Monday, 27 August 2018 00:00

የዚምባቡዌ ምርጫ ውጤት በፍ/ቤት ጸደቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 አውሮፕላን ማረፊያው በሙጋቤ ስም መጠራቱ እንዲቀር ተጠይቋል


    በቅርቡ የተካሄደውና ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋዋ ያሸነፉበት የዚምባቡዌ ምርጫ የተጭበረበረ ነው፣ ሊሰረዝ ይገባል በሚል በአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተመሰረተውን ክስ ሲመረምር የቆየው ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት ክሱን ውድቅ በማድረግ የምርጫ ውጤቱን አጽድቋል፡፡
በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው 44.3 በመቶ ድምጽ በማግኘት ሳይመረጡ የቀሩት ሙቭመንት ፎር ዲሞክራቲክ ቼንጅ የተባለው የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ኔልሰን ቻሚሳ፣ የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን የድምጽ አሰጣጡን ያለአግባብ በማከናወን ምናንግዋ እንዲያሸንፉ አስችሏል ሲሉ ክስ መስርተው ነበር፡፡
የፓርቲው ደጋፊዎች የምርጫ ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ማሰማታቸውንና ከፖሊስ ጋር ግጭት ተፈጥሮ ስድስት ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡ ባለፈው ሃምሌ ወር መጨረሻ ላይ የተካሄደው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ዚምባዌ ከ37 አመታት በላይ የገዟት ሮበርት ሙጋቤ ባልተወዳደሩበት ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዚዳንቷን ያስመረጠችበት ምርጫ ነው፡፡
በተያያዘ ዜናም የዚምባቡዌ የቀድሞ የጦር ሃይል አባላት የአገሪቱ አለማቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ስም መጠራቱን እንዲያቆም መጠየቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የጦር ሃይል አባላቱ የሮበርት ሙጋቤ ስም ከአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ እንዲነሳና የሌሎች ታላላቅ የአገሪቱ ባለውለታዎችና ጀግኖች ስም እንዲተካ የሚጠይቅ የድጋፍ ድምጽ አሰባስበው ለአዲሱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንግዋ ለማስገባት እየተዘጋጁ ነው ተብሏል፡፡
ለረጅም አመታት ሃራሬ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በሚል ስያሜ ሲጠራ የኖረው አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው፣ ባለፈው አመት ሙጋቤ ስልጣን ሊለቁ ጥቂት ሳምንታት ሲቀራቸው ስያሜው ወደ ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ እንዲቀየር መደረጉን ያስታወሰው ዘገባው፤”ስማቸውን ዘላለማዊ የማድረግ ጥማት ባለባቸው ሙጋቤ የተወሰደው የስም ለውጥ እርምጃ ተገቢ አይደለምና ስያሜው ይቀየርልን” ሲሉ የጦር ሃይሉ አባላት መቃወማቸውን አመልክቷል፡፡


Read 2411 times