Saturday, 25 August 2018 13:38

ሌ/ጄነራል ፃድቃን ገ/ተንሳይ ምን እያሉ ነው?

Written by  በመስከረም አበራ
Rate this item
(6 votes)

የህወሃት ነባር ታጋይ የሆኑት ሌ/ጄነራል ፃድቃን ገ/ተንሳይ፤ ከህወሃት ተለየሁ ካሉ በኋላም መለስ ቀለስ እያሉ ኢቲቪን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች ሃሳባቸውን ሲገልፁ እየሰማን ነው፡፡ ህወሃት አድራጊ ፈጣሪ በነበረበት ዘመን ሁሉ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በሃሳብ ልዩነት ተለይተው ከወጡ በኋላ የጦር አማካሪ መሆን፣እየነገዱ መኖር፣ በዩኒቨርሲቲ ማስተማር፣ በሚዲያ ብቅ እያሉ አስተያየት መስጠት… የሚቻለው ህወሃት የሆኑ እንደሆን ብቻ ነው፡፡
ህወሃት ያልሆኑቱ የኢህአዴግ የቀድሞ ባለስልጣናት ከቀናቸው እንደ እነ ኤርሚያስ ለገሰ፣ጁነዲን ሳዶ፣ኡሞድ ኦቦንግ ሃገር ጥለው ይሰደዳሉ፡፡ እንደ ታምራት ላይኔ ያሉት ደግሞ ብዙ አመት በእስር ቤት እንዲያሳልፉ ይሆናል፡፡ ህወሃት ሆነው እስር ቤት የገቡት እነ ስየ አብርሃ፤ እስራቸው የሌሎቹን የኢህዴግ አባላት ታሳሪዎች ያህል ያልረዘመ ከመሆኑም ባሻገር ከእስር ሲወጡ የገጠማቸው እድል እንደ ሌሎቹ ጡረታ ተከልክሎ፣ ከመኖሪያ ቤት ተፈናቅሎ በመዋጮ የመኖር እጣ አይደለም፡፡ ትክክለኛው፤ ለህወሃቶቹ የተደረገው ነው፡፡ በአንድ ወቅት በመንግስታዊ አስተዳደር ውስጥ ሆኖ ሲያገለግል የኖረ ሰው በሃሳብ ተለየ ተብሎ፤ ልጆቹን የሚያበላው እህል ውሃ፣ ጎኑን የሚያሳርፍበት ቤት እስከሚያጣ ድረስ መበቀል መንግስትነትን አይመጥንም፡፡
በጎ ባልሆነው የህወሃት ዘመን ሳይቀር በጎ የሆነላቸው ጄ/ል ፃድቃን፤ በተለያዩ ሚዲያዎች እየቀረቡ የሚሰጧቸውን አስተያየቶች እከታተላለሁ፡፡ብዙ ጊዜ በሚሰጧቸው ሃሳቦች ላይ ልዩነቶች አሉኝ። በሃሳቦቻቸው ውስጥ የህይወት ልምዳቸውን የሚመጥን ሚዛናዊነት አጣለሁ፡፡ ሚዛናዊ ለመምሰል የሚወረውሯቸው አንዳንድ ሃሳቦች ቢኖሩም አፍታም ሳይቆዩ ወደ ህወሃት ዘመም ዘመም ሲሉ ይገጥመኛል። የትግራይን ህዝብ ከሰው የተለየ ፍላጎት ያለው፣ ከህግ በላይ የመሆን መብት የተሰጠው፣ የተለየ እንክብካቤ የሚገባው ልዩ ፍጡር አድርገው የሚያቀርቡት ነገር አይዋጥልኝም፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ነሐሴ 12 ለንባብ በበቃው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በወጣው ቃለ ምልልሳቸው የተናገሩት ይህንኑ ነው፡፡
በቃለ ምልልሱ ላይ እርስ በርስ የሚጋጩ ብዙ ሃሳቦችን አስተውያለሁ፡፡ይህ የሆነው ፃድቃን በእውነት በሚያምኑትና መስለው መታየት በሚፈልጉት ነገር መሃል ባለ መጋጨት ነው፡፡ አስተውሎ ለተከታተለው ግን ፃድቃንም ሆኑ ባልንጀራቸው ጄ/ል አበበ ተክለሃይማኖት የህወሃትን የበላይነት አይጠሉትም። ይህን ያስባለኝ በብዙ ቦታዎች ካደረጓቸው ቃለ ምልልሶች፣ ከፃፏቸው ፅሁፎች ተነስቼ ቢሆንም ለዛሬ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከተናገሩት ብቻ እየጠቀስኩ ላስረዳ፡፡
