Tuesday, 21 August 2018 00:00

የመደመር ለውጥ ሥጋቶች፤ ደጋፊዎቹ እየሆኑ ነው

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(4 votes)

 (የመደመር ፍልስፍና)
                   
    የነበረው ነገር እንደነበረ መቀጠል ከማይችልበት ነጥብ የሚደረሰው፤ የነበረውን ነገር እንደነበረ ለማስቀጠል የሚደረገው የተለያየ ሙከራ ረጅም ጊዜ ከወሰደና ነባሩን ነገር ከዚያ በላይ ማስቀጠል ከማይቻልበት ደረጃ ሲደረስ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ነባሩን አቅቦ ለማቆየት ወይም ሚዛን ለመጠበቅ የሚወሰደው እርምጃ፣ ምንም ዓይነት ሥራ አለመሥራት ነው፡፡ ከአጭር ጊዜ አኳያ ሥራ ባለመሥራት ወይም የትኩረት አቅጣጫ በመቀየር ፋታ ማግኘት የሚቻል ቢሆንም፤ ከመካከለኛና ከረጅም ጊዜ አኳያ ግን ይበልጥ ተጋላጭ የሚያደርግ ነው፡፡ አሁን አንድ ነገር ይበልጥ ግልጽ ሆኗል፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም። ከዚህ በኋላ ማድረግ የሚቻለው ወደፊት መሄድ ብቻ ነው፡፡ ግን ብዙ ልፋትና ማስተዋልን የሚጠይቅ ሥራ በመሆኑ ወደፊት መሄድ እንዲህ ቀላል ነገር አይደለም፡፡
ከእነ ብዙ እንከኑ፤ በእኔ ግምት አሁን የምናየው ሰላም፤ በአንድ ቃል የመጣ ሰላም ነው፡፡ በግራ በቀኝ የሚናጠቁት ችግሮች ቢኖሩም፤ የሰላማችን ምንጭ ‹‹መደመር›› ነው፡፡ ‹‹መደመር›› ኢትዮጵያን ከመከራ የጠበቀች ቃል ነች፡፡ መደመር አሰባሳቢ ቃል በመሆን አገልግላለች፡፡ ‹‹መንግስቱ ኃ/ማርያምን ከሐራሬ፤ አቦይ ስብሐትን ከመቀሌ፤ ጃዋር መሐመድን ከሚኒሶታ፤ ኢሳያስ አፈወርቂን ከኤርትራ ወዘተን›› በአንድ ለማሰባሰብ የምትመኝ ቃል ነች፡፡ ‹‹መደመር›› ለኢትዮጵያ የተስፋ መዝሙር ሆናለች፡፡ ‹‹መደመር›› ባለፉት 50 ዓመታት የተበላሸውን ነገር ለማረም የሚያስችልና አዲስ ምዕራፍ በመክፈት ለገዢው ፓርቲም ሆነ ለተቃዋሚዎች መሰባሰቢያ ታዛ ሆናለች። ከዚህች ቃል ከዚህ በላይ የምንጠብቅ ከሆነ፤ ከዚህ በላይ ማሰብ ይኖርብናል፡፡
‹‹መደመር›› የታሪክ እልባት ሆናለች፡፡ የ27 ዓመታት የአመለካከት ሰልፍን ቀኝ ኋላ ዙር ያለች አዋጅም ሆናለች፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ምድር የመደብ እንጂ የብሔር ጭቆና አልነበረም›› የሚል የጥላቻ ግንብ ማፍረሻ መዶሻም ሆናለች፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ምድር የመደብ ጭቆና እንጂ የብሔር ጭቆና አልነበረም›› በሚል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ኦቦ ለማ መገርሳ የተናገሩትን ቃል፤ አንድም ሰው ቁም ነገር ብሎ ሲያነሳው አልሰማሁም። ነገር ግን ከመደመር ፍልስፍና የወጣችና ባለፉት ዓመታት የነበረውን የፖለቲካ ሐቲት የምታፈርስ አዋጅ ነች። የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለማጠናከር የምታግዝ አዋጅም ነች፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ በለውጥ ጉዞ ላይ ነች፡፡ ግን ይህን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ፡፡ ህዝብን ለብሶት የዳረጉት፤ በግል ፍላጎትና በሥልጣን ታውረው ስርዓቱን ለቀውስ ያጋለጡት ወገኖች፤ አሁን ከገባንበት አጣብቂኝ ውስጥ ከተውናል፡፡ ህዝብ አንድ ቀን እንዲህ እንደሚነሳ ስለማያውቁ አይደለም፡፡ ይልቅስ ሁልጊዜም ችግሩን ሊያቆሙት የሚችሉ ስለሚመስላቸው ነበር፡፡ አሁን ጠ/ሚ ዐቢይ እንዳሉት፤ ‹‹አንድ ነገር ሲኖር እና ሲሞት መለየት የሚሳናቸው ሰዎች ሆነዋል፡፡››
