Monday, 13 August 2018 00:00

በቲም ለማ እና በህወሓት መካከል ያለው ውጥረት ሊረግብ ይገባዋል!

Written by  መርስ ኤ ኪዳን (ከሜኔሶታ ሃገረ አሜሪካ)
Rate this item
(3 votes)

 ከሃምሌ 21 እስከ ሃምሌ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ክቡር ጠ/ሚኒስትር  ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እና ክቡር ዶ/ር ለማ መገርሣ በሰሜን አሜሪካ ሦስት ግዛቶች ባደረጓቸው ስብሰባዎች ዙሪያ ከብዙ ወገኖች ብዙ እየተባለ ነው። እኔም በሜኔሶታ የተደረጉት ስብሰባዎች አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት ውስጥ  አንዱ በመሆኔ፣ በሂደቱ የታዘብኳቸው አንዳንድ ነገሮች ላይ አስተያየት ለመስጠት ወድጃለሁ፡፡
በቅድሚያ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በአገራችን ጥላቻ፣ ጥርጣሬ፣ መናናቅ ተወግደው ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት እንዲሰፍን ጥረት እያደረጉ ያሉ፤ በኢትዮጵያ ህዝብና በወንድማችን በኤርትራ ህዝብ መካከል ሰፍኖ የቆየውን ግንብ አፍርሰው የፍቅር ድልድይ የገነቡ፣ በታላላቆቹ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና የእስልምና እምነት አባቶች መካከል ያለውን ልዩነት በሰላም ለመፍታት የጣሩ፣ በተለያዩ አገራት በእስር ቤቶች እየተሰቃዩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን እያስፈቱ ወዳገራቸው የመለሱ ታላቅ መሪ በመሆናቸው፤ ክቡር ዶ/ር ለማ መገርሣ ደግሞ የዚህ የለውጥ ሂደት ፈር ቀዳጅ ስለሆኑ፣ ለሁለቱም መሪዎቻችን የተደረገላቸው አቀባበልና ፍቅር ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡  
በሜኔሶታ የአዘጋጅ ኮሚቴው ፈተና
ሜኔሶታ እስከ ሃምሳ ሺህ የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባት የአሜሪካ ግዛት ናት። ከነሱም እጅግ የሚበዙቱ የኦሮሞ ብሄር አባላት በመሆናቸው ትንሿ ኦሮሚያ በመባል ትታወቃለች። የሜኔሶታ ኦሮሞ ማሕበረሰብ በብዛት ብቻ ሳይሆን በአደረጃጀትም ከሌሎች የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች እጅግ የላቀ ነው። የሜኔሶታ የኦሮሞ ማሕበረሰብ ይህ የዶ/ር ዐቢይ ጉዞ ከመታሰቡ በፊት የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርእሰ መስተዳድርን ክቡር ዶ/ር ለማ መገርሣን ጋብዞ፣ ከፍተኛ አቀባበል ለማድረግ ኮሚቴዎች አዋቅሮ ዝግጅት በማድረግ ላይ እያለ ነው፣ የክቡር ዶ/ር ዐቢይ መምጣትን ዜና ከኤምባሲው የሰማው። ኤምባሲው የኦሮሞ ማሕበረሰብን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም በሜኔሶታ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አደረጃጀቶች በመጋበዝ መሪዎቹን ለመቀበል በጋራ እንዲሰሩ ነው የጠየቀው። ሆኖም የኦሮሞ ማሕበረሰብ አስቀድሞ ዶ/ር ለማ መገርሳን ለመቀበል ኮሚቴዎች አዋቅሮ ቆይቶ ስለነበር፣ ሌሎቻችን በነዚያው ኮሚቴዎች ታቅፈን እንድንሰራ በጋራ ወሰንን።
