Print this page
Saturday, 01 September 2018 15:37

የኦሜዳድ የሩብ ክፍለ ዘመን ጉዞ ---

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  • ትውልድ የሚሻገር ኩባንያ የማቋቋም ህልምና ፈተናው ?
            • በአገራችን ላይ ትንሹን ዎልማርት ለመፍጠር በሂደት ላይ ነን

    ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በአምስት ጓደኛሞች የተቋቋመው ኦሜዳድ፤ የተመሰረተበትን የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል እያከበረ ይገኛል፡፡ ዛሬ በሂልተን ሆቴል በተዘጋጀ የእራት ግብዣ ላይም ድርጅቱን ለስኬት ያበቁ ትጉህ ሠራተኞቹንና ደንበኞቹን ይሸልማል፤ ያመሰግናል፡፡ ከኦሜዳድ ጋር ጥብቅ የቢዝነስ አጋርነት ያላቸው በርካታ የዓለም ታዋቂ ኩባንያዎች ባለቤቶችና ተወካዮች ከጣልያን፣ ኢንዶኔዥያ፣ ቻይና፣ ማሌዥያና ሌሎች አገራት በእራት ግብዣው ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ የፋይናንስ ባለሙያውና ከኦሜዳድ መሥራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ጌታ መሣይ ደገፉ፤ ኩባንያውን ሲያቋቁሙ አንድ ትልቅ ህልም ነበራቸው፤ ይኸውም 100 እና 200 ዓመት ዕድሜ የሚያስቆጥር፣ ከትውልድ ትውልድ የሚሻገር ስመ ጥር ኩባንያ መፍጠር የሚል  ነው፡፡ ይሄ ህልም የተሳካላቸው ይመስላል፡፡ ኦሜዳድ ይኸው 25 ዓመት ሞላው፡፡ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ማለት ነው፡፡ ስኬትና ተግዳሮቱስ? ከየት ተነስቶ የት ደረሰ? የቢዝነስ ዘርፉን ወዴት አሰፋ? ካፒታሉንስ ስንት አደረሰ? ለአገር ኢኮኖሚ ምን አበረከተ?
 የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ የኦሜዳድን 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ፣ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ከሆኑት አቶ ጌታ መሳይ ደገፉ ጋር በህይወታቸው፣ በሥራ ልምዳቸው፣ በቢዝነስ ተሞክሯቸው፣ በወደፊት ህልምና ራዕያቸው --- ዙሪያ አስተማሪና አነቃቂ  ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡


    እስኪ ስለ ትውልድዎና ትምህርትዎ  ይንገሩኝ…
እኔ ተወልጄ ያደግኩት ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ፣ ቦሎ ጊዮርጊስ በተሰኘች ትንሽ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ እስከ አራተኛ ክፍል ተምሬ፣ ከአንድ መምህሬ ጋር ክረምትን ለማሳለፍ ወደ አዲስ አበባ መጥቼ፣ ወደ ቤተሰቦቼ ሳልመለስ፣ አንድ ሁለት ዓመት በመድኃኒዓለም ት/ቤት ተማርኩ፡፡ ከዚያ ደግሞ ነቀምት ሄጄ፣ በዳግማዊ ኃ/ሥላሴ ት/ቤት ገብቼ፣ ከ7 እስከ 8ኛ ክፍል ለመማር ችያለሁ፡፡ እርግጥ የልጅነት ህልሜና ፍላጎቴ፣ ሀኪም መሆን ነበር፡፡ ፍላጎቱ ያደረብኝ በተወለድኩበት መንደር፤ ት/ቤታችንም ትንሿ ክሊኒክም ፍርድ ቤቱም አንድ ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ በዚያ የተነሳ በጤና ምክንያት ብዙ ወገን ሲቸገር እመለከት ስለነበር ነው፣ ሀኪም የመሆን ፍላጎት ያደረብኝ፡፡  
ታዲያ የልጅነት ህልምዎን እንዴት ሊቀይሩ ቻሉ?
