Monday, 20 August 2018 00:00

6ኛው ዙር “የበጎ ሰው” ሽልማት ነሐሴ 27 ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ቴዲ አፍሮ በጥበብ፣ አቶ ወልደሔር ይዘንጋው በንግድና ሥራ ፈጠራ፣ ጥበቡ በለጠ በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ ታጭተዋል


    6ኛው ዙር “የዓመቱ በጎ ሰው” ሽልማት ነሐሴ 27 ቀን 2010 ዓ.ም ከቀኑ 7፡00 ጀምሮ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ይካሄዳል፡፡ ለዘንድሮው ሽልማት ታዋቂው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን በጥበብ (ዜማ)፣ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ በንግድና ሥራ ፈጠራ፣ አንጋፋው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ ታጭተዋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ የሽልማቱ የቦርድ ሰብሳቢዎች በካፒታል ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በመምህርነት ዘርፍ በአዊ ዞን ትልልቅ ስራዎችን የሰሩት የአዊ ዞን መምህር ስዩም ቦጋለ፣ በደቡብ ጎንደር ዞን ታች ጋይንት ወረዳ በመምህርነታቸው ውጤታማ የሆኑትን መምህር ስመኘው መብራቱና በድሬደዋና በሃረር ታላላቅ ሥራዎች ያከናወኑት መምህር ስለሺ ካሳዬ ለሽልማቱ መታጨታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡  
ለኢትዮጵያ በጎ የሰሩ የውጭ ሀገር ዜጎች በሚለው ዘርፍ ደግሞ በጣሊያን ወረራ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ የተፈፀሙ ግፎችን በማጥናትና በማሳተም የሚታወቁትን ኢያን ካምፕቤል፣ የ”ብላክ ላየን” መፅሐፍ ደራሲ ሬዶልፍ ኬ. ሞልቬር እና ስለ ኢትዮጵያና መካከለኛው ምስራቅ ግንኙነት ብዙ መፅሐፍትን የፃፉት ሐጋይ ኡልሪክ የታጩ ሲሆን መንግሥታዊ የስራ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት ዘርፍ፡- ዶ/ር አበራ ደሬሳ፣ ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም እና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ስራ አስኪያጅ የነበሩት ወ/ሮ ሙሉወርቅ ገ/ህይወት እጩ ሆነዋል፡፡
በበጎ አድራጎት ዘርፍ መስማት የተሳናቸውን ከ30 ዓመታት በላይ በመርዳት የሚታወቁት አቶ መኮንን ሙላት፣ የጠብታ ውሃ (Dropwater) መስራች ሄርሜላ ወንድሙ “ህይወት የተቀናጀ ልማት” ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲተር (ሎሬት) ጥበበ ማኮ በእጩነት ቀርበዋል። በባህልና ቅርስ ዘርፍ ከ75 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረውና ከ48 ሺህ በላይ አባላት ያሉት የአዊ ፈረስ ማህበር፣ ላስታ ውስጥ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን የሰሩት አባ ገ/መስቀል ተሰማ እና የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ በመሰብሰብና በማጥናት የሚታወቀው የፈንዲቃ የባህል ማዕከል መስራች መላኩ በላይ እጩ ሆነዋል፡፡
በሳይንስ ዘርፍ ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ፣ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ እና በአገራችን የመጀመሪያውን የኩላሊት ንቅለ ተከላ ያካሄዱት ዶ/ር ሞሚና አህመድ በእጩነት ቀርበዋል፡፡
በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ፣ የተቻለ ጋራዥ ባለቤት አቶ ተቻለ ኃይሌ እና የጊዮን ኢንዱስትሪያል መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወልደሄር ይዘንጋው እጩ ሲሆኑ በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ ደግሞ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፣ ፀጋዬ ታደሰ (ፀጋዬ ሮይተርስ) እና ነቢዩ ሲራክ ታጭተዋል፡፡ በኪነ ጥበብ (ዜማ) ዘርፍ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ አበበ ብርሃኔ እና አየለ ማሞ (አየለ ማንዶሊን) እጩ ሆነዋል፡፡
የዘንድሮው  ሽልማት ከአዲስ አበባ ውጭ የተጠቆሙ እጩዎች የሚበዙበት በመሆኑ ከቀድሞዎቹ ለየት የሚል እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

Read 4506 times Last modified on Saturday, 18 August 2018 10:16