Sunday, 12 August 2018 00:00

የህሊና ህግ ሲመረመር--

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

 የሰው ልጅ ንቃተ ህሊና (conscience) ከፈጣሪ የመነጨ ነው ወይስ ከተፈጥሮ? ይሄ መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ ከቶማስ አኳይነስ ጀምሮ ያሉ የስነ መለኮት ልሂቃን፣ የሰው ልጅ ህሊና ምንጭ ፈጣሪ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ግን ይሄ የሰው ልጅ ህሊና ድንገት በሙሴ በኩል እንደ ህግጋት ተደንግጎ የተሰጠው ነው--- ወይስ የሰውን የተፈጥሮ ህሊና ፍላጎት ሙሴ ተገንዝቦ በፈጣሪ ስም ህግ አድርጎ መልሶ አስረከበው? “ሙሴ ፈጣሪን ፈጠረ?” ወይስ “ፈጣሪ ሙሴን ፈጠረ?” ወይስ ተዋነይ እንደተቀኘው፤ “ሙሴ ፈጣሪን /ፈጣሪ ደግሞ ሙሴን ፈጠረ?”
በሰው ልጆች አስተሳሰብ ንቃት ላይ ‹ህሊና› ከቀድሞውንም የነበረ እንደሆነ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ማስረጃዎችን ስንመረምር የሚገልፅልን ነገር በሰው ልጅ የተፈጥሮ ህሊና ምክኒያት በየዘመናቱ ሃይማኖቶች መነሳታቸውን ነው፡፡ ሃይማኖቶቹም በእነሱ ምክኒያት ለሰው ልጅ ህሊናን የሰጡት አስመሰሉ፡፡ ከሃይማኖቶቹ ወይም ከሞራል እሳቤዎቹ በኋላ ሰው ህሊና እንዳቀበለ ተደርጎ ተወሰደ፡፡ ወደ ሰው ልጅ የህሊና ስርዓት ለመድረስ በሃይማኖቶቹ በኩል ማለፍ ግድ መሰለ። የፈጣሪን መልዕክት ወደ ሰው የሚያደርሱትም ነቢያቶቹ ሆኑ፡፡
ዘመናዊ አሳቢዎች፤ የህሊና አስፈላጊነት በማህበረሰብ ከመኖር የመነጨ ነው ይላሉ፡፡ “ማንኛውም እንስሳ በማህበረሰብ የመኖር ንቃት በሂደት ከዳበረ፣ የስጋ ዝምድና እና አብሮ በመኖር የተዛመደ በቀጣይ እርስ በራስ የመተሳሰብ ንቃት ወይም ህሊና ያዳብራል፡፡ እንደ ሰው ልጅ ከዚህ አብሮ ተዛምዶ የመኖር ንቃት ጋር የሀሳብ ጉልበት ከታከለበት ደግሞ የህሊናው ብቃትም ከአስተሳሰቡ ውስብስብነት ጎን ለጎን ይዳብራል” ይላል፤ ቻርለስ ዳርዊን፡፡
ሙሴ በአስር ትዕዛዛት አጭር አድርጎ ያጠቃለለውን የህሊና ህግ ከሙሴ በፊት ደንግገው የተጠቀሙ ቀደምት ስልጣኔዎች ነበሩ፡፡ የሀሙራቢ ህግ (1780 B.C) ወደ 282 ዝርዝር ትዕዛዛት ያሉት ነው፡፡ አሁን የምዕራባዊያን ዴሞክራሲን ቅርፅ የነደፈው “Solon” (558 B.C) አቴናዊ ነው። የመጀመሪያውን የተፃፈ የህገ መንግስት ረቂቅ ያበረከተ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ዜግነትን የሚሰጠው የአቴንስ ተወላጅ በመሆን ሳይሆን በፆታ ወንድ ሆኖ፣ ለህገ መንግስቱ ለመገዛት የወደደ ሁሉ የሀገሪቱ ዜጋ መሆን እንዲችል የሚፈቅድ ነው፡፡ “ምንም አይነት ህግ እንዲፀድቅ የሀገሪቱ ዜጎችን የብልጫ ድምፅ ማግኘት ይገባዋል” … የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ ያስተዋወቀውም ይኼው ሰው ነው፡፡