እነዚህ ሰዎች ህዝቡ በቃኝ ብሎ ለመለወጥና ለውጥ ለመስራት ሲሞክር እንቅፋት ይሆናሉ። በቁጣ፣ እውነትን በመካድ፣ በመደናገጥ ወዘተ ለውጡን ማደናቀፍ ይዘዋል፡፡ በእርግጥ እነዚህ ወገኖች ውሎ አድሮ ለውጡን መቀበላቸው አይቀርም፡፡ ሆኖም አሁን ለውጡን ከመቀበል ደረጃ አልደረሱም፡፡ አሁን በቁጣ፣ እውነትን በመካድ፣ በመደናገጥ ስሜት ውስጥ ሆነው የቀቢፀ ተስፋ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ በሁከትና በጸያፍ ድርጊት ህዝቡን ከትኩረቱ ሊያናጥቡት እየሞከሩ ናቸው፡፡ ይህ ድርጊታቸውም ህዝቡ ለውጡ ሊቀለበስብን ይችላል ከሚል ስጋት ውስጥ እንዲገባ እያደረገው ነው፡፡ ስለዚህ ህዝቡ እነሱን አደብ ለማስገዛት በሚደረግ እንቅስቃሴ ከመደመር፣ ከሰላም፣ ከፍቅርና ከይቅርታ መንገድ እንዳይወጣ መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡ አሁን ‹‹ለውጡ ሊቀለበስብን ይችላል›› ከሚል ስጋት ሳይሆን፤ ‹‹ህግ በእኛ እጅ ነው›› በሚል ምክንያት ስርዓተ አልበኝነት የሚታይባቸው አጋጣሚዎች እየበረከቱ ነው፡፡  
የለውጥ ኃይሉ አሁን አንድ ነገር ማመን አለበት። የለውጥ ሂደቱ ሊሰናከል የሚችለው፤ አደናቃፊዎች የሚባሉት ወገኖች በሚሰሩት ሥራ ወይም በሚሸርቡት ሴራ አይደለም፡፡ ይልቅስ “የለውጥ ኃይል ነኝ” ብለው የሚያስቡ ወገኖች በሚፈጽሙት ስህተት ነው፡፡ ስለዚህ የለውጥ ኃይሉ በጥንቃቄ መራመድ ይኖርበታል፡፡ ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ሰዎችን እኩይ ተግባር ለመከላከል የሚደረገው ጥረት፤ ከመሠረታዊ መርሆአችን እንዳያወጣን በጥንቃቄ መራመድ ያስፈልገናል፡፡ አሁን የለውጡ ጉዞ የሚወሰነው በአብዛኛው በለውጡ አራማጅና ደጋፊዎች እርምጃ እንጂ በአደናቃፊዎች ተንኮል አለመሆኑን ማመን ይገባናል፡፡
ባለፈው ጊዜ ኢንጂነር ስመኘው በድንገት ሞተው ተገኙ ሲባል ተበሳጨን፡፡ ተበሳጭተን አደባባይ ወጣን፡፡ ተበሳጭተን በአንዳንድ ዜጎች ላይ የቁጣ እርምጃዎችን ወሰድን፡፡ ንብረት አወደምን፡፡ አሁን አንድ ነገር ልብ ማለት አለብን። የመደመር መንገድ ትዕግስትና ማስተዋል የሚጠይቅ መንገድ መሆኑን መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ከሚሽነሩ፤ ‹‹ትዕግስት ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡ ትክክል ናቸው፡፡ ይህ በህዝቡ በኩል ያለ አደጋ ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ አመራሩም ሊገነዘበው የሚገባ ነገር አለ፡፡ ህዝብ በመጨነቅ ስሜት ውስጥ ሆኖ ለብዙ ጊዜ መቆየት አይችልም፡፡ ህዝቡ ከጭንቀትና ሥጋት ለመጠበቅ የሚወስዳቸው እርምጃዎች (የመኖሪያ ቀዬን ከመልቀቅ ጀምሮ)፤ ከመድረሻ ግባችን