Print this page
Sunday, 12 August 2018 00:00

በኮንጎ የኢቦላ ክትባት መሰጠት ተጀምሯል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜን ምስራቃዊ አካባቢ በምትገኘው የኪቩ አውራጃ ባለፈው ሳምንት የተቀሰቀሰውን የኢቦላ ቫይረስ ወረርሺኝ ለመግታት የሚያስችል የኢቦላ ክትባት መሰጠት መጀመሩን የአለም የጤና ድርጅት ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡
ክትባቱ በተለይ ደግሞ ለኢቦላ ቫይረስ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ለሆነ ዜጎች በመሰጠት ላይ እንደሚገኝ ያስታወቀው ድርጅቱ፤ በቀዳሚነትም በአገሪቱ ሰሜን ምስራቃዊ አካባቢ በምትገኘውና ወረርሽኙ በተቀሰቀሰባት የኪቩ አውራጃ ውስጥ በስራ ላይ ለሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች መሰጠቱን ገልጧል፡፡
ከሰሞኑ የተቀሰቀሰውን ወረርሽኝ ለመግታት የሚደረገው ጥረት አካል የሆነው የክትባት አገልግሎት በስፋት ለአገሪቱ ዜጎች ለማዳረስ እየተሰራ እንደሚገኝ የዘገበው ዥንዋ በበኩሉ፤ 3 ሺህ 220 ሰዎችን ለመከተብ የሚያስችል የኢቦላ ክትባት መዘጋጀቱንም አመልክቷል፡፡ ባለፈው ሳምንት በኮንጎ ሰሜን ምስራቃዊ አካባቢ በምትገኘው የኪቩ አውራጃ የተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽኝ እስካለፈው ረቡዕ ድረስ 17 ሰዎችን ማጥቃቱ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ሌሎች ተጨማሪ 74 የአገሪቱ ዜጎችም በቫይረሱ ተይዘዋል በሚል ተጠርጥረው በህክምና ማዕከላት ውስጥ እንደሚገኙ ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ከአገሪቱ መንግስት የጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአገሪቱ ታሪክ ለ10ኛ ጊዜ በወረርሽኝ መልክ የተቀሰቀሰውን የኢቦላ ቫይረስ ለመግታት፣ የህክምና ባለሙያዎች ግብረ ሃይል አቋቁሞ ሰፊ ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ተነግሯል፡፡

Read 2549 times
Administrator

Latest from Administrator