Saturday, 11 August 2018 10:59

የለውጥ ሂደቱን የሚያደናቅፉ ግጭቶች እንዴት ይፈታሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

• ዘርና ሃይማኖትን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች የቅድሚያ ትኩረት ማግኘት አለባቸው
  • በዶ/ር ዐቢይ እየመጣ ያለው ለውጥ፣ በግማሽ የተረጋጋ ዘላለማዊ ለውጥ ይመስላል
  • አሁን የሚታየውን የለውጥ ጅማሮ ከአደጋ መጠበቅ ያለበት ህዝቡ ነው
  • ሰውን ያለ ማስረጃ ማሰር ማለት የህግ የበላይነትን ማስከበር አይደለም


    በዶ/ር ዐቢይ አህመድና በአመራር ቡድናቸው የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በሃገር ውስጥና በውጭ አገራት ለሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ተስፋን አሳድሯል፡፡ በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ግን ተስፋን የሚያጨልሙ ግጭቶች፣የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት መውደም እየተከሰቱ ነው፡፡ እነዚህ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በእጅጉ ተስፋ የተጣለበትን የለውጥ እንቅስቃሴ እንዳይቀለብሱት ብዙዎች ስጋት አላቸው፡፡ ለመሆኑ የግጭቶቹ መንስኤ ምንድን ነው? ግጭቶቹ እንዴት ሊፈቱ ይችላሉ? የለውጥ ጅማሮውንስ እንዴት ከአደጋ መጠበቅ ይቻላል? በሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ አንጋፋ ፖለቲከኞችንና የህግ ባለሙያዎችን አነጋግሮ፣ አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡  

   

                “ፍቅር ማለት የህግ የበላይነት የለም ማለት አይደለም”
                  አቶ ተመስገን ዘውዴ (የቀድሞ የፓርላማ አባል)


    ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ ልናልም በማንችላቸው ደረጃ የዲሞክራሲና የነፃነት ስሜት እየተሰማን መጥቷል። በኢትዮጵያ ታይቶ፣ ተሰምቶ የማይታወቅ የአመራር ብቃትና የህዝብ ክብርን የማስጠበቅ ሂደት እየታየ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ጠ/ሚኒስትሩ፣ በጣም የሚያኮሩ ሰው ናቸው፡፡ ግን እሳቸው በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ስለ ፍቅር፣ ይቅርታና አንድነት ሲሰብኩ፤ አንዳንድ ሰዎች ይሄን እንደ ድክመትና የህግ የበላይነት ያለመኖር አድርገው የወሰዱት ይመስላል፡፡ የእሳቸው መንገድ የዲሞክራሲና የነፃነት ሁኔታን በትክክል ተገንዝቦ ወደፊት የሚራመድ ህዝብ መፍጠር የሚያስችል ነው፡፡ በዚያው ልክ ግን ስለ ህግ የበላይነት አበክረው መናገር አለባቸው፡፡ የሁሉም ነገር ማሰርያ የህግ የበላይነት መሆኑን መግለጽ ይኖርባቸዋል፡፡
አሁን ከየትኛውም ጊዜ የተሻለ የፖለቲካ ስርዓት እየመጣ ነው፤ ነገር ግን ይህ ሁኔታ መሬት ረግጦና ሰክኖ እንዲጓዝ፣ የህግ የበላይነት የመጨረሻው መቋጠሪያ መሆኑ አብዝቶ ሊነገር ይገባል፡፡
በሌላ በኩል፤ ከዚህ ቀደም ህዝብ የበደሉና ብዙ ጥፋት የፈፀሙ፣ ጥፋታቸው በውል ታውቆ፣ ፍ/ቤት ቀርበው ሲቀጡ አላየንም፡፡ ለትርጉም ሰፊ በሆነው የመደመር የይቅርታና የፍቅር መርህ ተጠልለው እየታለፉ ነው፡፡ ፍቅር ማለት የህግ የበላይነት የለም ማለት አይደለም። እሳቸውም በወሳኙ ቦታ የተቀመጡት በዋናነት ህግን ለማስከበር ነው፡፡ ስለዚህም በሀገሪቱ ላይ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና የፀጥታ ችግርን ለመፍታት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ በጥቂቱ የተጀመሩ ግጭቶች መስመራቸውን ስተው ለሀገሪቱ ከባድ ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አዝማሚያውም ወደዚያው ነው የሚመስለው፡፡ ከዚህ አንጻር የህግ የበላይነት ጉዳይ ለድርድር መቅረብ የለበትም፡፡ በሶማሌ ሰሞኑን የታየው ግጭት አንዱ መነሻ የህግ የበላይነት ለሁሉም እኩል መሆኑን ያለመገንዘብ ጉዳይ ነው፡፡
በክልሎች ውስጥ ያሉ ችግር ፈጣሪዎችንና ባለስልጣኖችን ጉዳይ በቸልታ ማየት አያስፈልግም፤ ግጭት ማስቆም ያልቻለ ባለስልጣን በዝምታ መታየት የለበትም፡፡ በቸልታ የሚታይ ከሆነ ሃገሪቱ ስርአት አልባ ነች እንደ ማለት ነው። ግጭቶች ሊቆሙ፣ ለውጡ ሊሰክንና ወደ በለጠ ዲሞክራሲ ሊሸጋገር የሚችለው የህግ የበላይነት ጉዳይ ትኩረት አግኝቶ ሲተገበር ነው፡፡


