱን ሲጥስ ነው የኖረው፤ በቁም ነገር ይሠበሠባል፤ ውሳኔ ያሣልፋል፤ ነገር ግን ህግ አያከብርም ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በሁሉም ድርጅቶች ውስጥ ለውጥ የሚፈልጉ አሉ፤ በዚያው ልክ ደግሞ የለም የድሮው ይሻለናል የሚሉ አሉ፡፡ ህወኃት ውስጥ ለውጥ የሚፈልጉ አሉ፤ በሌላ በኩል የለም የድሮ ይሻለናል የሚሉ የድሮ አመራሮች አሉ፡፡ ብአዴንም፣ ኦህዴድም በተመሳሳይ፡፡ ስለዚህ አሁን ኢህአዴግ ከተቀየረ በአጠቃላይ አሠላለፉ ነው የሚቀየረው፡፡  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህገ መንግስቱን ወይም ፌደራላዊ ስርአቱን እንዴት ነው የሚያየው የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአማራ ክልል ህገ መንግስቱ አይወክለንም የሚሉ ሃይሎች አሉ፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ወዴት ያመራል ለሚለው ምናልባት አሠላለፉ ተቀይሮ አዲስ ኢህአዴግ ሊፈጠር ይችላል፡፡
የትግራይ ፖለቲከኞችና ምሁራን ከህወኃት ጋር በቅርቡ ያደረጉትን ምክክር እንዴት ያዩታል?
በእርግጥ እኔ የተሣተፍኩት በትግራይ ምሁራን ስብሰባ ላይ ሳይሆን የትግራይ ወጣቶች ባዘጋጁት ውይይት ላይ ነው፡፡ ትግራይ ውስጥ እስከዛሬ የመሠለንን ሃሳብ ለመግለፅ እድል አልነበረንም ነበር። የለውጡ ንፋስ እኛም ያለንን አስተያየት እንድንገልፅ እድል የሰጠ ነው ማለት ይቻላል። የተሠበሠብንበት አላማም አስተያየታችንን ለማቅረብ ነው፡፡ አንዳንዶች ተሰብስበን ለውጡን ለመቃወም ያቀድን ይመስላቸዋል ግን አይደለም። በዋናነት ለውጡ እንዴት ይቀጥል? በዶ/ር ዐቢይ የሚመራው ለውጥ ላይ ያለንን አስተያየት እንድናቀርብ ነው እድሉን ያገኘነው፡፡
እኛ ለውጥ ያስፈልጋል፤ ለውጡም ተጀምሯል የሚል እምነት አለን፡፡ ትግራይ ውስጥ እስካሁን የነበረው ፀረ ህገ መንግስት አካሄድ ነበር፤ ከዚህ በኋላ ግን መስተካከል አለበት የሚል ሃሳብ ነው የሠነዘርነው፡፡ ለውጡን የሚደግፍ በአንድ ወገን፣ ለውጡን የማይደግፍ በሌላ ወገን አለ፡፡ እኛ ደግሞ  ለውጥ ያስፈልገናል፤ ለውጡ ይጠቅመናል ትግራይ ውስጥ ለውጥ በምን አይነት መንገድ ነው መካሄድ ያለበት? ትግራይ ውስጥ ያለውን ፀረ ለውጥ እንቅስቃሴ ህዝቡ እንዴት ማየት ይገባዋል? የሚሉ ሃሳቦች ናቸው የተነሡት፡፡ ትግራይ ውስጥ ቀደም ሲል ህገ መንግስት ይጥሱ የነበሩ ሰዎች፤ ህገ መንግስት ይከበር ማለታቸው ለኔ ቀልድ ነው፤ ህዝቡ ማለቱ ግን ተገቢ ነው፡፡ የትግራይ ወጣቶች ባዘጋጁት ስብሰባ ላይ ሰፊና ጠቃሚ ውይይት ተደርጓል፡፡
እርስዎ የህወኃትን ወቅታዊ የፖለቲካ ቁመና እንዴት ይገመግሙታል?
