Saturday, 01 September 2018 15:41

ህይወት ለግለሰቦች ደንታ የላትም

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

  “ጠ/ሚ ዐቢይ ‹‹መደመር›› ሲሉ የህይወትን መሠረታዊ ህግ እያስታወሱን ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት በተጓዝንበት ጎዳና የታዩ አንዳንድ አጥፊ የሆኑ ነገሮችን አስተውለው፤ ይህን ስህተት ለማረም ‹‹እንደመር›› አሉ፡፡ መደመር ቀላል የፍቅር ህግ ማስታወሻ ቃል ነው፡፡ የህይወትና የህብረተሰብን ቋሚና ዘላለማዊ ህግ መዘከሪያ ዘይቤ ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች መድህን የሚሆን ፍልስፍና ነው፡፡”
 
    እያንዳንዳችን የየግል ህይወታችንን ለማቆየት የቻልነውን ጥረት ካደረግን በኋላ በመጨረሻ ባደረግነው ጥረት የተመዘገቡ ስኬቶች ካሉ፤ ስኬቶቹ በዘረ-መል ሰነድ ይሰፍራሉ፡፡ እኛ በሞት ስንሰናበት፤ እነዚህ ስኬቶችና ድክመቶች ወደ ቀጣዩ ትውልድ ይተላለፋሉ፡፡ ምንም ዓይነት ጥረት ብናደርግ ሞትን ማሸነፍ አይቻልም፡፡ ዞሮ ዞሮ ከቤት የሚመመለስ ሰው፤ ኖሮ ኖሮ ከመሬት መግባቱ አይቀርም፡፡ መሬት ሁሉ ወደ መሬት ይመለሳል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊ ሁሉ ኢትዮጵያ›› ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ እንጂ ኢትዮጵያዊ ለዘላለም አይኖርም፡፡ ‹‹ሞት ሊሸነፍ የሚችለው በመውለድ ብቻ ነው፡፡›› ኢትዮጵያዊም ማሸነፍ የሚችለው ጥሩ ኢትዮጵያዊ ልጅ በማፍራት ብቻ ነው፡፡
ህይወት ለጊዜው እንጂ ለፍጻሜው ለግለሰበች ደንታ የላትም፡፡ ግለሰቦችን የምትፈልጋቸው ለሰው ዘር መቀጠል ባላቸው ፋይዳ ነው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ግለሰብ በህይወት ለመቆየት በሚያደርገው ጥረት የሚጠበቀው የሰው ዘር ነው፡፡ እኛ ለራሳችን የምንኖር ይመስለናል እንጂ የምንኖረው ለሰው ዘር መቀጠል ነው፡፡
አንድ ሐኪም ጓደኛዬ፤ አንድ ለየት ያለ ሐሳብ ነበረው። የሰው ልጅ የህይወት ግንዛቤ ብልሽት እንዳለው ለማስረዳት የሚያነሳቸው ሐሳቦች ነበሩት። አንደኛው፤ ሰው ለህይወት ጥራት (quality) ሳይሆን፤ ለህይወት ርዝመት (longevity) መጨነቁን ይመለከታል፡፡ ስለዚህ፤ በህይወት መኖር አለመኖሩን መለየት እንኳን  የማይችልን (vegetate የሚያደርግን) ሰው፤ በአፉ - በአፍንጫው ኦክስጂን አድርገን፤ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ህክምና በመስጠት በህይወት ለማቆየት እንሞክራለን፡፡ ትኩረታችን ርዝመት (longevity) ላይ በመሆኑ፤ በተለያዩ መድኃኒቶች ድጋፍ ረጅም ዕድሜ እንዲኖር የሚደረገው ሰው፤ ጥራት የሌለው ህይወት የሚገፋ ነው፡፡ በተፈጥሮ በሽታን የመከላከል ብቃት ሳያዳብር ሞትን በመድኃኒት አታልሎ (ሸውዶ) የሚያልፍ በመሆኑ፤ ለልጆቹ የሚያወርሰው ዘረመል አካባቢው የሚያቀርብለትን ፈተና ለማለፍ የሚያደርገው አይደለም ይላል፡፡
