Print this page
Monday, 27 August 2018 00:00

የሽግግሩ መርከብና ወጀቡ

Written by  በጫላ ቀነኒሳ
Rate this item
(1 Vote)

ሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪካዊ በሆነውና ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ በሽግግር መርከብ ውስጥ ትገኛለች፡፡ አብዛኞቻችን ሽግግሩ በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የሚከሰትና ጥቂት ነገሮችን የሚያሻሽሉ ተራማጅ ሀይሎች ወደ በትረ ስልጣን ከመምጣት ያለፈ ትርጉም እንደማይኖረው ገምተን ነበር፡፡ ከዚህ መረዳት የተነሳም ብዙዎች ‹መሰረታዊ ለውጥ›፣ ‹የሽግግር መንግስት› እና የመሳሰሉትን ሃሳቦች ሲያስተጋቡ ነበር። ተጨባጩን የሀገሪቱን ሁኔታ ካየን ግን ኢትዮጵያ የምሯን በሽግግር ላይ ነች። ከአምባገነንነት ወደ ዲሞክራሲ የምትወስደው መርከብ ልትሻገር ወይም ልትሰምጥ የባህር ጉዞዋን በወጀብ ጀምራለች፡፡ ጉዞው ከተጀመረ ወዲህ አያሌ ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ እውነቱና እቅጩው ይነገር ከተባለ፣ በኢትዮጵያ መንግስትም ተቀይሯል። ሥርዓትም በመለወጥ ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት አሸባሪ ሲባል የነበረው አክቲቪስት ጀዋር፣ ዛሬ የሰላም አምባሳደርና አስታራቂ ሆኖ ተከስቷል፡፡ ሀገርን ያፈርሳል ያልነውም ለመገንባት እንቅልፍ ሲያጣ ታዝበናል፡፡ አጥፊ የተባለውም ለወገኑ ተስፋ እንደሆነ አስመስክሯል፡፡ ሀገር ሸጠ ተብሎ የተወራበትም የለውጥ ደጀንና ሀገር ወዳድ እንደሆነ እያየን ነው፡፡ ጊዜ ለታጋዥ ደግ ነው፤ ሁሉንም ግልፅ አደረገልን፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብም ነጋችን ብሩህ ነው፤ ሀገር ትለማለች፤ ዲሞክራሲ ይመጣል፤ ነፃነት በእጃችን  ነው ብሎ አምኗል፡፡ በተስፋና በደስታ ፈንድቋል። በህዝባዊ ሰልፍም በሰልፊ ፎቶም ድጋፉን ገልጧል፡፡ ይህ በጣም አበረታች ነው። በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ አብዛኞቻችን ፊት ቆሞ ሊያወያየን የሚችል መሪ አግኝተናል፡፡ ፅንፈኛና የማይታረቁ አስተሳሰቦችን ተረድቶ፣ መፍትሔ ሊሰጥ የሚችል ብቃት ያለው ጠቅላይ ሚኒስትር ተከስቷል፡፡ ለህዝቡና ለወገኑ የሚራራ፣ የሚጨነቅና የሚያስብ መልካም አገልጋይ ተሰጥቶናል፡፡ ይህ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ከፈጣሪ ብቻ የሆነ ግሩም ፀጋ! ሰው ሁሉ ለዚህ እውቅና መስጠት አለበት፡፡ ለኢትዮጵያ ትንታጎች ድጋፍ አለማድረግ ይባስ ብሎም በተቃራኒው መቆም ኢ-ምክንያታዊነት ነው፡፡ ለሀገርም ለራስም ምቀኛ መሆን ነው፡፡ ለገዛ ልጆቻችንም  የሚበጃቸውን አለማወቅ ነው፡፡ በእኔነት የታወረ የጥላቻ ዳስ ነው!
