Saturday, 18 August 2018 09:34

የ21ኛው ዓለም ዋንጫ ልዩ ማስታወሻ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ሴንት ፒተርስበርግና ሶቺ


     ፊልም  የሆነችብኝ ሴንትፒተርስበርግ
በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ከጎበኘኋቸው የራሽያ ግዛቶች አንዷ የሴንት ፒተስበርግ ከተማ ናት፡፡  ከ315 ዓመታት በፊት  ከተማዋን የቆረቆራት   ዛር ወይም ንጉስ የነበረው ታላቁ ፒተር ሲሆን ራሽያ ለምዕራቡ ዓለም በሮቿን መክፈቷን በማብሰር ነበር፡፡ ከሞስኮ  ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ለመድረስ 687 ኪሎሜትሮችን በአገር አቋራጭ የባቡር ትራንስፖርት በመሳፈር ለ12 ሰዓታት  ጉዞ ማድረግ ያስፈልግ ነበር፡፡  ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ያደረግነው ጉዞ በሌሊት ስለነበር በአገር አቋራጩ ባቡር የማረፊያ ክፍል መተኛት ነበረብን፡፡ በዘመናዊው የሴንት ፒተርስበርግ ስታድዬም የአርጀንቲና እና የናይጄርያን ጨዋታ ሜዳ ውስጥ ገብቶ ፎቶዎችን በማንሳት ለመዘገብ  በፊፋ ሙሉ ፈቃድ አግኝቻለሁ። ከአርጀንቲና ናይጄርያ ጨዋታ በፊት እና በኋላ የሴንት ፒተርስበርግን ከተማ በደንብ ጎብኝቻታለሁ። ከ5 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች የሚገኙባት ሴንት ፒተስበርግ በህዝብ ብዛትና የቆዳ ስፋቷ ከሞስኮ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ግዙፍ የራሽያ ከተማ ናት፡፡  በራሽያ ታሪካዊ መዲናነት የምትጠቀሰው ከተማዋ በዘመናዊነቷ እና ሁለገብ የባህል መናሐርያነቷም ትታወቃለች፡፡ ከ1713 እስከ 1918 እኤአ ለ206 ዓመታት የራሽያ ንጉሳዊ ስርወመንግስት  ዋና መዲና ሆና አገልግላለች፡፡ ነዋሪዎቿ የራሽያ ሆሊውድ ብለው ከተማዋን በማጋነን ሲጠሯት  ፒተርና ፒተርበርግ እያሉ በአጭሩ የሚጠቅሷትም አሉ፡፡ በ1914 ላይ ፔትሮጋርድ ከዚያም በ1924 እኤአ ላይ ደግሞ ሌኒንግራድ በሚሉ ስሞች ተጠርታ ነበር።  ሴንት ፒተርስበርግ በወንዞች እና የመተላለፊያ ሰርጦች፤ በድልድዮች እና በውሃ በተከበቡ ደሴቶች የተሞላች በመሆኗም ከፈረንሳይዋ የቬኒስ ግዛት ጋር በማመሳሰል የሰሜኗ ቬኒስ Venice of the North ነው የምትባለው፡፡
