Saturday, 11 August 2018 10:22

በአ/አበባ ሀገረ ስብከት 14 የዋና ክፍል ሓላፊዎች ምደባ ቅሬታ አስነሣ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

•    ግልጽነትና አርኣያነት የጎደለው ምደባ በሚል እየተተቸ ነው
•    በተደጋጋሚ በጥፋት የተነሡ ሓላፊ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ተመደቡ
•    በተደጋጋሚ ሕጸጽና ምዝበራ የታገዱት አስተዳዳሪም ተመለሰ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፥ በሙስና፣ በአስተዳደር በደልና
በአሠራር ጥሰት የተካሔደውን ማጣራት ተከትሎ፣ 14 የዋና ክፍል ሓላፊዎች ከቦታቸው ቢነሡም፣ በምትካቸው የተደረገው ምደባ፣ ግልጽነትና አርኣያነት የጎደለው ነው፤ በሚል ቅሬታ አስነሣ፡፡ በቅዱስ ፓትርያርኩ መመሪያ በተቋቋመው ኮሚቴና የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር
በታዛቢነት በተገኙበት ለአንድ ወር በተካሔደው ማጣራት፣ የአድባራት ካህናትንና ሠራተኞችን አላግባብ ከሥራ በማገድና በማሰናበት የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደፈጸሙ ለቋሚ ሲኖዶስ ሪፖርት የቀረበባቸው የዋና ክፍል ሓላፊዎቹ እንዲነሡ መደረጉ ተገልጿል፡፡ ኾኖም፣ በቦታቸው ከተተኩት ሓላፊዎች መካከል የአንዳንዶቹ ምደባ፣ ከለውጡ ርምጃ ጋራ የማይጣጣም እንደኾነ ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡ አገልጋዮችና ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል፣ ሓላፊነታቸውን አላግባብ ተጠቅመው በመዘበሩት የቤተ ክርስቲያኒቱ ገንዘብ ከፍተኛ የግል ሀብት
በማፍራትና አስተዳደራዊ በደል በማድረስ የታወቁ ግለሰቦች በተተኪነት መመለሳቸው፣ለቤተ ክርስቲያኒቱ አደጋ ነው፤ አገልጋዩንም ዋስትና የሚያሳጣ ነው፤ ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል - ሠራተኞቹ፡፡
“በሹም ሽረቱ የግብር ይውጣ ሥራ ተሠርቷል፤” የሚሉት ሠራተኞቹ፣ በ2007 ዓ.ም. በሀብት ብክነት፣
ሙስናና ሓላፊነትን በአግባቡ ካለመወጣት ጋራ ተያይዞ በቅዱስ ፓትርያርኩ መመሪያ ከሓላፊነታቸው ተነሥተውማጣራት እንዲካሔድባቸው የተወሰነባቸው የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ፣ በአዲሱ ምደባ በዚያው ዋና ክፍል ለ3ኛ ጊዜ መሾማቸውን በመጥቀስ ምደባው ግልጽነትና አርኣያነት የሌለው ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡ “በቂ ጥናት ሳይደረግና መመዘኛ መስፈርቱ ሳይታወቅ ወደ ሓላፊነት የመጡ ሰዎች ናቸው፤” የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ከተተኩት መካከል፣ ከቀድሞዎቹ ጋራ የጥቅም ግንኙነት እንደነበራቸው የሚወቀሱም
በመኖራቸው፣ የሀገረ ስብከቱን የለውጥ ርምጃ የሚመጥን አፋጣኝ ማስተካከያ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
በቅርቡ ተካሒዶ በነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ፣ በሀገረ ስብከቱ አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ፣
ሙስናን፣ ጥቅመኝነትንና የመልካም አስተዳደር ችግርን ለዘለቄታው የሚፈታ የአደረጃጀት ለውጥ እንዲደረግ
መግባባት ላይ ቢደረስም፣ የአስተዳደር ሓላፊዎቹ ምደባ ሒደቱን የሚያራምድ እንዳልኾነ ጠቁመዋል፡፡
ጥቅመኝነትን፣ ደላላነትንና ኑፋቄን ለማስወገድ ቃል ለገቡት የሀገረ ስብከቱ የወቅቱ ሥራ አስኪያጅም ፈተና
እንደሚኾንባቸው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ከቦታቸው በተነሡት የዋና ክፍል ሓላፊዎች፣ አላግባብ ከሥራቸው ታግደውና ተሰናብተው
በአቤቱታ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲጉላሉ የቆዩት ካህናትና ሠራተኞች፣ ደረጃቸውና ጥቅማቸው ተጠብቆ ወደ
ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ መደረጉን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን
በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ታግደው በቆዩባቸው እስከ ሁለት ዓመታት ገደማ ያልተከፈላቸው
ወርኀዊ ደመወዝም ተሰልቶ እንዲከፈላቸው መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
ኾኖም፣ ከታገዱት ሠራተኞች መካከል፥ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት፣ በገንዘብ ምዝበራና በከፋ ምግባር
ተደጋጋሚ ጥፋት በመፈጸም ከሥራና ከደመወዝ እንዲታገዱ፣ ጉዳያቸውም በሊቃውንት ጉባኤ እንዲጣራ በቋሚ
ሲኖዶስ ውሳኔ የተላለፈባቸው ግለሰብ ወደ ደብር አስተዳዳሪነታቸው መመለሳቸው ተጨማሪ ቅሬታ ማስነሣቱ
ታውቋል፡፡ ከሃይማኖት ሕጸጽና ከሙስና ነጻ መኾናቸው እየታየ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የተሰጠውን አቅጣጫ
እንደሚፃረርም ጠቁመዋል፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር፣ በውሳኔው አስተማሪነት ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ
በቀላሉ የሚታይ ባለመኾኑ በአፋጣኝ ሊጤን እንደሚገባም አሳስበዋል - ተቺዎቹ፡፡
 


Read 4941 times