የህወኃትን ነጥዬ ከመመልከቴ በፊት ኢህአዴግ በአጠቃላይ ሲታይ፤ ኢህአዴግ እንደ ኢህአዴግ የለውጥ ሃይል አይደለም፡፡ ብአዴን ለውጥ እንፈልጋለን ይላል፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ የሚሠሩት ነገር ፀረ ለውጥ ነው፡፡ አማራ ውስጥ ፀረ ትግራይ እንቅስቃሴ ሲደረግ በቸልታ እያዩ ነው፡፡ ኦህዴድ ውስጥ መሪዎቹ የለውጥ መሪዎች ናቸው፤ ነገር ግን በውስጡ ችግር አለበት፡፡ ብአዴን ገና በለውጡ ላይ ማንነቱ በግልፅ ያልታወቀበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡፡ በተመሳሳይ ህወኃት ውስጥም ለውጥ የሚፈልጉ ለምሳሌ ሊቀመንበሩን ብንወስድ አሉ። በዚያው ልክ  ለውጡን የማይፈልጉ አሉ። ስለዚህ የህወኃት አካሄድ ገና ጠርቶ አልተገለጠም። ጡረታ የወጡ አመራሮች የራሳቸውን እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ እንቅስቃሴያቸው ሠላማዊ እስከሆነ ድረስ መብታቸው ነው፡፡፡ አሁን ትልቁ ችግር እነዚህን ከትግራይ ህዝብ ጋር አንድ አድርጎ ማየቱ ነው፡፡
ለኔ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፤ በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ጭቆና የገለፀ መሪ አላውቅም፡፡ ነገር ግን በዚያው ልክ በሌላ ጊዜ የሚጠቀሙባቸው አገላለፆችና ቃላት መጥፎ አንደምታ ሲፈጥሩ እየተመለከትን ነው። ለምሳሌ በትግራይ የተደበቁ ወንጀለኞች አሉ፤ ልንይዛቸው ብንፈልግ ከትግራይ ህዝብ ያጣሉናል ማለታቸው አንደምታው ጥሩ አይደለም፡፡ መረጃው እስካላቸው ድረስ የትግራይ ህዝብ ሌባን አይሸሽግም፤ ስለዚህ የትግራይ ህዝብን የሌባ ደባቂ አድርገው መግለፃቸው ተገቢ አልነበረም። በጡረታ የተገለሉት ለውጡን የሚፈልጉ አይመስለኝም፡፡ ይህን ባለመፈለጋቸው ግን የተለየ ነገር ሊደርስባቸው አይገባም፡፡ በዚያው ልክ ግን የፈፀሙት ወንጀል ካለ በህግ ሊጠይቁ ይገባል። የትግራይ ህዝብ ዶ/ር ዐቢይን ተቀብሎ ነበር፤ ነገር ግን እነዚህ አደናጋሪ ንግግሮች ህዝቡን ወደ ፀረ ለውጥ እንቅስቃሴ እንዳያሠልፈው መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
ሠሞኑን በትግራይ የተካሄደውን ሠልፍ እንዴት ያዩታል?
አጠቃላይ ሠልፉ ለኔ አንድ የለውጥ ሠልፍ ነው፡፡ በትግራይ ሠልፍ አይፈቀድም ነበር፡፡ ለገዥው ፓርቲ ድጋፍ ካልሆነ በስተቀር እንዲህ ያለ ሠልፍ አይፈቀድም ነበር፡፡ ይሄን ሠልፍ ያመጣው የለውጡ ንፋስ ነው። በዚህ ሠልፍ ላይ ህገ መንግስቱ ይከበር መባሉ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ህገ መንግስቱ እንዲቀየር የሚፈልግ አካል ቢኖር እንኳ እስኪቀየር ድረስ ማክበር አለበት፡፡ ህገ መንግስቱ መከበር አለበት የሚለው ከዚህ አንፃር የህዝቡ ትክክለኛ መልዕክት ነው፡፡ ፀረ ለውጥ ሃይሎች ይሄን አጋጣሚ መጠቀሚያ ሊያደርጉት የሚችሉበት እድል ይኖራል፡፡ ትግራይ ውስጥ ህገ መንግስት እንደተከበረ፣ በሌላው ግን እየተጣሠ እንደሆነ አድርገው ሊጠቀሙበት ይችላል፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን ህዝቡ ባገኛት ትንሽ ነፃነት፤ ሰልፍ ማካሄድ እንደቻለ ያየንበት አጋጣሚ ነው፡፡
ከኤርትራ ጋር በተፈፀመው እርቅ ላይ ምን አስተያየት አለዎት? እርስዎ ደጋግመው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄን ያነሣሉ፡፡ አሁን የተፈጠረው እርቅና የእርስዎ ጥያቄ እንዴት ይጣጣማል?