በእጥፍ እያራቀንና ችግሮችን ይበልጥ እያወሳሰባቸው መሄዱ የማይቀር ነው። ስለዚህ አመራሩ ጭንቀትና ሥጋቱ በቶሎ የሚወገድበትን መላ መፈለግ አለበት። እንዲሁም ሁሉም ዜጎች ከለውጡ የሚጠብቁትን ነገር ማቀራረብ ይኖርበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ፤ ህገ መንግስቱን እንቀይር፣ የሽግግር መንግስት እንመስርት እና ፌዴራላዊ ስርዓቱን እንለውጥ ከሚለው ጀምሮ የተለያዩ ሐሳቦች ሲነሱ እናያለን፡፡ ይህ ፍላጎት በፍጥነት መቀራረብ አለበት፡፡
ከዚህ አንጻር የምሰጠው አንድ አስተያየት አለኝ፡፡ አሁን ያለው ስርዓት ከተጨባጭ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ግፊት ጭምር እንጂ በፖለቲከኞች ፈቃድ ብቻ የተፈጠረ አይደለም፡፡ ስለዚህ የፌዴራል ስርዓቱንና ህገ መንግስቱን ለመቀየር ከመነሳታችን በፊት፤ አስተሳሰብንና የፖለቲካ አደረጃጀትን ለመቀየር መስራት ያስፈልጋል፡፡ የሽግግር መንግስት ጉዳይ ከምርጫ ቢወጣ የግል ምርጫዬ ነው፡፡ ይህን ትቶ፤ የፖለቲካ ስርዓትን መለወጥ አረም እንደ መንቀል ቀላል እንዳልሆነ ተገንዝበን፤ ለውጡን በጥንቃቄ በመምራቱ ላይ ትኩረት አድርገን መስራቱ የተሻለ ምርጫ ይመስለኛል፡፡ በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች መካከል ያለው የአመለካከት ሸለቆ እንዲህ በቀላሉ የሚሞላ አይደለም፡፡ ይህ ሁኔታ እንደፈለጉ የሚያራምድ አይደለም፡፡ ስለዚህ የለውጥ አመራሩ በማስተዋልና በጥንቃቄ መራመድ አለበት፡፡
እንደሚታወቀው፤ በትናንሽ ንግዶች ስኬታማ የሚያደርግ የአመራር ዘይቤ በፖለቲካ አይሰራም። በትናንሽ ንግዶች ስኬታማ የሚሆኑ ሰዎች ሙሉ ትኩረታቸውን በሥራቸውና የሚሰሩትን ሥራ ምርጥ አድርገው በመስራት ላይ ማሳረፍ ይኖርባቸዋል። የስኬት ተነሳሽነት የሚመነጨውም፤ ከምንሰራው ሥራ ትክክለኛነት ነው፡፡ የስኬት ተነሳሽነት፤ አንድ ሰው በግለሰባዊ ወይም በህዝባዊ ህይወት መስክ፣ የላቀ ደረጃ የሚይዝ ሥራ ለመስራት ያለውን ፍላጎት የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ የስኬት ተነሳሽነት ያለው ሰው፤ የሚሰራውን ሥራ ምርጥ አድርጎ በመስራት እንጂ ከሰው የሚያገኘውን አድናቆት በመመልክት የሚተጋ አይደለም፡፡
ሆኖም የፖለቲካ ሥራ የሚሰራውን ሥራ ምርጥ አድርጎ በመስራት ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ እንዲህ ያለ ሰብእና ለኢኮኖሚያዊ እንጂ ለፖለቲካዊ ሥራዎች ብዙም ፋይዳ የለውም፡፡ ምክንያቱም ግለሰቦች ‹‹ምርጥ›› ተብሎ በሚገመተው ነገር ሊለያዩ ይችላሉ። ለአንዱ ሰው ‹‹ምርጥ›› የተባለ ተግባር፤ ለሌላው ‹‹ምርጥ›› ላይሆን ይችላል፡፡ በፖለቲካ መስክ የሚኖሩ የተለያዩ ወገኖች፣ የላቀ ነገር አድርገው በሚይዙት ነገር ሊለያዩ ይችላሉ። የፖለቲካ መሪዎች አንድን ፖሊሲ ተፈጻሚ ለማድረግ ሲሰሩ፤ የራሳቸው አንዳች ሥልጣንና ህዝባዊ መሠረት ያላቸው የተለያዩ ቡድኖች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ሥራ፣ የተለያዩ ቡድኖችን ማሳመንንና የእነሱን ፍላጎት ከግምት ማስገባትን የሚጠይቅ ነው፡፡
