Print this page
Saturday, 04 August 2018 11:09

ማምኮ “በጠራራ ፀሐይ እየተዘረፍኩ ነው” ሲል የድረሱልኝ ጥሪ አሰማ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

 ላለፉት 22 ዓመታት ጥራት ያለው ምርት በማቅረብ የሚታወቀው ማምኮ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ “በጠራራ ፀሐይ በሕገ ወጦች እየተዘረፍኩ ነው” በማለት አስታወቀ፡፡
ኩባንያው ከትናንት በስቲያ በሃገርመኒ ሆቴል በሰጠው መግለጫ፤ ያለ አግባብ ለመበልፀግ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሕገ-ወጥ ግለሰቦች፣ ከኩባንያችን ዓርማና ስም ጋር እጅግ ተቀራራቢ የሆነ “ማምኮ፣ ማዶ፣ማማ” የሚል ስም በመስጠት “ማምኮ የመፀዳጃ ቤት ሶፍት” በማቅረብ ገበያውን በማጥለቅለቅ ያለ ስጋት እየተቸበቸቡ መሆኑን ገልጿል፡፡
በ1987 ዓ.ም በ50 ሰራተኞች ምርት ጀምሮ ዛሬ የሰራተኞቹን ቁጥር ከ200 በላይ ያደረሰው ማምኮ፣ የመፀዳጃ ቤት፣ የፊት ማበሻ፣ የገበታ ወይም የአፍ ማበሻ፣ የወጥ ቤት ንፅሕና መጠበቂያ ሶፍቶችና የተማሪዎች መማሪያ ደብተር በማምረት ለኅብረተሰቡ በማቅረብ ላይ ቢቆይም፣ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ፣ ሕገ-ወጥ ግለሰቦች በኩባንያው ሕልውና ላይ እጅግ ፈታኝ ሁኔታዎች እየፈጠሩ መሆኑን አመልክቷል፡፡
በዓመት ከ8-9 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ግብር ለመንግሥት በመክፈል ግዴታውን እየተወጣ እንደሚገኝ የገለፀው ኩባንያው፤ ከሦስት ዓመት ወዲህ ገቢው እየቀነሰ መሆኑን ጠቅሶ፣ ሕገ-ወጥ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና በኩባንያው ላይ እየደረሰ ያለውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ኪሳራ እንዲጠይቁላቸው ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በተደጋጋሚ ቢያመለክትም፣ ሕገ-ወጦቹ ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ባለመደረጉ፣ ለሕግ ሊቀርቡና ሊጠየቁ አልቻሉም ብሏል፡፡
ኩባንያው፣ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬው ቀን ድረስ በከፍተኛ ደረጃ ለሚገኙ ሆቴሎች በትዕዛዝ ከሚያመርተው ባለ 130 ግራም፣ በየሱፐር ማርኬቶችና በየመደብሩ ከሚሸጠው ባለ 100 ግራም ሶፍት በስተቀር ባነሰም ሆነ በጨመረ ግራም የመፀዳጃ ቤት ሶፍት አምርተው እንደማያውቁ ጠቅሶ፣ ሕገ-ወጦቹ ግለሰቦች፣ የ “ማምኮ”ን አርማና ስያሜ ማሸጊያ በማሳተም ባለ 70 እና ባለ 80 ግራም ሶፍት ለገበያ ማቅረባቸው ሳያንስ ለተለያዩ የመንግሥት ድርጅቶች “ማምኮ” ባለ 70 እና ባለ 80 ግራም በማለት የጨረታ ሰነድ እንደሚያቀርቡ በግል ባደረጉት ክትትል እንደደረሰበት አስታውቋል፡፡
በሕግ ክፍሉ አማካይነት ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ለተለያዩ የመንግሥት አካላት የሕገ-ወጦቹን ግለሰቦች ድርጊት ቢያሳውቅም፣ ይህ ነው የሚባል ክትትል ባለመደረጉና ትኩረት ባለመሰጠቱ፣ የኩባንያው ሕልውና አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁሞ፣ ሕገ-ወጦቹ ግለሰቦችና ተባባሪዎቻቸው ኅብረተሰቡንና መንግሥትን በማሳሳት ያለ አግባብ ሀብት ከማከማቸታቸውም በላይ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በሕጋዊ መንገድ የሚሠራውን ኩባንያችንን ሽያጭ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሽቆለቁል በማድረግ “በጠራራ ፀሐይ ዘረፋ” እያካሄደብን ነው፣ “የመንግሥት ያለህ፣ የሕግ ያለህ” በማለት ጩኸቱን አሰምቷል፡፡
ሕገ-ወጥ ግለሰቦች፣ በአጭር ጊዜ ዝናን በማትረፍ ለመበልፀግ፣ ለ22 ዓመታት ምርቶቻችንን በጥራት በማቅረብ በጥረታችን ያገኘነውን መልካም ስም በማጉደፍ የገበያ ድርሻችንን በመሻማት የብዙ ሚሊዮን ብር ኪሳራ እያደረሰቡን ነው ያለው ኩባንያው፤ ይህ ድርጅት ሕጋዊ ከሆነና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ ኅብረተሰቡን ሊያሳስት የሚችልና ከማምኮ ጋር እጅግ ተቀራራቢ ስያሜና አርማ ሕጋዊ ፈቃድ እንዴት ሊሰጣቸው ቻለ? አሠራሩስ ፍትሐዊ ነው ወይ? በማለት ጠይቋል፡፡
መርካቶ ውስጥ የማምኮ ምርት ማከፋፈያ ሱቅ ያላቸው ወ/ሮ ኬሪያ አህመድ ከ10 ዓመት በፊት የቫት ተመዝጋቢ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በየጊዜው ሱቃቸው እንደሚበረበርና ሁለት ጊዜ ታስረው መፈታታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከእስሩ ጀርባ ማን እንዳለ አላውቅም ያሉት ወ/ሮ ኬሪያ፤ ታስረው ፍ/ቤት ሲቀርቡ የቫት መመዝገቢያ መሳሪያቸው ተመርምሮ “ምንም አልተገኘብሽም፣ ነፃ ነሽ” ተብለው እንደሚለቀቁ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል ሕገ-ወጡ ምርት ከንጋቱ 11 ሰዓት ነበር የሚከፋፈለው ያሉት ወ/ሮ ኬሪያ አሁን ግን በግልጽ በቀን ይሰራጫል፤ ኅብረተሰቡ ደግሞ ለዋጋው መቀነስ እንጂ ለጥራቱ አይጨነቅም፡፡ ስለዚህ የሚሰራጨው ሕገ ወጡ የሶፍት ምርት በቅናሽ ዋጋ ይሸጣል፡፡ በአዲስ አበባ ሱቆችም ሆነ በክልል ከተሞች ኪዮስኮች በብዛት ይቸበቸባል፡፡ ሕጋዊ የሆነው ምርት ግን በመጋዘን ተከማችቶ ይገኛል ብለዋል፡፡

Read 2461 times