Saturday, 11 August 2018 10:32

የሞስኮው አርባትና የጎርኪ አገር ኒዚሂኒ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

 አርባት ጎዳና ላይ
  • የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች በዝናብ የተጫወትነው መሓል ባልገባ
  • የፑሺኪን ቤተ ሙዝየምና የቪክቶር ሶይ መታሰቢያ ግድግዳ
  • በ30 ደቂቃዎች የተነሳሁት ስዕል

   በሞስኮ ከተማ መጎበኘት ካለባቸው አካባቢዎች ዋንኛው አርባት ጎዳና ነው፡፡ ይህን ጎዳና የእግረኞች አደባባይ ማለትም ይቻላል፡፡ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ሰሞን ከ144 በላይ አገራትን የወከሉ ህዝቦች ሌት ተቀን የማይጠፉበት ሰፈር ነበር፡፡ አርባት ጎዳናን ለመጀመርያ ጊዜ የረገጥኩት ፈረንሳይ ከአርጀንቲና በጥሎ ማለፍ ጨዋታ በተገናኙበት ቀን ነበር። ጨዋታውን  በጎዳናው ላይ በሚገኝ ታዋቂ ሬስቶራንት እንድንመለከት የኢትዮጵያን የስፖርት ጋዜጠኞች  የጋበዘን በሞስኮ የተማረውና የሚኖረው ዶክተር ፋሲል ነበር፡፡ የሞስኮ ከተማ አበይት አውራ ጎዳናን በጉብኝት እንድንተዋወቀው አስቦ ነው፡፡ በፊፋ እውቅና አግኝተን ዓለም ዋንጫን ለመዘገብ የሄድን እና በተለያየ ሁኔታ ለታላቁ የስፖርት መድረክ ሽፋን ለመስጠት ራሽያ የገቡ ሌሎች የስፖርት ጋዜጠኞች ጋር ሞስኮ በሚገኘው አዲስ አበባ ሬስቶራንት ተገናኝተን ነበር። የዓለም ዋንጫውን ሂደት እየተጨዋወትን በሬስቶራንቱ እንጀራውን፤ ዶሮ ወጡን፤ ክትፎውን፤ በያይነቱን ያማረንን ሁሉ ተገባበዝን። እኔ ከአዲስ አድማስ፤ ዳዊት ቶሎሳ ከሪፖርተር፤ አለምሰገድ ሰይፉ ከሊግ ስፖርት፤ ኤፍሬም የማነ እና ፍቅር ይልቃል ከትሪቡን ስፖርት እንዲሁም መኳንንት በርሄ ከስፖርት ዞን ማለት ነው፡፡
በሞስኮው አዲስ አበባ ሬስቶራት ከነበረን  ቆይታ በኋላ ፈረንሳይ ከአርጀንቲና የተገናኙበትን የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ለመመልከት አውቶብስ ተሳፍረን ወደ አርባት ጎዳና ለመሄድ ወሰንን፡፡ ዶክተር ፋሲል በአርባት የእግረኞች አደባባይ በሚገኘው  ታዋቂና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ሬስቶራንት ጨዋታውን በግዙፍ ስክሪን እንድንመለከት ባቀረበው ሃሳብ መሰረት ነው፡፡ እንደ ከተማው ነዋሪነቱ ሞስኮ ከመጣን አይቀር አርባት ጎዳናን ብናይ እንደምንደሰት በመገመቱ ነበር፡፡ አርባት ጎዳና ላይ ስንደርስ ሰማዩ ጠቋቁሯል፡፡ በእግረኞቹ አደባባይ መግቢያ ላይ የነበሩትን የጎዳና ሰዓሊዎች በአግራሞት እየተመለከትን፤ በራሽያ ቋንቋ ብቻ የተፃፉ መፅሃፍት የሚሸጡባቸውን ቦታዎች ስንጎበኝ ቆይተን፤ የተለያዩ የራሽያ አልባሳት፤ ጌጣጌጦች፤ ገፀበረከቶች እና ሌሎች ከዓለም ዋንጫ ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶችን በሚሸጡ መደብሮች እየተዘዋወርን ዝናብ በካፍያ መልክ መጣል ነበረ። የቱሪስቶች መናሐርያ በሆነው አርባት ጎዳና ዳር እና ዳር በነበሩት  መለስተኛ ፎቆች እና የመኖርያ አፓርትመንቶች እየተሹለኮለኩን መጓዙን ቀጥለናል፡፡  የትሪቡን ስፖርቱ ኤፍሬም የማነ አንዱ መደብር ጎራ አለና የዓለም ዋንጫ ቲሸርት እና  ኳስ ገዝቶ ተመለሰ። ያልተጠበቀው ዝናብ በአርባት ጎዳና ላይ መውረዱን ቢቀጥልም ኳሱን ወደ መሬት አወረዳትና ከዶክተር ፋሲል እና ከአለምሰገድ ጋር መቀባባል ጀመሩ፡፡ ከዚያም ሁላችንም ዝናቡ ምንም ሳይመስለን  ያለማመንታት በኳሷ መሃል ባልገባ እየተጫወትን በአርባት ጎዳና ላይ ቁልቁል መውረድ ጀመርን። የዓለም ዋንጫ ጨዋታውን የምንመለከትበት ሬስቶራንት እስክንደርስ ቢያንስ ከ400  ሜትር  በላይ ያህል በአርባት ጎዳና ላይ  መሐል ባልገባ እየተጫወትን ነበር፡፡ በእግረኞች አደባባዩ ግራና ቀኝ ዝናብ የተጠለሉ፤ በየሬስቶራንቱ የነበሩና ጥላ ይዘው የሚያልፉ በርካታ ቱሪስቶችና የከተማው ነዋሪዎች ኳስ መጫወታችን ትኩረታቸውን ስቦታል፡፡ የዓለም ዋንጫው ልዩ ገጠመኝ ሆኖላቸው ፎቶዎችን ያነሱንና ቪድዮዎችን የቀረፁን ጥቂት አልነበሩም፡፡
አርባት ጎዳናን  ከሙያ ባልደረቦቼ የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ጋር በተጫወትነው መሐል ባልገባ ለመጀመርያ ጊዜ የጎበኘሁት ቢሆንም ዋና ትኩረት ሰጥቼ ካሜራዬን በመደቀን ከተሟላ መረጃ ጋር የጎበኘሁት በሌላ አጋጣሚ ነበር፡፡ ከሞስኮ  በ38 ሰዓታት አገር አቋራጭ የባቡር ጉዞ ወደ ሶቺ ከተማ ለማቅናት በተዘጋጀሁበት ቀን በቀሩኝ የመጨረሻ ሰዓታት ነበር፡፡ አርባት ጎዳናን ለሁለተኛ ጊዜ ስጎበኘው ለራሽያው እውቅ የስፖርት ሚዲያ ማች 4 ቲቪ የሚሰራው አርቴየም የተባለ ጋዜጠኛ አብሮኝ ነበር፡፡
ከራሽያው ጋዜጠኛ አርትዬም ጋር የተገናኘነው ቢብሎቴካ ኢምሌኔያ በተባለው የሜትሮ ጣቢያ ነበር፡፡ ከሜትሮው መውጫ ላይ በራሽያ እና በዓለም ዙርያ በግዝፈቱ ተጠቃሽ የሆነው ብሄራዊ ቤተመፅሃፍት ላይ የሚገኝ ሲሆን ትኩረቴን የሳበው ግን ከግዙፉ ህንፃ ደጃፍ ላይ የነበረው የፊዮዶር ዶስቴቪስኪ ግዙፍ ሃውልት ነው፡፡ ሃውልቱ ዶስቶቪስኪ የድርሰት ስራውን ጨርሶ ወይንም ለመጀመርያ በሃሳብ ተመስጥኦ የተቀመጠበትን ሁኔታ የሚገልፅ ነው፡፡ በሞስኮ የተመለከትኩት ይህ ሃውልት ለዶስቴቭስኪ ብቸኛው አይደለም በራሽያ የተለያዩ ከተሞች የተለያዩ መታሰቢያዎች ተሰርተውለታል፡፡ ለራሽያ እውቅ ደራሲዎች ሐውልቶች መስራት የአገሬው ባህል ነው በቃ፡፡