ፍላጎቴን የቀየረው ጉዳይ የመጣው እንዴት መሰለሽ---ነቀምት ስምንተኛን እንደጨረስኩ ኮሜርስ እንድገባ ቅድሚያ ተሰጥቶኝ ነበር፤ እኔ ደግሞ ሀኪም መሆን ስለምፈልግ ኮሜርስ አልገባም አልኩ፡፡ አንድ መምህሬ ግን “ግዴለህም አንድ ሁለት ዓመት ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ነገር ኮሜርስ ስለሚያዘጋጅ በኋላ ይሄንን እድል አታገኝም” ሲለኝ፣ እሺ ብዬ በ1954 ዓ.ም ኮሜርስን ተቀላቀልኩ፡፡ በፋይናንስ የትምህርት ዘርፍ በ1957 ዓ.ም ተመረቅኩ፡፡ በዚያን ወቅት ገና ትምህርት ሳንጨርስ፣ ሶስት አራት ወር ሲቀረን፣ ድርጅቶች ተሻምተው ነበር የሚወስዱን፡፡ እኔም “ኤቤስ” የተባለ ኩባንያ ወሰደኝና እዚያ መስራት ጀመርኩኝ፡፡ ይህ ድርጅት በኋላ ጅንአድ የተካው ነው፡፡ በኩባንያው ውስጥ አንድ ዓመት ተኩል ከሰራሁ በኋላ “ፊሊፕስ ኢትዮጵያ” ገባሁ፡፡ እዚያ ለሰባት ዓመት ተኩል ሰራሁ፡፡ ከዚያም ኢቴልኮ ውስጥ በሥራ አስኪያጅነት ተቀጠርኩ፡፡ በመጨረሻም አማልጋሜትድ ኢትዮጵያ ገባሁ፤እ.ኤ.አ በ1974 ዓ.ም መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ድርጅት ውስጥ ለህይወቴ ሁሉ መሰረት የሆነ ስራ ሰርቼ ነው የወጣሁት፡፡ የፋይናንስ ስራ አስኪያጅና ተተኪ ዋና ስራ አስኪያጅ ነበርኩ፡፡ በኮሞዲቲ ንግድ፣ በሺፒንግ፣በትራንዚትና በመሳሰሉት ስራዎች በአሰብና በምፅዋ ከፍተኛ ስራ ይሰራ ነበር፤ አማልጋሜትድ፡፡ እኔም እ.ኤ.አ ከ1982 እስከ 1992 ዓ.ም በአማልጋሜትድ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ስሰራ ቆይቼ ወጣሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ከጓደኞቼ ጋር ኦሜዳድን የመሰረትኩት፡፡
ሃኪም የመሆን ህልሜም በዚያው ቀረ ማለት ነው። ነገር ግን ትምህርቴን በመቀጠል፣ ቀን ቀን እየሰራሁ፣ ማታ ማታ በመማር የኮሜርሱን ዲፕሎማዬን ወደ ዲግሪ አሳድጌዋለሁ-በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፡፡
ከአምስታችሁ ጓደኛማቾች “የራሳችንን ድርጅት እናቋቁም” የምትለዋን የመጀመሪያዋን ሃሳብ ያፈለቀው ማን ነበር?
ይህንን ሀሳብ መጀመሪያ ያነሳው የቦርዳችን ሰብሳቢ አቶ ኩመላ ግራኝ ነው፡፡ በት/ቤትም የኛ ሲኒየር ነው፤ ሁለት ዓመት ከእኔ ይቀድማል፡፡ ግን ግቢ ውስጥ አብረን ተምረናል፡፡ ፊሊፕስ ኢትዮጵያም በፋይናንስ ክፍል ውስጥ አብረን ሰርተናል፡፡ ከዚያ እሱ ውጭ አገር ስራ አግኝቶ ሄዶ ሲመለስ ኢትሆፍ ተቀጥሮ ገባ። እዚያ አንዱ መስራች የሆነውን አቶ ለገሰ ይርጋን አገኘ። የቴክኒክ ባለሙያውን አቶ ክንፈሚካኤልንም አገኘ፡፡ እኔ ደግሞ የግል ንግድ ድርጅቶችን የመምራት ልምድ ስለነበረኝ ጠርቶ አማከረኝ፡፡ እኔ በወቅቱ የራሴን ድርጅት ለመክፈት እቃ ገዝቼ፣ቤት ብቻ ነበር የሚያስፈልገኝ፡፡ ይህን ሀሳብ ሲያካፍለኝ፤ “ጥሩ ነው ብቻ ከመሮጥ በጋራ መሮጥ ይሻላል፤ ይህን ለማድረግ ግን ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች ላይ መስማማት አለብን” አልኩኝ፡፡
ቅድመ ሁኔታዎቹ ምን ምን ነበሩ?