ከአምባገነንነት ወደ ዲሞክራሲ የምታደርሰን መርከብ፣ አስተማማኝ መርከበኛ ብታገኝም፣ በተለያየ የአየር ፀባይ፣ የተጓዦች ሁኔታና ከባህሩ ልማድ የተነሳ በተደጋጋሚ ስትናወጥ ተመልክተናል፡፡ እንዲህ አይነቱ መንገጫገጭ በሽግግር ጊዜ የሚጠበቅ ቢሆንም ከመጠን ያለፈ ከሆነ ግን መርከቧን የማስመጥ ወይም አቅጣጫ የማሳት ዕድል ሊኖረው ይችላል፡፡ አውሎ ነፋሱ ወጀብን በመፍጠር ተጓዦቹን ተስፋ ሊያስቆርጥ፣ እንደ ጌታ ደቀ-መዛሙርት የአለቅን ጩኸት ሊሰማ ይችላል፡፡ የምንወዳቸውንና የምንሳሳላቸውን መሪዎችም ሊያዝል ይችላል። ስለዚህ ሁሉም ለራሱም ጥቅም፣ ለሀገሩም ሲል ወጀቡ እንዳይከሰት መከላከል፣ ካጋጠመም አደጋ ሳያደርስ መቆጣጠር ይገባዋል፡፡ እነዚህ የሽግግር ወቅት አውሎ ነፋሶች፡- ህገ-ወጥነት፣ ቡድንተኝነት፣ ዝርፍያ፣ የመከፋፈል ዝንባሌ፣ ግድያ፣ መንጋነት፣ አሸባሪነት ወዘተ ያጠቃልላል። እነዚህን የመርከባችንን ጠላቶች ለመዋጋት የተለያዩ ጠቃሚ  እርምጃዎችን መውሰድ ግድ ይለናል፡፡
አንደኛው፤ አክራሪ ብሔርተኝነትን ሰከን ማድረግና ለህዝባችን የሚበጀውን ቀና ብሔርተኝነትን መያዝ ነው፡፡ አክራሪ ብሔርተኝነት እውር ነው፤ የራሱን እንጂ የሌላውን አያይም። ቀና ብሔርተኝነት ግን በኔ ላይ እንዲደርስ የማልፈልገው ነገር ሌላው ላይም አይድረስ ይላል፡፡ አክራሪ ብሔርተኝነት ከወጣበት ወግና ባህል ውጭ የሌላውን ከቁብ አይቆጥርም። ቀና ብሔርተኛ ግን ህዝቤ አቃፊ ነው አቅፋለሁ፤ አባቶቼ ሌላውን የገዛ ቤተሰባቸው ያደርጋሉ እንጂ አያጠቁም፣ እኔም ያንን አደርጋለሁ ይላል። አክራሪ ብሔርተኝነት ለህዝቡ የምወስነው እኔ ነኝ ይላል፡፡ ቀና ብሔርተኛ ግን ህዝቡ የወደደውን ይወዳል፡፡ አክራሪ ብሔርተኛ፤ እኔ እኔ ሲያበዛ፣ ቀናው ግን እኛ እኛን ያስተጋባል፡፡ አክራሪ ብሔርተኛ፤ ጎረቤቶቼ ስጋቶቼ ናቸው ሲል፣ ቀናው ብሔርተኛ ግን ደህንነቶቼና አለኝታዎቼ ናቸው ይላል፡፡ አክራሪ ብሔርተኝነት በሴራ ሲመራ፣ ቀናው ግን በእውነትና ቅንነት ላይ ይተማመናል። ስለዚህ ለመርከባችን ደህንነት ብሔርተኞች ቀና ሁኑ፡፡ በቀና ብሔርተኝነት የመርከቡን መልህቅ እናጠንክር!