የከተማዋ አጠቃላይ ገፅታና ውበት በፊልም ትእይንት ላይ የሚታይ ይመስላል፡፡ በአውሮፓ የሬነሳንስና ባይዛንታይን ዘመን የስነህንፃ አሰራሮች የተዋቡት ህንፃዎች፤ ታሪካዊ ስፍራዎች፤ ሃውልቶች፤ አደባባዮች… የከተማዋን የተስተካከለ ገፅታ ፈጥረዋል። አጠቃላይ ውበቷ ከአውሮፓ  ምርጥ ከተሞች  የሚያስጠቅሳት ሲሆን በ2017 ከአውሮፓ ምርጥ የቱሪስት መዳረሻዎች ግንባር ቀደም መሆኗ እና በዎርልድ ትራቭል አዋርድ ሶስት ተከታታይ ሽልማት ማግኘቷ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል፡፡ በየዓመቱ በሚጎበኟት ከ7 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች  ከራሽያ ከተሞች ከፍተኛው ሲሆን በ21ኛ የዓለም ዋንጫ ላይ ከ750ሺ በላይ ቱሪስቶች በአንድ ወር ውስጥ በማስተናገድ ስኬታማ ነበረች፡፡  
በነገራችን ላይ የሴንት ፒተርስበርግ ውበት  በታሪካዊ ስነህንፃዎች፤ ግዙፍ የመታሰቢያ ሃውልቶች እና የስነጥበብ ሙዚዮሞች … ወዘተተረፈ የተወሰነ አይደለም፡፡ በተፈጥሮ ሃብትና ልምላሜዋ በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የሚስተካከላት የለም፡፡ በከተማዋ 64 ወንዞች እና 50 የውሃ መተላለፊያ ሰርጦች ይገኛሉ። ከ200 በላይ መናፈሻዎችና የተፈጥሮ ፓርኮችም የሚገኙባት ሲሆን፤ በአረንጓዴ ልምላሜ የተከበቡ ከ700 በላይ አደባባዮች  ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ሴንት ፒተርስበርግን ልዩ የሚያደርጓት ዘመናዊ እና ጥንታዊ ድልድዮቿ ሲሆኑ በከተማዋ የሚፈሱትን ከ64 በላይ ወንዞች የሚያገናኙት ከ800 በላይ ድልድዮች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ድልድዮች መካከል በልዩ አሰራር ተነስተው የሚከፈቱ እና የሚዘጉም ይገኙበታል፡፡ በሴንት ፒተርስበርግ ቆይታዬ በተለይ ሁለቱን ታዋቂ ድልድዮች ለመጎብኘት እቅድ ነበረኝ፡፡ የመጀመርያው  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተማዋን የቱሪስት መናሐርያ ካደረጉት አንዱ ነው፡፡  በኔቫ ወንዝ ላይ የተገነባው ይህ ድልድይ በየጊዜው ተጣጥፎ የሚነሳና መልሶ የሚዘረጋ  ነው፡፡ ይህ ዘመናዊ እድል ተከፍቶ በሚነሳበት እና   በስሩ መርከቦችና ጀልባዎች በሚያሳልፍበት አጋጣሚ ለመልከት ባልችልም በስፍራው ተገኝቼ አስደናቂ አሰራሩን ተመልክቸዋለሁ፡፡ ኔቫ በሚባለው የከተማዋ ዋና ወንዝ ላይ  በየጊዜው ተጣጥፈው የሚነሱና መልሰው የሚዘረጉ ከ13 በላይ ድልድዮች መኖራቸውን ለማወቅ የቻልኩ ሲሆን በተለይ ከሚያዝያ እስከ ጥቅምት ባሉት ወራት በውሃ ላይ መጓጓዣዎች መተላለፊያነት ስራ እንደሚበዛባቸው ተነግሮኛል፡፡   በሴንት ፒተርስበርግ ቆይታዬ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ተመላልሼ የጎበኘሁት በከተማዋ እምብርት ላይ የሚገኘው የድሮ ድልድይ ነው፡፡  በፎንታንካ ወንዝ ላይ የተገነባው ይህ ድልድይ አንቺኮቭ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ከተማዋን የሚጎበኙ ቱሪስቶች የሚያዘወትሩት ነው፡፡ የሰዎች ትርምስ እና የትራፊክ ግርግር የበዛበት