‹‹ይህ አካሄድ የህይወትን መርሐ ግብር ያበላሻል። ህይወት በእያንዳንዱ ሰው ሰውነት ሥነ ህይወታዊ  ብቃት በመፍጠር፤ ለሰው ዘር መቀጠል የምታደርገውን ጥረት ያሰናክላል፡፡ ሥነ ህይወታዊ ብቃት የሌለውን ግለሰብ፤ በመድኃኒት ጥበብ ለጊዜው ከሞት ዓይን ይሰውረዋል፡፡ ግን አንድ ቀን በጥበቡ የማይመልሰው በሽታ ይከሰታል፡፡ የሰው ዘርን በሙሉ የሚያጠፋ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል›› ይል ነበር ጓደኛዬ፡፡ በእርሱ እይታ፤ ኤድስ ተከማችቶ የመጣ አደጋ ነው። የዚህ አደጋ ምንጩ አስተሳሰብ ነው፡፡ በህይወት ርዝመት (longevity) የታወረ ግለኛ አመለካከት ነው፡፡  እንደ ሐኪም ጓደኛዬ ሐሳብ፤ እኛ የምንኖረው ሥነ ህይወታዊ ብቃትን በማዳበር ለሰው ዘር መቀጠል ለመስራት እንጂ፤ በመድኃኒት ‹‹ኮክቴል›› ተሸሽገን የግል ህይወታችንን ለማርዘም አይደለም፡፡
ከተፈጥሮ ወደ ማህበራዊ ህይወት ስንመለስ፤ እኛ የምንኖረው፤ የእኛ ልጆችና የልጅ ልጆች (በጥቅሉ መጪዎቹ ተከታታይ ትውልዶች) ጥራት ያለው ህይወት መኖር የሚችሉባትን ዘላለማዊት ኢትዮጵያ ለመገንባት ጭምር እንጂ፤ ሟች መሆናችንን በመዘንጋት ግለሰባዊ ጥቅማችንን ለማሳደድ አይደለም፡፡ ታዲያ በስግብግብነት እየተጎተትን፤ ግለሰባዊ ጥቅማችንን ማዘግየት፣ መግታትና መስዋዕት ማድረግ ቢሳነን፤ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ከሚጎዳ እንቅስቃሴ መራቅ ይኖርብናል፡፡ ሁላችንም ይህን ለማድረግ የሚያስገድድ የሞራል ዕዳ አለብን፡፡
ይህች የምንኖርባት ኢትዮጵያ የተባለች ሐገር እንድትኖር፤ የእርሷ ህልውና ተጠብቆ ከእኛ ትውልድ እንድትደርስ እልፍ አእላፍ ኢትዮጵያውን ህይወታቸውን ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ዛሬም ከአልሸባብ ጋር ለመፋለምና ክቡር ህይወታቸውን ለመስጠት በአውደ ግንባር ተሰልፈዋል፡፡ ሲቪክ ግዴታችን የሚመነጨው፤ እነሱ እየሞቱ እኛን ከሚያኖሩን የሐገራችን ልጆች ነው፡፡ ዛሬ የምንኮራበት ኢትዮጵያዊ ማንነትና የምናጣጥመው ከቅኝ ግዛት የሥነ ልቦና ኮተት የጸዳ ነጻነት የተገኘው በአባቶቻችንና እናቶቻችን ደምና አጥንት ግብር ነው፡፡ ይህ ዕዳ ሲቪክ ግዴታን ያመጣል፡፡ ሐገርን በሚጎዳ መንገድ የግል ጥቅምን ከማሳካት እንድንታቀብ ስሜት መግቻ ልጓም ይሆናል፡፡ የምኖረው የግል ጥቅምንና ህይወትን በማሳደድ ብቻ ከሆነ፤ እንደ ህብረተሰብና እንደ ሰው ዘር መቀጠል አንችልም፡፡
