Saturday, 01 September 2018 15:40

መተቸት ደግ ነው ግን ቢያንስ መጽሐፉን አንብበው ይጨርሱ!

Written by  ከእሳቱ ሰ.
Rate this item
(2 votes)

(ደረጀ በላይነህ “የዶክተር ዐቢይን ህዝባዊ መሰረት የካደ መጽሐፍ” በሚል ርዕስ ለጻፉት ችኩል ትችት የተሰጠ ትሁት አጸፋ)
            
    በጋዜጣ ትችት ታሪካችን እንደ ጊንጥ መነዳደፍን የምንኩራራበት ጋዜጣዊ ባህል ካደረግን ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ የዚህ ልማድ  መነሻው የስልሳዎቹ ማርክሲስቶች የትቸት ባህል ሳይሆን አይቀርም። በዚያን ዘመን አለመከባበር ስላቅና ነቀፋ አድናቆትን ያስገኝ ነበር፡፡  እነሆ ትውልድ ተሻግሮ ይህ ሃሳብን ሳይሆን ባለ ሃሳቡን የመናደፍ ባህል ለልጅ ልጆቻችን እየተረፈ ነው፡፡ በእውቀትና በመረጃ በተደገፈ ክርክርና ውይይት ወደ ብርሃን ለመውጣት የሚደረግ የመከባበር አንድምታና ሃተታ ሳይሆን አንዱን ነቅፎና ዝቅ አድርጎ፣ ባናቱ ላይ ተንጠላጥሎ ራስን ማሳየትን ኢትዮጵያዊ የትችት ባህል እያደረግነው መሆኑ እነሆ ባገራችን ውይይትና ምርምርን ገድሎና ተክቶ፣ እርስ በእርስ  መነጋገር ከማንችልበት ደረጃ አደረሰን፡፡ በዚህ አስተያየቴ ላይ በተቻለኝ አቅም ከዚህ ነውር ራሴን ለመጠበቅ እሞክራለሁ፡፡ ምክንያቱም የምፈልገው አቶ ደረጀ ራሳቸው እንዲሰሙኝ አንጂ እርሳቸውን በሌሎች ፊት ለዳኝነት ለማቅረብ አይደለም፡፡
ይህን ያልኩበት ምክንያት  ሃያሲው ከላይ ባስቀመጥኩት ርዕስ አርኪቴክት ሚካኤል ሺፈራው “የማስጠንቀቂያ ደወል” በሚል ርእስ በቅርቡ ያሳተሙትን መጽሐፍ ለመተቸት የጻፉትን፣ ደራሲውን፣ ዶክተር ዐቢይን ለሚወድደውና ለሚያከብረው ህዝብ ለማሳጣትና በጭፍንና በድፍረት ለመወንጀል ያለመ የሚመስል ጽሁፍ ሳነብብ በተፈጠረብኝ ስሜት ምክንያት ነው፡፡ ሃሳቤን በስሜት በመጀመሬ አስቀድሜ አቶ ደረጀን ይቅርታ ልጠይቅ፡፡ በኔ በኩል ይህን ስጽፍ አስቀድሜ መጽሃፉን ሙሉ በሙሉ አንብቤ ብቻ ሳይሆን ደረጀ በላይነህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን በወጡ ሰሞን “ትንታጎቹ” በሚል ርዕስ የጻፉትን መጽሐፋቸውን አንብቤና አቅሜ በፈቀደልኝ መጠን  አነጻጽሬ ጭምር ነው፡፡ የደረጀ በላይነህን “ትንታጎቹ”ን በሚመለከት አገራችን በቸር ውላ ትደር፣ እድሜ ይስጠንና ለወደፊት በሌላ ትሁት ትችት ልመለስበት እሞክራለሁ፡፡
ነገር ግን እንዲያው እግረ መንገዴን ለማመልከት ያህል ያን ሰሞን ዶክተር ዐቢይን ከፍ ከፍ በማድረግና በማክበር ህወሃትና የለውጡን ተቃዋሚዎች በማውገዝና በመርገም የተጻፉት መጻሕፍት ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኛዎቹ ከዚህ በታች የሚመለከቱት ባህሪይ ይታዩባቸዋል፡፡