አንቺኮቭ ድልድይ በላዩ መኪናዎችን ሲያሳልፍ በስሩ ደግሞ የመዝናኛ መርከቦች እና ጀልባዎች የሚተላለፉበት ነው፡፡ በድልድዩ አራት ማዕዘኖች ላይ የተተከሉት አራት የፈረሰኛ እና ፈረሶች ሃውልቶች በተለያዩ ሁኔታዎቻቸው አላፊ አግዳሚውን የሚማርኩ ናቸው፡፡ በኔቭስካይ ጎዳና ቤሎሴልስኪ ቤሎዜራስኪ ቤተመንግስት አቅራቢያ በሚገኘው ድልድዩ ላይ እነዚህን ሃውልቶች የሰራው ፒተር ኮልዶት ቮን ጀርገንስበርግ የተባለ ጥበበኛ አርቲስት ነው፡፡ ፈረሰኛ እና ፈረሱ የሚያደርጉትን ልዩ ትንቅንቅ የሚያንፀባርቁት ሃውልቶቹ በከፍተኛ የጥበብ ደረጃ የተቀረፁ ናቸው፡፡ ሌላው የከተማዋ ውበት በተለያዩ ስፍራዎች ለንጉሳውያን ቤተሰቦች፤ ለሶሽያሊስት አብዮተኞች፤ ለፈላስፎች፤ ለደራሲዎች፤ ለስነዕንፃ ባለሙያዎች፤ ለሳይንቲስቶች እና በአጠቃላይ ለታላላቅ የራሽያ ጀግኖች የቆሙ ከ50 በላይ ግዙፍ ሃውልቶች ናቸው፡፡ በምርጥ ጥቁር የግራናት ድንጋይ፤ በእምነበረድ፤ በነሓስ እና በብረት የተሰሩት ሃውልቶች የከተማዋን አደባባዮች፤ ቤተመንግስቶች፤ ፓርኮችና መናፈሻዎች በልዩ ውበት እና ንፅህና ቆመዋል፡፡ በቅርበት ከጎበኘኋቸው አንዱ በኦስትሮቭስኪ አደባባይ ላይ አሌክሳንደርስኪ ከተባለ ቲያትር ቤት ፊት ለፊት የቆመው ለታላቋ ካተሪን መታሰቢያ የቆመው ሃውልት ነው፡፡ በወርቃማ ዘመን ራሽያን በንግስትነት ለበርካታ ዓመታት የገዛችውን ንግስት ካተሪን ለማድነቅ የተሰራው የመታሰቢያ ሃውልት በ1873 እኤአ የቆመ ነበር፡፡ ቀራፂው ደግሞ ሩስያዊው ኤም ኦ ሚኬሽን ነው፡፡
ሴንት ፒተርስበርግን ከሌሎች ግዙፍ የዓለማችን ከተሞች ልዩ የሚያደርጋት እና የሚያስገርመው ሁኔታ አንዳንዴ ፍፁም ጭለማ የማይደርስባት ግዛት መሆኗ ነው፡፡ በየዓመቱ ከተማዋ ውስጥ 24 ሰዓት ብርሃን ወይንም ነጭ ምሽት ሆኖ የሚያልፍባቸው 21 ቀናቶች አሉ፡፡ በከተማዋ ጉብኝት ያደረግኩበት ወቅት ላይ ይህ ሙሉ ብርሃን የሚሆንበት የሴንት ፒተርስበርግ ሁኔታ እንደሚያጋጥመኝ ተስፋ አድርጌ የነበረ ቢሆንም አልተሳካልኝም፡፡ የከተማው ነዋሪዎች እንደገለፁልኝ በሴንት ፒተርስበርግ ጨለማ የማይኖርባቸው ቀናት ብዙውን ጊዜ በሰኔ ወር ላይ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ለነገሩ በከተማዋ ያሳለፍኳቸው ሁለት ምሽቶች  እስከ ሌሊቱ ስምንት ሰዓት አለመጨለሙን መጥቀስ ሳይሻል አይቀርም፡፡ በመጨረሻም በከተማዋ ከጎበኘኋቸው የድሮ ስነህንፃዎች አንዱን መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ የዓለማችን ግዙፉ የስነጥበብ ሙዚዬም ሄርሚቴጅ ነው፡፡ በየዓመቱ እስከ 3 ሚሊዮን ጎብኝ ያለው ነው፡፡ በዚህ ሙዚዬም በ6 የተለያዩ ህንፃዎች የተሰባሰቡ የዓለማችን ታላላቅ ሰዓሊዎች ውብና ውድ ስራዎች ሙሉ በሙሉ የምጎበኝበት ግዜ አልነበረኝም፡፡ የሙዚዬሙን አካባቢ ግን ዙርያ ገባውን ፎቶ እያነሳሁ ተመልክቸዋለሁ፡፡