የሰው ዘር በምድር መቀጠል የቻለው፤ የሰውን ልጅ የሚያጠቃ በሽታ ሲመጣ፤ በበሽታው በተያዘው በእያንዳንዱ ሰው ሰውነት ውስጥ፤ የሰውን ልጅ ከመጣው በሽታው ለመከላከል የሚያስችል ሥነ ህይወታዊ ብቃት እየተገነባና ይህም በዘረ-መል ቀመር ለትውልዶች እየተላለፈ ነው፡፡ ይህ ከባለ አንድ ሴል ፍጥረት ጀምሮ፤ በማንኛውም ህይወት ያለው ፍጡር ውስጥ የሚፈጸም የህይወት ህግ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሚያደርግ ህይወታዊ ብቃት እናገኛለን፡፡
የወባ ትንኞችን ነገር ተመልከቱ፡፡ የወባ ትንኞች ዲዲቲን ለመከላከል የሚያስችል አቅም እስኪገነቡ ብዙ የወባ ትንኞች አልቀዋል፡፡ ነገር ግን በእያንዳንዱ የወባ ትንኝ ሞት፤ የወባ ትንኝ ዘር ከምድር ሳይጠፋ መቀጠል የሚችልበት ሥነ ህይወታዊ ብቃት ተገንብቷል፡፡ እናም ዲዲቲ የማይገድላቸው የወባ ትንኞች ተፈጥረዋል፡፡ የወባ ትንኞች ለመድኃኒቱ የማይበገር ሥነ ህይወታዊ ብቃት አዳብረዋል፡፡ ታዲያ ይህን ብቃት ያዳበሩት ብዙ የወባ ትንኞች አልቀው ነው፡፡ ስለዚህ በተናጠል የሚከሰተው የወባ ትንኞች ሞት፤ ለዘሩ መቀጠል ዋስትና ሆኗል ማለት ነው፡፡
የእኛም ነገር ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ነገር ግን የእያንዳንዳችን ህይወት ለራሳችን ብቻ ይመስለናል። ሁላችንም ለራሳችን ስንል የምንኖር ይመስለናል። ‹‹ውሻው የሚጮኸው እኛን ለመጠበቅ አይደለም። ለራሱ ፈርቶ ነው›› ይል ነበር ጋሽ ስብሐት፡፡ እኛም የምንኖረው ለራሳችን ይመስለናል፡፡ እኛ የምንኖረው ለሰው ልጅ ህይወት መቀጠል የሚበጅ ጥረት ለማድረግ ነው፡፡
በርግጥ የግል ህይወታችንን ማስቀጠል መቻል ትልቅ ነገር ነው፡፡ የሰው ዘር መቀጠል የሚችለው በእኛ በግለሰቦቹ መቀጠል ነው፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል እንዳየነው፤ የግል ህይወታችንን ባልተገባ መንገድ ለማስቀጠል ስንጣጣር፤ የሰው ዘር አደጋ ላይ ይወድቃል። እኛ የግል ህይወታችንን ለማስቀጠል የምናደርገው ትግል፤ ለሰው ልጅ ህይወት መቀጠል የሚበጅ ትግል መሆን አለበት፡፡ የሰው ዘር ሳይቀጥል፤ የግል ህይወት ሊኖር አይችልም፡፡ እንዲያውም፤ ‹‹ውሻው የሚጮኸው እኛን ለመጠበቅ አይደለም›› እንደተባለው፤ ህይወትም የምትጮኸው ለሰው ልጅ ህልውና መቀጠል እንጂ ለግለሰብ ደንታ ያላት አትመስልም፡፡ ስለዚህ ሰው በግለሰባዊ ትግሉ ለሰው ዘር መቀጠል እየሰራ ያልፋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው የሚኖረው ለሰው ዘር ህልውና ነው፡፡ የሰው ዘርም በጋራ ለእያንዳንዱ ግለሰብ መኖር አለበት፡፡ አስደሳች ግለሰባዊ ህይወት ለመምራት የሚያስችል ማህበራዊ ስርዓትን መስራት አለበት፡፡ ይህን ማድረግ ለሰው ዘር ህልውና ዋስትና ይሆናል፡፡ ይህ የህይወት የመደመር ፍልስፍና ነው፡፡