አንደኛው፤ በጠንካራ መሰረት ላይ ያረፈ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ስራ መስራት እንድንችል የሚል ነው፡፡ እኔ አማልጋሜትድ ኢትዮጵያ ስሰራ ያልዞርኩበት የዓለም ክፍል አልነበረም፡፡ በጣም በጣም ይቆጨኝ የነበረው ታዲያ እንደ ሌላው አለም፣ “ይሄ 200 ዓመቱ ነው፤ ይሄ 150 እና 100 ዓመቱ ነው” የሚባል ከትውልድ ትውልድ የተላለፈ የንግድ ድርጅት አለመኖሩ ነበር፡፡ እኛ እንሰራበት የነበረው ፊሊፕስ ኢትዮጵያም ረጅም እድሜ የነበረውና እኛ ስንሰራ የሚመሩት የመስራቾቹ ሦስተኛ ትውልዶች ነበሩ፡፡ እኔም ይህ አይነት ሀሳብ ስለነበረኝ ይህን እንደ ቅድመ ሁኔታ አቅርቤ ነበር። ሁለተኛው፤ ሁላችንም በእኩል ድርሻ መመስረት ከቻልንና እኩል ጥቅም እኩል ጉዳት መካፈል የምንችልበት አካሄድ ከተቀበላችሁ ይሁን፣ካልሆነ ሁልጊዜ ላለመስማማት ምክንያት ይሆናል፤በዚህ ካልተስማማን ይቅርብኝ አልኩ፡፡ ነገር ግን ተስማማንና ተጀመረ፡፡
ለኦሜዳድ የመጀመሪያዎቹ ተቀጣሪዎች መሥራቾቹ ነበራችሁ፡፡ እርስዎ ምን የስራ ድርሻ ላይ ነበር የተመደቡት?
እኔ የፋይናንስ ባለሙያ ብሆንም፣ በኦሜዳድ የተቀጠርኩት ግን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሆኜ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት በንግድ አስተዳደር ለረጅም ጊዜ ስለሰራሁ ነው፡፡ ኦሜዳድን ጨምሮ ለ53 ዓመታት ስሰራ የቆየሁት በግል ድርጅቶች ውስጥ ነው፡፡ አንድም ቀን መንግስት ቤት ተቀጥሬ አልሰራሁም፡፡ ለዚህ ነው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አድርገው የሾሙኝ፡፡ አቶ ለገሰም ከሞዝቮልድ ጀምሮ የንግድ ስራ ሲያካሂድ የነበረ በመሆኑ በንግድ ዳይሬክተርነት ተሾመ፡፡ አቶ ክንፈሚካኤል ደግሞ የቴክኒክ ዳይሬክተር ሆነ፡፡ አቶ አባተን አስገባንና ስራውን ተሰባስበን ጀመርን፡፡  
ሥራውን  የጀመራችሁት በወቅቱ ብቸኛ ከነበረው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1 ሚ. ብር ተበድራችሁ ነው፡፡ ብድሩን ለማግኘት ደግሞ ወደ 10 ሚ. ብር የሚያወጡ ንብረቶችን በመያዣነት ማቅረብ ነበረባችሁ፡፡ ይሄን ፈተና እንዴት አለፋችሁት?
ይሄንን ተግዳሮት መቼም አንረሳውም፡፡ እኛ ከራሳችን 1 ሚ. ብር አዋጣንና ንግድ ባንክ ደግሞ 1 ሚ. ብር ፈቀደልን፡፡ ያንን ብር ለማበደር ግን የ10 ሚ. ብር ንብረት ነው የያዘው፡፡ በዚያች 1 ሚ. ብር የፈለግነውን ያህል መሮጥ አልቻልንም፤ ገበያው የተራበ ነው፤ በውስጡ እቃም የለም፡፡ እኛ ሥራውን ስንጀምር ጠረጴዛ፣ ታይፕራይተርና ካልኩሌተር የሚያቀርብ ድርጅት አልነበረም፡፡ ታዲያ ይህንን የተራበ ገበያ ለማርካት ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቅ ነበር፤ እኛ ግን በአጥጋቢ መልኩ ማግኘት አልቻልንም፡፡
ከዚያስ  ምን መላ ዘየዳችሁ?