አርባት ከሞስኮው የክሬምሊን ቤተመንግስት በስተምዕራብ 800 ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ግራና ቀኝ የእግረኞች መተላለፊያ አስፋልት ያለውና ኮብልስቶን መሃሉ ላይ የተነጠፈበት ይህ የእግረኞች አደባባይ ከ1 ኪሎሜትር በላይ ርዝማኔ አለው፡፡ ይህ ጎዳና ከ15ኛው መቶ ክፍለዘመን ጀምሮ በአገልግሎት ላይ የነበረ መሆኑን ለማመን ይከብዳል። ምክንያቱም የመንገዶቹ አለመበላሸት፤ በዙርያው ያሉት ህንፃዎችና አፓርትመንቶች ወቅታዊ ሁኔታ እና ንፅህና ነው፡፡ በራሽያ እና የቀድሞ ሶቭዬት ህብረት ታሪክ  ጦርነቶች የተደረጉበት፤ አብዮት  የተፋፋሙበትና ኪነጥበብ የተስፋፋበት አርባት  በሞስኮ ከተማ ከሚገኙ የድሮ ጎዳናዎች እንደነበረ በመቆየቱ ያስገርማል፡፡
አርባት የራሽያ ኪነጥበብ፤ ስነጥበብ፤ ፤ ባህልና ኑሮ መናሐርያ ሆኖ ይታወቃል፡፡ በጎዳናው ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ተገኝቼ በጎበኘሁበት ወቅት የዓለም ዋንጫው ቱሪስቶች ከላይ እስከታች በብዛት እየተመላለሱበት ነበር፡፡ በእግረኞቹ አደባባይ መግቢያ  ላይ የተመለከትኳቸው የጎዳና ላይ ሰዓሊዎች ትኩረቴን በመሳብ የመጀመርያዎቹ ነበሩ፡፡ በጎልማሳና በአዛውንት እድሜ ላይ የሚገኙት እነዚህ የጎዳና ሰዓሊዎች በየራሳቸው ስፍራ መሳያ ቦርዳቸውን ተክለው ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶቹ ሰው አስቀምጠው፤ ሌሎቹ ፎቶግራፍ እየተመለከቱ ይስላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ‹‹እንሳል›› በሚል ወጭ ወራጁን ለማግባባት ይሞክራሉ፡፡ በየራሳቸው ስፍራ የሰሯቸውን የራሳቸውን ምስሎች እና ሌሎች ስራዎቻቸውን በመደርደር ያስተዋውቃሉ፡፡ አንዱ ሰዓሊን ተጠግቼ ስንት እንደሚስለኝ ጠየቅኩት፡፡ 1ሺ ሩብል አለኝ በኢትዮጵያ 500 ብር እንደማለት ነው፡፡ ከሰዓሊዎቹ ሌላ በአርባት ጎዳና ላይ ላይ ታች ሲሉ የምትመለከቷቸው ደግሞ የተለያዩ የንቅሳት፤ የውበት ስራ እና ሌሎች የታላቅ ቅናሽ የቦርድ ማስታወቂያዎችን በጀርባና ደረታቸው ላይ አንጠልጥለው አላፊ አግዳሚውን ለመሳብ የሚሞክሩት ናቸው፡፡
ለመኪና ዝግ በሆነው አርባት ጎዳና ላይ የሞስኮ ነዋሪዎች፤ ከተለያዩ የራሽያ ግዛቶች የሚመጡ ጎብኝዎች እና ቱሪስቶች ያሻቸውን ለብሰው እና የፈለጉትን ተግባር እያከናወኑ እንደልብ መንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡  አውራ ጎዳናው የእግረኞች አደባባይ ብቻ ሳይሆን አስቀድሜ እንደጠቀስኩት የጎዳና ላይ ሰዓሊዎች፤ መፅሃፍ ሻጮች፤ የተለያዩ አርቲስቶች፤ ሙዚቀኞች፤ የሰርከስ ባለሙያዎች፤  ዳንሰኞች፤… ልዩ ልዩ ሙያተኞች እና ጥበበኞች የሚሰበሰቡበት፤ የሚነግዱበት እና ትርኢቶቻቸውን የሚያሳዩበት ነው፡፡  በአካባቢው በከፍተኛ ደረጃ የተማሩ የራሽያ ምሁራን፤ ታዋቂ ሰዓሊዎች እና ደራሲዎች ከድሮ ጀምሮ እንደሚኖሩ የራሽያው ጋዜጠኛ አርትየም ሲነግረኝ፤ አሌክሳንደር ፑሺኪን፤ ቪክቶር ሶይ፤ የቶልስቶይ ቤተሰቦች፤ ሌሎች እውቅ ምሁራን፤ ሙዚቀኞች እና አርቲስቶች መኖርያቸው በዚህ አካባቢ እንደነበር በመጠቃቀስ  ነበር፡፡ በጎዳና ግራና ቀኝ የሚገኙ አፓርትመንቶች እና ቪላዎች ዛሬም