Sunday, 05 August 2018 00:00

ጅቡቲ ኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ መጠየቁን ተቃወመች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ጅቡቲ፤ የሱማሌው ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ፣ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ባለፈው ሳምንት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያቀረቡትን ጥያቄ በጽኑ መቃወሟን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
የሱማሌው ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ ባለፈው ሳምንት በኤርትራ የሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ፕሬዚዳንቱ በጉብኝታቸው ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እ.ኤ.አ በ2009 በኤርትራ ላይ የጣለውን የኢኮኖሚና የጦር መሳሪያዎች ማዕቀብ እንዲያነሳ ጥሪ ማቅረባቸው ጅቡቲን ክፉኛ ማስቆጣቱን አመልክቷል፡፡
በጅቡቲ የሶማሊያ አምባሳደር አደን ሃሰን፤ “የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ለተመድ ያቀረቡት የማዕቀብ ይነሳ ጥያቄ እጅግ አስደንግጦናል፣ በጽኑም እንቃወመዋለን” ሲሉ መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ “ኤርትራ የይገባኛል ውዝግብ ያለባቸውን የሩሜራ ደሴቶችን ያላግባብ ይዛብናለች፣ ከአስር በላይ ዜጎቻችንንም በእስር ቤት እያሰቃየችብን ነው፣ ስለዚህም ተመድ የጣለባት ማዕቀብ ሊነሳላት አይገባም” በሚል ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውንም ገልጧል፡፡
“ሶማሊያ በአካባቢው ካሉ ጎረቤት አገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን የማጠናከር ህጋዊ መብት ቢኖራትም፣ የረጅም ዘመናት ወዳጃችን የሆነቺው ሶማሊያ ሉአላዊ ግዛታችንን ለወረረቺውና ዜጎቻችንን በእስር ለምታሰቃየው ኤርትራ እንዲህ አይነት ድጋፍ ማድረጓን መንግስታችን በጽኑ ይቃወመዋል” ማለታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 1415 times