በአንጻራዊ ሚዛን ካየነው፤ አዲስ ፖሊሲ ማሰብና ለህዝብ ይፋ ማድረግ እጅግ ቀላል ነገር ነው፡፡ ነገር ግን አዲስ መንግስታዊ ፖሊሲ የተለያዩ የፍላጎት በድኖችን ጥቅም በተለያየ መንገድ ይነካል፡፡ ስለዚህ አዲስ ፖሊሲ የተለያዩ የጥቅም በድኖች የሚያነሱትን ጥያቄ የመመለስ ዕዳ አለበ፡፡ የአዲስ ፖሊሲ ትግበራ፤ በበጀት ጉዳይ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር ከስምምነት መድረስን፤ ወደ ሙሉ ትግበራ ለመሄድ የፓይለት ጥናት ማካሄድን የሚጠይቅ ከመሆኑ ባሻገር፤ አንዳንድ ጊዜ በፖሊሲው የመጣውን ለውጥ ለማጣጣም ወይም ለውጡን በተጨባጭ ለማየትም በርካታ ዓመታትን ሊጠይቅ ይችላል። በፖለቲካ ህይወት ውስጥ የተለመዱ የሆኑት እነዚህ የሥራ ሂደቶች፤ ከፍተኛ የስኬት ተነሳሽነት ያላቸውን ሰዎች ትዕግስት የሚፈታተኑ ናቸው። ይህ ሁኔታ የፖለቲካ አመራሩ፣ በስራ ገበታው በየዕለቱ እንዲፈተንና ቀስ በቀስም የስኬት ተነሳሽነቱ እንዲፈተን ያደርገዋል፡፡
እንደሚታወቀው በለውጥ ሂደት ውስጥ የመሪው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ሾፌሩ የመኪናው ወሳኝ ክፍል ነው። አዎ፤ ይህ ሐሳብ በአንድ አንጻር ትክክል ነው። ነገር ግን የዚህ እውነት ሌላ ክንፍ የሆነ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ያለ መኪናው ሰውዬው ሾፌር አይሆንም፡፡ ይህም እውነት ነው።  መኪናውም ሰዋዊ (human) እና ኢ-ሰዋዊ (nonhuman) በሆኑ ነገሮች የሚገነባ ነው። ስለሆነም፤ አመራሩ ሰዋዊ (human) እና ኢ-ሰዋዊ (nonhuman) አላባዎችን ከግምት ያስገባል፡፡ የአመራሩ ስኬት የሚወሰነውም፤ በሁለቱ አላባዎች ቅንጅት ነው፡፡
በመሆኑም፤ የመደመር ሰዋዊ እና ኢ-ሰዋዊ አላባዎች በደንብ ሊተነተኑና ህዝቡም ፍልስፍናውን በአግባቡ እንዲገነዘብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሰዋዊ አላባዎች ያለ ኢ-ሰዋዊ (nonhuman) አላባዎች አይቆሙም።  ስለዚህ ዋናው ነገር የቱ ነው የሚለው ጥያቄ ከንቱ ነው። ምክንያቱም ዋናው ነገር፣ የሁለቱ አላባዎች ውህድ ነው፡፡
ሰዋዊ አላባዎችን ስንመለከት፤ መሪና ተመሪ አሉ። መሪና ተመሪ ሁለቱ ጥምር ቃላት ይመስላሉ። ግን አይደሉም፡ ትክክለኛው የአመራር ዘይቤ ሲተገበር፤ ሰዎች ከመመራት ስሜት ጋር በሩቁ እንኳን የሚዛመድ ስሜት አይኖራቸውም። ምርጥ አመራር የሚታየው፤ ሰዎች ተመሪነት ሳይሰማቸው ‹‹ተመሪ›› በሚሆኑበት ሁኔታ ነው። ወዳጆችና አጋሮች ንቅናቄ ውስጥ እንዲገቡ ሲደረጉ፤ ተከታዮች ሳይሆኑ ተነሳሽነት ያላቸው ተሳታፊዎች ይሆናሉ፡፡ ተነሳሽነት ያላቸው ተሳታፊዎች - (ሠራተኞች ወይም ዜጎች) ብዙውን ጊዜ ከሚጠበቀው በላይ በሆነ መጠን፤ እንዲሁም ከኃላፊነት ክልላቸውም ተሻግረው በመሄድ ከለውጡ ፊት የተጋረጡ ተግዳሮቶችን ለማስወገድ በገዛ ራሳቸው ለሥራ ይነሳሳሉ፡፡ አጋሮችም ይሆናሉ፡፡
ሆኖም ብዙዎቹ ምርጥ ‹‹አመራሮች››፤ ወዳጅና ደጋፊዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚዎቻቸውንና አጥር ላይ ቆመው የሚመለከቱትን ሰዎች ጭምር የሚያነቃንቁ ናቸው፡፡ በለውጥ ሂደት ውስጥ ወዳጆችንና አጋሮችን (በአንጻራዊ ሚዛን) ያለ ብዙ ድካም፤ ጉዞውን በቀላሉ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ይቻላል። አስቸጋሪው ሥራ በለውጥ ሂደቱ ብዙ ነገር የሚያጡትንና በተቃውሞ ጎራ የሚገኙትን ሰዎች የለውጡ አካል እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ የመደመር ፍልስፍና ትልቁ ፈተና ይህ ይመስለኛል፡፡