---------


            “ግጭቶችን የሚያመክን የህግ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል”
               ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም (ዓለማቀፍ የህግ ባለሙያ)


     በማንኛውም የለውጥ ጊዜ አሁን እያጋጠመን ያለው አይነት ሁከት ይጠበቃል፡፡ ዋናው ነገር ሁከቱን ማሳነስና ጉዳቱን መቀነስ መቻል ነው፡፡ የትኛውም መንግስት የመጀመሪያ ተግባሩ ህግን ማስከበር ነው፡፡ አሁን በየቦታው የሚፈጠሩ ግጭቶች ፖለቲካዊ አመክንዮ አያስፈልጋቸውም፤ በህግ የበላይነት መቆም አለባቸው፡፡ እነዚህን ሁከቶች የሚያመክን እርምጃ የግድ ይላል፡፡ ይህ ማለት ግን ህዝብን መደብደብ፣ መግደልና በጅምላ ማሰር እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በተቻለ መጠን ህግ በሚፈቅደው መሰረት እልባት መሰጠት አለበት፡፡ በተለይ ዘርንና ሃይማኖትን ለይቶ የሚፈጸሙ ግጭቶች አፀያፊ ናቸው፡፡ ጉዳታቸውም  ዘለቄታ ያለው ነው፡፡ ባለስልጣናት በዚህ ጥፋት ውስጥ እጃቸውን የሚያስገቡ ከሆነ፣ በሰው ዘር ላይ የሚፈፀም ጥቃት ነው የሚሆነው። እነዚህ ሰዎችን ሀገር በተረጋጋ ጊዜ ለህግ ማቅረብ የግድ ይላል፡፡
የህግ ጥሰትን በህግ ተጠያቂ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ምናልባት በህግ ተጠያቂ የሚሆኑ ወገኖች፤ ለበደሉት ህዝብ ይቅርታ አቅርበው፣ በይቅርታ ከቅጣት ሊድኑ ይችሉ ይሆናል፡፡ ዝም ብሎ በይቅርታ እንለፈው ከተባለ ግን የህግ የበላይነት ዋጋ ያጣል፡፡ ፍ/ቤትና የህግ ስርአት የተበጀው ተጠያቂነትን ለማስፈን እንጂ ሰዎችን ለማሰር አይደለም፡፡ በዚህ መንገድ ተጠያቂነትን ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ በደቡብ አፍሪካም የተደረገው ይሄው ነው፡፡ በዳዮቹ ከተበዳዮቹ ተገናኝተው፣ ይቅርታ ጠይቀው፣ ይቅርታ ወርዶ ነው ቅጣቱ የቀረላቸው። ኢትዮጵያ ውስጥም ይሄ ዓይነቱ ሂደት አስፈላጊ ነው፡፡ ይሄ ቀጠሮ የሚሰጠው ነገርም አይደለም፡፡
የወንጀል ድርጊት በይቅርታ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ምናልባት ተጠያቂነቱ ከሰፈነ በኋላ ቅጣቱ ሊቀር ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን አንድም ወንጀል በቸልታ መታለፍ የለበትም፡፡ በተለይ ከባድ ወንጀልን ዝም ብሎ በይቅርታ ማለፍ ራሱ ወንጀልን ይወልዳል፡፡ ሰውየው ተጠያቂ ካልሆነ ሌላ ወንጀል እየተወለደ ይሄዳል፡፡ ይህ እየታየ ያለው የለውጥ ሂደትም በዚህ መንገድ ነው መያዝና መተዳደር ያለበት፡፡ አሁን አጀማመሩ ጥሩ ነው፤ ነገር ግን ዘርና ሃይማኖትን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች የቅድሚያ ትኩረትና መፍትሄ ማግኘት አለባቸው። እነዚህ ችግሮች ተፈትተው ሰላም ሲሰፍን ነው ዲሞክራሲ ሊገነባ የሚችለው፡፡


