Saturday, 18 August 2018 14:02

ሁለተኛው “ሆሄ” የሥነ - ፅሑፍ ሽልማት፣ ተጠናቀቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

በረጅም ልቦለድ ዓለማየሁ ገላጋይ፣ በግጥም በዕውቀቱ ሥዩም አሸንፈዋል
ሁለተኛው ዙር “ሆሄ” የስነ-ፅሑፍ ሽልማት ባለፈው ሰኞ ምሽት በብሔራዊ ቴአትር በተካሄደ ደማቅ ሥነ ሥርዓት አሸናፊዎቹን በመሸለም ተጠናቅቋል፡፡ በረጅም ልቦለድ ዘርፍ የዓለማየሁ ገላጋይ “በፍቅር ሥም”፣ በግጥም ዘርፍ የበውቀቱ ሥዩም “የማለዳ ድባብ” ያሸነፉ ሲሆን በልጆች መፅሐፍ ዘርፍ የዳንኤል ወርቁ “ቴዎድሮስ፣ ኡጋዝ መሃመድ” አሸናፊ ሆኖ ተሸልመዋል፡፡
በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የብሔራዊ ቤተ መፃህፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖ አምላክ መዝገቡን ጨምሮ በርካታ ደራሲያን፣ ገጣሚያን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የታደሙ ሲሆን ፕሮግራሙ የተጀመረው በሰዓሊና ገጣሚ ገ/ክርስቶስ ደስታ “ሀገሬ” ግጥም ተውኔታዊ ክንውን ነበር፡፡ በቅርቡ በሞት ለተለየን የመድረክ ፈርጥ አርቲስት ፍቃዱ
ተክለማርያም የ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት ከተደረገ በኋላ ወደ ሽልማቱ ተገብቷል፡፡ የ“ሆሄ” የሥነ ፅሑፍ የዓመቱ ምርጥ ተሸላሚ የሆኑት ደግሞ ለ48 ዓመታት መፅሐፍትን በመሸጥ ለአንባቢያን ትልቅ ውለታ ያበረከቱት አቶ ተስፋዬ አዳል ናቸው፡፡
ከጊዮን ከፍ ብሎ በሚገኘው የ7ኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ጎን ከፅድ ተከርክማ በተሰራች ጎጆ ለ48 ዓመታት የውጭና የአገር ውስጥ መፅሐፍትን በመሸጥ ውለታ የዋሉት አዛውንቱ አቶ ተስፋዬ አዳል ሽልማቱን ከተቀበሉ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ “ሽልማቱ ለእኔ እንደገና እንደመፈጠር ነው በጣም ተደስቻለሁ” ብለዋል፡፡ ከኦሎምፒያ እስከ አምባሳደር ጋዜጣና መፅሔት በመሸጥ 3 ዓመት፣ መፅሐፍትን
በመሸጥ 48 በድምሩ 51 ዓመታትን በዘርፉ ያሳለፉት አዛውንቱ፤ ዶ/ር ከበደ ሚካኤል፣ ከንቲባ ዘውዴና ሌሎች ትልልቅ ሰዎች ደንበኞቻቸው እንደነበሩ ጠቅሰው፤ በተለይ ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ሌላ የሚገዙት ባይኖር እንኳን የራሳቸውን መፅሐፎች ገዝተው ይሄዱ እንደነበር አውስተዋል፡፡ የቀድሞው የደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንትና ደራሲ ጌታቸው በለጠ “ከእኔ የ7ኛ ክፍል የሂሳብ መፅሐፍ ገዝተው
ተምረዋል” ብለው ሲናገሩ፤ ደራሲ ጌታቸው በአዳራሹ ውስጥ ነበሩ፡፡ ታዳሚው ቆሞ በማጨብጨብ ለአዛውንቱ የንባብ ባለውለታ ያለውን አድናቆትና አክብሮት ገልፆላቸዋል፡፡
“ለአካል ጉዳተኞች ንባብን ተደራሽ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ” በሚል ዘርፍ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማህበር ተሸላሚ ሲሆን የትምህርትና የሙያ መፅሐፍትን በአገራችን ቋንቋ በመፃፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉትና በ1878 በአድዋ ተወልደው በኦስትሪያ ህክምና የተማሩትና በሱዳን ስደት ላይ በነበሩ ጊዜ “መንግሥትና አስተዳደር” የተሰኘ መፅሐፍና ሌሎች ሥራዎችን በማበርከት
የሚታወቁት ነጋድረስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ሶስተኛ ትውልድ የልጅ ልጃቸው ተገኝቶ ሽልማቱን እንዲወስድ ጥሪ ቢደረግም ሳይመጣ ቀርቷል፡፡
“በህይወት ዘመን የስነ ፅሑፍ ባለውለታ” ዘርፍ ከ70 በላይ መፃሕፍት ያበረከቱት አንጋፋው ደራሲ፣ ተርጓሚና አርታኢ አማረ ማሞ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ አንጋፋው የሥነ ፅሑፍ ባለሙያ የሶስተኛ ዙር የ“ንባብ ለህይወት” የወርቅ ብዕር ተሸላሚ እንደነበሩም ይታወሳል፡፡“ይህ ቤት ትልቅ ስፍራ ነው ድሮ ድሮ በዓመት አንድ ጊዜ ዘፈን ለመስማት እህቶቼን ይዤ እመጣ ነበር” ያሉት አቶ አማረ፤ እዚህ
ትልቅ ሥፍራ ላይ በመሸለማቸው ትልቅ ደስታና ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል፡፡ ኖርዌይ በነበርኩበት ጊዜ የአገሩ ዜጎች ብርዱ ከቤት ስለማያስወጣቸው ቁጭ ብለው መፅሐፍ ያነብባሉ ያሉት ተሸላሚው፤ እሳቸውም እዛ መኖራቸው እንደጠቀማቸው ጠቁመው፣ “የዛሬ ወጣቶች ኪሳቸው በገንዘብ የተሞላ ነው፤ በብሩ መፅሐፍ ገዝተው ያንብቡ” ሲሉ መክረዋል፡፡ በአርቲስት አለማየሁ ታደሰ የመድረክ አመራር ብቃትና በበኃይሉ ገ/እግዚአብሔር ወግ እየተዋዛ የቀጠለው የሽልማት ሥነ ስርዓቱ ሳይሰለችና ሳይንዛዛ በጥሩ ሁኔታ ተጠናቅቋል፡፡ በነገራችን ላይ 30 ደቂቃ ብቻ በማርፈድ ቶሎ የተጀመረ ብቸኛ ሥነ ሥርዓትም ይመስለኛል፡፡   


 

Read 4700 times