አሁን ለመጣው ለውጥ መፅናት መንግስት በሰላማዊ ተፎካካሪዎችና ህዝብን በሚያናውጡ ታጣቂዎች መሃል ልዩነት አስምሮ፣ በበጥባጮች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ያስቀመጡትን ሃሳብ እጋራለሁ፡፡ ያለውን ስጋት ሲያስቀምጡ “....የዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራትና የመኖር መብታቸው አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ ሰዎች በማንነታቸው ይገደላሉ.....” ያሉት ነገር  ግን በተለይ ለአማራው ህዝብ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ለሌ/ጄ/ል ፃድቃንም አዲስ ነገር አይመስለኝም፡፡
ወላድ፣እርጉዝ፣ህፃን፣አዋቂ ሳይል ሰባ ምናምን ሺህ ህዝብ አማራነቱ ብቻ ጥፋት ሆኖ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በተባሉ ባለስልጣን ፊርማ፣ ከጉራፈርዳ ሲባረሩ ፃድቃን ያልሰሙት ጉዳይ አይደለም፡፡ የፃድቃን የትግል ጓድ አቶ መለስ ስለዚሁ ጉዳይ ፓርላማ ቀርበው ሲጠየቁ፤ “ደግ አደረግን” አይነት መለስ ሲሰጡ፣ የህዝብ በማንነቱ ብቻ መፈናቀል ስጋት ሆኖባቸው፣ ፃድቃንም ወደ አዲስ አድማስም ሆነ ወደ ማንኛውም ሚዲያ ቀርበው ዛሬ የሚናገሩትን አልተናገሩም፡፡ በዚሁ መከረኛ ህዝብ ላይ በበደኖና በአርባ ጉጉ የሆነው ሲሆን ፃድቃን አድራጊ ፈጣሪ የመንግስት ባለስልጣን ነበሩ፡፡ እኔ በወቅቱ ሚዲያ መከታተል የምችል ሰው ባልሆንም ነገሩን ሲያወግዙ ሰማሁ የሚል ገጥሞኝ አያውቅም፡፡
በአንፃሩ ዐቢይ በሚመሩት መንግስት ውስጥ የሚደረገውን ማንኛውንም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያወግዛሉ፡፡ የድርጊቱን ፈፃሚዎች ይኮንናሉ፡፡ ይህ ነገር ሲደረግ ዝም ብለው ያዩ የመንግስት አካላትንም ራሳቸውን ከስልጣን እንዲያገሉ እያደረጉ ነው፡፡ የጠፋው የሰው ነፍስ የሚያሳዝን ቢሆንም ዐቢይ ለነገሩ እልባት ለመስጠት ያላቸው ዝንባሌና ቁርጠኝነት ደግሞ የነገሩ ማብቂያ እንደደረሰ ተስፋ የሚጭር እንጅ እንደ ፃድቃን  ዛሬ የተጀመረ አድርገው እንደሚያወሩት፤ “እግዚኦ” የሚያስብል ነገር አይመስለኝም፡፡
ሌ/ጄ/ል ፃድቃን ነገሩን አተኩረው እንዲያዩት፣ በሚዲያም መጥተው አፅኖት እንዲሰጡት ያደረጋቸውም ምናልባት ህወሃት እሳቸውም አባል በነበሩበት ወቅት ማኒፌስቶ ፅፎ ጠላቴ ነው ላለው የአማራ ህዝብ የደገሰው የማፈናቀል፣ የማሳደድ፣ የመግደል ክፉ ድግስ፤ ዛሬ ህወሃት ጠመንጃወን ታቅፎ ከኖረበት መንበሩ ሲጠፋ፣ ህዝቤ ለሚለው የትግራይ ህዝብም የተረፈ ስለመሰላቸው ይሆናል፡፡ ለዚህ ማስረጃው ፃድቃን ስጋታቸውን ሲያስረግጡ ጣና በለስ ላይ ስለሞቱ ሁለት ሰዎች (እነዚህ ሰዎች የትግራይ ተወላጆች ናቸው የሚል ወሬ ሲናፈስ ሰንብቷል) ማንሳታቸው ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንደሚያሳስባቸው መግለፃቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ማንነትን ማዕከል አድርጎ መሞት የተጀመረው ዛሬ አይደለም፡፡ የሰው በማንነቱ መሞት የሚያሳስበው፣በሰው ሁሉ እኩልነት የሚያምን ሰው፤ እሪ የሚለው ድርጊቱ የተጀመረ እለት እንጂ ሄዶ ሄዶ፣ የእሱን ሰፈር ሰዎች ሲያሰጋ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ፤ ምንም አይነት ሰራተኞች እንዳልሞቱበት ለዋዜማ ሬዲዮ ተናግሯል፡፡