-------------


             “ትልቁ ለውጥ የሚመጣው የጎሳ ፌደራሊዝሙን መቀየር ሲቻል ነው”
                አቶ አሰፋ ሃ/ወልድ (ፖለቲከኛ)


     የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር በጎሳ መቧደናችን ነው፡፡ የብሄር ግጭቱም ሆነ ለውጦችን በአግባቡ ማስተዳደር ወይም ወደበለጠ ደረጃ ለማሻገር መቸገር ዋነኛ ችግር የጎሳ ፖለቲካ ነው፡፡ ይህን በደርግም አሁንም እያየነው ያለ ነው፡፡ አሁን ያለው የጎሳ ፌደራሊዝም ደግሞ ለዚህች ሀገር ትልቁ ችግር ነው፡፡ ኬንያ፣ ሶቪየት ህብረትና ናይጄሪያ እንዲህ ያለ ፌደራሊዝም የነበራቸው ሲሆን በኋላ ላይ አገራቱ ብዙ ዋጋ ከፍለውበታል፡፡ የዘር ጭፍጨፋን አስተናግደዋል፣ ፌደሬሽናቸው የፈረሰባቸውም አሉ፡፡ ዛሬ ኬንያ፣ ናይጄሪያ (በከፊል) ሩዋንዳ ከዚህ በሽታ ነፃ የሆኑት የዘር ቡድንተኝነትና ፌደራሊዝምን በህግ በመከልከላቸው ነው። በሃይማኖት መቧደን በኛ ሃገር በህግ ክልክል ነው፡፡ በዘር መቧደንና የጎሳ ፌደራሊዝም ክልክል የማይደረግበት ምክንያት ምንድን ነው? ለአገራችን ትልቁ ነቀርሳ ይሄ የዘር ፖለቲካና ፌደራሊዝም ነው፡፡ ለምሳሌ ለምን በኤርትራ፣ ኡጋንዳና ሴኔጋል ውስጥ የዘር ግጭቶች የሉም? ምክንያቱም በእነዚህ ሃገራት የዘር ፌደራሊዝም ህገ ወጥ ነው፡፡ ስለዚህ ዜጎች በዘር ጎራ ለይተው ለግጭት አይጋበዙም፡፡ ግጭቶችን ለማስወገድ መፍትሄው ፌደራሊዝም በዘር የተመሰረተ እንዳይሆን በህግ መከልከል ነው፡፡ አሁን ዶ/ር ዐቢይ የፌደራሊዝምን ጉዳይ እያስጠኑ ነው፡፡ ምናልባት በጎ ውጤት ሊመጣ ይችላል፤ ዜጎችም ግፊት ማድረግ ይኖርብናል። በሀገሪቱ እስካሁን የተፈጠሩ ግጭቶች ሙሉ በሙሉ ዘርን ማዕከል ያደረጉ ናቸው፡፡ ስለ ግጭት ስንነጋገር፣ ይሄን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን።
ለውጥ ዘላለማዊ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ የለውጥ ፍላጎት ሲከማች ነው የኖረው፡፡ ይህ ሲከማች የኖረ የለውጥ ፍላጎት፣ ከሀገሪቱ የዘር ፌደራሊዝም ጋር ተዳብሎ፣ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል መገንዘብም ያስፈልጋል፡፡ በለውጥ ፍላጎትና በአናሳዎች አስተዳደር መካከል ከበድ ያለ ግንኙነት ነው ያለው፡፡
ለውጥ ሲመጣ አናሳዎች (Minority) የአስተዳደር ስጋት ውስጥ ስለሚወድቁ በስጋት ነው የሚመለከቱት፡፡ በአንፃሩ የብዙኃን (Majority) አስተዳደር ለውጥን በልበ ሰፊነት ነው የሚቀበለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየመጣ ያለው ለውጥ ተገቢ ነው፤ ነገር ግን ለውጡ በይዘት ደረጃ የሚጮህ ለውጥ ነው፡፡ ይሄንን ለውጥ ሰላማዊ ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ፓርላማው ማከናወን ያለባቸው ሥራ  አለ፡፡ አንደኛ ጠንካራ ተቋማት መፈጠር አለባቸው፡፡ ግለሰብ ወሳኝ የሚሆንባቸው ሳይሆን ህግ ወሳኝ የሚሆንባቸው ተቋማት መገንባት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ መከላከያ፣ ደህንነት፣ ፖሊስ፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ታሳቢ ይደረጋሉ፡፡
ሁለተኛ ለመሪነት የሚታጭ ሰው ብቃት ያለው፣ እድሜው ከፍ ያለ፣ እውቀትና ልምድ ያዳበረና በማህበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ያለው መሆን አለበት፡፡ ሶስተኛ ለውጥ የተረጋጋ፣ ዘላለማዊ ሂደት ነው፡፡ ይሄን የሂደት ስርአት ካልተከተለ ለግጭት ነው የሚጋብዘው፡፡ የደርግ ለውጥ አብዮታዊ ስለነበር ውሎ አድሮ ለግጭት ነው የዳረገን፡፡ ለውጥ አብዮታዊ ሳይሆን የተረጋጋ፣ ዘላለማዊ ሂደት ነው መሆን ያለበት፡፡ (ሪቮሊሽነሪ ሳይሆን ኢቮሊሽነሪ) በዶ/ር ዐቢይ እየመጣ ያለው ለውጥ፣ በግማሽ የተረጋጋ ዘላለማዊ ለውጥ ይመስላል፡፡
አሁን ቀጣዩ ሥራ ተቋማትን፣ ተጠያቂነትን፣ የህግ የበላይነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህም በዝግታ ነው መመራት ያለበት፡፡ የአመራር ጥራት መፈጠር አለበት፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ለውጡን በጎ አቅጣጫ ማስያዝ ከፈለጉ፣ ህዝቡ የአካባቢውን መሪ  እንዲመርጥ ማድረግ አለባቸው፡፡ በየሴክተሩ መሪዎች በህዝብ እንዲመረጡ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡  