ሁሉም የግብረ ገብ ህጎች ምንጫቸው የሰው ልጅ ህሊና ነው፡፡ ህሊና ደግሞ ከሃይማኖቶችም ሆነ ከህገ መንግሥቶች የቀደመ ስለመሆኑ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
“ጥሩ ለሆኑልኝ ጥሩ እሆናለሁኝ፡፡ ጥሩ ላልሆኑልኝም ጥሩ እሆናለሁ፡፡ ስለዚህም መልካምነት ተጨባጭ ይሆናል፡፡ በሀቅ ለሚቀርቡኝ ሀቀኛ ሆኜ እቀርባቸዋለሁ፡፡ ሀቅን ይዘው ለማይመጡም ግን ሀቀኛ እሆናለሁኝ፡፡ ይህን ጊዜ ብቻ ሀቀኝነት ይሰፍናል፡፡” ይላል፤ ታው (የታውይዝም ፍልፍስና ልሂቅ)፡፡
“ቁጣን በፍቅር አሸንፉ፡፡ እኩይን በመልካም ርቱ፡፡ ስግብግቦችን በመስጠት ድል ንሱ፡፡ ቀጣፊዎችን በእውነተኝነት አንበርክኩ፡፡” ይላል ቡድሂዝም (Dhammapada/223)
“ልቀት ያለው ፍጡር ክፉን በክፉ አይመልስም፤ ይኼ በተለይ ልብ ሊባል የሚገባው ህግ ነው። ለፃድቅ ሰዎች ስነ ምግባራቸው ጌጣቸው ነው። የፅድቅ ሰው መጥፎንም፣ አልያም ጥሩንም ወይም ነፍሰ ገዳይን ሞት እንዲያገኘው አይሻም (Hinduism.Ramayana kanda/115)”
የህሊና ህግን፤ አንዱን ከአንዱ ጋር በማመሳከር ሳይሆን ተፈጥሮአችንን (ህሊናችንን) በማድመጥ የምናረጋግጠው እውነት ነው፡፡ “አይንን ያጠፋ አይኑ ይጥፋ” የሚል ህግን ተፈጥሮአችን ይደግፋል። አፀፋን በመመለስ ወይም የተደረገብንን መልሰን በማድረግ የሚረካ ተፈጥሮ አለን፡፡  ከዚህ ተፈጥሮአችን አንፃር ሌላኛውን ተፈጥሮአችንን ጎን ለጎን ስንመዝነው ግን ሁለተኛው የረቀቀ ይሆንብናል፡፡ “ግራ ጉንጭህን ለሚመታህ ቀኙንም አዙረህ ስጥ” የሚለው “ይቅር ባይነትን” ከበቀል ተፈጥሮአችን ጋር የምንመዝንበት ነው። … የትኛውን እንደሚመርጥ የህሊናው ባለቤት ያውቀዋል፡፡
ሃይማኖቶቹ፣ ወይንም የግብረ ገብ እሳቤዎቹ ከግብፅ፣ ከባቢሎን፣ ፐርሺያ፣ ግሪክና ህንድ የመጡ መሆናቸው በተቀረው የዓለም ክፍል በወቅቱ ይኖር የነበረውን የሰው ዓይነት ህሊና አልባ አያደርገውም፡፡ ምክንያቱም፤ ሰው ሁሉ የህሊናውን አቅም ያገኘው ከተፈጥሮ ስለሆነ ነው። ወይም ደግሞ ዳርዊን እንዳለው፤ በማህበር ሆኖ የሚኖር እንስሳ (ማህበረሰባዊ እንስሳ) ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በዛው ተያይዞ ህሊናዊ ፍጡርም ሆኗል፡፡ በእርግጥ እንደ ደረሰበት የማህበረሰብ ስልጣኔ የህሊና ህጎቹን በጥሩ መልክ አደርጅቶ፣ በሃይማኖትም ሆነ ህገ መንግስት ደርዝ የመቅረፅ አዝማሚያ ላይ ልዩነት እና ብልጫ ቢኖርም … መሰረታዊ ተፈጥሮው ግን በሀይማኖቱ ምክኒያት የሚመጣ አይደለም፡፡
የህሊና ህጎች የማህበረሰብም የመተዳደሪያ ደንብ ናቸው፡፡ ከግለሰቡ ጋር ብቻ የተወሰኑ እንዳልሆኑ ለማስተዋል የሙሴን ኦሪታዊ ሃይማኖት ህጎችን ከ5-10 ማስተዋል ይጠቅማል፡፡ ከ1-5 ያሉት ግለሰቡ ከፈጣሪው ጋር ላለው ግንኙነት መከተል ያለበትን ህግና ስርዓት የሚደነግጉ ናቸው፡፡
“Have no other gods before me”
“Make no images of anything in heaven, earth, or sea, and do not worship or labor for them.”