አጥር ላይ ተቀማጮችና ተቃዋሚዎች፣ ንቅናቄ ውስጥ ሲገቡ፤ እንዲለወጡ ከሚያስገድዳቸው የለውጥ ሂደት ጋር ይጋፈጣሉ፡፡ ከለውጡ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ፈተናዎች ፊት ይቆማሉ። ያገኙት የነበረውን ጥቅም ከማጣትና ለለውጡ ታማኝ ከመሆን ተቃራኒ ምርጫዎች ጋር ይፋጠጣሉ፡፡ እንዲሁም ከለውጡ ጋር ለመራመድ ብቃት ከማግኘት ጋር ተሳስረው የተቀሰቀሱ ችግሮችን መጋፈጥ ይጀምራሉ። በእርግጥም መዋጋታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በዚህም ለለውጡ አስፈላጊ ለሆነው የሐሳብ ብዝሐነት ምንጭ ይሆናሉ። በተዘዋዋሪ መንገድ፣ ለለውጡ ስኬት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡
በአመራሩ የላቀ ሚና የሚደመሩትና ንቅናቄ ውስጥ የሚገቡት ሁለቱ ኃይሎች (አጥር ላይ ተቀማጮችና ተቃዋሚዎች)፤ የአሰራርና የአኗኗር ዘይቤ ማመቻመችን ከሚጠይቁ አዲስ ውስብስብ አጀንዳዎች ጋር ግብግብ ይገጥማሉ፡፡ ተቃዋሚዎቹ  ‹‹አጋር›› ከመሆን ሳይደርሱ፤ ደጋፊዎቹም ‹‹በተከታይነት›› መንፈስ ሳይታሰሩ፤ የአሰራርና የአኗኗር ዘይቤ ማመቻመችን ከሚጠይቁ አዲስ ውስብስብ አጀንዳዎች ጋር ግብግብ ይገጥማሉ። ቀስ በቀስም ለውጡን የሚመራውን ግለሰብ ወይም ቡድን ማመን፣ ማድነቅና የለውጡን ፋይዳ መገንዘብ ይጀምራሉ፡፡ በዚህም ለመሪው ግለሰብ ወይም ቡድን ኢ-መደበኛ ስልጣን ይሰጡታል። ሆኖም የለውጡን ፋይዳ በቶሎ ከመገንዘብ አይደርሱም፡፡ ‹‹እኔ የአመራሩ ተከታይ ሆኛለሁ›› በሚል የአመኔታ ስሜት የታጀበ ድጋፍ አይሰጡም።  
አመራር የሚፈጠረው በችግሮችና በተግዳሮቶች ውስጥ ነው፡፡ ዘወትራዊ ሥራዎችን ለማስተባበር የሚያስችል የተጽዕኖና የሥልጣን ችሎታ በሁሉም ሥፍራና ደረጃ ባለበት፤ ሁሉም ሰው ‹‹በጥሩ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን›› የሚል ዜማ በሚያዜምበት ጊዜ፣ የአመራርን ፋይዳ መገንዘብ አይቻልም፡፡ የአመራርን ፋይዳ መገንዘብ የሚቻለው፤ አንድ ነባር መዋቅር፣ የአሰራር ስልትና ሂደት እንዳለ እንዲቀጥል በሚደረግበት ሁኔታ ውስጥ ሳይሆን፤ መቀየርን ግድ በሚል ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ አስተዳደራዊ ብቃት መያዝ ብቻ በቂ በሚሆንባቸው ሁኔታዎች ውስጥ የሚገጥሙን ችግሮች ቴክኒካዊ ናቸው፡፡ አመራር የሚፈተነው ነባር አሰራርን መለወጥን በሚጠይቅ ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ አመራር የሚፈተነው፤ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመጋፈጥ፤ ከሚለወጠው ዓለም ጋር የተጣጣመ ብቃት በመያዝ፤ አንዳንድ የቅደም ተከተል፣ የዝንባሌና የባህርይ ለውጥ ማድረግን በሚጠይቁ አዳፕቲቭ ተግዳሮቶች (adaptive challenges) ውስጥ ነው፡፡  