አዘጋጅ ኮሚቴው ሁሉንም ማህበረሰቦች ማቀፉ የሁላችንንም ደስታ የፈጠረ ቢሆንም፣ ለብዙ አመታት በጠላትነት ስንተያይ የነበርን በመሆናችን ብዙ ስራዎች ላይ መተማመን እንዳይኖርና ነገሮችን ሁሉ በጥርጣሬ የማየት አዝማሚያ ፈጥሯል። ስለሆነም በመካከላችን የነበረው የመረጃ ልውውጥና አሰራር ግልፅነት የጎደለው እንዲሆን አድርጓል። በዚህ ሂደት የተሳተፍን አብዛኞቹ የኮሚቴ አባላት የተረዳነው አንድ ቁምነገር ቢኖር፣ ሁላችንንም የሚያቅፍ አንድ ጠንካራ የኢትዮጵያውያን ማሕበር አለመኖር አሰራራችን እጅግ ደካማ እንዲሆን አድርጎታል። በብሄራዊ ማንነታቸው ራሳቸውን ማደራጀት የማይፈልጉ ብዙ ኢትዮጵያውያንንም በተገቢው መልኩ እንዳናሳትፍ አድርጓል። ስለሆነም መላው በሜኔሶታ የምንኖር ኢትዮጵያውያን አንድ ጠንካራ የኢትዮጵያ ማሕበር የመፍጠሩን ነገር በርትተን ልንሰራበት ይገባል። እንደዚህ ቀደሙ አንድን አመለካከት የሚወክል ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚመች ማሕበር ማቋቋም አስፈላጊ ነው። 
በዚህ ሂደት የነበረው መጠራጠር፣ መደባበቅና አለመተማመን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በአንፃሩ ደግሞ እንዲህ ለብዙ አመታት አይን ለአይን መተያየት የማይፈልጉ ሰዎችን ሳይወዱ በግዳቸው ሰላምታ እንዲለዋወጡና አብረው እንዲሰሩ አድርጓቸዋል። በመካከላችን የነበረው መከባበርና መቻቻልም እጅግ የሚያስመሰግን ነው። በእኔ እምነት የእነ ዶ/ር ዐቢይ ጉዞ ዋና መልእክት የሆነው “ግድግዳው ይፍረስ ድልድዩ ይገንባ” የሚለው ዓላማ፣ በዚህ ሂደት ግቡን መምታት ጀምሯል። በመካከላችን ከፍተኛ የጥላቻ ግንብ የነበረን የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የሶማሌ፣ የትግራይና የተለያዩ በኢትዮጵያዊነት  የተደራጁ ማሕበሮች (ለሦስት የተከፈሉትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት ሳይቀር) በአንድ ላይ አሰባስቦ፣ በኢትዮጵያዊነት ድልድይ እንድንሰራ መንገድ የከፈተ ሂደት ነው። ይህ እጅግ በጎ ገፅታው ነው።
የታርጌት ሴንተር ዝግጅት
በሚኒያፖሊስ ታርጌት ሴንተር በመባል በሚታወቀው ስቴዲየም የተደረገውን ዝግጅት ስንመለከት፤ አንዳንድ ብስለት የጎደላቸው ሰዎች የራሳቸውን ባህል፣ ባንዲራና ሙዚቃ ብቻ እንዲጎላና የሌላው ኢትዮጵያዊ ባህል፣ ባንዲራና ሙዚቃ እንዳይጎላ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በዚህም ብዙ ሰዎች ቅር ተሰኝተዋል። ሆኖም ሁለቱ መሪዎች በተለይም ዶ/ር ለማ መገርሣ፤ ይህን የእኔ ብሄር ብቻ ጎልቶ ይታይ የሚል አስተሳሰብ የሚያርም ግሩም ንግግር አድርገዋል። በተለይ በባንዲራ ጉዳይ ያለው ልዩነት በሜኔሶታ እጅግ ጎልቶ ታይቷል። በባንዲራ ጉዳይ የሚንፀባረቁት አመለካከቶች አሳሳቢ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር አንዱን ባንዲራ የሚደግፉ ሰዎች ሌሎቹ ባንዲራዎች ላይ የሚያሳዩት የከረረ ጥላቻ ነው። በዚህ ጉዳይ የማህበረሰብ ልሂቃን ብዙ ስራ ይጠበቅብናል። እኛ ማተኮር ያለብን የባንዲራዎቹ ቀለሞች ላይ ሳይሆን በአገራችን የሚሰፍነው ስርዓት ላይ ነው። ኮከብ ያለው ባንዲራ ሆኖ የብሄር መብት ላይከበር ይችላል፣ የኮከቡ መኖር የብሄር መብት መኖርን አያረጋግጥም። በተመሳሳይ መልኩ ልሙጡ ባንዲራ ሆኖ፣ የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል፣ የባንዲራው ልሙጥ  መሆን አንድነትን አያረጋግጥም። የብሄር መብትም ሆነ የኢትዮጵያ አንድነት የሚከበሩት አንዳችን ሌላውን ለማክበር ስንፈቅድ ነው። በመካከላችን መከባበር ካለ፣ የባንዲራው ጉዳይ ብዙም አሳሳቢ አይሆንም።
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በታርጌት ሴንተር ካደረጉት ንግግር፣ ከህወሓት ጋር መቃቃር ውስጥ መግባታቸውን መገንዘብ  ይቻላል፡፡ በዚህ ንግግራቸው ላይ ቲም ለማ፤ ከኦህዴድ ዶ/ር ለማንና እሳቸው ራሳቸውን፣ ከብአዴን ደመቀ መኮንንንና ገዱ አንዳርጋቸውን፣ ከደኢህዴን  ሙፈሪሃት ካሚልን እንደሚያካትት ጠቅሰው፤ ህወሓትን ዘለውታል። በእርግጥ ህወሓት ውስጥ ከዶ/ር ዐቢይ ጋር ለመስራት የሚፈልጉ የለውጥ ሃይሎች ሳይኖሩ ቀርተው ከሆነ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