በጣም የሚገርመው ፃድቃን በዚሁ በማንነት ምክንያት፣ የመሞትንና ሌሎችን በሃገሪቱ አልፎ አልፎ የሚታዩ ግርግሮችን በተመለከተ የዶ/ር አብይን መንግስት ሊወቅሱ መነሳታቸው ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ ፃድቃን፤ “በአሁኑ ወቅት ህዝብ ብሶቱን እየገለፀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ጉዳቱን የሚያመጣው የብሶት አገላለፁ ነው፡፡ የማዕከላዊ መንግሥቱ ደግሞ ሁኔታውን ተረድቶ ብሶቱን ከማባባስና ሂደቱን ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ ከመግፋት ይልቅ ሁኔታውን ማርገብ ይገባው ነበር፡፡....ቀደም ሲል በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ተሰርቶ ነበር፡፡ የበደሉ፣ የብሶቱ ሁሉ ምንጭ፣ እሱ ነው ተብሎ፣ ውስጥ ለውስጥ በርካታ የፕሮፓጋንዳ ስራ ተሰርቷል። በአንፃሩ፤ ይሄን ፕሮፓጋንዳ የመመከት ስራ አልተሰራም፡፡…” ቀደም ሲል የማዕከላዊ መንግሥት ስልጣንን ይቆጣጠራል ተብሎ የነበረው ኃይል ከቦታው ሲወጣ፣ ለዘመናት የነበሩ ጥላቻዎች ፊት ለፊት እየወጡ ነው ያሉት። ወደ አንድ ህዝብ ያተኮረ የጥላቻ ፖለቲካ ደግሞ ለወደፊት በሃገራችን ውስጥ ልንፈጥር የምናስበውን ሀገራዊ አንድነትና ሰላም የሚበርዝ ነው፡፡ አንደኛውን ወገን ተስፋ የሚያስቆርጡ ጠባሳም ጥለው የሚያልፉ ናቸው፡፡.” (የአፅኖት መስመር የእኔ)፡፡
በፃድቃን አስተሳሰብ የዶ/ር አብይ መንግስት የህዝብን ብሶት እያባባሰና ሁኔታውን ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ እየመራ ነው፡፡ አድማጭ እስኪሰለቻቸው ድረስ በየደረሱበት ሁሉ “የትግራይ ህዝብ እና ህወሃትን ለዩ” እያሉ የሚወተውቱት ጠ/ሚ/ር ዐቢይ፤ የትግራይ ህዝብ ራሱ ብሎት የማያውቀውን “የትግራይ ህዝብ በህወሃት እንደ ሁላችሁም የተበደለ ነው፣ እኔን ከወደዳችሁኝ በዚህ ህዝብ ላይ አንዳች ክፉ እንዳታስቡ” እስከ ማለት የደረሱ ሰው ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየደረሱበት ስራዬ ብለው፤ “የትግራይን ህዝብ እባካችሁ አትጥሉት፣ ምስኪን ደሃ ህዝብ ነው፣ ህወሃት ማለት የትግራ ህዝብ አይደለም” እያሉ በሃገር ውስጥ ሆነ በውጭ መድረክ፣ በአደባባይ ሰልፍ ሆነ በቤት ውስጥ ውይይት ሁሉ መወትወት ፃድቃን፤ “በትግራይ ህዝብ ላይ ተነጣጥሮ ተሰራ” የሚሉትን ፕሮፓጋንዳ የመመከት ስራ አይደለም እንዴ?! ዶ/ር አብይንም ሆነ መንግስታቸውን በዚህ መውቀስ ትልቅ ፍርደ ገምድልነት፤ ነው፡፡
በበኩሌ አንድም ሁለትም የትግራይ ተወላጅ ‘እንዲህ በተባለ ሃገር ሞተ’ የሚለው ነገር በማስረጃ ተረጋግጦ ቢያንስ ሞቱ የተባሉት ሰዎች ፎቶ በማህበራዊ ድረገፅ ሲቀርብ፣ ዘመዳችን ሞተብን የሚሉ ሰዎች በገለልተኛ ሚዲያ ቀርበው ስለ ሁኔታው ሲያወሩ ሰምቼ አላውቅም፡፡ በአንፃሩ ህወሃት በማንነታቸው ሲያስር ሲገድል ሲያፈናቅላቸው የነበሩ ሰዎች በየሚዲያው ሲቀርቡ ከራሳቸው አንደበት ብሶታቸውን እንሰማለን፡፡
