Saturday, 01 September 2018 15:09

የኤርትራ መንግሥት የተሰደዱ ዜጎቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳለህ ከጀርመን ድምፅ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ከሃገራቸው የተሰደዱ ኤርትራውያን ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፖለቲካዊ ምክንያትና በሌሎች ምክንያቶች ከሃገራቸው ተሰደው በመላው ዓለም ተበታትነው የሚገኙ ኤርትራውያን፤ ያለፈውን ነገር ረስተው ወደ ሃገራቸው በመመለስ፣ ህዝባቸውን እንዲያገለግሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።
ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የሚፈልጉ ዳያስፖራ ኤርትራውያን፤ በኤርትራ በነፃነት እንዲኖሩ ህጋዊ ዋስትና ያገኛሉ ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ዳያስፖራዎች ሃገራቸውን በኢኮኖሚው የመለወጥ አቅም አላቸው ብለዋል፡፡
የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግስት እርቅ ከፈፀሙ በኋላ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የኤርትራ መንግሥት፤ የተለያዩ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን እያደረገ ሲሆን በቅርቡም ሃገሪቱ የተፃፈ ህገ መንግስት ይኖራታል፣ የህገ መንግስቱ ረቂቅም እየተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ከኢትዮጵያና ከሌሎች ጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እቅድ ነድፋ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ኤርትሪያን ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ኤርትራ ኢኮኖሚዋን ለማነቃቃትም የኢትዮጵያን የፖታሽ ማዕድን ብቻ ወደ ውጪ የሚያስተላልፍ አዲስ ወደብ እንደምትገነባ ማስታወቋ የሚታወስ ሲሆን ይህ ወደብ ከምፅዋ እና ከአሰብ በተጨማሪ ለሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ ያስገኝላታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 3788 times