የእራት ግብዣ፡ ጥያቄና መልስ
በእራት ግብዣው ላይ ዋነኛው አትኩሮት የጥያቄና መልስ ሂደቱ ነበር። በአዳራሹ የተገኘው ከአንድ ሺህ በላይ ሰው በሙሉ ለዶ/ር ዐቢይ ጥያቄና መልእክት ነበረው። ስለሆነም ጊዜው ማስተናገድ ከሚችለው በላይ የጠያቂ ብዛት ተሰልፎ ነበር። ከተነሱት ጥያቄዎች መሃል ብዙ አትኩሮት የሳበው በእህታችን በልልይቲ እና በእኔ ለተነሱት ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጧቸው ምላሾች ናቸው። እኔ ብዙ ጥያቄዎች ቢኖሩኝም፣ በሜኔሶታ የትግራይ ማሕበረሰብን ወክዬ ስለተገኘሁ ያነሳኋቸው ጥያቄዎችም ያንን ማሕበረሰብ የተመለከቱ ነበሩ። ዶ/ር ዐቢይ ለኛ ጥያቄዎች ከመለሷቸው መልሶችም ሆነ ከንግግራቸው እንዲሁም በኤርፖርት ስንቀበላቸው ከሰጡኝ አስተያየት ልረዳ የቻልኩት፣ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከህወሓት አመራሮች ጋር ከፍተኛ እልህ ውስጥ መግባታቸውን ነው። ይህ ከህወሓት አመራሮች ጋር የገቡበት እልህ ደግሞ ማንኛውንም ከትግራይ የሚመጣ ጥያቄን ሲመልሱ ስሜታዊ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በእህቴ በልልይቲ ለተነሱት ጥያቄዎችም በቀጥታ መልስ ከመስጠት ይልቅ ለህወሓት ሰዎች መልእክት ማስተላለፉን መርጠዋል። ከእኔ የተነሱትን ጥያቄዎችም በቅንነት የተነሱ መሆናቸውን ከገለፁ በኋላ ጥያቄዎቹን በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ ለህወሓት ሰዎች መልእክት ማስተላለፉን ነው የመረጡት። እኔ ያነሳኋቸው የተራው ህዝብ ጥያቄዎችንም ሳይመልሱ አልፈዋቸዋል። እዚያው ደግሞ ጥያቄዬን በሌላ ተርጉመው ስለመለሱልኝ ይቅርታ ጠይቀውኛል። ብዙ የትግራይ ማሕበረሰብ አባላት ዶ/ር ዐቢይ የያዙትን የፍቅርና የአንድነት አላማ ደግፈው በቦታው ተገኝተው የነበሩ ሲሆን፤ ለእኔና ለልልይቲ የመለሱት መልስ ግን እሳቸው ከሚሰብኩት የፍቅር፣ የአንድነትና የመቻቻል አላማ ጋር የማይሄድ ሆኖባቸው ግራ ተጋብተዋል።
በቲም ለማ እና በህወሓት መካከል ውጥረት
ዶ/ር ዐቢይን ያክል ፍቅርንና መቻቻልን የሚሰብክ ሰው፣ እንዲህ እልህ ተጋብቶ ስመለከት የነገሩን ከባድነት ያሳየኛል። ስለሆነም ሁላችንም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፣ ይህ በቲም ለማና በህወሓት መካከል ያለው ውጥረት ተፈትቶ፣ ህወሓትም ቲም ለማን የሚቀላቀልበትን (የሚደመርበትን) መንገድ መፈለግ ይገባናል። የዚህ ጉዳይ አሳሳቢነት ከገባቸው ሰዎች አንዱ ጃዋር መሃመድ ነው። ዶ/ር ዐቢይን ለመቀበል በሚኒያፖሊስ አየር ማረፊያ፣ ከእንግዳ ማረፊያው እስከ አውሮፕላኗ ድረስ ከጃዋር ጋር በአንድ መኪና ነው የሄድነው። ባለችን ትንሽ ደቂቃም ስንጨዋወት፣ በቲም ለማና በህወሓት አመራሮች መካከል የሰፈነው መካረር እንዳሳሰበውና ሁላችንም ይህን ለመፍታት መጣር እንዳለብን፣ እሱም ይህን ችግር ለመፍታት ከሁለቱም አመራሮች ጋር እንደሚነጋገር ገልጾልኛል። በዚህ አጋጣሚ በሃይማኖት አባቶች መካከል ያለውን ችግር በመፍታት ላይ ያሉ ያገር ሽማግሌዎች፣ በቲም ለማና በህወሓት መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት መሸምገል ያለባቸው ይመስለኛል፡፡
