Saturday, 25 August 2018 13:52

“ታዋቂ ያልሆነ ሰው” ታሪክም ይጻፋል፤ ይነበባል

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(5 votes)

 - ፕሬዚዳንት ቲቶ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በአሰብ በኩል ነው
  - እቴጌ መነን ሲሞቱ ወታደሩ ፂሙን እንዳይላጭ ታዞ ነበር
  - ኤርትራ ስትዋሃድ ሥራ አጥነት ይከሰታል የሚል ስጋት ነበር
          
     ‹‹ይህ (መጽሐፍ) ትኩረት ያደረገው በአንድ ታዋቂ ባልሆነ፣ ልዩ ታሪክ በሌለው ሰው የሕይወት ተሞክሮ ላይ ነው፡፡ አብዛኞቻችን ታሪክ ሲባል የሚገባን ነገር፣ በጦር ሜዳ ጀብዱ ስለፈፀሙ ሰዎች ወይም እጅግ ታላላቅ ሥራዎችን ስላከናወኑ ሰዎች ገድል ማውራት፣ መስማትና ማንበብ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ በዕውቀትም፣ በሥልጣንም እዚህ ግባ በማይባል ሁኔታ የሚኖሩ፣ ሕይወት ያስተማራቸው ብዙ ሰዎች አጠገባችን መኖራቸውን አናስተውልም፡፡›                                                                                  
ከላይ የቀረበው “ቅብብሎሽ” በሚል ርዕስ ከታተመው የህይወት ታሪክ መጽሐፍ መቅድም ላይ የተቀነጨበ ነው፡፡ የመጽሐፉ ዋጋ 40 ብር እንደሆነ በሽፋኑ ላይ ቢገለጽም  ለሽያጭ አልቀረበም፤የባለታሪኩ ቤተሰቦች፤ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው በነፃ ነው ያደሉት፡፡ ‹‹ቅብብሎሽ›› የተሰኘውን የአስር አለቃ ገብረሕይወት ተፈራን የሕይወት ታሪክ የሚያስቃኝ መጽሐፍ ያዘጋጁት ልጃቸው አቶ አበበ ገበረህይወት ተፈራ ናቸው፡፡ ጸሃፊው መረጃውን እንዴት እንዳጠናቀሩ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ እንዲህ ይገልጻሉ፡-
‹‹በመጽሐፉ የቀረበውን የሕይወት ታሪኩን ሲያጫውተኝ 94 ዓመቱ አካባቢ ነው፡፡ የታሪኩ ፍሰት፣ የማስታወስ ችሎታው እያስገረመኝ፣ በልጅነታችን በተደጋጋሚ የሰማነውን ታሪክ እንደገና ሥርዓት ባለው መልክ ጥያቄ፣ ማብራሪያ፣ መረጃና ማስረጃ እየጠየኩ እንደ አዲስ ሰማሁት፤ አሁን ደግሞ ጻፍኩት፡፡ ታሪኩን በተደጋጋሚ የነገረን ለእኛ ለልጆቹና ለልጅ ልጆቹ ነው። አሁን ደግሞ በዋነኛነት የተፃፈው ለቤተሰቡ አባላት ነው፡፡ በተደጋጋሚ የሰማነውንና በተግባር ያየነውን በጽሁፍ መልክ ለማኖር ነው፡፡ ሌላው ቁም ነገር ግን የአባታችንን ታሪክ በሕይወት እያለ መጻፉ፤ ታሪኩ በሕይወታችን ላይ ምን ያህል በጎ ተፅእኖ እንዳሳረፈ እንዲያውቀው ለማድረግ ነው፡፡››