ለወጥን የሚጠይቁ ተግዳሮችን ለመጋፈጥ ህዝቡን የማንቀሳቀስ ሥራ፤ የአንድ አመራር ዋና ተግባር ነው፡፡ ከአጭር ጊዜ አኳያ፤ ከፊቱ የተደቀኑ ወቅታዊ ችግሮችን ለመጋፈጥ ህዝብን ሞቢላይዝ የማድረግ ሥራ ነው፡፡ ከመካከለኛና ከረጅም ጊዜ አኳያ፤ ተከታታይ ለውጥን የሚጠይቁ እውነታዎችን ወይም ግፊቶችን እያግተለተለ አዳፕቲቭ ተግዳሮቶችን (adaptive challenges) የሚያመጣውን ዓለም ለመጋፈጥ የሚያስችል አዲስ አስተሳሰብና ምግባር መፍጠር ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ፤ ከረጅም ጊዜ አንጻር፤ የአመራሩ ሚና የድርጅቱን ወይም የማህበረሰቡን ‹‹ለአዲስ ሁኔታ ብቁ ሆኖ የመገኘት አቅምን›› (አዳብቲቭ ካፓሲቲ) ማሳደግ ነው፡፡
ሁሉም ችግር፤ በመሻታችንና በተጨባጩ ሁኔታ ያለ ክፍተት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ አሁን ባለው ብቃት ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉ ገዳዮች ‹‹ቴክኒካዊ ተግዳሮቶች›› ናቸው፡፡ በተቃራኒው አሁን ባለው ብቃት ምላሽ ሊያገኙ የማይችሉ ችግሮች ‹‹አዳብቲቭ ተግዳሮቶች›› ናቸው፡፡ ‹‹ቴክኒካዊ ተግዳሮቶች›› የሚደቅኑት፤ አሁን ባለን ዕውቀት ሊዘጋ የሚችል ክፍተት ሲፈጠር ነው፡፡ በተቃራኒው፤ ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮት›› በመሻታችንና በተጨባጩ ሁኔታ ያለው ክፍተት አሁን ባለው አሰራርና ዕውቀት ሊሸፈን የማይችል ክፍተት ሲጋፈጠን ነው፡፡ ስለዚህ ለችግራችን መፍትሔ የሚሆነው ነገር የሚገኘው አሁን ከዘረጋነው ስርዓትና ከምናደርገው ድርጊት ክልል ውጭ ባለ አውድ ይሆናል፡፡
አንድ ሰው በኢንፌክሽን በሽታ ታሞ ወደ አንድ ሐኪም ቢሄድ፤ ዶክተሩ ቀድሞ የነበረውን ዕውቀት በመጠቀም በሽተኛውን ይመረምራል፡፡ መድኃኒትም ያዝለታል፡፡ ቀድሞ በነበረ ዕውቀት ችግሩ ይፈታል። በሌላ በኩል፤ ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮት›› በተጨባጭ ባለው ሁኔታና በምንመኘው ነገር መካከል ያለው ክፍተት፤ አሁን ባለው ባህል በተቀረጸ ባህርይ፣ የአሰራር ዘዴ፣ እውቀትና ክህሎት ችግሩ ሊሸፈን አይችልም። አንድ ሰው የልብ በሽታ ቢይዘው፤ የኑሮ ዘይቤውን ለመቀየር ይገደዳል፡፡ ማለትም አመጋገቡን መቀየር ይኖርበታል፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ሲጋራ አጫሽ ከሆነም ማጨሱን ማቆምና ጤናማ ያልሆነ ወይም ሚዛን የሳተ የኑሮ ዘይቤን ማስወገድ ይኖርበታል፡፡ ለውጥ ለማምጣት ህመምተኛው ለራሱ ጤና ኃላፊነት መውሰድ ወይም አዲስ የኑሮ ዘይቤን መማር ይኖርበታል፡፡
ስለዚህ ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮት›› አዳዲስ ነገሮችን መማርን የሚጠይቅ ነው፡፡ ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮት›› የሚፈጠረው፤ ራሳቸው ሰዎቹ የችግሩ ምንጭ ሲሆኑና የተፈጠረውም አዲስ ሁኔታ የምንሰራበትን መሣሪያ (የአስተሳሰብና የአሰራር ዘይቤን) መቀየርን (retooling) የሚጠይቀን ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ በተጨባጭ ባለው ሁኔታና በምንመኘው ነገር መካከል ያለው ክፍተትም ሊሞላ የሚችለው፤ አዳዲስ ነገሮችን በመማር ብቻ ነው፡፡