የግል ባንክ ቢኖር ብዙ ሰርተን ብዙ መለወጥ እንችል እንደነበር ስለማውቅ፣የኢንሹራንስ ገበያው ለግል ድርጅቶች ሲፈቀድ፣ መጀመሪያ ህብረት ኢንሹራንስ አቋቋምን፡፡ ከዚያ ደግሞ በባንክ ደረጃ ቀድሞ የመጣው አዋሽ ባንክ ነበር፡፡ አዋሽንም አብረን አቋቋምን፤ቀጥሎ ህብረት ባንክን መሰረትን፡፡ እርግጥ ከህብረት ባንክ በፊት አቢሲኒያ ባንክን አቋቁመን፣ ሁሉን ከጨረስን በኋላ ጥለን ወጣን፡፡
በምን ምክንያት ጥላችሁ ወጣችሁ?
ትልልቅ ጡንቻ ያላቸው ሀብታሞች መጡና አንድ ጊዜ ወደ ግራ፣ አንድ ጊዜ ወደ ቀኝ ዙሩ ሲሉን፣ አይ ይሄ ነገር ለወደፊት የሚያዛልቅ አይደለም፤አቅማችንን እንወቅ አልንና እያንዳንዳችን ትንንሽ ገንዘብ እያዋጣን በ17 ሚ. ብር ነው ህብረት ባንክን ያቋቋምነው፡፡ ኦሜዳድ በህብረት ባንክ ባለድርሻ ነው፤ እኔ በግሌም ባለድርሻ ነኝ፡፡ አብዛኞቹ መሥራቾችም ባለድርሻ ናቸው፡፡ የአዋሽ ባንክም ባለድርሻ ነን፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከ95 በመቶ በላይ ብድርና ለሌሎች ስራ ማስኬጃዎች ገንዘብ የምንወስደው ከመሰረትናቸውና ከሌሎች የግል ባንኮች ነው፡፡ ኦሜዳድ በበሳልና እውቀት ባላቸው አመራሮች ስለሚመራ የትኛውም ባንክ ሄደን ብድር ብንጠይቅ የሚከለክለን የለም፡፡ ስራችን ግልጽ ነው፤ እድሜያችንም አንጋፋ ነው፡፡
ወደ ገበያው ስትመጡ መጀመሪያ ግባችሁ ከውጭ አገር እቃዎችን አምጥቶ መሸጥ ነበር፡፡ መጀመሪያ ላይ ወደዚህ አገር አምጥታችሁ የምትሸጧቸው እቃዎች ምን እንደነበሩ ሊነግሩን ይችላሉ?
እውነት ነው፤ አጀማመራችን የሚገርም ነው፡፡ በዚያን ጊዜም የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ትልቅ ፈተና ነበር፡፡ ኦሎምፒያ ኢንተርናሽናል የሚባል የመርሴዲስ ቤንዝ እህት ኩባንያ አለ፡፡ የቢሮ መሣሪያዎችን የሚሸጥ ነው፡፡ ካልኩሌተር፣ ታይፕራይተር፣ ፎቶኮፒ ማሽን፣ ፋክስና ሌሎችንም ይሸጣል፡፡ የዚህ ድርጅት እቃዎች ቀደም ሲል በኢትሆፍ የሚከፋፈል ነበር፤ከአምስታችን የኦሜዳድ መስራቾች ሦስቱ ደግሞ በኢትሆፍ ይሰሩ ስለነበርና ትውውቁ ስለተፈጠረ፣የዚህን ድርጅት ውክልና ለመውሰድ ከሚወዳደሩ በርካታ ድርጅቶች መካከል አንዱ ለመሆን ቻልን፡፡  የዚህ ድርጅት ብቸኛ ወኪል አከፋፋይነቱንም አገኘን፡፡ በዚያን ጊዜ እነሱም አቅም ስላላቸው፣ “ፍራንኮ ቫሉታ” የሚባል አሰራር ነበር፤ገንዘብ ሳይከፈል እቃ ይሰጡሻል፡፡ አንቺ ሸጠሽ ነው ገንዘቡን የምትከፍይው፡፡ በዚህ አሰራር የ25 ሺህ ዶላር እቃ በፍራንኮ ቫሉታ ሰጡን፤ ያንን እቃ ሸጠን አቅም የሚያጠነክር ስራ ሰራን፡፡ ከነሱ በኋላ ደግሞ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች የመጡ ሲሆን ዘላቂ ወደ ሆነ ቴክኖሎጂ መሸጋገር ነበረብን፡፡ በአሁኑ ወቅት 10 