‹‹ታዋቂ ያልሆነ›› እና ‹‹ልዩ ታሪክ የሌለው ሰው ነው›› የተባለላቸው ባለታሪክ፤ ከደብረ ዘይት ከተማ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ሸንኮራ አካባቢ ነው የተወለዱት፡፡ የ3 ዓመት ልጅ ሲሆኑ የወላጆቻቸው ትዳር ፈረሰ፡፡ እናታቸው ሌላ ትዳር ቢመሰርቱም ከወሊድ ጋር በተያያዘ ችግር ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ልጅ ገብረህይወት ከእናታቸው እናት ጋር መኖር ጀመሩ፡፡ አያትየው ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን በሞት በማጣታቸው ምክንያት፤ ደጋፊ ስላስፈለጋቸው ትዳር መመስረት ነበረባቸው፡፡ አዲሱ ባል ለልጅ ገብረሕይወት ከእረኝነት በላይ የማይመኙለት መሆኑን በተግባር አሳዩ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የ1928ቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ፤ የሸንኮራ አካባቢ ነዋሪዎችን ሕይወት አመሰቃቀለው፡፡ መገፋቱ በዝቶባቸው የነበረው ልጅ ገብረሕይወት በአካባቢው የተፈጠረው ማህበራዊ ቀውስም ተጨማሪ ምክንያት ሆኗቸው፤ ከትውልድ መንደራቸው በመሰደድ፣ ወደ ደብረ ዘይት ከተማ ሄዱ፡፡ የፋሽስት ጣሊያን ወረራን ተከትሎ፣ በዚያን ዘመን በደብረ ዘይትና አካባቢው በልጅነታቸው ያዩትን ባለታሪኩ ሲመሰክሩ ፡-
‹‹የጣሊያን ወረራ ተጀምሮ የአካባቢው ሰው ወደ ከሰም በረሃ መውረድ ጀምሯል፡፡ ጣሊያኖች መጀመሪያ ላይ ሸንኮራ ዮሐንስ (ባልጪ) አካባቢ ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት ለቅኝት በሚል የእኛን መንደር አልፈው ወደ ቅዳሜ ገበያ ሲሄዱ ያደፈጡ ሽፍቶች ሦስት የጣሊያን ወታደሮችንና ሌሎች ብዙ ጀሌዎችን ገደሉ፡፡ በሽፍቶቹ ድርጊት የተበሳጩት ጣሊያኖች ገበያው አካባቢ የጦር ካምፕ መሠረቱ፡፡ የጣሊያን ጦር ወደ አካባቢው የዘመተበት ዋናው ምክንያት ወደ ከሰም በረሃ ወርደዋል የተባሉትን ራስ አበበ አረጋይን ለመያዝ ነበር፡፡ ነገር ግን ራስ አበበ አረጋይን ለመያዝ አልተቻለም፡፡ የጣሊያን ጦር የኛን አካባቢ በወረረ ጊዜ ሕፃናት የሆነውን (እኔ በዚያን ጊዜ 12 ዓመቴ ነበር) ውሃ እንድናመላልስ ያደርጉ ነበር፡፡ ጣሊያኖቹ ወደ ቢሾፍቱ ሲመለሱ ውሃ ስናመላልስ የነበርነውንም ይዘውን ይሄዳሉ፡፡ ቢሾፍቱ እንደደረስን አዲስ አበባ ለመሄድ ሲንቀሳቀሱ እኔ አልሄድም ብዬ እዛው ቀረሁ፡፡››
በቢሾፍቱ የጣሊያኖች አስተርጓሚ በነበሩ ሰው ቤት የጉልበት ሥራ በመስራት አንድ ዓመት ያህል አገለገሉ። ጣሊያኖች በአቃቂ አካባቢ በጀመሩት አባ ሳሙኤል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ላይ ለመሳተፍ ሞክረዋል፡፡ ‹‹ድንጋይ የምናመላልሰው በሃዲድ ላይ በምትሄድ ጋሪ ነበር፡፡ አንድ ቀን ጋሪዋ ሃዲዱን ስታ ስትገለበጥ በስራ ላይ ከነበርነው የተወሰኑ ልጆች››  ስለሞቱ በሁኔታው የተደናገጡት ልጅ ገብረሕይወት ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ፡፡ እዚያ የመኪና ረዳት ሆነው ተቀጠሩ፡፡ ሥራና የኑሮ ዋስትና ማግኘትን ዓላማ አድርጎ በመቶ ኪሎ ሜትር የተጀመረው ስደት፤ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ድረስ አድጎ፤ እስከ ኤርትራ (አስመራ) ድረስ ዘለቀ፡፡