ለትግራ ተወላጅ ለማዘን የግድ ትግሬ መሆን አያስፈልግም፡፡ ነገር ግን ባልተረጋገጠ ወሬ፣ ሞቱ የተባሉ ሰዎች ይሰሩበት ነበር የተባለው መስሪያ ቤት ለሚዲያ “የሞተብኝ ሰው የለም” እያለ እየተናገረ ባለበት ሁኔታ፣ የሞተው ሰው ስም ማን ይባላል? ቢባል እንኳን መጥራት በማይቻልበት ነገር፤ ፃድቃንን የሚያክል የእድሜ ዘመን ፖለቲከኛ፤ “የትግራይ ህዝብ ሞት ታወጀበት” ብሎ ማውራት በማንነቱ ሲሞት በኖረው ህዝብ ላይ መቀለድ ነው፡፡
እንደ ማንኛውም የትግራይ ፖለቲከኛ፤ ፃድቃን የመሃል ሃገር ሰው ትግሬ ወገኖቹን ለማጥፋት ዘመቻ እንደጀመረ አፋቸውን ሞልተው ያወራሉ፡፡ይሄ መዓት መጥራት በትግራይ ፖለቲከኞች ዘንድ የተለመደ፣ይበልጥ የተበደሉ አስመስሎ አስቀድሞ በመጮህ፣ የህወሃትን በደል ለመሸፈን የሚሞከርበት አስቀያሚ አካሄድ ነው፡፡ በተረፈ የኢትዮጵያ ህዝብ እነሱ በሚያወሩት መጠን በትግራይ ወንድሞቹ ላይ ሴራ አሲሮ፣ አንዳች ክፉ ነገር ለማድረግ የሚያስብ ሆኖ አይደለም፡፡
ፃድቃን ግን ያለምንም የሃላፊነት ስሜት እንዲህ ይላሉ፤ “አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በመሃል ሀገር የሚደረገው ፀረ-ትግራይ እንቅስቃሴ፣ በነበረው ይቀጥል የሚሉትን ኃይሎች የሚያጠናክርና ድጋፍ የሚያስገኝላቸው ነው የሚሆነው፤ ግን በግልፅ በህወሓት ውስጥ ሁለት ኃይሎች ፍትጊያ እያደረጉ ነው......በኋላ ግን በጅምላ የሚፈርጀውና ትግራይ ላይ ያነጣጠረው እንቅስቃሴ ሲመጣ፣ ህዝቡ ለውጡን በስጋትና በጥርጣሬ ለማየት ተገድዷል፡፡.......በየሄድንበት እየተሸማቀቅን ልንኖር ነው ወይ? በሀገራችን ተዘዋውረን ሃብት አፍርተን፣ እንደ ማንም ሰው መብታችን ተጠብቆ በስርአት መኖር ልንከለከል ነው ወይ? የሚል ስጋት አለው፡፡ ለዚህ ስጋት ደግሞ ዋናው ምክንያት በየአካባቢው የትግራይ ህዝብ ዒላማ እየተደረገ፣ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት የመንጋ ፖለቲካ ነው።” መሃል ሃገር የት ቦታ የተጀመረ፣ ምን በሚባል ስም ስለሚጠራ፣ በእነማን ስለሚመራ ፀረ-ትግራይ እንደቅስቃሴ እንደሆነ የሚያወሩት አልገባኝም፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ምክንያት ሰለባ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ስንት እንደሆኑ፣የት ቦታ ምን እንደደረሰባቸው በተጨባጭ ያስረዱን ይሆን? ይህ ጥያቄ በቃለ ምልልሱ ወቅት ቢነሳ መልካም ነበር፡፡
እውነት እንዲህ ያለ በመሃል ሃገር ሰዎች የሚደረግ እንቅስቃሴ ካለ፣ ለምን ወደ ህግ አልወሰዱትም? ምን እስኪሆን ነው የሚጠበቀው? አሁን በተጨባጭ በደልን አቅርቦ ተበደልኩ ማለት የሚቻልበት ዘመን ነው፡፡ በተጨባጭ በደል ካለ ማስረጃ ይዞ መቅረብ ነው፤ የማይጨበጥ ነገር እያነሱ ማውራት ግን ዓላማው ሌላ መሆን አለበት፡፡       
በህወሃት መንደር የደረሰ ሰው መቼም እፍረት የለውምና ፃድቃን ወደ አንድ ህዝብ ላይ ያተኮረ ጥላቻ ለወደፊቱ ሃገራዊ አንድነት ችግር እንዳለው ኮራ ብለው ይናገራሉ፡፡ በመጀመሪያ ወደ አንድ ህዝብ ያተኮረ የሚሉት ጥላቻ የትኛው ነው? ይሄኔ እኔም በዚህ ፅሁፍ እሳቸው የተናገሩትን በመሞገቴ፣ በትግራይ ህዝብ ላይ ጥላቻ እንደምሰብክ እያሰቡ ይሆናል፡፡