ተጓዦች መውሰድ ያለብን ሁለተኛው እርምጃ፤ በትናንሽ ነፋሶች ከመረበሽና ከመጨነቅ ይልቅ ከወከባና ጫጫታ በመታቀብ፣ ወደ የራሳችን ስራና ኑሮ መመለስ ነው፡፡ እስኪ መሪዎቻችን እንዲመሩን እድል እንስጣቸው፡፡ መረጋጋትና ወደ አቅላችን መመለስ ያስፈልገናል፡፡ ለጥቅመኞች ፕሮፓጋንዳና ለሴረኞች ወሬ ጆሮ ዳባ በማለት፣ ተማሪው ወደ ደብተሩ፣ መምህሩ ወደ ጠመኔው፣ ገበሬው ወደ ሞፈሩ፣ ሀኪሙም ወደ መርፌው በሙሉ ልብና መሰጠት መመለስ አለበት፡፡
ከዚህ ውጪ ደግሞ መሪዎቻችን ወጀብን ለመቀነስ ሰላም ማውረድ ካለባቸው አካላት ጋር በፍጥነት የመደመሩን ነገር ማድረስ አለባቸው። የህግ የበላይነትንም በቴሌቪዥን መስኮት ሳይሆን በገጠር በከተማው ለማረጋገጥ ቆፍጠን ይበሉ። የፀጥታ ሀይሉም ለህዝቡና ለህገ መንግስቱ በመወገን፣ ሙያዊ ብቃቱን ያሳይ፡፡ ሌላው ወጀብን ሊጋብዝ የሚችለውና በጥንቃቄ መያዝን የሚፈልገው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ  ነው፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ታረቅን ብሎ መግለጫ አብሮ በመስጠት ብቻ ረጅም መንገድ መሄድ አይቻልም፡፡ በትጥቅም ሆነ በሰላማዊ ትግል ላይ የነበሩ አባሎቻቸው በየቀበሌውና ወረዳው ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በኢህአዴግ የታችኛው ካድሬ ብዙ ግፍ የደረሰባቸው ይገኙበታል፡፡ አሁን ጊዜው በዳይና ተበዳይን በአንድ ላይ ሰብስቧቸዋል፡፡ ስለዚህም በየቦታውና በየቀበሌው አስቸኳይ የእርቅ ጉባኤ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፡፡
በአጠቃላይ ሀገራችን ስር ነቀል የፖለቲካ ሽግግር ውስጥ ትገኛለች፡፡ የሽግግሩ መርከብ ባህሩን ግማሽ መንገድ ገፍታበታለች፡፡ በሰላም ከተሻገረች ልማት፣ ነፃነትና ዲሞክራሲ ይጠብቀናል፡፡ ከሰጠመች ወይም አቅጣጫ ከሳተች ደግሞ የሁሉም ነገር ፍፃሜ ሊሆን ይችላል። ታሪካችንም በዚያ ቅፅበት ይታጠፋል፡፡ ይህ እንዳይሆንም እንዲሆንም ማድረግ የምንችለው እኛው ነን፡፡
ለሀገራችንም ለራሳችንም ስንል፣ ይቺ መርከብ በስኬት እንድትሻገር በሙሉ ልብ ማገዝ  አለብን። የሚነሱ አውሎ-ነፋሶችን፡- እነ ህገ-ወጥነት፣ ዘረኝነት፣ ዝርፍያ፣ ግድያ ወዘተ መከላከል ይኖርብናል። አክራሪ ብሔርተኝነት ሰከን ማለት አለበት። የታወቁ የሚያለያዩና ፀብ-ጫሪ አጀንዳዎችን ስንሻገር እንድንመክርባቸው ብናሳድራቸው የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ቀና በሆነው በአባቶቻችንን አብሮ የመኖር እሴት ላይ የሙጥኝ እንበል፡፡ መንግስት በዘመናዊ መልክ ህግን ያስከብር፣ እርቁን እስከ ታች በማውረድ ተግባራዊ ያድርግ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን በሀላፊነት ይምሩ፣ በቅርበት ይከታተሉ!
እንደ እኔ እምነት፣ በፈጣሪ ረድኤት ይሄን ወቅት በስኬት መሻገራችን አይቀሬ ነው! መርከቧ ግስጋሴዋን አላቆመችም፡፡ ጉዞ ወደ ዲሞክራሲ! የሰላም ሽግግር ያድርግልን! ቸር ያሰማን!
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡-  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 3238 times