ኑሯቸውን ለማሸነፍ ባገኙት ሥራ ላይ ሁሉ መሰማራት ስለነበረባቸው፤ አስመራ እያሉ በቤት ሠራተኛነት፣ በኩሊ (የቀን ሠራተኛነት)፣ በእንጨት ፈላጭነት፣ በሽንኩርት ከታፊነትና ሳህን አጣቢነት፣ በሊስትሮነት፣ በዘበኛነት፣ በወጥ ቤት ሠራተኛነት … ሥራዎች ውስጥ አልፈዋል፡፡ ልጅ ገብረሕይወት ኤርትራ (አስመራ) በሄዱበት ወቅት ሀገሪቱ የምትመራው በጣሊያን ስለነበር ግልጽ የዘር መድሎ ይታይ ነበር፡፡ አንዱ ገጠመኛቸው እንዲህ ቀርቧል፡፡
‹‹አስመራ ከተማ ውስጥ ውሃ በመኪና ላይ በተጫነ ቦቴ የሚያከፋፍል አንድ ጣሊያናዊ ነበር፡፡ ስሙም ሲኞር ጆቫኒ ይባላል፡፡ እኔም የእሱ ረዳቱ ሆኜ እሰራ ነበር፡፡ አንድ ቀን በጠዋት ለስራ ከመሄዳችን በፊት ቁርስ አድርግ ብሎኝ ወደ አንድ ሆቴል ገባን፡፡ እኔን ‹ጓዳ ይግባ ጥቁር ስለሆነ፣ እዚህ ተቀምጦ መመገብ አይችልም› ተባልኩ፡፡ እኔም ጓዳ ቁጭ እንዳልኩ አንድ ዳቦና ሻይ በቲማቲም ቆርቆሮ ቀረበልኝ፡፡ የቆርቆሮ ጣሳው ስለሚያቃጥል ለመጠጣት አልቻልኩም፡፡ ሲኞር ጆቫኒም ‹ምንድን ነው፣ ለአንድ ብርጭቆ ሻይና ዳቦ እንደዚህ መቆየት? ይሄን ያህል በሬ አትበላ› እያለ ወደ ጓዳ መጣ፡፡ እኔም ‹ጣሳው ያቃጥላል› አልኩት፡፡ እሱም ‹ለምንድነው በብርጭቆ የማይሰጠው? ይኸው እነሱ በብርጭቆ አይደለም ወይ የሚጠጡት?› ብሎ ወደ ኤርትራውያን አስተናጋጆች አመለከተ፡፡ ባለቤቱም ‹እነሱ እዚህ ነው የሚሰሩት ስለዚህ የራሳቸው ብርጭቆ አላቸው፡፡ እነሱ በጠጡበት ማንም አይጠጣም› አለው። ሲኞር ጆቫኒም ‹በብርጭቆ ይሰጠው እኔ እከፍላለሁ› አለ፡፡ ሻይ በብርጭቆ ተሰጥቶኝ ከጨረስኩ በኋላ ዓይኔ እያየ ብርጭቆው ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ተጣለ… ››
ከዚያ በመቀጠል ምፅዋ ሄደው ለ6 ወራት ያህል በአናፂነት ሥራ ተሰማርተዋል፡፡ ጣሊያኖች፤ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያንን ሲኒማ ቤት እንዳይገቡ፣ አውቶቢስ እንዳይጠቀሙ፣ ከ3ኛ ክፍል በላይ እንዳይማሩ … በመከልከላቸውና በሌሎችም ምክንያቶች፤ ልጅ ገብረሕይወት ልባቸው ወደ አያታቸው ቤት መመለስን ስለፈለገ ወደ ትውልድ መንደራቸው መጡ፡፡ ሆኖም ሴት አያታቸውን ማግኘት ስላልቻሉ ተመልሰው ወደ ደብረ ዘይት፣ በመቀጠል ወደ ኤርትራ ሄዱ፡፡
ለመኖር በሚያደርጉት ጥረት የበርካታ ባለሙያዎች ባለቤት ለመሆን ችለው  ነበር፡፡ በሁለተኛው የኤርትራ ጉዟቸው የተለያዩ ሥራዎችን እየሰሩ፣ ቁጠባቸውን በማሳደግ መንጃ ፈቃድ የማውጣት እቅዳቸውን እውን አደረጉ፡፡ በሹፌርነት ሥራ ማግኘት ደግሞ የማይታሰብ ሆነ፡፡ የ‹‹ማኅበር ፍቅረ ሀገር ኢትዮጵያ›› አባል የሆኑት ከዚህ በኋላ ነበር፡፡ ‹‹…የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ (ማኅበር) አቋቁመን ነበር። ለመሰብሰቢያ የሚሆን ሻይ ቤትም ከፍተን ነበር። በተጨማሪም የእግር ኳስ ቡድንም ነበረን፡፡ የቡድኑም ስም የአማራ ኮከብ ወይም በጣሊያንኛ ‹እስቴላ አማራ› ይባል ነበር፡፡ እኔም የቡድኑ ምክትል አምበል ነበርኩ፡፡ የኤርትራ ተወላጆች እኛ ቡድን ውስጥ ነበሩ፡፡ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ኤርትራዊያን ነበሩ፡፡ አማራ የሆንን ቋሚ ተጫዋቾች አምስት ብንሆን ነው፡፡ አሰልጣኛችንም ኤርትራዊ ሲሆን በስራው መምህር ነበር፡፡››