ድረስ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፤ ለካፌ እና ለሬስቶራንት አገልግሎት ለመኖርያ እና ለሌሎች ስራዎች የአካባቢውን ታሪካዊ ይዘት እና ሁኔታ በመጠበቅ የተገነቡ ህንፃዎች እና ቪላዎችም ይገኙበታል፡፡ አሌክሳንደር ፑሽኪን ከሚስቱ ጋር የኖረበትን ቤት በጎዳናው ላይ የተመለከትኩት ቀልብን በሚገዛው የህንፃው ውሃ ሰማያዊ ቀለም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት  የፑሽኪን መታሰቢያ ሙዚዬም ሆኖ የሚያገለግለው ቤቱ ደጃፍ ላይ ደግሞ የአሌክሳደር ፑሽኪንና የባለቤቱ ሐውልትም ቆሟል፡፡ በርካታ ቱሪስቶች ፎቶ ለመነሳት የሚመርጡት ቦታ ነው፡፡ በአርባት ጎዳና ላይ ትኩረቴን ከሳቡ ስፍራዎች  ሌላኛው ለታዋቂው የራሽያ ሙዚቀኛ ቪክቶር ሶይ መታሰቢያ ተብሎ የተተወ የድሮ ግድግዳ ነው፡፡ ቪክቶር ሶይ በራሽያ እጅግ ታዋቂ የሆነው የሮክ ባንድ ኪኔ መስራች ሲሆን በሶቪዬት ህብረት የለውጥ ታሪክ እና በአዲስቷ ራሽያ በጥበቡ ተፅእኖ ለመፍጠር የበቃ ሆኖ በመላው አገሪቱ ከፍተኛ ክብር ይሰጠዋል፡፡ አርባት ላይ ለቪክቶር ሶይ መታሰቢያ የሆነው ግድግዳ በቀለማት፤ በተለያዩ ግራፊክ ፅሁፎች የተዋበ እና የተዥጎረጎረ ነው፡፡ ቪክቶር ሶይ ሞስኮ ውስጥ በጣም ዝነኛ መሆኑን ለመገመት በስፍራው በነበርኩበት ወቅት የታዘብኩትን ልጥቀስላችሁ፡፡ የተወሰኑ ወጣቶች ከመታሰቢያው ግድግዳ ፊት ለፊት ተሰብስበው በቦክስ ጊታር ሙዚቃውን ሲጫወቱ ተመልክቻለሁ፡፡ በየ5 ደቂቃውም ግድግዳው አካባቢ ፎቶ የሚነሳ አይጠፋም ነበር፡፡ ራሽያዊው ጋዜጠኛ አርትዬም እንደገለፀልኝ በስራ ዘመኑ ከ20 በላይ ምርጥ አልበሞችን የሰራው ቪክቶር፤ ለራሽያውያን ለውጥ የቆመ እና ለጥበብ ራሱን የሰጠ አብዮተኛ ሙዚቀኛ ነው።   ቪክቶር ሶይ አብዮተረኛ ሙዚቀኛ ቢሆንም በድህነቱም ይታወቅ ነበር፡፡
ወደ አርባት ጎዳና ለ3ኛ እና ለመጨረሻ ጊዜ የተመለስኩት 21ኛው የዓለም ዋንጫ በተጠናቀቀበት ማግስት ነበር፡፡ በእግረኞች አደባባዩ የዓለም ዋንጫ ቱሪስቶች ብዛት ቢቀንስም ግርግሩ እንደነበር ነው፡፡ ወደ ጎዳና የተመለስኩትም ከጎዳና ሰዓሊዎቹ በአንዱ የማታወሻ ስዕል ለመሰራት ወስኜ ነበር፡፡ ዞር ዞር እያልኩ ሰዓሊዎቹንና ስራዎቻቸውን ከተመለከትኩ በኋላ በመጨረሻም አንድ ጎልማሳን ጠጋ ብዬ ተዋወቅኩት፡፡ በራሽያ ቋንቋ ያወራ ስለነበር ከጅምሩ ለመግባባት ቢቸግረንም መሳል መፈለጌን በመረዳቱ በ400 ሩብል በኢትዮጵያ 200 ብር በ30 ደቂቃ እስልሃለሁ ብሎ እቅጩን ነገረኝ፡፡ በዋጋው ተስማምቼ ፊት ለፊቱ ካለው ወንበር ላይ ተሰየምኩለት፡፡ በራሽያ ቋንቋ እየዘፈነ አንዳንዴም እያፏጨ በ30 ደቂቃ ውስጥ ምስሌን እንደ ፎቶ ስሎ ሰጠኝና የሚገርም ማስተወሻ ስንብት ሆነልኝ፡፡
የማክሲም ጎርኪ ግዛት ኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ
በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ከሞስኮ ውጭ ለመጀመርያ ጊዜ የጎበኘኋት የራሽያ ከተማ  ኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ ትባላለች። ከሞስኮ 425 ኪሜትር ርቃ ወደ የምትገኝ ሲሆን ወደዚያ ለመድረስ የ5 ሰዓታት አገር አቋራጭ የባቡር ጉዞ አድርጊያለሁ፡፡ በራሽያና በፊፋ የተመደበው ዘመናዊ እና ምቾት ያለው ባቡር  በመሆኑ ጉዞው የሚያሰለች አልነበረም። ከባንግላዴሽ፤ ህንድ እና ከአርጀንቲና ጋዜጠኞች ጋር አንድ አካባቢ ስለነበርን የዓለም ዋንጫውን በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ስንወያይበት ቆይተን ከዚያም በየአገራችን ያለውን የሚዲያ ሁኔታም አውግተናል፡፡ የአርጀንቲናው ጋዜጠኛ ስለ አርጀንቲናዊያን ደጋፊዎች በብዛት ምናልባትም ከ20 ሺ በላይ ሆነው ወደ ራሽያ የገቡበትን  ምክንያት ሲያስረዳኝ ዋንጫውን እናሸንፋለን በሚል ተስፋ መሆኑን በመጥቀስ ሲሆን፤ አንዳንድ ደጋፊዎች ከየኩባንያቸው ብድር ወስደው አንዳንዶች ደግሞ ቤታቸውን ሁሉ ሸጠው ራሽያ መድረሳቸውን  ሁሉ ገልፆልኛል፡፡ የህንድ እና የባንግላዴሽ ጋዜጠኞች በበኩላቸው ደግሞ በየአገሮቻቸው ስለሚሰሯቸው ጋዜጣዎቻቸው ከፍተኛ የኮፒ ሽያጭ እና ተነባቢነት አውግተውኛል፡፡ በሁለቱ አገራት የጋዜጦች ሽያጭ በማህበራዊ ሚዲያው መስፋፋት እና በኢንተርኔት ደንበኛ ሆኖ የማንበብ ባህል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መቀነሱ ቢያሳስባቸው በየአገሮቻቸው እለታዊ እና ሳምንታዊ ጋዜጦች በአንድ እትም ከ50 እስከ 100ሺ ኮፒዎች እንደሚሸጡም ነግረውኛል፡፡ በተጨማሪም ከሁሉም ጋዜጠኞች ጋር በየአገራችን ስለሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን እያነሳን ስንጫወትም ስለነበር ጉዟችንን ምቹ ለማድረግ ችለናል፡፡ በተለይ ግን ከራሽያዊው ጋዜጠኛ እና የሞስኮ ነዋሪ አርትዬም  ጋር በባቡሩ አገር አቋራጭ ጉዞ ላይ ባቡር ውስጥ የጀመርነውና በኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ እውቅ አደባባይ እና አውራጎዳና ላይ እየተዘዋወርን የተሰራው የቪድዮ ቃለምልልስ  የማልዘነጋው ነበር፡፡ በቃለምልልሱ ስለራሽያ የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ፤ ስለሞስኮ ከተማ አጠቃላይ ገፅታ እና የእድገት ደረጃ፤ ራሽያ ከገባሁ ወዲህ በራስታ ፀጉሬ እና በማደርጋቸው አረንጓዴ ቢጫ ኮፍያዎች  ትኩረት ስለመሳቤ ፤ ስለ ኢትዮጵያ እና የራሽያ ህዝቦች የጋራ ባህልና ሃይማኖት፤ ስለ ሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች፤ ስለቀድሞዋ ሲቪዬት እና ኢትዮጵያ ወዳጅነት፤ በራሽያ ተምረው በስነጥበብ እና በስነፅሁፍ የላቁ ስራዎች ስላበረከቱ ኢትዮጵያውያን፤ በኢትዮጵያውያን ስለሚታወቁት የራሽያ የጥበብ ሰዎች ፑሽኪን፤ ጎርኪ፤ ዶስቶቭስኪ እና ሌሎችም በማንሳት በስፋት ተጨዋውተናል፡፡ አርቲዬም የተባለው የራሽያ ጋዜጠኛ የቪድዮ ቃለምልልሱን የሰራው PROSTOPROSSPORTS ለተባለ የራሽያ ኢንተርኔት ቲቪ ላይ ለማቅረብ ነበር፡፡ እኔም ለቃለምልልሱ ሙሉ ትብብር ሳደርግ ጥንታዊቷን የራሽያ መዲና ኒዚሂኒን ኖቭጎሮድ ከላይ እስከታች በተሟላ መረጃ ለመጎብኘት አግዞኛል፡፡
ኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ነዋሪ ያላት ስትሆን ከተቆረቆረች ከ797 ዓመታት በላይ አስቆጥራለች፡፡  በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የራሽያ መንግስት መቀመጫ ሆና ያገለገለችው ከተማዋ በሶቪዬት ህብረት ዘመን ለማናቸውም የውጭ አገር ዜጋ ጉብኝት  ዝግ ነበረች፡፡ ከተማዋ የማክሲም ጎርኪ የትውልድ ስፍራ በመሆኗ በመላው ዓለም የሚታወቅ ሲሆን  በታላቁ የቮልጋ ወንዝ ላይ ከተመሰረተች በኋላ  በራሽያ ታሪክ እና ባህል ያለፈችባቸው ዘመናት በርካታ የቱሪዝም መስህቦች  እንዲኖራት አድርጎ  በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት አስመዝግቧታል፡፡
የኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ ከተማን የጎበኘሁት አርጀንቲና ከክሮሽያ ከተገናኙበት የዓለም ዋንጫው ጨዋታ በፊት ነበር። ከተማዋ ከገባሁ በኋላ የመጀመርያው ተግባሬ 44899 ተመልካች የሚያስተናግደውንና  በ290 ሚሊዮን ዶላር ወጭ የተገነባውን ኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ ስታድዬም መጎብኘት እና በሚዲያው ማዕከል በመገኘት አስፈላጊውን የስታድዬም መግቢያ ከፊፋ ዴስክ መቀበል ነበር፡፡ 21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ እኔ የተመለከትኩትን የአርጀንቲና እና ክሮሽያ ጨዋታ ጨምሮ ስድስት የምድብ ጨዋታዎችን ያስተናገደው ይህ ዘመናዊ ስታድዬም ከተማዋን በሚያካልሉት እና በሚያቆራርጡት የቮልጋ እና ኦካ ወንዞች ዳርቻ ላይ መገንባቱ ልዩ ውበት ፈጥሮለታል፡፡ ስታድዬሙ ከሚያምር ግዝፈቱ ጋር ከዓለም ዋንጫ በኋላ ያለ አገልግሎት ወና ሆኖ እንደሚቀር የከተማው ነዋሪዎች ስጋት ነበራቸው፡፡ ዋኛው ምክንያት የኒዚሂኒ ነዋሪዎች ከእግር ኳስ ይልቅ የሚያፈቅሩት የሆኪ ስፖርትን በመሆኑ ነው፡፡ ምናልባትም በአጭር ጊዜ ውስጥ የስፖርት መሰረተልማቱን ወደ ሆኪ ስታድዬም ሊቀየር እንደሚችል ነው የተረዳሁት፡፡ በኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ ስታድዬም ከጨዋታው በፊት ከነበረኝ አጭር ቆይታ በኋላ ከአርቴየም ጋር በሜትሮ ባቡር ተሳፍረን ወደ ከተማዋ እምብርት ለጉብኝት አምርተናል፡፡ ጉብኝቱን የጀመርነው የማክሲም ጎርኪ ሃውልት ከሚገኝበት አደባባይ  ነበር፡፡ የጎርኪ ሃውልት ገዝፎ የሚታይበት አደባባይ ላይ ስንደርስ በአለባባሴ እና በአጠቃላይ ሁኔታዬ የተማረኩ የዓለም ዋንጫው በጎ ፈቃደኞች ለትውውቅ ወዲያውኑ ነበር የተጠጉኝ፡፡ ያው እንደተለመደው የመጀመርያው ጥያቄያቸው ከየት ነህ የሚለው ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ መሆኔን ስነግራቸው ከፊታቸው ላይ ደስታ ይነበብ ነበር፡፡ ይሄኔ ነበር ራሽያዊው ጋዜጠኛ አርትዬም በማክሲም ጎርኪ ሃውልት መማረኬን ተረድቶ ጥያቄ ያነሳው፡፡ ስለ ማክሲም ጎርኪ ታውቃለህ እንዴ ነበር ጥያቄው፡፡  በምላሼ ማክሲም ጎርኪ በኢትዮጵያ ከፍተኛ እውቅና ካላቸው የዓለማችን ደራሲዎች አንዱ መሆኑን የግጥም ስራዎቹ፤ አጭር ልቦለዶቹ እና የቲያትር ድርሰቶቹ በአማርኛ ቋንቋ ተተርጉመው በስፋት መነበባቸውን ነግሬዋለሁ፡፡ በምላሼ የተገረመው አርቲዬም ብቻ አይደለም የኒዚሂኒ ከተማ የዓለም ዋንጫ በጎ ፈቃደኞችም የሚኮሩበትን ማክሲም ጎርኪ ሳነሳላቸው ከፍተኛ ኩራት ይስተዋልባቸው ነበር፡፡ ስለዚህም ለአስገራሚው ትውውቃችን ማስታወሻ ያስፈልጋል ካሉ በኋላ ከሐውልቱ ስር ቆመን ፎቶ በመነሳት ተለያይተናል፡፡ በነዋሪዎቿ ኒዚሂኒ በሚል ስያሜ በአጭሩ የምትጠራው ከተማዋ ከ1932 እስከ 1990 እኤአ  ድረስ ትውልዱ በዚያ በሆነው ታላቁ የዓለማችን ገጣሚና ደራሲ ማክሲም ጎርኪ መታሰቢያነት ጎርኪ ተብላ ትጠራ ነበር። የጎርኪ ሃውልት በሚገኝበት አደባባይ  የተመለከትኳት አንዲት በአበባ ቅርፅ የተሰራች ሃውልት ትኩረቴን የሳበችው ከዚህ በኋላ ነበር፡፡ አብረውኝ ፎቶ የተነሱት የዓለም ዋንጫ በጎ ፈቃደኞች አለቃ የነበረችው ሴት ይህንኑ በመታዘብ ቀረብ ብላ አወያየችኝ፡፡ በውይይቱም በራሽያ አበባ ትልቅ ትርጉም እና ክብር እንደሚሰው የተረዳሁበት አጋጣሚ ነበር። ስለራሽያውያንና ስለ አበባ ባህላቸው በቀጣይ ሳምንት በማቀርበው ማስታወሻ እመለስበታለሁ፡፡
ከማክሲም ጎርኪ አደባባይ ተነስተን ጉብኝታችንን የቀጠልነው ግዙፉ የክሬምሊን ግንብ እስከሚገኝበት የከተማው እምብርት በሚወስደው አውራጎዳና ላይ ነበር፡፡ እንደብዙዎቹ የራሽያ ከተሞች በዓለም አቀፍ መስተንግዶዎች ብዙ የማትሰራው ከተማዋ በዓለም ዋንጫው መስተንግዶ በከፍተኛ ጉጉት ነዋሪዎቿን አስተባብራ እንግዶችን ለመቀበል ጥረት ማድረጓን እየታዘብኩ ነው፡፡ በአውራጎዳናው ወደፊት ወደ ወደኋላ ወደ ጎን እየተዘዋወርኩና እያማተርኩ የተመለከትኳቸው ሁሉ ከምናብ ሊረሱ የማይችሉ ትእይንቶች  ነበሩ፡፡ በየህንፃዎቹ ደጃፍ የነበሩ የአበባ መናፈሻዎች፤ የታላላቅ ራሽያውያንና ባለታሪኮች የሙሉ ሰውነት ሃውልቶች፤ የዓለም ዋንጫው ቱሪስቶችን ለማዝናናት በአውራ ጎዳናው ላይ በየቦታው የሚሰሩ ሙዚቀኞች፤ የተለያዩ ትርኢቶችን የሚያሳዩ እና ልዩ አለባበሶችን የሚያስተዋውቁ አርቲስቶች፤ በቡድን ሆነው አስገራሚ የጎዳና ላይ አክሮባት እና ትርኢት የሚያቀርቡ ወጣት ዳንሰኞች ናቸው፡፡ እነዚህን የጎዳና ላይ ትእይንቶች እየተመለከትኩ፤ ፎቶ እያነሳሁ ከራሽያው ጋዜጠኛ አርትዬም ጋርም የቪድዮ ቃለምልልሱንእየሰራን በከተማው እምብርት ወደ የሚገኘው የክሬምሊን ግንብ ደርሰናል፡፡ በዚሁ ግንብ ዙርያ የሚገኙትን ሚኒን እና ፖዝ ሃርስኪ የተባሉ አደባባዮች በማዋሃድ የተዘጋጀ የፊፋ ፋን ፌስት ነበር፡፡  የዓለም ዋንጫ ጨዋታ በስክሪን እንዲታይበት በተዘጋጀው የደጋፊዎች አደባባይ በነበረኝ የተወሰነ ቆይታ ዓለም ዋንጫው ወደዚህች ጥንታዊ ከተማ በመምጣቱ ከመላው ዓለም በርካታ ህዝብ ሊስብ መቻሉን ነው፡፡ በሁለቱ አደባባዮች ላይ ያረፉት ግዙፎቹ የፊፋ ፋን ፌስት ጨዋታ መመልከቻ ስክሪኖች ታላቁን የስፖርት መድረክ አድምቀዋል ከተባሉት የተጠቀሱ ናቸው፡፡
ራሽያዊው ጋዜጠኛ አርትዬም እንደገለፀልኝ የራሽያ ሁለት ግዙፍ ወንዞች ቮልጋ እና ኦካ የሚገኙባት ኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ በወንዝ መዝናኛዎች እና ትራንስፖርት ቱሪዝም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ቢኖራትም በኢኮኖሚ፤ በትራንስፖርት፤ በሳይንስ፤ በትምህርት እና በባህል ማዕከልነትም  ከራሽያ ግዛቶች ጎልታ የምትጠቀስ ናት፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በራሽያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከልነት እየታወቀች መምጣቷን ነው፡፡
በኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ ከተማ እምብርት ላይ ጎልቶ የሚታየው  የድሮው  የመንግስት መቀመጫ እና ዙርያውን የከበበው የክሬምሊን ግንብ በርዝመቱ እና ግዝፈቱ ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ታሪክ በወራሪ ሃይልና በጠላት ያልተደፈረ በመሆኑ ይታወቃል፡፡ በዙርያው ደግሞ በርካታ ዩኒቨርስቲዎች፤ ቲያትር እና ሲኒማ ቤቶች እንዲሁም ሙዚዬሞች ተሰባስበው መገኘታቸው ከግንቡ ታሪካዊ ገፅታ እና ውበት ጋር ተዳምሮ ልዩ ድባብ ፈጥሮለታል፡፡ ከ600 በላይ ታሪካዊ ስነህንፃዎች፤ የታላላቅ ሰዎች መታሰቢያ እንዲሁም የተለያዩ የታሪክ ምዕራፎች እና የባህል መገለጫ የሆኑ ሃውልቶች እና ቅርፃቅርፆች ከተማዋን ዙርያ ገብ የሞሏት ሲሆን በተለይ የስታሊንና የሶቪዬት ህብረት ዘመን አሻራዎች በብዛት ይስተዋልባቸዋል፡፡
ኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ በራሽያ የስነጥበብ ታሪክም ጉልህ ቦታ እንደሚሰጣት ከአርትዬም ማብራርያ መገንዘብ ችያለሁ፡፡ ከተማዋ እና ነዋሪዎቿ ለስነጥበብ ከፍተኛ ፍቅር እንዳላቸው በአውራጎዳናው፤  በአደባባዩ እና በየፓርኩ የሚሰሩ ሰዓሊዎችን በብዛት መመልከቴ አረጋግጦልኛል፡፡  አርቲዬም  እንደነገረኝ ኒዚሂኒ በዓመት ከ12ሺ በላይ የስዕል ኤግዚብሽኖች በማስተናገድ ለራሽያ እውቅ የስነጥበብ እና የቅርፅ ባለሙያዎች መናሐርያ ሆናለች፡፡  ይቀጥላል

Read 4487 times