ሴንት ፒተርስበርግ በአሁኑ ዘመን የራሽያ የንግድ እንቅስቃሴ መናሐርያ እና መተላለፊያ፤ የፋይናንስ እና የኢንዱስትሪ ማዕከል፤ የመርከብ ግንባታ የጠፈር ኢንዱስትሪ እና የቴክኖሎጂ ፋብሪካዎች መናሐርያ እየሆነች ነው፡፡ ከተማዋ በመድሃኒት እና በምግብ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ የምርት አቅም ያላቸው ትልልቅ ኩባንያዎችም ይገኙባታል፡፡  የሴንት ፒተርስበርግ ማዕከላዊ ክፍል ከ8000 በላይ ልዩ የከተማ ስፍራዎች ወይንም ላንድማርኮች ይገኙበታል፡፡ በተለይ የከተማዋ ሞገስ ሆነው የሚታዩት ከ36 በላይ ታሪካዊና ዘመናዊ ስነህንፃዎች ሲሆኑ ከ4000 በላይ ልዩ ልዩ  የመታሰቢያ ሃውልቶች እና ቤተመንግስቶች፤ ሙዚዬሞች እና ታሪካዊ ስፍራዎች በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆነው የተመዘገቡ ናቸው፡፡  ከ221 በላይ ሙዚዬሞች፤ 2000 ቤተመፅሃፍት፤ 80 ቲያትር ቤቶች፤ ከ100 በላይ የኮንሰርት ድርጅቶች፤ 45 የስነጥበብ ጋለሪዎች እና ከ60 በላይ የባህል ማዕከሎች በሴንት ፒተርስበርግ ይገኛሉ። በዓመት ከ100 በላይ ብሄራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፌስቲቫሎችም ይካሄዱባታል፡፡ የከተማው ምጥን ያሉ እና ተመሳሳይ የፎቅ ብዛትና ቁመት ያላቸው ህንፃዎች፤ ጉልላታቸው በወርቅ እና በወርቅ ቅብ የተንቆጠቆጡት ቤተክርስትያናት፤ በተለያዩ ቅርፃቅርፆች እና ሐውልቶች የተጌጡ ግዙፍ አፓርትመንቶች፤ በየአደባባዩ ያሉ ስነ ህንፃዎች እና ሃውልቶች በከፍተኛ እንክብካቤ የተያዙ መሆናቸው በከተማው እያንዳንዱ ስፍራ ፊልም መቅረፅ የሚቻል አድርጎታል፡፡  በተጨማሪ ከተማዋን ልዩ ውበት የሚያጎናፅፏት በአረንጓዴ ልምላሜ መከበቧ ሲሆን ከ200 በላይ ፓርኮች እና መናፈሻዎች ይገኙባታል፡፡ በከተማዋ ጎዳናዎች እየተዘዋወርኩ የታዘብኩት ትራም የሚባሉ የህዝብ መጓጓዣዎች መብዛታቸውን ሲሆን ጠይቄ እንደተረዳሁት የሴንት ፒተርስበርግ የትራም ትራንስፖርት በራሽያ ረጅሙ እንደሆነና እስከ 600 ኪሎሜትሮች በመሸፈን በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብም የሰፈረ ነው፡፡  በቱሪስቶች የተጨናነቁት የከተማዋ አውራጎዳናዎች ጉብኝት እያደረግኩ ሳለ አንዲት አስገራሚ መተላለፊያ ተመልክቼ ነበር፡፡ በ34 ርምጃ የምታልቅ ናት፡፡ ይህች አቋራጭ መንገድ ፔስኮቭስኪ ሌን ተብላ ስትታወቅ  በሩስያ አጭሯ መንገድ እንደሆነች  ነግረውኛል፡፡ በነገራችን ላይ በራሽያ ረጅሙ ጎዳናም በ11 ኪሎሜትር ርዝማኔው የሚገኘውም በዚያው ከተማ መሆኑ ነው፡፡ ኦቡኮሆቭስኮይ ኦፕሮኒ ጎዳና ይባላል፡፡
