Saturday, 18 August 2018 09:36

መንግሥት የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት እንዲያስከብር ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

· በሃገሪቱ በተፈጠሩ ግጭቶች በአንድ ሳምንት 65 ሰዎች ተገድለዋል
              · ከመስከረም ወዲህ ብቻ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል


    በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ 65 ሰዎች መገደላቸው የተረጋገጠ ሲሆን መንግስት የዜጎችን በህይወት የመኖር ሰብአዊ መብት እንዲያስከብር ተጠይቋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ 2.8 ሚሊዮን ህዝብ የተፈናቀለ ሲሆን ከዚህ ቁጥር ውስጥ 1.4 ሚሊዮን ያህሉ ከመስከረም ወዲህ በአንድ ዓመት ብቻ የተፈናቀለ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት አስታውቋል፡፡  
ከሳምንት በፊት በሶማሊያ ክልል ጂግጂጋና ሌሎች ከተሞች በተፈጠረ ግጭት በርካቶች ለአሰቃቂ ሞትና የአካል ጉዳት መዳረጋቸው ይታወቃል፡፡ ከዚያም በኋላ ግን ግጭቱና ህልፈቱ አልቆመም - ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተስፋፋ እንጂ፡፡ እሁድ ነሐሴ 6 ቀን 2010 ዓ.ም በሻሸመኔ ከተማ፣ በቅርቡ ወደ ሃገር ቤት የተመለሱትን የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ስራ አስኪያጅና አክቲቪስት ጀዋር መሃመድን ለመቀበል አደባባይ በወጡ ዜጎች መካከል በተፈጠረ ግጭትና ግርግር፣ 3 ሰዎች ተረጋግጠው መሞታቸው የታወቀ ሲሆን አንድ ሰው ደግሞ “ቦንብ ይዘሃል” በሚል በወጣቶች ተደብድቦ፣ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉ ተዘግቧል፡፡
ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ አራት ተጠርጣሪዎች መታሰራቸውን የገለፁት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኮሙኒኬሽን ቦሮ ኃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው፤ ግድያው የተፈፀመበት ወጣት የዚያው አካባቢ ተወላጅ መሆኑን በመግለፅ፣ እኩይ ድርጊቱን የብሔር ጥቃት በማስመሰል ግጭት ለማነሳሳት የሚሞክሩ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡
በነጋታው ሰኞ ነሐሴ 7 የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በምስራቅ ሀረር ዞን ሙሉ ሙሉቄ ነዋሪዎች ላይ በፈፀመው ጥቃት፣ 41 ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት ተደብድበው መገደላቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን የዞኑ አስተዳዳሪዎች ለመገናኛ ብዙኃን አስታውቀዋል፡፡
ከ6 ሰዓታት በላይ በዘለቀው ጥቃት፤ ከህፃናት እስከ አዛውንት የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን የገለፁት የዞኑ አመራሮች፤ በአካባቢው ሰላም ለማስከር የተሰማራው የሃገር መከላከያ ኃይል ጥቃቱን በጊዜ ሊያስቆመው አለመቻሉ እንዳስከፋቸው ገልፀዋል፡፡ አንድ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት፤ “ከዚህ ቀደም ይፈፀም ከነበረው ጥቃት እጅግ የከፋ ነው፤ ብዙ ወንድም እህቶቻችንን አሳጥቶናል” ሲሉ በሃዘን ተውጠው ተናግረዋል፡፡
ማክሰኞ ነሐሴ 8 ደግሞ በምስራቅ ወለጋ ሁለት ወጣቶች፣ በቡድን በተደራጁ ግለሰቦች ተደብድበው መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚሁ እለት በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ፣ የዞኑ ተወላጆች “የስራ ዕድል እያገኘን አይደለም” በሚል ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በተፈጠረ ግጭት፣ የሶስት ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፡፡