አንድ አማካሪ ድርጅት ስለ አንድ ድርጅት ጥናት አድርጎ፣ ምክረ ሐሳብ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ሆኖም የድርጅቱ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ምክረ ሐሳቡን ካልተገበሩት ወይም የአስተሳሰብና የአሰራር ዘይቤ ለውጥ እስካላመጡ ድረስ ችግሩ አይወገድም፡፡ እንዲሁም ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮት›› ኃላፊነትን ከስልጣን መዋቅሩ ወይም ከባለስልጣናት ትከሻ ወደ ባለድርሻ አካላት (በአንድ የሥራ ውጤት ተጠቃሚ ወደ ሆኑ ሰዎች) ማዛወርን ይጠይቃል፡፡
ችግሩ በአንድ ባለሙያ ክንውን መፍትሔ የሚያገኝ ሲሆን፤ ችግሩ ቴክኒካዊ መሆኑ ነው፡፡ በተቃራኒው፤ ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮት›› ለየት ያለ ውይይት፣ ምክክርና ለየት ባለ ሁኔታ ኃላፊነትን የመሸከም ውሳኔን ይጠይቃል፡፡ ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮትን›› በምንጋፈጥበት ጊዜ፤ በርካታ ሰዎች የኃላፊነት ስሜት ሊሰማቸውና ሸክሙን ሊጋሩት ይገባል፡፡ ለቴክኒካዊ ችግሮች፤ ባለሙያዎች መፍትሔ ሊኖራቸው ይችላል። ሆኖም ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮቶች›› ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከተው አንድ ባለሙያ ወይም መሪ መፍትሔ ሊያገኙ አይችሉም፡፡ አሁን እኛን የገጠመን ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮት›› መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ መደመር ይህን ሁኔታ መገንዘብን ይጠይቃል፡፡ ከችግሩ ለመውጣት ሁሉም ዜጎች (ባለድርሻ አካላት) ኃላፊነት እንዳለባቸው ሲገነዘቡ መደመር እውን ይሆናል፡፡ መደመር የተለየ አስተሳሰብን የሚፈልግ ፍልስፍና ነው፡፡ መደመር ለውጥ ለማምጣት የሚሞክረው፤ ችግሩን የተገነዘቡ የለውጥ ኃይሎችን በማሳተፍ ብቻ አይደለም፡፡ መደመር የችግሩ መንስዔ የሆኑ ሰዎችን የመፍትሔው አካል የማድረግ የይቅርታና የፍቅር ብሩህ ጎዳና ነው፡፡ ሰላማዊ አብዮት ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮቶችን›› ቴክኒካዊ አድርጎ የማየት ከባድ ስህተት ሲፈጽሙ፤ ኃላፊነት ላይ ያለው ሰው ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲነግራቸው ይጠብቃሉ፡፡ ሆኖም በኃላፊነት ላይ ያለው ሰው አስተያየት እንጂ የብቻ እውነት ወይም መፍትሔ ሊኖረው አይችልም፡፡ ሊያደርግ የሚችለው መገመት ብቻ ነው፡፡ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ስህተት ሲፈጽሙ፤ ጥሩ መሪ ብናገኝ ኖሮ፤ ችግራችን መፍትሔ ሊያገኝ ይችል ነበር ብለው ያስባሉ፡፡ ባልሆነ ነገርም ይታመናሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የአመራሩ ዋና ተግባር፤ ኃላፊነቱ በባለ ድርሻዎቹ ትከሻ እንዲያርፍ ማድረግ ነው፡፡ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ፤ የምናካሂደው ለውጥ ጥቂቶች ተዋናይ የሚሆኑበትና ብዙዎች ተመልካች የሚሆኑበት ጉዞ አይደለም ማለታቸው ለዚህ ነው፡፡