የትግራይ ህዝብ እውነት ህወሃት እንደበደለው ካሰበ  ለምን ተቃውሞውን አይገልፅም፣ ለምን በስሙ ሲነገድ ዝም ይላል ለምን እኛን ወገኖቹን አግዞን ሁላችንም ከህወሃት ግፈኛ አገዛዝ ነፃ እንድንወጣ አይሆንም፣ ማለት በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ የጥቃት ፕሮፓጋንዳ ከሆነ፣ ማኒፌስቶ ፅፎ አንድን ህዝብ  በጠላትነት ፈርጆ፣ ሃያ ሰባት አመት ሲያስገድሉ መኖር ምን ሊባል ነው? “የትግራይን ህዝብ አትንኩት” እያሉ በየደረሱበት በሚማልዱት በዐቢይ ዘመን ቀርቶ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪም  ያለ አንዳች እፍረት በአንድ ህዝብ ላይ ሞት ሲያውጅ፣ ገድሎ ሲያስገድል፣ሰድቦ ሲያሰድብ በነበረው አመራርም ተኑሯል፡፡
ዛሬ ደርሰው የሰብአዊነት ዘበኛ ሊሆኑ የሚቃጣቸው ፃድቃንም ጠመንጃቸውን አንግበው ይህንኑ የሞት አዋጅ ሲያስፈፅሙ የኖሩ ሰው መሆናቸውን ሌላው ቢረሳ “የውሻ ሞት” ሲሞት ከኖረው የአማራ ህዝብ የወጣን እኛ አንረሳውም! ጅብ እንኳን ቁርበት አንጥፉልኝ የሚለው በማያውቁት ሃገር ሄዶ ነው፡፡ ሰው ደግሞ በሚታወቅበት ሃገር ቁጭ ብሎ ደርሶ ሩህሩህ፣ የሰብዓዊነት ዘብ ሲሆን የሚያስገምተው ራሱን ነው።
አንድን ህዝብ ነጥሎ ማጥቃት ተጎጂውን ህዝብ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ያሉት ፃድቃን፤ ይህ ዛሬ ለምን እንደገባቸው ግልፅ ቢሆንም ሃሳቡ እውነት ነው። በማንነቱ ብቻ እንደ ውሻ በየሜዳው ሲገድሉት፣ በየእስር ቤቱ ሰውነቱን ሲተለትሉት፣ አእምሮውን በርካሽ አንደበታቸው ሲያደሙት የኖረው አማራ የሚወደውን ኢትዮጵያዊነቱን ድርድር ውስጥ አስገብቶ በማያውቀው የጎጥ ከረጢት ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ፃድቃን ጭምር ታጥቀው የሰሩበት ዘር ተኮር ጥቃት ተስፋ አስቆርጦት ነው፡፡ በዘር ማንነት ምክንያት የመገለል፣ በሃገር ዳርቻ የመሳደድ ጠባሳውም በሁላችንም አእምሮ ውስጥ አለ። አሁን በወንበሩ ላይ ያሉት አብይ መሆናቸው ነው ተስፋን የሚያሰንቀው መልካሙ ዜና!
ሌ/ጄ ፃድቃን ስለ ትግራይ ህዝብ ወቅታዊ ስሜት የተናገሩት፣ ካሉት ነገር ሁሉ ይበልጥ ያደናገረኝ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ፃድቃን ስንቱን የትግራይ ተወላጅ አናግረው፣ ምን ያለ ጥናት አድርገው እንዲህ የአንድ ክልልን ህዝብ ሁሉ ስሜት ማውራት እንደቻሉ ጥያቄ ነው። ሲቀጥል ስብሰባ ለማድረግ ስሄድ ካየሁት ትዝብቴ ተነስቼ የተገነዘብኩት እያሉ የሚያወሩት ነገር፣ እውነት የትግራይን ህዝብ ስሜት የሚወክል ከሆነ አሳሳቢ ነው፡፡
የትግራይ ህዝብ ቁጣው ነዷል የሚሉት ፃድቃን፤ የቁጣውን ምክንያት እንዲህ ያስረዳሉ፤ “ቁጣው ምንድን ነው? ከተባለ፣ መሪዎች አጥፍተው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከትግራይ የወጡ መሪዎችን ጥፋት መነሻ በማድረግ፣ የህዝቡን መስዋዕትነት ማራከስ፣ እንደ እላፊ ተጠቃሚ መቆጠር ህዝቡ ውስጥ ቁጣ እየፈጠረ ነው፡፡ የዲሞክራሲ እጦትና የመልካም አስተዳደር ችግር ከየትኛውም የሀገሪቱ ክልል  በትግራይ የባሰ ሆኖ ሳለ፣ እላፊ የስርአቱ ተጠቃሚ ተደርገን በጅምላ መፈረጃችንና የጥላቻ ፖለቲካ ሰለባ መሆናችን ተገቢ አይደለም ከሚል የመነጨ ቁጣ ህዝቡ ውስጥ እንዳለ መረዳት ይቻላል።  ለውለታችን ምላሽ ይሄ ነው ወይ የሚል ቁጣ አለ፡፡”