ከሳምንት በፊት በጅግጅጋ በተፈጠረው ግጭት ተጎድተው፣ በህክምና ላይ የነበሩ 16 ሰዎችም በዚሁ ሳምንት ህይወታቸው ማለፉ ተዘግቧል፡፡ የድሬደዋ ፖሊስ በበኩሉ፤ ሰኞ ነሐሴ 7 በድሬደዋ ከተማ በተፈፀመ ጥቃት 10 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል፡፡
ከመንግሥት  አካላት ይፋ ከተደረጉ አሃዛዊ መረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለው፣ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ በየአካባቢው በተፈጠሩ ግጭቶች፣ የ65 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
“የሰዎች በህይወት የመኖር ህገ መንግሥታዊ መብት እየተጣሰ፣ በየቀኑ ዜጎች ያለ ፍትህ በአደባባይ መገደላቸው አሳሳቢ ነው” ያሉት አስተያየት ሰጪዎች፤ “ድርጊቱ በአጭሩ ካልተቀጨ ለሀገሪቱ የለውጥ ሂደት ስጋት ነው” ብለዋል፡፡ የህግ ባለሙያዎች በበኩላቸው፤ መንግሥት ተመጣጣኝ የኃይል እርምጃን ጨምሮ በመጠቀም፣ የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡
“ሁከቶችን የሚያመክን ህጋዊ እርምጃ አስፈላጊ ነው” ያሉት አለማቀፍ የህግ ባለሙያው ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፤ “በሀገሪቱ በጅምላ አካሄድ እየተፈፀሙ ያሉ ወንጀሎችን መከላከል የሚቻለው ጠንካራ የህግ ተጠያቂነት በእያንዳንዱ ድርጊት ላይ ማስፈን ሲቻል ነው” ብለዋል፡፡
“መንግስት ዋነኛ ኃላፊነቱ ህግ ማስከበር ነው” ያሉት ሌላው የህግ ባለሙያ አቶ አዲሱ ጌታነህ፤ ከእያንዳንዱ የህግ ጥሰት ጀርባ ያሉ አካላትን ያለ ርህራሄ ወደ ፍትህ በማቅረብ፣ በሀገሪቱ ህጋዊ ተጠያቂነት መኖሩን ማስረገጥ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡  “በዚህ የህግ ማስበር ሂደት ውስጥም ህገ ወጥና ጥፋት ሊያስከትሉ የሚችሉ ሰልፎችን አስቀድሞ ከመከላከል ጀምሮ በአደባባይ በተደራጁ ኃይሎች የሰው ህይወትን የሚያጠፋ እርምጃ ሲወሰድ፣ የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ የመከላከል እርምጃ መውሰድ አለባቸው” ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል - የህግ ባለሙያው፡፡
“አሁን በአብዛኛው እየደረሱ ያሉ ጥፋቶችና ሰዎች በአደባባይ እየተገደሉ ያሉት የፀጥታ አካላት ተገቢውን የመከላከል ተግባር ባለመፈፀማቸው ነው” ያሉት የህግ ባለሙያው፤ “የፀጥታ አካላት ወንጀል ሲፈፀም በቸልታ በመመልከታቸው በራሱ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ ይህ አይነቱ ተጠያቂነትም መስፈን አለበት” ብለዋል፡፡
ሌላው የህግ ባለሙያ አቶ ወንድሙ ኢብሣ፤ ለውጡን በስልጣን ላይ ሆኖ በመምራት ላይ ያለው ኃይል፣ ፊቱን ወደ ህግና ስርአት ማስከበር ማዞር አለበት ባይ ናቸው፡፡ “በአሁኑ ወቅት በየቦታው ግጭቶች እየተፈጠሩ፣ የሰዎች ህይወት የሚያልፈው የህግ የበላይነት ባለመስፈኑ ነው” ብለዋል፡፡
መንግሥት ፖለቲካዊ ጥያቄ ያዘሉ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎችንና በቡድን የሚፈፀሙ ወንጀሎችን እየለየ ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰድ አለበት ያሉት ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ፤ በሃገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችና ብሄር ተኮር ጥቃቶች ለውጡን ሊያደናቅፉት ይችላሉ - ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
በአገሪቱ በየጊዜው የሚፈጠሩ ግጭቶች፣ ዜጎችን ለሞት መዳረጋቸው ሳያንስ ሚሊዮኖችን ከቀዬአቸው እያፈናቀሉ ነው፡፡
ባለፉት 2 ዓመታት በሀገሪቱ በተፈጠሩ የተለያዩ ግጭቶች 2.8 ሚሊዮን ያህል ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀላቸውን የገለፀው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ፤ ከእነዚህ ውስጥ 1.4 ሚሊዮኑ ዘንድሮ ከመስከረም ወዲህ የተፈናቀሉ መሆናቸውን አስታውቋል - በሰሞኑ ሪፖርቱ፡፡

Read 7573 times