Sunday, 12 August 2018 00:00

በሶማሌ ክልል ግጭት የተሳተፉ ባለሥልጣናት ለፍርድ እንዲቀርቡ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

 የህገ መንግስቱ አንቀፅ 39 በአስቸኳይ እንዲሰረዝ መኢአድ ጠየቀ

     በሶማሌ ክልል ለበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋት ምክንያት በሆነው የሰሞኑ ግጭት የተሳተፉ የመንግስት ባለሥልጣናት በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ሰማያዊ ፓርቲ የጠየቀ ሲሆን መኢአድ በበኩሉ፤ በሃገሪቱ ለሚፈጠሩ መሠል ግጭቶች ምክንያት ነው ያለው የህገ መንግስቱ አንቀፅ 39 በአስቸኳይ እንዲሰረዝ ጠይቋል፡፡
በሶማሌና በሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች የሚፈጠሩ ግጭቶች ዘላቂ አልባት እንዲያገኙ በየጊዜው ግጭቶችን የሚፈጥሩና የሚያነሳሱ የመንግስት አመራሮችን በህግ መጠየቅ ወሳኝ ነው ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ህግ የማስከበሩንና በህግ  የማስጠየቁን ጉዳይም የፌደራል መንግስቱ በጥንካሬ ሊያከናውን ይገባል ብሏል፡፡
የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በመንግስት የስልጣን መዋቅር ላይ ተቀምጠው ወደ ኋላ ለመመለስ የሚጥሩ ወገኖች አሉ የሚለው  ፓርቲው፤ የለውጡ ሃይሎች ይህን በአፋጣኝ ማጥራት አለባቸው ብሏል፡፡  
“ሃገር ለማፍረስ የተቀመጠው አንቀፅ 39 የወለደው ችግር የበርካታ ዜጎችን ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል” በሚል ርዕስ መግለጫ ያወጣው የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በበኩሉ፤ በሃገሪቱ ለሚፈጠሩ መሠል ግጭቶች ምክንያቱ፣ በቋንቋና ብሄር ላይ የተገነባው ፌደራሊዝም በመሆኑ እንደገና መፈተሽ አለበት ብሏል፡፡
በሶማሌ ክልል ለተፈጠረው ግጭትም የህገ መንግስቱ አንቀፅ 39 ወሣኝ ሚና መጫወቱን የጠቆመው መኢአድ፤ በአስቸኳይ የህገ መንግስት ማሻሻያ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡ አያይዞም፤ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመኖር መብታቸው እንዲጠበቅ፣ መንግስት ለዜጎች ጥበቃ የማድረግ ሃላፊነቱን እንዲወጣ እንዲሁም የተዘረፉና የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናትና ቤቶች መልሰው እንዲሰሩ፣ በድርጊቱ ተሳታፊ ናቸው የተባሉ ባለስልጣናትም ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡

Read 7264 times