“Do not use the name of your God in rain”
“Do not work on the sabbath.”
ግለሰቡ ከህብረተሰቡ ጋር ወዳለው መስተጋብር የሚመለሰው ከአምስተኛው ህግ ጀምሮ ነው። የሰው ልጅ አእምሮ የሚሰራው በማነፃፀር (Relations) ነው፡፡ የህሊና ህግ በማህበረሰቡ ላይም ይኼንኑ የግንኙነት ቅርፅ የሚይዝ ነው። ህጉ የሚነግረው ለግለሰቡ ቢሆንም ተግባራዊ የሚደረገው ወይም የሚሳካው ግን በሌሎቹ ላይ ነው፡፡
ወላጆችህን አክብር
አትግደል (ግድያ፡- ገዳይ እና ሟች በድርጊት አማካኝነት የሚተሳሰሩበት ነው)
አታመንዝር (አድራጊ እና ተደራጊ አለው)
አትስረቅ (ይሄም ተመሳሳይ ነው)
በሀሰት አትመስክር
የሌላ የሆነን ሀብትም ሆነ ሚስት አትመኝ
እነዚህን አስር ህጎች፣ ከ5-10 ያሉትን በጠቅላላው የሰው ልጅ ይቀበላቸዋል፡፡ የትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ብትሄዱ፣ ህጎቹ በተመሳሳይ መንገድ ተቀርፀው ይገኛሉ፡፡ … ኢ-ፍትሃዊ ተግባር የሚመነጨው እነዚህን ህጎች በተለያየ መንገድና ምክኒያት የተላለፈ አካል ሲኖር ነው፡፡ በየትኛውም የሰለጠነ ማህበረሰብ ውስጥ መግደል፤ መስረቅ፣ መዋሸት ወንጀል ነው። ምናልባት በመንግስት ደረጃ ይደረግ እንደው እንጂ---ተራው ህዝብ ወይም የማህበረሰቡ አባል ሀጢአት የተባለው ነገር ወንጀልም እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል። … ማመንዘርም ህሊና የማይቀበለው ተግባር እንደሆነ የማያውቅ የለም፡፡ ግን ከተደነገጉት ትዕዛዛት መሃል በሞራል ደረጃ ሀጢአት የሆነ ነገር ግን በተግባር ደረጃ ወንጀል ያልሆነ የስህተት አይነት አለ፡፡ የሚያስንቅ ግን የማያስከስስ፡፡
በዚሁ ብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር በፈቀደው ጦርነት ምክኒያት ግድያዎች ሲከናወኑ እናነባለን፡፡ “አትግደል” የሚለው ህግ ለአለም አቀፍ ሰው ልጅ ሁሉ ሳይሆን በማህበረሰቡ ውስጥ ለታቀፉት ብቻ የሚሰራ እንደሆነ እንጠራጠራለን። የእግዚአብሔር ህግጋትም ለሀገሩ ህዝብ ብቻ የሚሰራ ህገ መንግስት ይሆናል ይሄኔ፡፡ የሀገሩ ህዝብ ደግሞ አንድም በአስርቱ ትዕዛዛት መልክ የወረደውን ሃይማኖት የተቀበለ ህዝብና ህዝቡ በደም ዝምድና የተሳሰረ ነገድ ቅርፅ የያዘ ይሆናል። … ይሄ አንደኛው መላ ምቴ ነው፡፡