በራሽያ የሲኒማ ኢንዱስትሪ እና ፊልም ሰሪዎች ተመራጭ የሆነችው ከተማዋ፤ የዓለማችን ታላላቅ ፊልም ሰሪዎች ለተለያዩ የፊልም ስራዎች እና ቀረፃዎች በየጊዜው የሚከትሙባትና የሚመላለሱባትም ናት፡፡ ስለ ከተማዋ ውበት ታላላቆቹ የዓለማችን ደራሲዎች እነ አሌክሳንደር ፑሽኪን፤ ኒኮላይ ጎጎል እና ዶስቶቭስኪ ብዙ መፃፋቸውም ከዓለም ህዝብ ጋር በስፋት አስተዋውቋታል፡፡  ስለዚህም ሴንት ፒተርስበርግ በራሽያ የፊልም ኢንዱስትሪ እና በሆሊውድ ከሚፈለጉ የዓለማችን ከተሞች ተርታ ትጠቀሳለች፡፡ ከ250 በላይ እውቅ ፊልም ሰሪዎችና ሌሎች ኩባንያዎች በከተማዋ ይንቀሳቀሳሉ፡፡  የፊልም ባለሙያው ማክሲም ሻላኔቭ እንደነገረኝ ትውልዱ በሞስኮ ቢሆንም ከሙያው ጋር በተያያዘ ዋንኛ መኖርያውን ሴንት ፒተርስበርግ ላይ አድርጎታል፡፡ ማክሲም ሻላኔቭ በ2013 እኤአ ላይ ሞስኮ 14ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ስታስተናግድ የተዋወቅኩት ራሽያዊ ወዳጄ ነው። ከ5 ዓመታት በፊት ለራሽያ ብሄራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ዋና ቪድዮ ቀራፂ የነበረው ማክሲም፤ አሁን በፍሪላንሰርነት የሚሰራ ሆኗል፡፡ በታዳጊነቱ ከአባቱ ጋር በሻሸመኔ ኢትዮጵያ የኖረው ማክሲም ሻላኔቭ ስለ ኢትዮጵያ የነበረውን ናፍቆት በሞስኮ ቆይታዬ በደንብ ገልፆልኛል፡፡ ዘንድሮ ከታዋቂ ፊልም ሰሪ ጋር በሴንት ፒተርስበርግ በፊልም ፕሮጀክት ላይ እየሰራ መሆኑን የገለፀልኝ ማክሲም ፤ ትልልቆቹ የራሽያ ፊልም ሰሪ ኩባንያዎች በሴንትፒተርስበርግ ፅህፈት ቤት እንዳላቸው የእንግሊዝ፤ የአሜሪካ እና የፈረንሳይ ፊልም ሰሪዎችም በከተማዋ እየኖሩ እና እየተመላለሱ እንደሚሰሩ አጫውቶኛል፡፡
ለድጋሚ ጉብኝት የተጋበዝኩባት ሶቺ  
ከሁለት  ሳምንት በፊት ‹‹እኔ ከኢትዮጵያ ነኝ›› በሚል ርእስ ባቀረብኩት የ21ኛው የዓለም ዋንጫ ልዩ ማስታወሻ ላይ አስገራሚ የክብር አቀባበል ያገኘሁባትን የራሽያ ግዛት ሶቺ በተመለከተ የተወሰኑ ወጎችን አንስቼ ነበር፡፡   ጥቁር ባህር የሚያዋስናት  ከተመሰረተች 180 ዓመታትን በማስቆጠሯ ከራሽያ ከተሞች ገና ወጣቷ ናት ማለት ይቻላል፡፡  ከሞስኮ 1697 ኪሜትር ርቃ ወደ የምትገኘው ሶቺ ለመድረስ በአገር አቋራጭ ባቡር ደርሶ መልስ ከ78 ሰዓታት በላይ የሚወስድ ነው፡፡ በሰሜን ምስራቅ ኤሽያ ክልል ላይ የሰፈረችው ሶቺ የአየር ንብረቷ በከፊል ትሮፒካል ሲሆን ከዓመት ውስጥ 300 ቀናት ፀሃያማ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ጥቁር ባህርና ግዙፍ ተራሮች የሚያወስነው በ145 ኪሎሜትሮች መዋሰኗ በዚያ የዓለም ክፍል ከሚገኙ ግዛቶች ረጅሙ ድንበር ያላት አድርጓታል፡፡  በሶቺ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎቿ በጥቁር ባህር ዳርቻ ላይ ቤቶቻቸውን ገንብተው የሚኖሩ ናቸው፡፡ የባህር ዳርቻ እጅግ በጣም ከመንጣለሉ የተነሳም እያንዳንዱ ነዋሪ ሪዞርት ያለው ይመስላል፡፡ በርካታ ራሽያውያን እንዲሁም የአውሮፓ እና የኤስያ አገራት ህዝቦች የሶቺን የባህር ዳርቻዎችን ለመዝናኛ ያዘወትራሉ፡፡ በዓመት እስከ 2 ሚሊዮን ቱሪስት  እየጎበኟትም ነው፡፡  ከጥቁር ባህር ውብ የመዝናኛ ዳርቻዎቿ ባሻገር  የሶቺ ከተማ በግዝፈታቸው የሚታወቁ የራሽያ ተራሮችም ከብበዋታል፡፡ የአውሮፓ ከፍተኛው ተራራም በዚያው የሚገኝ ነው፡፡ በሶቺ ከሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶች 2.9 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው  ብዝሃ ህይወት የሚጠቀስ ሲሆን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡
ሶቺን በ2014 እኤአ ላይ የክረምት ኦሎምፒክ ማስተናገዷ ከዓለም ጋር አስተዋውቋታል፡፡ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ደግሞ ከአስተናጋጅ ከተሞች ለቱሪስቶች በነበራት ልዩ ምቾት የምትጠቀስ ሆናለች። በሶቺ በሚገኘው የፊችት ስታድዬም በዓለም ዋንጫው ከተመለከትኳቸው ዘመናዊ ስታድዬሞች የሚስተካከለው አልነበረም፡፡የክረምት ኦሎምፒኩ ከ51 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ ስለሆነበት በታሪክ ውዱ የስፖርት መስተንግዶ ነበር፡፡  88 አገራትን ለማስተናገድ በ7 ዓመታት የተሰሩት የኦሎምፒክ ፓርክ እና ሌሎች የስፖርት መሰረተልማቶች እና የመወዳደርያ ስታድዬሞች ከፍተኛ ወጭ የወጣባቸውና ጥራት ያላቸው ናቸው፡፡ በስታድዬሙ ዙርያ ከሚገኙት የስፖርት መሰረተ ልማቶች መጠቀስ ያለበት ከ2014 ጀምሮ እስከ 2020 እኤአ የሩስያን ኤፍ 1 ግራንድ ፕሪ የሞትር ስፖርት የሚያስተናግድ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ የራሽያ ዲዝኒ ላንድ ተብሎ የሚጠራው ሶቺ ፓርክ በስታድዬሙ አቅራቢያ የሚገኝና በቀን ከ2000 በላይ ሰዎች የሚዝናኑበት ነው፡፡
በነገራችን ላይ በሶቺ ከተማ ‹‹እኔ ከኢትዮጵያ ነኝ›› የሚል ቲሸርት ለብሼ ከገባሁ በኋላ በፊችት ስታዬም የፕሬስ ማዕከል የራሽያን ባንዲራ ከጥቁር ባህር በወጣ ድንጋይ ላይ እንደሳልኩና ስለ ተደረገልኝ ልዩ አቀባበልም በቀደመው ማስታወሻ አንስቼ ነበር። ያልጠቀስኩት ጉዳይ ቢኖር የከተማው አስተዳደር እና በፊቸት ስታድዬም ዙርያ የሚገኘው የኦሎምፒክ ማዕከል ሃላፊዎች ወደፊት ከተማዋን እንድጎበኝ እንደጋበዙኝ ነው፡፡ ከሶቺ ሚዲያዎች በጋዜጣ፤ በቲቪ እና በራድዮ ካደረግኩት ቃለምምልስ በኋላ ነው። በማዕከሉ የነበሩ የሶቺ ነዋሪዎች ጋበዙኝ፡፡ ከተማዋ የምትታወቅበትን ሻይና ብስኩቶች ነበር ነበር፡፡ አስተናጋጆቼ እንደገለፁልኝ ሶቺ ራሽያን በሻይ ቅጠል ምርቷ የምታንበሸብሽ  ናት፡፡ …ይቀጥላል

Read 4139 times