የእንግሊዝ የሞግዚት አስተዳደር አብቅቶ፣ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ለማዋሀድ በነበረው ትግል ውስጥ፣ ውህደቱን የሚቃወሙ አካላት አንዱ ስጋት፣ ሥራ አጥነት ይከሰታል የሚል ነበር የሚሉት አስር አለቃ ገብረሕይወት ተፈራ፤ የስጋቱ አንዱ ሰለባ እርሳቸው መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ መንግስት ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል በማለት፤ ‹‹ከ30 ዓመት በታች የሆነና ጤናው ተመርምሮ ብቁ መሆኑ የተረጋገጠ ውትድርና ተቀጥሮ ወደ መሐል አገር መሄድ ይችላል›› ሲል ያወጣውን ማስታወቂያ ተከትሎ፣ በውትድርና መቀጠራቸውን ይገልጻሉ፡፡
ውትድርና ከተቀጠሩ በኋላ በመካኒክነት፣ በሹፌርነት፣ በስፖርተኛነት … አገልግለዋል፡፡ ኮንጎ ዘምተዋል፡፡ በ1956 በተካሄደው የኢትዮ ሶማሌ ጦርነት ተሳታፊ ነበሩ፡፡ እቴጌ መነን ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ‹‹ፂማችሁን አትላጩ›› ተብለው ሀዘናቸውን ጺማቸውን በማጎፈር ከገለጹ ግለሰቦች አንዱ እንደነበሩ ይገልጻሉ። የፕሬዚዳንት ቲቶና የንግስት ኤልሳቤጥ የኢትዮጵያ ጉብኝት ምን ይመስል እንደነበር ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ቲቶ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በአሰብ በኩል  እንደነበር፤ ንግስት ኤልሳቤጥ ወደ አዲስ አበባ በአውሮፕላን መጥተው፣ የመልስ ጉዟቸውን በአሰብ በኩል ማድረጋቸውን ይናገራሉ- ባለታሪኩ፡፡
ከውትድርና ከተሰናበቱ በኋላ በተለያየ የቅጥርና የግል ሥራዎች ውስጥ  የተሳተፉ ሲሆን በ1948 ዓ.ም ከመሰረቱት ትዳር በርካታ ልጆችንና የልጅ ልጆችን አፍርተዋል፡፡ አስር አለቃ ገብረሕይወት ተፈራ በመጨረሻ መልዕክታቸውም፤ ‹‹እኔ እናት፣ አባት፣ እህት፣ ወንድም የሌለኝ አንድ ምስኪን፣ እንደዚህ በዝቼ ተባዝቼ ራሴን ሳገኘው፣ ለኃያሉ አምላክ ወደር የሌለው ምስጋና አቀርባለሁ›› ይላሉ፡፡
“ቅብብሎሽ” የሚያስተምሩና የሚያዝናኑ ብቻ ሳይሆን ለጥናትና ምርምር አድራጊዎች የሚረዱ በርካታ መረጃዎችንም ይዟል፡፡ ይህን መጽሐፍ መነሻ በማድረግ አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፤ ለወዳጅና ቤተሰብ ለማሰራጨት ብቻ ታስበው፣ ምን ያህል መጻሕፍት በሀገራችን ታትመው ይሆን? የሆነ ሆኖ  ግን ለቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ ታስቦ የተዘጋጀው መጽሐፍ በሽያጭ ለአንባቢያን የሚደርስበት ሁኔታ ቢመቻች ጠቃሚ ነው የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ በ165 ገጾች ተቀንብቦ፣ በሚያዚያ ወር 2009 ዓ.ም የታተመው ይሄ መጽሐፍ፤ 56 ፎቶግራፎችንና የተለያዩ ሰነዶችን አካትቶ ይዟል፡፡

Read 1929 times