ሁለተኛው መላ ምቴ … ህጎቹ በምንም ዓይነት ሁኔታና ጊዜ (Unconditionally) የሚሰሩ ላይሆኑ ይችላሉ የሚል ነው፡፡ “all is fair in love and war” እንደሚባለው ምሳሌያዊ አነጋገር:: … በሰላሙ ጊዜ፤ ትዕዛዛቱ በማህበረሰቡ ውስጥም ሆነ ውጭ ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡ ማህበረሰቡ ውስጥ እርስ በራሱ ባለው መስተጋብርም ሆነ ማህበረሰቡ በጥቅል ከሌላ ማህበረሰብ ጋር ባለው ግንኙነት መሃል የህሊና ህጎች የሚሰሩበት ጊዜ አለ፡፡ ግን እንደ “ጦርነት” የመሰለ ከተለምዶው ሁኔታ ውጭ የሆነ እክል ሲከሰት፣ ህጎቹ እዛው ማህበረሰቡ ውስጥ ይመለሳሉ፡፡ ምናልባት በማህበረሰቡ ውስጥ የተነሳው ጠብ በህጎቹ አተገባበር ላይ በሁለት የማህበረሰቡ አካላት መሀል የትርጉም ግጭት ተፈጥሮ ሊሆንም ይችላል፡፡
ፍቅር የያዘው ሰው … ፍቅር ሳይዘው በፊት ይከተላቸው የነበሩ የህሊና ህጎችን ለመቀበል ሊያዳግተው ይችላል፡፡ … ጦርነት ውስጥ የገባ ህዝብም ጠላቱን በህሊና ህግ ተጠቅሞ እንዲቀጣ አይጠበቅም። … ከተራው ጊዜ የተለወጡ ክስተቶች ሲመጡ የህሊና ህጎች ይቆማሉ፡፡ እንደ ጦርነትም ሆነ እንደ ፆታዊ ፍቅር የመሰሉ ክስተቶች፡፡ ያኔ በጠላቱ ላይ የሚደረግ ክፉ ተግባር ሁሉ ለጊዜው ልክ ይሆናል፣ ፍቅር የያዘው ሰው ያፈቀራትን በእጁ ለማስገባት ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ህሊናውን እንደሚስተው፡፡
ስለዚህ፤ ህሊና የተፈጥሮ መገለጫ ነው። …. እንደ ተፈጥሮ አስፈላጊነት እየለዋወጠ የሚገለገልባቸው ህጎች አሉት፡፡ ተገልጋዩ እንዳለበት የብስለት ደረጃና እንዳሳለፈው ተሞክሮ … እንደገጠመው ችግር አስገዳጅነት፡፡
የተፈጥሮ ትርጉም በግለሰቡም ላይ ሆነ በማህበረሰቦች መሃልም የተለያየ የምርጫ ፍላጎት ትርጉም ያለው መሆኑ እውነታ ሆኖ ሳለም--- አስር ተመሳሳይ የህሊና ህግ ማውጣት እንደ መተግበሩ ከባድ አይደለም፡፡ የህሊና ህጎቹ በራሳቸው ትክክል ቢሆኑም በተለዋዋጭ የህልውና ፈተና ውስጥ ለሚያልፈው የሰው ልጅ ግን የሚመለኩ እንጂ የማይተገበሩ የሚሆኑበት ጊዜ ያይላል፡፡ … የህሊና ህጎቹን እንደ አመቺነታቸው እየለዋወጠ ይጠቀማል፡፡ ጦርነት ግድ ሲሆን የጦረኛ ህሊና፣ ማፍቀር ግድ ሲሆን የአፍቃሪ ህሊና ይጠቀማል። ግለሰቡ ከሌሎች የማህበረሰቡ አባላት ጋር ከራሱ ምርጫና ፍላጎት አንፃር የተሰጡትን ህጎች መላውን ማህበረሰብ በማይጎዳ መልኩ ትዕዛዙን ይተላለፋል፡፡ ፍቅር ሲይዘውና በቀጥተኛ መንገድ ያፈቀራትን በደንቡ መሰረት ሊያገኝ ሳይችል ሲቀር ያመነዝራል፡፡ ሰው መግደል ፈፅሞ ባይፈልግም ሊገድለው የመጣ ጠላት ሲመጣ ግን ትዕዛዝ ተላልፎ ይገድላል፡፡ --- የገደለበትን ምክንያት ለማሳመን “ራስን ለመከላከል ሲባል” ብሎ ማስረጃ ያቀርባል፡፡