እንዲሁም ‹‹አዳብቲቭ ተግዳሮት›› ከባለ ጉዳዮቹ የሚጠይቀው ሌላ ሥራ አለ፡፡ ‹‹አዳብቲቭ ተግዳሮት›› በመደመር ጎዳና የተሻለ መፍትሔ የሚያገኝ ይመስለኛል፡፡ የመደመር ፍልስፍና ካለፈው ነገር የትኛው ውድና ሁነኛ ሐብት ወይም ቅርስ እንደሆነ፤ የትኛውስ ሊወገድ የሚገባው ነገር እንደ ሆነ የመለየት ፍልስፍና ነው፡፡ ለምሣሌ ባህልን ለዘመኑ ተስማሚ እንዲሆን የማድረግ ሥራ፤ ከታሪካችን ውስጥ ምርጥ የሆነውን መውሰድና ሊጠቅም የማይችለውን ደግሞ አራግፎ መጓዝ ጥረት ነው፡፡ በአዲሱ ሁኔታ ውስጥ በድል ለመጓዝ የሚያስችለውን መንገድ ማወቅ ጥረት ነው፡፡ ስለዚህ የመደመር ፍልስፍና የተራማጅና የወግ አጥባቂነት ባህርይ ያለው ፍልስፍና ነው፡፡
ለነገሩ፤ ስኬታማ ሥነ ህይወታዊ የለውጥ ጉዞ፤ ካለፈው ነገር ምርጡን መውሰድና ከእንግዲህ ወዲህ ሊረባ የማይችለውን DNA ገድፎ የመጣል ጉዞ ነው፡፡ በተመሳሳይ፤ በለውጥ ወደፊት በምንራመድበት ጊዜ፤ ጥበብን በተመረኮዘ አኳኋን፤ ከታሪካችን ምርጡን ለይቶ አውቆ ትውልድ እንዲሻገር ማድረግ ያስፈልጋል።  
ሁኔታዎች በተለወጡ ጊዜ ከለውጡ ጋር የተጣጣመ አቋም ይዘን ለመገኘት ስንሞክር፤ በውስጣችን ለውጥን የመግፋት ዝንባሌ ይፈጠርብናል፡፡ ምክንያቱም፤ ከለውጡ ጋር የተጣጣመ  አቋም ይዞ የመገኘት ሥራ፤ ካለፈው የአሰራርና የአኗኗር ልማዶቻችን ውስጥ የተወሰኑ ነገሮችን መተውን ወይም መጣልን የሚጠይቅ ነው፡፡ በውስጣችን የሚፈጠር ለውጥን የመግፋት ዝንባሌ፤ ከያዝናቸው ነገሮች የተወሰኑ ነገሮችን የመጣል ብቃት ከማጣት ዝንባሌ የሚፈጠር ነው፡፡ ልማድን የመተው አቅም ማጣት ነው፡፡ ይዘናቸው የቆየናቸውን ትውፊቶች የመቀየር፤ ትውፊቶቹን ላስተማሩን ሰዎች ያለንን ታማኝነት የመንፈግ አቅም ማጣት ነው፡፡
ስለዚህ፤ ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮቶች›› ከባድ ሰጥቶ የመቀበልና ሚዛን የመጠበቅ ፈተና ውስጥ እንድንቀረቀር የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ያመጡብናል። ሰዎች ለውጥን ለመቀበል የሚያደርጉት ማንገራገር ምንጩ፤ በቀጥታ ለውጥን ካለመቀበል ግፊት ጋር የሚያያዝ ብቻ ሳይሆን፤ የተወሰኑ ነገሮችን የመጣል ብቃት ከማጣት ጋር የሚያያዝም ነው፡፡ ሰዎች ጠቃሚ ሆኖ የታያቸውን ለውጥ በጣም ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ ነገሮችን የመጣል ብቃት ያጣሉ፡፡ ስለዚህ የመደመር አመራር፤ አዲስ ለውጥን ከማከናወን ጋር ተያይዞ በተለያየ መልክ የሚነሱ (እውነተኛና በሥጋት የተፈጠሩ) ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል ብቃት ለመፍጠር መታገል ይኖርበታል፡፡ መደመር እውን የሚሆነው በዚህ መንገድ ነው፡፡
በአጠቃላይ፤ ከዚህ በላይ የተባለው ነገር የመደመር ፍልስፍና አንድ ዐ.ነገር ነው፡፡ የተሳካ ሥራም ባይሆን የመደመር ፍልስፍና የመጀመሪያ ረቂቅ (ዜሮ ድራፍት) ሊሆን የሚችል ነው፡፡

Read 3048 times