Saturday, 11 August 2018 10:40

የፊሊፒንሱ መሪ ሙሰኛ ፖሊሶችን እገድላለሁ አሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 5.5 ሚ ዶላር የሚያወጡ 77 የኮንትሮባንድ መኪኖችን አውድመዋል

     የፊሊፒንሱ ፕሬዚዳንት ሮዲሪጎ ዱቴሬ ሙስናን ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽመዋል የተባሉ ከ100 በላይ የአገሪቱ ፖሊሶችን ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ ያለ ምህረት እንደሚገድሉ ከባድ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውና በድምሩ 5.5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ መኪኖችን በአደባባይ ማውደማቸው ተዘግቧል፡፡
በስልጣን መባለግ፣ የአደንዛዥ ዕጾች ህገ ወጥ ዝውውር፣ አስገድዶ መድፈር፣ ጠለፋና ዝርፊያን ጨምሮ በተለያዩ የወንጀልና የአስተዳደራዊ ድርጊቶች ክስ የተመሰረተባቸው ከ100 በላይ የሚሆኑ የአገሪቱ ፖሊሶች፣ በመንግስት ይቅርታ እንደተደረገላቸው የጠቆመው ዘገባው፤ ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ማክሰኞ በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር ፖሊሶቹ ለወደፊት በመሰል ተግባራት ላይ ተሰማርተው ከተገኙ ያለ አንዳች ማመንታት እንደሚገድሏቸው አስጠንቅቀዋል፡፡
“በእያንዳንዳችሁ ላይ ዕድሜ ዘመናችሁን በሙሉ እንደ ጥላችሁ እየተከተለ ምን እንደምትሰሩ የሚከታተል ስውር ሰላይ አሰማርቼባችኋለሁ፤ አንዲት ቅንጣት ስህተት ብትፈጽሙ ሰላዩ ከመቅጽበት መረጃ ይልክልኛል፤ ያን ጊዜ እናንተን አያድርገኝ” ሲሉም ጠበቅ ያለ ማስጠንቀቂያ ለፖሊሶቹ ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለፖሊሶቹ ቤተሰቦችም ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ “እነዚህ የውሻ ልጆች ከወንጀል እንዲታቀቡ ብትመክሯቸው ጥሩ ነው፡፡ በኋላ ቤተሰቦቻችን ተገደሉ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጸመ ምናምን እያላችሁ ብታላዝኑብኝ አልሰማችሁም!... ምክንያቱም እንደምገድላቸው አበክሬ አስጠንቅቄያቸዋለሁ!” ማለታቸውን አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ የጸረ ሙስና ዘመቻ የጀመሩት ፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዱቴሬ፣ በኮንትሮባንድ ወደ አገሪቱ የገቡ 76 የቅንጦት መኪኖችንና ሞተር ብስክሌቶችን ባለፈው ሳምንት እሳቸው በተገኙበት በአደባባይ እንዲጨፈለቁ ማድረጋቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል። በፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ በቡልዶዘር ተጨፍልቀው እንዲወገዱ የተደረጉት የቅንጦት መኪኖችና ሞተር ብስክሌቶች በድምሩ 5.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያወጡ የጠቆመው ዘገባው፤ ከተደመሰሱት እጅግ ዘመናዊ መኪኖች መካከል ላምቦርጊኒ፣ መርሴድስ ቤንዝ እና ፖሽ እንደሚገኙበትም አመልክቷል፡፡

Read 1882 times