Print this page
Saturday, 04 August 2018 10:56

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

 “ቦታ የሚጠበው አዕምሮህ ሲጠብ ነው”
              
    “My house is small,
No mansion for a millionaire,
But there is room for a friend,
And room for love,
And that is all what I care”
እያንዳንዱ ህይወት ያለው ፍጡር፤ የየራሱን ‹አሁን› የሚከውንበት ጊዜና ጥግ አለው፡፡ … ንጉሡ በወርቅ ዙፋን ላይ ሊቀመጥ ይችላል፡፡ … ምስኪን ደግሞ ብርኩማው ላይ፡፡ … ወይም ጎዳና ጥግ። … ሁለቱም ግን ተቀምጠዋል፡፡ … ቢቆሙም፣ ቢቀመጡም፣ ቢላፉም በየራሳቸው ቦታ ሆነው ነው፡፡ … ቦታ ቢቀያየሩም ለውጥ የለውም፡፡ … አውሮፓ ወይም አሜሪካ ብትሄድ ወይ እነሱ ወዲህ ቢመጡ አንተ የቆምክበት ቦታ፣ የምትተኛበት ጥግ፣ የምትራመድበት መንገድ ያንተ ብቻ ነው። …. ዞር ብለህ መንገድ ብትለቅ፣ ከመቀመጫህ ተነስተህ ሌላውን ብታስቀምጥም የራስህ ቦታ አለልህ፡፡ … አየር ላይ አትንሳፈፍም፡፡
በጠባብ ጎዳና ላይ ሺ ሰዎች ሲተረማመሱ እያቸው፡፡ … አውቶብስና ታክሲ ውስጥም ጭምር። አይተዋወቁም ግን ይግባባሉ፡፡ ተጋፍተውና ተጣበው ይተላለፋሉ፡፡ ግን አይገፈታተሩም፣ አይጣሉም፡፡ … ሁሉም በራሱ መንገድ ወደ ራሱ ጉዳይ ይጣደፋል፡፡ … በጎ የመሆን ፈቃድና መተሳሰብ ካለ፣ ትንሽ ቦታ ለብዙ ሰዎች ትበቃለች። … ፍቅር፣ መተሳሰብና በጎነት የሃሳብ ልቀት ነው፡፡ ሌሎችን ሰዎች የተረዳኸው፣ ለሌሎች ሰዎች ያሰብከው ወይም ሌሎችን ሰዎች የምትወደው በሃሳብህ ነው፡፡ ይህም ማለት ለሌሎች ሰዎች ቦታ የምትሰጠው አእምሮህ ውስጥ በመሆኑ ነው፡፡ አእምሮ ደግሞ ወሰን የለውም፡፡ አንተ ከፈለግህ ለቢሊዮንና ቢሊዮን ሰዎች የሚሆን ቦታ አለው፡፡
ወዳጄ፡- ቦታ የሚጠበው አእምሮህ ሲጠብ ነው። አእምሮህ ከጠበበ ቦታ አይበቃህም፡፡ ትልቁ ግቢ ያንስሃል፤ ትልቁ መንገድ ይጠብሃል፡፡ ግቢውን ታጥረዋለህ፣ መንገዱን ትዘጋዋለህ፡፡ … ማንም ድርሽ እንዲልብህ አትፈልግም፡፡ … የሌሎችን ቦታም ትገዛለህ ወይ ትቀማለህ፡፡ በቦታ ትጣላለህ፣ በድንበር ትካሰሳለህ። … አንዳንዴም ትጋደላለህ። … ደውሉ ሲደወል፣ ተራህ ደርሶ ስትሞት ግን ሌላው ላይ ትደረባለህ፡፡ … እንደ ዕቃ! … ወይ ሳርና ዛፍ ይበቅልብሃል፣ ቤት ይሰራብሃል፣ ወይ መንገድ ይወጣብሃል፡፡ … ራስህ ቦታ ትሆናለህ!!
***
“ሁለት መላዕክቶች ናቸው፡፡ … ታላቅና ታናሽ። በሰው ተመስለው ይዘዋወራሉ፡፡ ሲጓዙ ውለው መሸባቸው፡፡ በቅርብ ወዳዩት ግቢም ተጠጉ።” እያለ የሚተርክልን የማናውቀው ሰው ነው፡፡ … ግቢው ትልቅና ያማረ ነው፡፡ መሃል ላይ ብዙ ክፍሎች ያሉት ትልቅ ቤት አለ፡፡
“ምን ትፈልጋላችሁ?” በማለት ጠየቃቸው ባለቤቱ።
“ሩቅ መንገደኞች ነን፣ መሸብን ደክሞናል፤ ማደሪያ እየለመንን ነው” አሉ፡፡ ባለቤቱም ሲያቅማማ ከቆየ በኋላ ከአገልጋዮቹ አንዱን ጠራ፡፡ ከቤቱ ስር ያለውን ጋጣ እንዲሳያቸውና እንዲተኙ አዘዘ፡፡ እንግዶቹም እጅ ነስተው ሄዱ። ሲነጋጋም አመስግነው መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ … እንደገና መሸ፡፡ ማደሪያ ሲፈልጉ አንዲት ደሳሳ ጎጆ በአካባቢው ተመለከቱና ወደዚያ አቀኑ፡፡ ቀርበውም፤