ሙሴ ሶስት ሺ ሰዎች በጎራዴ እንዲሰዉ በፈጣሪ ኃላፊነት የተሰጠውን ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ እንደሚከተለው ይላል፡- “And he said to them, ‘Thus says the Lord GoD of Isreal, “Put every man his sword on his side, and got to and fro from gate to gate throughout the camp, and slay every man his companion, and every man his neighbor” (Exod, 32:27, Revised standard version) የራስን ፍላጎት ለማስቀደም የህሊና ህጎቹን ችላ ማለት … በአንድ ግለሰብና ማህበረሰብ መሀል (በግለሰብ እና በህዝብ መሀል)፣ በአንድ ማህበረሰብ (ሀገር) እና በሌላ መሀል ይከሰታል፡፡ በመከሰቱም ህግ ተላላፊ ይኖራል፡፡ የህሊና ህግን ችላ ብሎ ለራስ የፍላጎት ምርጫ ቅድሚያ መስጠት ስሙ “ሀጢአት” ይባላል፡፡ በእግዚአብሔር ስርዓት ለሚተዳደር ህዝብ፣ ግለሰብ የሚሰራው ሀጢአት ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው፡፡ በፈጣሪ ትዕዛዝ በሚሰሩ ህግ አስፈፃሚዎች የፈጣሪን ቅጣት ይቀበላል፡፡ ሀጢአቱ ታዛዥ አለመሆን ነው። ወይም ያልታዘዘውን አከናውኖ መገኘት። ግለሰብ ምርጫ የማድረግ አቅም ባይኖረው ኖሮ ሀጢአት የመፈፀም ጉድለትም ባልተገኘበት ነበር። ህጎቹንም ፅፎ ማስተማር ባላስፈለገ ነበር። ምርጫ ማድረግ የማይችልን ፍጡር አድርግ/ አታድርግ የሚል ትዕዛዝ መስጠት አያስፈልግም። ተፈጥሮው አድርግ የሚለውን ያደርጋል፡፡ አታድርግ ብትለውም ያደርጋል፡፡ የሰው ልጅ የሀጢአትም ሆነ የህግ ተላላፊነት ችግር መሰረቱ፣ ምርጫ የማድረግ የተፈጥሮ አቅሙ ነው፡፡
… ተፈጥሮ ለፍጡሩ፣ ከህሊና በፊት በህልውና መቆየትን ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ በህልውና ለመቆየት የሚያደርገው ነገር ሁሉ የህሊና ተፈጥሮና መሰረት አለው ማለት እንችላለን፡፡ … ግን የሰው ልጅን በተመለከተ ምርጫ ማድረግ መቻል ራሱ የተፈጥሮ አንዱ አካል ነው፡፡ በብዙ የተግባር ቅጥልጥሎሽና የምርጫ ቅያሶች ውስጥ ነው፣ ህልውናውን ይዞ መቀጠል የሚችለው፡፡ … ህልውናው ማለት ምርጫው ማለት ነው፡፡ ምርጫው እምነቱ ላይ ነው ወይስ ተግባሩ ላይ ቁልጭ ብሎ የሚታየው? ብሎ መጠየቅ ይቻላል። ንዴት ወይም ስሜታዊነት ግን ጥሩ ህሊና የነበረውን በመጥፎ ተግባር ውስጥ የምርጫ አቅሙን አዛብቶ ሊጥለው ይችላል፡፡… ተከናውኖ የተገኘው ተግባር ግን ያደረገው የሞራሉ ምርጫ ቀጥተኛ ውጤት መሆኑን አይክድም፡፡
በዚህም ምክኒያት፤ የሃይማኖት ሞራል የቀረጹ ሰዎች፤ ተከታዮቻቸው ከተቀረፀው የህሊና ደንብ እንዲያፈነግጡ … ለማጠር እንዲችሉ የአማኙን ምርጫ ያጠቡታል፡፡ አስርቱን ትዕዛዛት ከማክበር ውጭ ሌላ ምርጫ ቢወስድ በህይወቱ ዘመን በድንጋይ ተወግሮ ይሞታል፡፡ ከሞቱ በኋላ ደግሞ በገሀነም እሳት ላንቃ ይቃጠላል፡፡

Read 2168 times