የአሁኑ ስምምነት የአልጀርስን ስምምነት ማዕከል ያደረገ ስለሆነ በደንብ ካልታሠበበት አደገኛ ነው። ምክንያቱም የአልጀርስ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚፃረር ነው፡፡ በሁለት መንገድ ይፃረራል፡፡ በአንድ በኩል አሸናፊና  ተሸናፊን አንድ አድርጎ ይመለከታል፤ ወራሪና ተወራሪን አንድ አድርጎ ነው የተመለከተው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የባህር በርም፣ የኢትዮጵያን ድንበርም አሣልፎ የሠጠ ስምምነት ነው። ይሄ ስምምነት መሰረዝ አለበት፡፡ የባህር በር ጉዳይ የድንበር ጉዳይም ነው፡፡ የኢሮብ ማህበረሰብ ለሁለት መከፈል አይፈልግም፡፡ ስለዚህ የአልጀርስ ስምምነት የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሠጠ ነው። እኔም ሁለተኛ ድግሪዬን የሠራሁት በዚህ ውሳኔ ላይ ነው፡፡ ውሳኔው እጅግ አሳፋሪ ነው፤ ጥፋቱ ደግሞ በወቅቱ የነበረው መንግስት ነው፡፡ የአሁኑ መንግስት ይህን ጥፋት መድገም የለበትም።
ታዲያ እንዴት ነው የባህር በር ባለቤት መሆን የምንችለው?
አሁን የተፈጠረው የእርቅ መንፈስ ጥሩ ነው፤ መፈጠር ያለበትም የሚደገፍም ነው። ወደ ዋናውና ጠንካራው ጉዳይ ሲገባ ግን መንግስት መጠንቀቅ ይገባዋል፡፡ አንደኛ የኤርትራ መንግስት እንኳን ከኢትዮጵያ ጋር ሠላም ሊፈጥር ከራሱ ህዝብ ጋር እንኳ ሠላም መፍጠር ያልቻለ ነው። ሁለተኛ ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት በሚመለከት የእነ ሡዳንና ጅቡቲ ሁኔታንም ማየት ይገባል፡፡ ሶስተኛ የአካባቢውንም በተለይ የመካከለኛው ምስራቅ አጠቃላይ ሁኔታን መመልከት አለባቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህር በር ጉዳይን በተመለከተ ምሁራንን ሠብስበው፣ ሰፊ ውይይት ቢያደርጉ ይመረጣል። ምሁራን ኢትዮጵያ በባህር በሩ ላይ ሉአላዊ መብት አላት የላትም? የሚለውን አጥንተው እንዲያቀርቡ መጋበዝ አለባቸው፡፡ ወደ አልጀርሱ ስምምነት ሲኬድ እንዲህ ያለ ጥናት ቢደረግ ኖሮ፣ ችግሩ አይፈጠርም ነበር፡፡ እኔ በጥናት እንዳረጋገጥኩት በባህር በሩ ላይ ሉአላዊ መብት አለን፡፡ ወደቡ ልክ እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ግዛት ነው መታየት ያለበት፡፡ ጥያቄውም በዚህ መልክ ነው መቅረብ ያለበት፡፡ ስለዚህ መንግስት ወደ ዝርዝር ጉዳይ ከመግባቱ በፊት የግንኙነቱን ጉዳይ ተቋማዊ አድርጎ በጥናት ነው መሄድ ያሉበት፡፡ ይህን የሚያደርጉት ያለፈውን ስህተት ላለመድገም ነው። ሁለተኛ ድንበር አካባቢ ያሉ ህዝቦችን፣ ምንም እንኳ የድንበር ጉዳይ የፌደራል መንግስቱ ስልጣን ቢሆንም ማወያየቱ ጠቃሚና ተገቢ ነው። በሌላ መንገድ አሁን የተፈጠረው ግንኙነት ጠቃሚ ነው። ምናልባት ኤርትራ ውስጥ የተሻለ መንግስት የሚመሠረትበት ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል፡፡
በመከላከያ ውስጥ የተጀመረውን ሪፎርም (ለውጥ) እንዴት ይመለከቱታል?
አሁንም በመከላከያ ውስጥ የሚታየው የለውጥ ጅማሮ ነው፡፡ መከላከያው ለህገ መንግስቱና ለህገ መንግስቱ ብቻ ነው የሚታዘዘው የሚለውን ነገር ኢታማዦር ሹሙም ጠ/ሚኒስትሩም ተናግረውታል። በአንድ ወቅት ለቀድሞ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሣለኝ መከላከያውን በተመለከተ ደብዳቤ ፅፌላቸው ነበር። የሃገሪቱ መከላከያ ኢንዶክትርኔሽን “መከላከያው የኢህአዴግ የመጨረሻው ምሽግ ነው” የሚል ነበር፤ ይሄ ፀረ ህገ መንግስት የሆነ አስተሳሰብ ነበር፡፡ አሁን ወደ ህገ መንግስቱ የገለልተኝነት መርህ አስተሣሠብ ማቅናት ተጀምሯል፡፡ ጅምሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ደግሞ የኢትዮጵያ የደህንነት ፖሊሲ መሻሻል አለበት። ይሄ እስካልተሻሻለ ድረስ የቃል ለውጦች ብዙ አያስኬዱም፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የደህንነት ም/ቤቱ ጠንካራ መሆን አለበት። የጠ/ሚሩ የደህንነት አማካሪና ቢሮም በጣም ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ መከላከያውም አዲስ ኢንዶክትርኔሽን ያስፈልገዋል፡፡ ጅምሩ ጥሩ ነው፣ ነገር ግን ከዚህ አኳያ ብዙ ርቀት መጓዝ ያስፈልገናል፡፡ የብሄራዊ ደህንነትና መረጃ ተቋሙም በዚህ መንገድ ነው መጠናከር ያለበት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሠሞኑን በአሜሪካ ከኢትዮጵያውያን ጋር ያደረጉትን ውይይት እንዴት አገኙት?