አንድ ወታደር ለሐገሩ ሲል ይሞታል፡፡ በእርሱ ሞት የሐገር ህልውና ይጸናል፡፡ ይቀጥላል፡፡ እያንዳንዳችን በህይወት ህግ ተመርተን ለሰው ዘር መቀጠል የሚያገለግሉ ሥነ ህይወታዊ ሥራዎችን እየሰራን እንደምናልፍ፤ ወታደርም በህብረተሰባዊ የሲቪክ አስተሳሰብ መርህ የሐገሩን ህልውና እያስከበረ ያልፋል፡፡ የየግል ህይወታችን በማትረፍ ስሌት ሲቪክ አስተሳሰብን ካጠፋነው፤ የሐገር ህልውና ሊከበር አይችልም፡፡ የመደመር ፍልስፍና ለሲቪክ አስተሳሰብ ትኩረት እንድንሰጥ ጥሪ የሚያደርግ ፍልስፍና ነው። ‹‹ለእኔ›› ብቻ በሚል አስተሳሰብ ሳንታወር፤ ‹‹ለእኛ›› ብሎ የመስራት አመለካከትን ለመፍጠር የሚሞክር ፍልፍና ነው። ‹‹የእኔን›› ፍላጎት ‹‹በእኛ›› አስተሳሰብ ለማሳካት የሚደረግ ጥረት ነው፡፡
ወታደር የህዝብ ነጭ የደም ሴል ነው፡፡ በአካላችን ላይ አንድ አደጋ ሲደርስ፤ ነጭ የደም ሴሎቻችን ሰውነታችንን ከጥቃት ለመከላከል እንደሚዘምቱ፤ ወታደርም ሐገርን የሚያጠፋ ኃይል ሲነሳ ይዘምታል። ሁለቱም ታግለው እየሞቱ ህልውናን ያስከብራሉ።  ነጭ የደም ሴሎች ለአካላችን፤ ግለሰቦች ለሰው ዘር፤ ወታደርም ለሐገር ህልውና መቀጠል ይሞታል፡፡
የህይወት ስርዓት እንዲህ ያለ መሆኑን የምናረጋግጠው፤ እናትና አባት ለልጆቻቸው በሚያደርጉት እንክብካቤ ነው። በወላጆች ልብ ውስጥ የምናገኘው፤ ለሰው ዘር መቀጠል አስፈላጊ የሆነ ‹‹ፍቅር›› የሚሉት የህይወት ‹‹ሶፍትዌር›› ነው። እናት ልጇን እንደ ወለደች የምትጥል ቢሆን የሰው ዘር ገና ድሮ ከምድረ ገጽ ይጠፋ ነበር፡፡ ግን የህይወት ኢንጂነር ራስን የሚያስክድ ፍቅርን በእናት ልብ አሳደሮ አደጋውን አስወገደ፡፡
በአንዳንድ የምዕራብ ሐገራት ህብረተሰብ ዘንድ የሚታይ አንድ የአስተሳሰብ ብልሽት አለ። ለግለሰባዊ ህልም መሳካት ብቻ የሚኖሩ የሚመስላቸው የአንዳንድ ምዕራባዊ ሐገራት ዜጎች፤ ቤተሰብ መመስረትና ልጆች መውለድን እየፈሩ፤ ሐገራቸውን የአዛውንቶች ሐገር እያደረጓት ነው። ፍቅር የሌለበት ሐገር ህይወት ይርቀዋል። መቃብር ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ሰው ህይወት፤ ለሰው ልጅ ህይወት መረጋገጥ የሚበጅ ነገር በፍቅር እንዲከናወን ይፈልጋል። በራሳቸው ‹‹ፍቅር››  የታሰሩ የአንዳንድ ምዕራባዊ ሐገራት ዜጎች፤ ፍቅርን ፈርተው ልጅ ሳይወልዱ ያረጃሉ፡፡ ስለዚህ እንደ ሐገር