-------------


              “ህዝቡ ለውጡን በጥርጣሬ ሳይሆን በጥንቃቄ ነው ማየት ያለበት”
                 አቶ ወንድሙ ኢብሳ (የህግ ባለሙያ)


     ለውጥ በባህሪው መጀመሪያ ላይ መንገራገጭ ያጋጥመዋል፡፡ ለውጡ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከተካሄዱ ለውጦች ዘገምተኛው ነው። ዘገምተኛው የመሆኑን ያህልም ቅፅበታዊ ለውጦችንም አስተናግዷል፡፡ በአፍሪካ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ገዥው ፓርቲ ውስጥ ነው የለውጥ ኃይሉ የተፈጠረው፡፡ ይሄ ትልቅ ነገር ነው። የለውጥ ኃይሉ እስካሁን ድረስ ያሳየው ትዕግስት የሚደነቅ ነው፡፡ ይህ ትዕግስት ደግሞ ሞኝነት የሆነባቸው ኃይሎች እንዳሉም አይተናል፡፡ ዜጎች በትንሽ ጥርጣሬ ያለ ማስረጃ ከሚታሰሩበት ሁኔታ ወጥተን፣ ዜጎች የሚታሰሩት በማስረጃ ብቻ ነው ወደሚል መንግስት ነው እየተሸጋገርን ያለው። ይህ ደግሞ መሰረታዊ የህግ አስተዳደር መርህ ነው፡፡ ሰውን ያለ ማስረጃ ማሰር ማለት የህግ የበላይነትን ማስከበር አይደለም፡፡ አሁንም ይህ መርህ ነው መቀጠል ያለበት፡፡ ታግሶና አጥንቶ በማስረጃ እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አሁን የምናስተውላቸው ዓይነት ግጭቶች መፈጠራቸው አይቀርም፡፡ ምክንያቱም የህግ የበላይነት ካልሰፈነበት ሁኔታ፣ ወደ የህግ የበላይነት የሰፈነበት ስርአት ስንሸጋገር ይህ አይነቱ ክስተት የተለመደ ነው፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን  የህግ የበላይነት ለማስፈን የሚደረገው ጥረት ጥሩ ነው፤ ነገር ግን የበለጠ ማጠናከርና ማጥራት ያስፈልጋል፡፡  
ህብረተሰቡ ይሄን ለውጥ መጠራጠር የለበትም፤ መጠንቀቅ ነው ያለበት፡፡ መጠራጠር ማለት ለውጡን መፍራት ማለት ነው፡፡ መሆን ያለበት ለውጡን ያለ ጥርጣሬ ተቀብሎ በጥንቃቄ ማየት ነው፡፡ የሰለጠኑ ሀገራት ዛሬ የደረሱበት ደረጃ የደረሱት በዚህ ሁኔታ ነው፡፡ የህግ የበላይነት የበለጠ እንዲሰፍን ፀጥታ አስከባሪው መጠናከር አለበት፡፡ ክልሎች የራሳቸውን ፀጥታ ማስከበር መለማመድ አለባቸው፡፡ እነሱ ማስከበር ካቃታቸው የፌደራል መንግስት ድጋፍ መስጠት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ነው ለውጡን በሰከነ መንገድ ይዘን፣ ወደተሻለ ፍፁማዊ ለውጥ መሻገር የምንችለው፡፡    

Read 5056 times