አንደኛ አብዛኞቹ በወቅቱ በህዝብ ዘንድ በህወሃት ላይ ታምቆ ቆይቶ በዴሞክራሲው መድረክ መከፈት ምክንያት የፈነዳውን መራር ጥላቻና የዶክተር ዐቢይን ህዝባዊ ድጋፍ በትኩሱ ወደ ገበያ ለመለወጥ በተጣደፉ “ኦፓርቹኒስት” የፖለቲካ ነጋዴዎች፣ ገበያው ሳያልፍ ተጠብሰው ገና ሳይበስሉ  የቀረቡ ትኩስ ፓስቲዎች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ የነዚህ መጻህፍት ደራሲያን አስቀድሞ በፖለቲካው አለም በትችትም ይሁን በአክቲቪስትነት እጅግም የማይታወቁ  በድንገት የተፈጠሩ  አየር ወለድ የፖለቲካ ተንታኞች ናቸው፡፡
ደረጀ በላይነህ በአርኪቴክት ሚካኤል ሺፈራው መጽሐፍ ላይ የጻፈውን ትችት በሚመለከት ያለኝን ሃሳብ ለማካፈል ከርዕሱ ልጀምር፡፡
ርዕሱ በትልልቅ ፊደሎች የተጻፈ  ነው - “የዶክተር ዐቢይን ህዝባዊ መሰረት የካደ መጽሃፍ!” ይላል። ከስሩ ደግሞ ከርዕሱ አነስ ባለ ግን ግዙፍ ፊደል የሚካኤል ብዥታ ይላል፡፡ ርዕሱ እነሆላችሁ የዶክተር ዐቢይ ተቃዋሚ፣ ስሙም እገሌ ይባላል ለማለት ታስቦ የተጻፈ ይመስላል፡፡ እርስዎ ሲጽፉት ይህን አስበው ላይሆን ይችላል፡፡ ለኔ ያስተላለፈልኝ መልዕክት ግን እንዲህ ያለውን ነው። የማሪያም ጠላት እንደማለት፡፡ በተለይም በስሜት ውስጥ ላሉ ወጣቶች ያስተላለፉት መልዕክት፣ መጽሐፉን አንብበው የራሳቸውን ሚዛናዊ ብያኔ እንዲወስዱ ሳይሆን፣ የዶክተር ዐቢይ ተቃዋሚ ነውና  እንዳታነብቡት የሚል ነው፡፡ ዝቅ ይሉና ደግሞ ደራሲውን እንደሚያውቁት በሚዛናዊነቱ በብስለቱና በመረጃ ተደግፎ የሚጽፍና የሚናገር መሆኑን እንደሚያውቁ ይመሰክራሉ፡፡ ተቃውሞ ሲቀርብበት እንኳን ከቁጣና ከመከላከል ይልቅ በእርጋታና በምክንያታዊነት ሃሳቡን እንደሚገልጽ ይጠቅሳሉ፡፡ ሃሳቡን ተቃውሜ አይቼዋለሁ፤ለምን ተቃወምክ የሚል ምልክት እንኳን አላሳየኝም ይላሉ፡፡  
“በዚህ መጽሃፍ ግን የታደሰውን ሳይሆን ነባሩንና ያረጀውን የወደቀውን ኢህአዴግ እንዲያውም ህወሃትን ቅዱስ ለማድረግ የሚሞክር ያፈጠጠ ፍቅር ስለሚታይበት ይህን ፍቅር ለህዝብ ለማሳየት መሞከሩ ስንፍና እንደሚመስልም ለማሳሰብ እፈልጋለሁ።” ይልና ይህን ፍቀር ለማሳየት መሞከራቸው የህዝብ ህመም የማይሰማቸውና ባይተዋር ያደርጋቸዋል ይላል። ይልቁንም ያረጀውንና በመሞት ላይ ያለውን ህወሃት  ለመጠበቅ ጉበኛ ሆኖ መቆሙን በድፍረት ይመሰክራሉ፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚጠቅሱት የኢህአዴግና የህወሃት መሪዎች ትግሉን ሲጀምሩት ብሄር ተኮሩን ፌዴራሊዝም ያመጡት  አገራቸውን እርስ በእርስ ከፋፍለው ለመግዛት ነው ብሎ መፍረድ ፍትሃዊ አይመስለኝም የሚለውን ሃሳብ ነው፡፡ አቶ ደረጀ ይሄን ሃሳብ ሲጠቅሱ ለወቀሳ እንዲያመቻቸው፣ ከደራሲው መጽሐፍ ከተጻፈበት አውድ ነጥለውና ቀንጭበው በመንቀስ ነው፡፡ ለዚሁ እንዲያመቻቸው ከፍና  ዝቅ ብለው  የተገለጹትን ሃረጎች ሆን  ብለው ይገድፏቸዋል።  እርሳቸው ከጠቀሷት ሃረግ በላይ ያለችው ሃረግ አንዲህ ትላለች፡-
