Saturday, 11 August 2018 10:37

በአርጀንቲና ጽንስ ማቋረጥ መከልከሉ ተቃውሞና ድጋፍ ገጥሞታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የአርጀንቲና ፓርላማ የአገሪቱ ሴቶች ባረገዙ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ጽንስ ማቋረጥ እንዲፈቀድላቸው የሚደነግገውን ረቂቅ ህግ ውድቅ ማድረጉ በበርካታ የአገሪቱ ዜጎች ዘንድ ተቃውሞ ቢገጥመውም፣ድጋፋቸውን የገለጹ እንዳሉም ተዘግቧል፡፡
የፓርላማው አባላት በረቂቅ ህጉ ላይ ለ15 ሰዓታት ያህል ክርክር ካደረጉ በኋላ 38 ለ32 በሆነ አብላጫ ድምጽ ህጉ ውድቅ መደረጉን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ ይህም የሴቶች መብት ተሟጋች ተቋማትንና በርካታ የአገሪቱ ዜጎችን ማስቆጣቱን ጠቁሟል፡፡
የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የፓርላማ አባላቱ ህጉን እንዳያጸድቁት ግፊት አድርገዋል፣ ሴቶች ጽንስ የማቋረጥ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል በሚል የመብት ተሟጋቾቹ ተቃውሟቸውን መግለጻቸውን የጠቆመው ዘገባው፤በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች በቦነሳይረስ ጎዳናዎች ላይ በእንባና በቁጣ የታጀበ ተቃውሞ ማድረጋቸውን አመልክቷል፡፡
ህጉ ውድቅ መደረጉን የተቃወሙ አርጀንቲናውያን የመኖራቸውን ያህል፣ ውሳኔውን ደግፈው በአደባባይ ደስታቸውን የገለጹ የጽንስ ማስወረድ ተቃዋሚ ዜጎች በርካቶች እንደሆኑም ዘገባው ገልጧል፡፡ በቅርቡ የተደረገ ጥናት፤ አብዛኛው የአገሪቱ ዜጋ የጽንስ ማስወረዱን እንደሚደግፍ ለማረጋገጥ መቻሉንም አስታውሷል፡፡
በአርጀንቲና የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ማሬላ ቤልስኪ፤ ረቂቅ ህጉን በተመለከተ ዜጎች የያዙትን አቋም ለመፈተሽ በተደረገው ጥናት፣ 60 በመቶ ያህል ዜጎች ህጉ እንዲጸድቅ እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን አስታውሰው፣ ፓርላማው ህጉን ውድቅ ማድረጉ አግባብነት የለውም ሲሉ ተችተዋል፡፡
በአርጀንቲና የጽንስ ማቋረጥ ማድረግ የሚቻለው ሴቶች በአስገድዶ መድፈር ሲያረግዙና እርግዝናው ለእናትየዋ ጤና አስጊ ሲሆን ብቻ እንደሆነም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 1141 times