የሚደርሱ በጣም ጠንካራና መልቲ ሚሊየነር አለም አቀፍ ድርጅቶች ከእኛ ጋር ይሰራሉ፡፡ ከነዚህ መካከል ዛሬ ነሐሴ 26 በሂልተን ሆቴል በምናካሂደው ትልቅ ዝግጅትና “ጋላ ዲነር” ግብዣ ላይ ሰባት ያህሉ ይገኛሉ። ለምሳሌ “ሪሶ ኢንተርናሽናል” የተባለው ዲጂታል ፕሪንተርስ፤ በርካታ ከለር የሚያትሙ መፅሐፍ አትሞ ቆርጦ ጠርዞ የሚሰጥ ማሽን ነው፡፡ “ሪኮ” የተባለውም ይመጣል፡፡ የተለያዩ የካተሪንግ እቃዎችን ለሆቴሎች የሚያመርቱ የጣልያን ኩባንያ ኃላፊዎችም ይገኛሉ፡፡ ፈርኒቸር አቅራቢዎቻችን ከማሌዢያ፣ ከቻይናና ከቱርክ ይመጣሉ፡፡ ብዙዎቹ ይገኛሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡
በኤሌክትሮኒክስ ደረጃም ፓናሶኒክ የተባለው የታዋቂው ኩባንያም ብቸኛ ወኪል ነን፡፡
አሁን ወደ ሌሎች የሥራ ዘርፎችም መግባታችሁን፣ አዳዲስ ዕቅዶች እንዳላችሁም ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ስለዚህ ጥቂት ያብራሩልኝ?
ትክክል ነው፤የመጀመሪያ ስራችንን በሁለት እግሩ ካቆምንና አስተማማኝ ካደረግን በኋላ ወደ ሌሎች ዘርፎች ገብተናል፡፡ እኛ የአሜሪካኑን ትልቁን ዎልማርት ባያክልም፣ በአቅማችን አገራችን ላይ ትንሹን ዎልማርት እንፈጥራለን የሚል ሀሳብ ነበረን፡፡ አሁን ትንሹን ዎልማርት ለመፍጠር በሂደት ላይ ነን፡፡ ሰባት ወለል ያለው ትልቅ ህንፃ ከገነባን በኋላ ከሱፐር ማርኬት ጀምሮ ሁሉንም ነገር ሰዎች የሚያገኙበት የገበያ ማዕከል እንፈጥራለን፡፡ ሁሉን በአንድ ቦታ የግብይት ስርዓት ይኖረዋል፡፡ ደብረዘይት መንገድ ላይ አመቺ የሆነ ቦታ አለን፤ህንፃው በቅርቡ ይጀመራል፡፡ ፈርኒቸርና ሌሎችንም እቃዎች ለመገጣጠም የሚያገለግል ፋብሪካ ደብረዘይት ላይ ለመክፈት በእቅድ ላይ ነን፡፡ ፋብሪካው ሲከፈት ኦሜዳድ አሁን ካለው አቅም እጥፍ እንዲኖረው ያስችላል፡፡
በሆቴሉም ዘርፍ ተሰማርተን ባለ አራት ኮከብ ደረጃ የሚመጥንና 12 ወለል ያለው ሆቴል፣ ኦሎምፒያ አካባቢ ተገንብቶ ወደ መጠናቀቁ ነው፡፡ አሁን ባለበት ደረጃ እንኳን በቀላሉ 1 መቶ ሚ. ብር ወጥቶበታል፤ ገና ማስፋፊያ አለው፤ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ ነው። ሸዋ ዳቦ ፊት ለፊት፣ በጣም አማካይና አመቺ ቦታ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ስያሜው “ኦሜዳድ ኢንተርናሽናል ሆቴል” ይሆናል ብለናል፡፡
ወደ ሪል እስቴት ዘርፍ የመግባት ዕቅድም ያላችሁ ይመስለኛል?
አዎ እቅድ አለን፤ የስብሰባ ማዕከልና አፓርትመንቶችን ለመገንባት አቅደናል፡፡ ለዚህም የሚሆን ሰፋ ያለ ቦታ አለን፡፡
ኦሜዳድ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ያለው አስተዋጽኦ እንዴት ይገለፃል?