ከሁሉ በፊት ዛሬ ለደረስንበት ውስብስብ የታሪክ ምዕራፍና የተካረሩ የጎሳና የብሄር ግጭቶች ህወሃትና ኢህአዴግ ሃላፊነቱን መውሰድ እንዳለባቸው ብንረዳም ይልና “የህወሃትና የኢህአዴግ አመራሮች ብሄር አቀፉን ፌዴራላዊ ሥርዓት የተከተሉት ሆን ብለው አገራቸውን ከፋፍለው ለማባላትና ለመግዛት ሲሉ ነው የሚለው አስተሳሰብ ግን ፍትሃዊነት የጎደለው አመለካከት ይመስለኛል፡፡…” ይላል፡፡ ከዚሁ ዝቅ ብሎም የሚከተለውን ሃረግ ገድፈዋል። ምክንያቱም ሃያ አመት ሳይሞሉ ወደ በረሃ የወጡ ወጣቶች ከአመታት በኋላ ቤተ መንግስት ገብተን ይህን ህዝብ በብሄርና በጎሳ ከፋፍለን አንገዛለን ብለው ያስቡ ነበር ብሎ ማሰብ ታላቅ ስህተት ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ብሎ ማሰብ ስህተት የሚሆነው ሆን ብሎ ሊከፋፍል የተነሳን ጠላት በተለይም ከህወሃት ጋር ተቀላቅሎ የሚታየውን ህዝብ አምርረን እንድንጠላ በማድረግ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ስለሚመራን መሆኑንም ያስረዳሉ። ይህ ለህወሃት ጉበኛ ሆኖ መቆምንና ያፈጠጠ ፍቅርን የሚያሳይ ነው ካሉ እንጃ፡፡
ግድ የለዎትም አቶ ደረጄ መጽሐፉን ካላነበቡት እንደገና ያንብቡት፤ አንብቤዋለሁ ካሉም በድፍረቴ ይቅር ይበሉኝ፣ እንደኔ እንደኔ አልገባዎትምና ይድገሙና ያንብቡት፡፡ እርስዎ የሶቪየት ህብረት ታሪክ ብለው አግድም ባለፉት በመጽሐፉ ሰፊ ክፍል ደራሲው የሚተርከው ስለ ሶቪየት ህብረት ሳይሆን ስለኛ ነው። በሶቪየት ህብረት ከፍተኛ ቀውስ ያስከተለውና በመጨረሻም አገሪቱን ያፈራረሳት የብሄር ፖለቲካ እንዴት በሶቪየት ህብረት እንደተወለደና እንዴት አድርጎ ወዳገራችን እንደተሻገረ ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ይህን አስተሳሰብ በመጀመሪያይቱ ጽሁፍ ወደ ኢትዮጵያ ስላሻገራት ስለ ዋለልኝ መኮንን የሚሰጠው ትንተናም አስገርሞኛል፡፡ ከልብዎ ካነበቡት እርስዎንም ያስገርምዎታል ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ የመጽሐፉ ክፍል ዋለልኝ ይህን ሃሳብ ወደ ኢትዮጵያ ባሻገረበት በፈረንጆቹ በ1969፣ ይህ ሃሳብ ሩሲያን ወደ ማያባራ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ከትቷት እንደነበር ባስደናቂ የትረካ ጥበብ ሲተርከው ያነበብኩት እንደ ልብ አንጠልጣይ ልቦለድ ነበር። ግድ የለዎትም ወዳጄ አቶ ደረጀ፣ እንደ ስንዴ ለቃሚ አቃቢት ገለባና እንክርዳድ ፍለጋ ሳይሆን በተከፈተ ልብ እንደገና ያንብቡት፡፡ አንብበው ሲያበቁ ሃሳብዎን ከቀየሩም በግልጽነት በስሜት ተነሳስተው ያሳሳቱትን አንባቢ ይቅርታ ይጠይቁ። አርኪቴክት ሚካኤል ካፈርኩ አይመልሰኝ ሳይል ይህን በድፍረት አድርጎታል። ከዚህ ቀደም በጸጋዬ ገብረመድህን ላይ ገና አእምሮው ሳይበስል የጻፈውን ትችት፣ በልጅነት ባለማወቅና በድፍረት እንደሰነዘረው አምኖ፣ ጸጋዬን የሚያስተዋውቅ አንድ ሙሉ መጽሐፍ ጽፏል፡፡
ደራሲው የኢህአዴግና የህወሃት ጠበቃ ላለመሆኑ ሌላም ሃሳብ ልጨምርልዎ፡፡ “የራስን እድል በራስ መወሰን በኢትዮጵያ” በሚለው ርዕስ ስር በከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በፌዴራላዊ ስርዓቱ ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት ፖለቲካዊ የስልጣን ውክልና ሳይኖራቸው እንዴት ባለ ግዞት ውስጥ እንደኖሩ፣ ራስዎ እንዳሉት በስታትስቲካዊ ማስረጃ ጭምር አስደግፎና ተንትኖ  ጽፏል፡፡