ኢትዮጵያውያን ሁላችንም በአንድ ላይ እንሠለፍ፤ ሁላችንም በጋራ ለሃገራችን እንስራ የሚለውን፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋም በጣም ነው የምደግፈው። “ግንብ እናፍርስ ድልድይ እንስራ”፣ “ጥላቻን በፍቅር እንተካ” የሚለው አቋማቸው ሲታይ ጥሩና የሚደገፍ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ዋናው የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ውጪ ነው ያለው፡፡ አሁን ያ ተቃውሞ ሃገር ውስጥ ገብቶ በሠላማዊ ሁኔታ የሚሠራበት መንገድ እየተፈጠረ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ አካሄዱ ጥሩ ነው። ፖለቲካችን ሁሉን አካታች መሆን አለበት፡፡ እሣቸውም ጥላቻው እንዲፈርስ አድርገዋል፡፡ ስለዚህ ዲያስፖራው አካባቢ የነበረው ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሚና ሊቆም ይችላል፡፡ ነገር ግን ስብሰባዎቹ ድብልቅልቅ ውጤት ነበራቸው። በ27 ዓመት ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግስት ፀድቋል፡፡ ለመተግበርም ተጀምሮ ነበር። በማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ የመጡትን ከፍተኛ ለውጦች የማንኳሰስና ሁሉንም ነገር የማንቋሸሽ አካሄድ ለውጥን ወደ ኋላ የሚጎትት ነው፡፡ ለውጥ ቀጣይነትም ጭምር ነው፡፡ ለውጥ ከባዶ አይነሳም፡፡
ህወኃትን በድፍን የማጥላላት ዘመቻም ነበረበት። ይህ ደግሞ በህወኃት ውስጥ ያሉትን ፀረ-ለውጥ ሃይሎች እንደ መደገፍ ይቆጠራል። በዶ/ር ደብረፅዮን የሚመራውን የለውጥ እንቅስቃሴም እውቅና ሰጥቶ አብሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡
 ለኔ የተሻለ ፌደራሊስት የነበረው የሚኒሶታው መድረክ ነው፡፡ የተለያዩ ብሄር ብሄረሠቦች የተወከሉበት፣ በልዩነት ውስጥ አንድነት የታየበት የተሻለ መድረክ ነበር፡፡
ሌላው አወዛጋቢ የሆነው ጉዳይ የሰንደቅ አላማ ጉዳይ ነው…
ባንዲራ የአንድ ህዝብ፣ ሃገር መለያ ምልክት ነው፡፡ ይህ ምልክት በህግ መደንገግና መጠበቅ አለበት፡፡ ህዝብ የሚፈልገው ነው መሆን ያለበት። ህዝብ ያልፈለገው እስከሆነ ድረስ አንድ ፅንፍ ላይ ተንጠልጥሎ፣ ህገ መንግስት ተጥሷል ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ አሁን በህገ መንግስት የፀደቀውን ሠንደቅ አላማ፤ ህዝቡ ለምንድን ነው ያልተቀበለው የሚለውን ጉዳይ በሚገባ መመርመር ያስፈልጋል። ኮከብ ያለበትን ባንዲራ አንፈልግም ሲባል “አካኪ ዘራፍ” ማለት ተገቢ አይደለም፡፡
ትልቁ ነገር አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የለውጥ ስካር ነው ያለው፡፡ ከዚህ በኋላ ሰከን ብሎ ማየት ያስፈልጋል። ፍቅር፣ ሠላም አንድነት መሰረት መሆን አለባቸው፡፡  እነዚህ በጊዜ መገራት አለባቸው፡፡ በተለይ ሚዲያዎች የሃሳብ ብዝሃነትን ማስተናገድ ይገባቸዋል። አግላይ መሆን የለባቸውም፡፡ ሁሉም ሃሳብ ወደ መድረክ እንዲመጣ፣ የተገለለ ሃሳብ እንዳይኖር መትጋት ከሚዲያዎች ይጠበቃል፡፡ ለውጡን በሠከነ መንገድ መምራት ይገባናል፡፡

Read 2391 times