በህወሓት አመራር በኩል የለውጥ ሃይል የሆኑት  አሸንፈው በመውጣት የለውጡ ባቡር ላይ መሳፈር ብቻ ሳይሆን ከእነ ዶ/ር ዐቢይ ጋር በጋራ መምራት ይገባቸዋል። በትንንሽ ጉዳዮች ላይ የሚኖርን ልዩነት በማክረር እልህ ከመጋባት ይልቅ ትልቁን የአገርና የህዝብ ጉዳይ በመመልከት፣ግማሽ መንገድ ሄደው፣ በጋራ ለመስራት መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። በመጪው ድርጅታዊ ጉባኤም፤ የለውጡ ሃይል አሸናፊ ሆኖ፣ በአዲስ ሃይል ሊወጣ ይገባዋል። የለውጡ ሃይል ማሸነፍ ያለበት ከእነ ዶ/ር ዐቢይ ጋር አብሮ ለመስራት ብቻ ሳይሆን በዋናነት የትግራይ ህዝብ ልክ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ለውጥ እንዲመጣ ስለሚፈልግ ነው።
በቲም ለማ በኩልም ከሌሎች ሃይሎች ጋር ለመታረቅና ይቅር ለመባባል የሚደረገው ጥረት ከህወሓት ጋርም ሊደረግ ይገባል። በአላስፈላጊ ነገር እልህ መጋባት የተጀመረውን የሰላምና የእርቅ ጥረት ሊያበላሽ፣ አገሪቱንም የከፋ አደጋ ውስጥ ሊከታት ይችላል። ስለሆነም በሰጥቶ መቀበልና በመቻቻል መርህ፣ ህወሓት ውስጥ ያሉ የለውጥ ሃይሎችን መሳብ ያስፈልጋል። ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ከዚህ በኋላ የአገር መሪ መሆናቸውን ተረድተው፣ የሚናገሯቸውን ቃላት መምረጥ ይኖርባቸዋል።
የትግራይ አክቲቪስቶችና የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ሰሞኑን በትግራይ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን የአካል የመንፈስና የህይወት ጉዳት በመመልከት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህን ችግር በተመለከተ ምንም ባለማለታቸው ወደ ጥርጣሬ እየገባችሁ እንደሆነ ይታያል። ነገር ግን ጉዳዩን በስክነት ማየት ያስፈልጋል። በአገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ካሉ ችግሮች አንፃር፣ የትግራይን በተለየ ትልቅ የሚያስብለው ሁኔታ የለም። ከሚሊዮን የማያንሱ ኦሮሞዎችና ኢትዮጵያውያን ሶማሌዎች የተፈናቀሉበት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ የሞቱበት ሁኔታ ተከስቷል። በቤኒሻንጉልና አንዳንድ የኦሮምያ ከተሞችም በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ህይወታቸው አልፏል። በደቡብም በመቶዎች የሚቆጠሩ ወላይታዎች፣ ስልጤዎች፣ ጌዴኦዎች፣ ጉጂዎች እየሞቱና እየተፈናቀሉ ያሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄ ሁሉ ጉዳይ ይመለከታቸዋል። ሁሉንም ነገር በአጭር ጊዜም ለመፍታት የሚያስችል ሁኔታም የለም። ስለሆነም ጊዜ መስጠት ብቻ ሳይሆን እኛም የሰላም ጥረቱ አካል በመሆን ልናግዛቸው ይገባል። አንዱ ጥረት መሆን ያለበት በህወሓት ውስጥ የለውጥ ሃይሉ አሸንፎ እንዲወጣ እገዛ ማድረግ ነው። ቀጥሎም በህወሓት እና በቲም ለማ መካከል ያለውን ውጥረት እንዲረግብ የበኩላችንን ግፊት ማድረግ ነው።
ሌሎች አክቲቪስቶችና የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም በጊዜያዊ ስሜት እየተነሳሳን የምናስተላልፋቸው አሉታዊ መልእክቶች ሄደው ሄደው ሁላችንንም የሚጎዱ መሆናቸውን ተረድተን፣ ሰከን ባለ ሁኔታ መጓዝ ይኖርብናል። መነቋቆሩን ትተን ወንድሜን ላክብረው፣ እህቴን ላክብራት መባባል ይገባናል። መሰልጠን ማለት የልዩነት መጥፋት አይደለም፤ ልዩነትን በመከባበርና በመተሳሰብ መፍታት ወይም ማስኬድ ነው።
ሰላም ለሁላችን!
አምላክ አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክ!
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- (ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡)

Read 3904 times