ሌላው ወቀሳዎ ኢህአፓንና ኢህዴንን ነቅፏል፤ ይልቁንም ህብረ ብሄራዊ ሳይሆን የአማራ ድርጅቶች ሊሆኑ ይገባ ነበር፡፡ ህወሃት የተሳካለት ብሄራዊ ድርጅት ስለሆነ ነው ብሏል የሚል ነው፡፡ ይህን ምዕራፍ እኔ የተረዳሁት እንዲህ አይደለም፡፡ በዚህ ምዕራፍ ደራሲው የሚለው፣ አማራ ኢትዮጵያውያን የብሄረተኝነት ጥያቄ አልነበራቸውም ይልቁንም ራሳቸውን የሚያውቁት እንደ ኢትዮጵያዊያን ነበር ነገር ግን ከህወሃት በተነሳው ብሄረተኛ ማንነት፣ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ሁሉም በየብሄሩ እንዲከትት ሲደረግ ኢህዴን የአማራ ድርጅት የሆነው በሁኔታዎች አስገዳጅነት ነው የሚል ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን ብሄረተኝነት ከተጠቂነት ወይም ከተበዳይነት ስነልቡና የሚመነጭ ስለሆነ ይህ ስነልቡና ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት በአማራው ህዝብም ሆነ በአማራው ምሁር ዘንድ አልነበረም ይልና ሲያበቃ፣ ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት በትምክህተኝነት የሚያስፈርጅ ወንጀል ስለሆነ ከዚህም በተጨማሪ ከፖለቲካው አውድ በመገለልና በመገፋት. በመፈናቀልና በመበደል ብዛት ይህ ክፉ የሆነ መራራ የአማራ ብሄረተኝነት ዛሬ እየተፈጠረ ነው ይላል። ሰሞኑን የአማራ ክልል ባለስልጣናት ወደ አስመራ ሄደው የትብብር ውል የፈረሙት ከዚህ የፖለቲካ ሃይል ጋር ይመስለኛል።
በጥቅሉ ይህ መጽሐፍ የዶክተር አቢይ ተቃውሞ ከቶም አይደለም፡፡ ይልቁንም በምክንያታዊነትና በምርምር ለዶክተር ዐቢይ በፖለቲካው መድረክ ላይ ዛሬ የተሰለፉትን የፖለቲካ ሃይሎች አሰላለፍ ገላልጦ ለማሳየት የሚሞክር መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህም እይታ ዶክተር ዐቢይና የለውጡ ሃይል ዙሪያ ገባውን ቃኝቶና ተመልክቶ ፖለቲካዊ ጨዋታውን ለመምራት እንዲችል ታየኝ የሚለውን ብርሃን የሚፈነጥቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
እንደ አርኪቴክት ሚካኤል ያሉ ደራሲያንን ለመንቀፍም ይሁን ለመተቸት ቢያንስ መጽሐፉን አንብቦ ባግባቡ መረዳት ከፍ ሲልም እንዲህ ያሉ ሰዎች ያነበቡዋቸውን ዋቢ መጻህፍት ጭምር መቃኘትና ምክንያታዊ ሆኖ መገኘትን ይጠይቃል። እና ወዳጄ አቶ ደረጀ፣ ትችትዎ የሚያሳየው የደራሲውን የህወሃት ጠበቃነት ሳይሆን መጽሐፉን በቅጡና በጥልቀት አለማንበብዎን ነው፡፡ መጽሃፉን አንብበውና ተረድተው በአቋምዎ ከጸኑም ለራስዎ የሚጠቅሙዎትን ሃረጎች እየመዘዙና የማይገባ ትርጉም እየሰጡ ሳይሆን መተቸትም ይሁን መንቀፍ የሚችሉት በሰፊውና ምናልባትም በሌላ መጽሐፍ ይሆን ይሆናል፡፡ አለበለዚያ ግን በማሽላ ማሳ ገብቶ ያገኘውን እያጨደ፣ አንዳንዴ እየገነጠለ፣ ቀምሶ ቀምሶ እንደሚጥል ገመሬ፣ የሰው ማሳ ያበላሻሉ፡፡


Read 3288 times