ይህ አባባል እንደተባለው የትግራይ ህዝብ ስሜት ከሆነ፣ የሚያስነሳው ጥያቄ ብዙ ነው፡፡ ከትግራይ የወጡ ሰዎች ባጠፉት ጥፋት የህዝብን መስዋዕትነት ማራከስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም፡፡ማን ነው መስዋዕትነታቸውን ያራከሰው? የትግራይን ህዝብ መስዋዕትነት ማክበር ማለት እንደ አቶ ኃ/ማርያም ሶስት ገበያ ህዝብ አስከትሎ፣ኩሽሽ አንገት ላይ ጠምጥሞ፣ ደደቢት በረሃ ወርዶ፣ የጥንቱን የህወሃት ቢሮ መሳለም ነው? አብይ አሁን ያሉበት ሃገራዊ ፈተና ይሄን ለማድረግ ጊዜ የሚሰጣቸው አይደለም፡፡ በተቀረ መቀሌ በሄዱበት ወቅት በሰማዕታት ሃውልት ተገኝተው የሚደረገውን አድርገው ነው የተመለሱት፡፡
ከዚህ በላይ ምን መደረግ ነበረበት? እውነት እንነጋገር ከተባለ፣ ልጅ ያልሞተበት ኢትዮጵያዊ የለም። የትግራይ ህዝብስ ለሞቱት ልጆቹ ሃውልት አቁሞ የመጣው ሁሉ ለቅሶ እየደረሰ ነው፡፡ እነዚህ የትግራይ ሰማዕታት የገደሏቸው የሌላው ኢትዮጵያዊ ልጆች ግን መታሰቢያ እንኳን የቆመላቸው አይደሉም፡፡ የሞቱለት አላማ ቢመረመር ደግሞ የማናቸውም ሞት ለኢትዮጵያ የተሻለ ቀን አላመጣም፡፡ ስንሞትም ስንቆምም እንበልጣለን ካልተባለ በቀር!
የዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር እጦቱ በትግራይ ይብሳል ለሚለው የባሰው ሰው ተነስቶ ታግሎ ቀንበሩን ያሽቀነጥራል፡፡ የትግራይ ህዝብ ደግሞ ለዚህ የታወቀ ነው። ደርግን ለመታገል አንድ አመት አልጠበቀም። ደርግ ተስተካክሎ ወንበሩ ላይ ሳይቀመጥ ነው ህወሃት ወደ ጫካ የገባው፣ የትግራይ ህዝብም ትግሉን የተቀላቀለው፡፡ አሁን ህወሃት በደለኛ ነው ከተባለም ተመሳሳዩን ለማድረግ አፈናው ከለከለ የሚለው ለኔ በግሌ አይዋጥልኝም፡፡ ኦሮሞ የመታገያው ሜዳ እነሆ ተብሎ ተሰጥቶት አይደለም “ሆ!” ብሎ ወጥቶ የሞተው፣ ሞቶ የተረፈው የተሻለ ስርዓት ለማየት የበቃው፡፡ አማራ የልጁ ደም ጣናን ሲያቀላ እያየ ነው ሲታገል የነበረው፣ ኮንሶው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ ወዘተ መንግስት እየደጎመው አይደለም በቻለው ሁሉ ሲታገል የነበረው፡፡
ሰው ተበድያለሁ ብሎ ያሰበውን ያህል ይታገላል። እውነቱ ያ ነው! መበደል ብቻውን ቁምነገር አይደለም፤ ለትግል እኩል አስፈላጊው ነገር፤ ተበዳዩ በደልን የመቁጠር ጭካኔ ላይ ደርሷል ወይ የሚለው ነው፡፡ ህወሃት የትግይራን ህዝብ እንደሚበድል ይታወቃል፤ ጥያቄው የትግራይ ህዝብ የደርግን በደል ይቆጥር በነበረበት መንገድ የህወሃትን በደል ይቆጥራል ወይ? የሚለው ነው፡፡ ይህን በተመለከተ ፃድቃን ራሳቸው በዚሁ ቃለ መጠይቃቸው”የትግራይ ህዝብ ከፈለገ ህወሓትን ያጎለብታል፤ ካስፈለገው ደግሞ ይገድለዋል” ሲሉ ጨርሰውታል፡፡