“የመሸብን መንገደኞች ነን” በማለት ጮክ ብለው ተናገሩ፡፡ ባለቤቱም ወጥቶ …
“ቤት ለእንግዳ ነው፡፡ እባካችሁ ግቡ” አላቸውና አስገባቸው፡፡ የገበሬው ሚስት ታማ መደብ ላይ ተኝታለች፣ አጠገቧ ደግሞ ላማቸው ታስራለች። እንግዶቹ የጎጆዋን ጥበት ሲያውቁ አፈገፈጉ። ባለቤቱ ግን መውጫውን ይዞ … “በጭለማ አትሄዱም” በማለት ከለከላቸው፡፡ ባለቤቱም እያቃሰተች፤ “እባካችሁ ደስ እንዲለን ይሁን” ብላ ለመነቻቸው፡፡ … ጥግ ላይ አረፍ አሉ፡፡ ወተትና ቤት ያፈራው እህል ቀርቦ ደስ እያላቸው ተመገቡ። ሲጫወቱና ሲስቁ አምሽተው በያሉበት ድብን ያለ እንቅልፍ ወሰዳቸው፡፡
በማግስቱ ረፋድ ላይ ከመኝታቸው ሲነሱ፣ ገበሬውና ሚስቱ እያለቀሱ ነበር፡፡ ላማቸው ሞታ ነበር ያደረችው፡፡ እንግዶቹም አፅናንተዋቸው መንገዳቸውን ጀመሩ፡፡ … ትንሽ እንደተጓዙም …
“እንዲህ ዓይነት ጭካኔ ሊዋጥልኝ አይችልም!!” አለች፡፡ … ትንሿ መልዓክ እየተበሳጨች፡፡
“አንዳንድ ጊዜ ነገሮች እንደምናያቸውና እንደምናስባቸው ላይሆኑ ይችላሉ” አላት ትልቅየው፡፡
“በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡ እንዴት ሊኖሩ ነው?”
“ህይወት ረቂቅና በተዓምራት የተሞላ ነው። በጥልቅ ለማይመረምረው ችግር ነው፡፡ የተዛባ ፍርድ እንዲሰጥ ሊያደርገውም ይችላል፡፡”
“እንዴት? … ምን ማለት ፈልገህ ነው?”
“ምክንያቱም ሁላችን ሁሉም ነገር ላይ ዕኩል ዕውቀት የለንም፤ ሊኖረንም አይችልም፡፡ ዕኩል ካላወቅን ደግሞ እኩል መረዳት አንችልም፡፡ ዕኩል ካልተረዳን ዕኩል ትዕግሥት አይኖረንም፡፡ ዕኩል መታገሥ ካልቻልን ደግሞ ብዙዎቻችን ስሜታዊ ነን ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ፍርድ የሚዛባው፡፡ … ለመሆኑ እንዲህ የተቆጣሽው ምን ነክቶሽ ነው?”
“እንዴት አልቆጣም? … ከትናንት ወዲያ ያደርንበት ግቢ ባለቤት ጥሩ ሰው አልነበረም፡፡ ብዙ ባዶ ክፍሎች እያሉ፣ ብዙ የሚበላ ነገር ሞልቶ ሳለ ጋጣ ውስጥ፣ ጦማችንን አሳደረን፡፡ … አንተ ግን ምንም አልተሰማህም፡፡ ትናንት ማታ ደግሞ እነዚያ ምስኪኖች በፍቅር ተቀብለው፣ ያላቸውን አብልተው፣ መኝታቸውን አጣበን ማደራችን አንሶ ወተቷን እየሸጡ የሚተዳደሩባት አንዲት ላማቸው በድንገት ስትሞት እያየህ ዝም ማለትህ ነዋ ያበሳጨኝ፡፡”
“አየሽ ነገሮች ሁልጊዜ እንደሚታዩትና ሌሎች እንደሚያስቧቸው አይደሉም … ያልኩሽ ለዚህ ነበር፡፡”
“ማለት?”
“የመጀመሪያው ግቢ ባለቤት ገብጋባና ክፉ ነው፡፡ ወርቅና ገንዘቡን የቀበረው እኛ ያደርንበት ጋጣ ውስጥ ነበር፡፡ ከአሁን በኋላ ግን አያገኘውም። … ድህነትን እንዲያውቅ፣ እንግዳ እንዲያከብርና እንዲወድ ሆኗል። … ገበሬውና ሚስቱ ግን ደግና ትሁት ሰዎች ናቸው፡፡ ሌሊት አንቺ ተኝተሽ መልዓከ ሞት መጥቶ ነበር፡፡ … የገበሬውን ሚስት ለመውሰድ፡፡ … ከለከልኩት። በሷ ፈንታ ላማቸውን ሰጥቼው ሄደ፡፡ አሁን የገበሬው ሚስት ድና ተነስታለች፡፡ ወደፊት ብዙ ላሞች ይኖራቸዋል” አለ፡፡ … ትንሿ መልዓክ በጣም ደስ አላት፡፡
“እውነትም ነገሮች ሲመረመሩ እንደሚታዩትና እንደሚታሰቡት አይደሉም” አለች፡፡
ወዳጄ፡- “There is no mathimathical certainity in life” … ሲባል ምን ማለት ይመስልሃል? … ለሌሎች ሰዎች የሚሆን ቦታ አዕምሮህ ውስጥ አለ? ወይስ የለም?….
ሠላም!!

Read 1511 times