አሁን ብዙ ነገሮች በሚሊዮን መገለፃቸው ቀርቶ በቢሊዮን እየሆኑ ነው፡፡ ገንዘቡ ይቅርና እኛ አገልግሎቱን በሚፈለገው ጥራትና ቦታ ላይ ማቅረብ መቻላችን ትልቅ ነገር ነው፡፡ እከሌ ከእከሌ ሳንል ለሁሉም ነው አገልግሎት መስጠት የጀመርነው፡፡ እኛ የመጀመሪያውን ቅርንጫፍ መቀሌ ላይ ስንከፍት በደርግ ጊዜ በነበረው ጦርነት አካባቢው ተራቁቶ ምንም አልነበረም፡፡ ሰዎች አብዳችኋል ብለውን  ነበር፡፡ ነገር ግን አገልግሎት መስጠት ያለብን እንዲህ ልማት በሌለበት ቦታ ነው ብለን ነው የጀመርነው። አሁን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ከ25 በላይ ቅርንጫፎችን ከፍተን፣ ከ620 በላይ ሰራተኞችን ቀጥረን፣ አቅማቸውን በትምህርት ገንብተን ብዙ ስራዎችን ላለፉት 25 ዓመታት ሰርተናል። ይሄ ለአገር ኢኮኖሚ ያበረከተው አስተዋፅኦ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡፡
መሥራቾቹ ኩባንያውን ለ22 ዓመታት ከመራችሁ በኋላ ባለፉት 3 ዓመታት ስራውን ለሁለተኛው ትውልድ አንዳስተላለፋችሁ ይነገራል፡፡ ሁለተኛው ትውልድ ስራውን በብቃት እየተወጣ ነው ትላላችሁ?
በትክክል! ብዙ ለውጥና ፍጥነት ያለው ስራ እየሰሩና ውጤት እያስመዘገቡ ነው፡፡ ምክንያቱም ከ10 ዓመት በፊት ነው ለስራው ያዘጋጀናቸው፡፡ ሁለተኛው ትውልድ ስልሽ፣ ስራው ለእኛ ልጆች ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ እዚሁ እየሰሩ ራሳቸውን በትምህርት ያበቁና ችሎታ ያላቸው ሰራተኞችንም ማለቴ ነው፡፡ እኛን ከተኩን ወጣት አመራሮች፣ ሶስቱ ብቻ ናቸው የአመራር ልጆች፡፡ ሌሎቹ በችሎታቸው በትጋታቸው የተመረጡ፣ ሰራተኛው እነ እከሌ ይምሩን ብሎ ድምፁን የሰጣቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህን ድርጅት ከዚህ በላይ ለማሳደግ ወጣቶቹ እንደኛ 22 ዓመት አይፈጅባቸውም። እኛ ድርጅት ውስጥ ዘር ሃይማኖት የሚባል ነገር የለም፡፡ ሁሉም ከእኛ ጋር የቆዩ ቤተሰቦቻችን ናቸው፡፡ እኛም በህይወት እያለን ተተኪዎቻችን በዚህ ብቃት ሲሰሩ ከማየት የበለጠ የሚያስደስተን ነገር የለም፡፡ አሁን እኛ እድሜያችን እስከፈቀደ ከጀርባ ሆነን ማገዝ መደገፍ ነው የሚጠበቅብን፡፡
የሚጨምሩት ሀሳብ ካለ?
ብዙ ተጨዋውተናል፡፡ 25ኛ ዓመታችንን በጥሩ ሁኔታ እያከበርን ነው፡፡ ለ45 ቀናት ከብሄራዊ ሎተሪ እውቅና ያለው ሎተሪ ሸጠን ባለዕድሎችን ሸልመናል፡፡ በቅዳሜው ትልቅ በዓል ሰራተኞቻችንንና ደንበኞቻችንን እናመሰግናለን፡፡ አሁን የምናየው የአገር መረጋጋት ወደፊት በሁሉም መስክ የመሮጫ ሜዳውን የተስተካከለና እኩል ያደርገዋል የሚል ተስፋ አለን፡፡ እኛ ያለፍነው ፈተና ለቀጣዩ ትውልድ ይደርሳል ብለን አናምንም፡፡ ያለፈው አልፏል፤ ከዚህ በኋላ አገርን አንድ በሚያደርግ ጉዳይ እንጂ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በብሔር የሚደረግ ማንኛውም ነገር እንዲቀር የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች ወጣቱ ላይ ከሰሩ አገር ትለወጣለች፡፡ ህዝብ እኩልና ደስተኛ ይሆናል፤ ግን ሁሉም  ኃላፊነቱን እንዲወጣ አደራ እላለሁ፡፡    

Read 2570 times