የትግራይ ህዝብ ለሌላው ህዝብ ውለታ ውያለሁ፤ የውለታዬ ምላሽስ ይህ ነው ወይ እያለ ያዝናል ይቆጣል የተባለው ነገር ግራ አጋቢ ነው፡፡ ውለታ የተባለው እነዚሁ ዘወትር የሚነሱት ስልሳ ምናምን የትግራይ ሰዎች ህወሃትን ወግነው ደርግን ሲታገሉ መሞታቸው መሰለኝ፡፡ ህወሃት ትግራይን እገነጥላለሁ እያለ በነበረበት ዘመን፣ ትግራይን ለመገንጠል የሞቱት ሰዎች ውለታቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ የሆነበት መንገድ አልገባኝም፡፡ ህወሃት ብድግ ብሎ “ትግራይን መገንጠሉን ትቼዋለሁ” ሲል ደግሞ “ታዲያ ለምን እንዋጋለን” እስከማለት ተደርሶ እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ አቶ መለስም በዚህ ጉዳይ ተቸግረው እንደነበር በራሳቸው በአንደበት ተናግረዋል፡፡ መለስ እንደምንም ብለው አሳምነዋቸው ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግሱ የሞቱት ደግሞ ባለውለታችን ይሆኑ ዘንድ የሞቱለት ስርዓት ሲዘርፈን፣ ሲገድለን፣ ሲያሰድደን ኖረ እንጂ ውለታቸውን እንቆጥር ዘንድ ዲሞክራሲን አላመጣልንም፡፡ በአጭሩ የማንም ውለታ የለብንም!
“[ኢትዮ-ሶማሌ ክልል] ሶማሌ ውስጥ የተደረገው ነገር ትግራይ ውስጥ ሊመጣ እንደሚችል ወጣቱ ይነገረዋል፤ በዚህም ይሰጋል። የትግራይ ህዝብ በትግሉና በመስዋዕትነቱ ያገኘውን መብት ማንም ሰው መጥቶ እንዲድጠው አይፈልግም። ከውስጡ የወጡት አጥፊ ኃይሎችንም ቢሆን ራሱ ሊቀጣቸው ይፈልጋል እንጂ በሌላ ኃይል ተድጠው፣ አንተ የትም አትደርስም የሚል መልዕክት እንዲተላለፍለት አይፈልግም፡፡ ጥፋት ያጠፉ ካሉ በህገ መንግሥቱ መሰረት ይስተካከል እንጂ ኃይል ያለው ሁሉ በዘፈቀደ ከህግ ውጪ፣ እኛን ወደ ጎን ትቶ ለውጥ አመጣለሁ የሚል ከሆነ፣ የኛን ክብርና ማንነት ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም” የሚል ነገር ይፈጠራል፡፡” ይላሉ ፃድቃን በሌላ ንግግራቸው፡፡
ኢትዮ-ሶማሌ ክልል ውስጥ ምን ሆነ? ህወሃት ቀብቶ በህዝብ ላይ የጫነው፣አንድ ሚሊዮን ህዝብ ሲያፈናቅል ቅር የማይለው፣የራሱን ህዝብ እስር ቤት ከቶ መከራ የሚያሳይ፣ሃገር ያስመረረ አብዲ ኢሌ የሚባል ወንበዴ፤ የኢትዮ-ሱማሌ ህዝብ አዲስ አበባ ድረስ ተጉዞ አቤት በማለቱ ሳቢያ ከስልጣን እንዲነሳ ህጋዊ መንገድ እንዲጀመር ሲጠየቅ፤ አሻፈረኝ ብሎ ህዝብ አስጨረሰ፤ የእምነት ቦታዎችን በተላላኪዎቹ አወደመ፤ በስተመጨረሻው ተያዘ። ይሄ እንዴት ነው በትግራይ የሚደገመው? በማዕከላዊ መንግስቱ የሚፈለጉ የትግራይ ተወላጅ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ ባለስልጣናት፣ ትግራይ መሽገው የክልሉ መንግስት ደግሞ ለወንጀለኛ ከለላ የሰጠ እንደሆን ነው፡፡
ስለዚህ ይህ እንዳይሆን ማድረግ የሚችለው የትግራይ ህዝብና የክልሉ መንግስት ነው፡፡ ቀላሉ መንገድ ትግራይ የከተሙ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ የቀድሞ ባለስልጣናት የፍርድቤት ጥሪ አክብረው በህግ ፊት እንዲቀርቡ ማድረግ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ጥፋተኛ መሆን አለመሆናቸውን የሚመረምረው የወጡበት ጎሳ የቤተ-ዘመድ ጉባኤ አይደለምና ፃድቃን እንደሚሉት፤ የትግራይ ህዝብ “ተጠርጣሪዎቹ ካጠፉም እኔ ልቅጣቸው” የማለት መብት ፈፅሞ የለውም! ፍርድቤት ችሎት ላይ ተቀምጦ የጎሳውን ሰው የክስ መዝገብ የመረመረ ህዝብ፣ በዓለም ላይ ታይቶ ስለማይታወቅ፣ የማይመስል ነገር ነው፡፡
የትግራይ ተወላጅ የሆነ የቀድሞ ባለስልጣን፤ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ቀርቦ በመጠየቁ የሚጎድል የትግራይ ህዝብ ክብር የለም፡፡ እንዲህ መታሰቡ ራሱ ስህተት ነው፡፡ ‘እኛን ወደ ጎን ትቶ ለውጥ ማምጣት አይቻለም’ ማለትስ ምን ማለት ነው? የትኛው ህዝብ ሁሉ ተሰብስቦ ስልጣን ላይ እንደወጣ ነው የትግራይ ህዝብ ሁሉ ተሰብስቦ ወንበር ላይ የሚወጣው? ወይስ “የትግራይ ህዝብ አልተገለለም” እንዲባል፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘላለሙን በህወሃት ጊንጥ ሲገረፍ መኖር አለበት? ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት እኛን ያልጨመረ፣ ግልፅ ያልሆነ ነው ማለትስ ምንድን ነው ትርጉሙ? ሁለት ሃገሮች በሚያደርጉት ዲፕሎማሲያዊ ድርድር የትኛው ጎሳ ነው መሃላቸው ቁጭ ብሎ የድርድር አካል የሆነው?
የህወሃት ማኒፌስቶ ግልባጭ የሆነው ህገ-መንግስትም በትግራይ ህዝብ ዘንድ አለው ስለተባለው ትልቅ ቦታ እንዲህ ብለዋል ፃድቃን፤ “የትግራይ ህዝብ ታግሎ ያመጣውን ህገ-መንግስት እንደ ዋስትና ያየዋል። አንቀፅ 39ን እንደ ዋስትና ነው የሚመለከተው፡፡ ይህ ሲባል በኢትዮጵያዊነት ይደራደራል ማለት አይደለም። ራሱን ከኢትዮጵያዊነት ነው የሚያስተሳስረው። ኢትዮጵያዊነት ከደሙና ከአጥንቱ ጋር የተዋሃደ፣ ታሪኩም ነው፡፡ የመነጠል ፍላጎት ትግራይ ውስጥ የለም፡፡ ነገር ግን አንቀፁ ዋስትና ይሰጣል፣ መብትን ለማስከበር ይረዳል ብሎ ያምናል፡፡ የትግራይ ህዝብ፣ ህገ መንግስቱ ይከበር ሲል ከዚህ አንፃር ነው፡፡”
ህወሃት ጠላቴ የሚለውን የአማራ ህዝብ አግልሎ፣በአመዛኙ እንደ እሱው የአማራን ህዝብ በመጥላት በሽታ  የታወሩ የጎሳ ፖለቲከኞችን ሰብስቦ ያወጣው ህገ-መንግስት፤ ለትግራይ ህዝብ በስስት የሚታይ ክቡር ነገር ነው - እንደ ፃድቃን ገለፃ፡፡ ህወሃት በሌሎች ላይ ላይ ያልተገበረው ምናልባት ስልጣኑን ያጣ እለት ኤርትራ ፊት ከሰጠችው ትግራይን ገንጥሎ በሚወደው የገዥነት ስልጣን ላይ ለመቀመጥ ሲል ያስቀመጠው አንቀፅ 39፤ ለትግራይ ህዝብ ዋስትና መሆኑ እውነት ከሆነ፤ ስለ ትግራይ ህዝብ እና ህወሃት ልዩነት ፃድቃን ሲያወሩ የዋሉት ሁሉ ማሞ ቂሎ ብቻ የሚያምነው ተረት ነው የሚሆነው። ለማንኛውም የትግራይ ህዝብ የሚሰስትለት ያሉት ህገ-መንግስት፤ የአማራ ህዝብን እንደ ዘውግ ያገለለ፣ ከሁለት ዘውግ ለተወለዱ ኢትዮጵያዊያንና ራሳቸውን እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ብቻ የሚገልፁ ሰዎችን ያገለለ በመሆኑ፣ ሌላው ህዝብ ስፍስፍ ሊልለት እንደማይችል ሌላው ቢጠፋው፣ የፖለቲካ አዋቂ ነኝ የሚሉት ፃድቃን አይጠፋቸውምና ላልገባቸው ወገኖቻቸው ማስረዳት ይኖርባቸዋል፡፡
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡-  ፅሑፉ የፀሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ልንገልፅ እንወዳለን፡፡

Read 4446 times