ያላቸው ህልውና ለአደጋ ተጋለጠ፡፡ አስተሳሰባቸው በግለኝነትና በስግብግብነት በመታወሩ፤ መሠረታዊ የተፈጥሮና የህብረተሰብ ህግን የሚጻረሩ፤ ፀረ-ህይወትና ፀረ-ህብረተሰብ ዜጎች ሆኑ። ጥሩ መንግስታዊ ስርዓት ቢኖራቸውም፤ ህይወትን ለሌሎች በመኖር መባረክ የሚችል ጥሩ የፍቅር አመለካከት የላቸውም፡፡ የአዛውንቶች ቀኬ እንጂ፤ የልጆች ድሱት ድምጽ የማይሰማበት ቤት ይሰራሉ። እኛ ደግሞ ቤት የሌላቸውን ልጆች፣ በአናት በአናቱ እንወልዳለን፡፡
ከወራት በፊት ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ለህዝብ ተካዮች ምክር ቤት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ፤ ጥሩ መንግስታዊ ስርዓት እንዳይጸና የሚያደርግ፤ የጠባብነት፣ የጥላቻ፣ የቂምና የስግብግብነት መንፈስ ይዘን፤ ፀረ-ህይወትና ፀረ-ህብረተሰብ አካሄድ እየተከተልን ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ ገርሟቸው፤ ልጆቻችን በሰላም ሊኖሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ሳንፈጥር ልጅ መውለዳችን አስደንቋቸው የተናገሩት አንድ ነገር ነበር፡፡ ለልጆቻችን ፍቅርን ሳይሆን ጥላቻን እያወረስናቸው፤ እርስ በእርሳቸው እንዲባሉ የሚያደርግ ቂም እያወረስናቸው፤ ልጆች መውለዳችን አስደምሟቸው፤ በአግራሞት ‹‹…በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ልጆች እንወልዳለን›› ብለው ነበር፡፡ የምንወልዳቸው ልጆች፤ ለእነርሱ ወደዚህ ምድር መምጣት መሠረት በሆነው የፍቅር ወይም የመደመር ህግ ካልታነጹ፤ በአንድ ቤት ሲኖሩ ይጠፋፋሉ፡፡ እናም ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ በፍቅር የመኖር ህግ በቤተሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በህብረተሰብም ደረጃም አስፈላጊ እንደሆነ ሲያስረዱ ‹‹እንደመር›› አሉ፡፡
ህብረተሰብ ወይም መንግስት የብዙ ሰዎች ስብስብ ከሆነ፤ ከሁሉ አስቀድሞ ይህ ስብስብ ሊኖር የሚችለው፤ ተጋበተው ለመውለድ የሚችሉ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሲኖሩ ነው፡፡ ሁለቱን በአንድ የሚያስተሳስረውም ፍቅር ነው፡፡ ሴትና ወንድ ሳይኖሩ ህብረተሰብ ሊኖር አይችልም። አንድ ወንድና አንዲት ሴትን የሚያስተሳስረውና የሚያስተዳድረውም ፍቅር ነው፡፡ የሰው ዘር በምድር መኖሩን ይቀጥል ዘንድ፤ የአንድ ሴትና ወንድ መኖር ብቻ ሳይሆን የእነሱ በፍቅር መተሳሰር ግድ ነው፡፡ ስለዚህ የህብረተሰብ መሠረት ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ‹‹የመደመር›› ወይም ‹‹መደመር›› የፍቅር ተለዋጭ ስም ነው፡፡ ይህ የተፈጥሮ ህግ እንጂ ሐይማኖታዊ እሳቤ አይደለም። ፍቅር ወይም ‹‹መደመር›› የተፈጥሮ መላ ነው፡፡ ፍቅር ወይም ‹‹መደመር›› የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡
የሰው ልጆች አምሳያቸውን ተክቶ በማለፍ የተፈጥሮ ዝንባሌ የሚገዙ ናቸው፡፡ በዚህም ዘራቸው ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ያደርጋሉ፡፡ ይህም ዝንባሌ ከማናቸውም ሌሎች እንስሳት ወይም ዕጽዋት ጋር የሚጋሩት አጠቃላይ የተፈጥሮ ዝንባሌ ሲሆን፤ በዚሁ አግባብ ወንድና ሴት የተፈጥሮ ግብራቸውን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ፤ አምሳያቸውን በመተካት ራሳቸውን ህያው ያደርጋሉ፡፡ በእኛ ፈቃድ በኩል የአጠቃላይ የተፈጥሮ መሻትና ዝንባሌ እውን ሆኖ ልጆች ይወለዳሉ፡፡ ካህሊል ጅብራን፤ ‹‹ልጆች በእናንተ በኩል መጡ እንጂ ከእናንተ አልመጡም›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ አዎ በፍቅር ልጆች ወደዚህች ምድር ይመጣሉ፡፡ በዚህ ምድርም ከሌሎች ሰዎች ጋር አብረው ይኖራሉ፡፡ ወደዚህ ምድር በፍቅር እንደ መጡ፤ በፍቅር ወይም በ‹‹መደመር›› ህግ ከሌሎች ሰዎች ጋር ይኖራሉ፡፡ የፍቅር ወይም የ‹‹መደመር›› ህግ የሌሎችን ነጻነት በማክበር፣ ለሌሎች በማሰብ፣ ለፍትሕ በመቆም ወዘተ ይፀናል፡፡ ታዲያ ልጆቻችን በዚህ ህግ ካልታነፁ ከመጠፋፋት ይደርሳሉ፡፡
ሰው ገና ሲወለድ አዕምሮ የሚባል ልዩ ጸጋ ታጥቆ የሚወለድ ነው፡፡ ታዲያ ይህ መሣሪያ ለልማትም ሆነ ለጥፋት ሊውል ይችላል፡፡ ይህ የታጠቀው መሣሪያ በአስተዋይነት፣ በግብረ ገብነትና በትክክለኛ የፖለቲካ መርህ ተገርቶ በጥቅም ላይ ካልዋለ፤ በአጭሩ ሰው ግብረ ገብነት የሌለው ፍጡር ከሆነ፤ በማዕረጉ ከእንስሳትም የወረደ ርኩስ፣ ጨካኝ ወይም አረመኔ ይሆናል፡፡ የ‹‹መደመር›› ህግ መገለጫ የሆኑትን (የሌሎችን ነጻነት ማክበርን፤ እንስሳትና ዕጽዋትን ጨምሮ ለመሰሉ ለሌሎች ፍጡራን ማሰብን፤ ፍትሕን ማክበርን) ካላከበረ፤ ርኩስ፣ ጨካኝ ወይም አረመኔ ይሆናል፡፡ አዕምሮን የመሰለ ልዩ ጸጋና ከባድ መሣሪያን የታጠቀው የሰው ልጅ፤ ኢ-ፍትሐዊ ከሆነ በጣም አደገኛ ጥፋት ሊያመጣ የሚችል ነው። በመልካም እሴት ያልታነጸ አዕምሮ፤ አደገኛ መሣሪያ የታጠቀ የሲዖል (የኢ-ፍትሐዊነት) ዘበኛ ነው፡፡ ለሌሎች ፍጡራን የማያስብና በፍቅር ስሜት ያልተገራ አልጠግብ ባይነት፤ ጌታ ለመሆን ተወልደን የማይረቡ ነገሮች ባሪያ ያደርገናል፡፡
ሰዎችን እንደ አንድ አካል በሰላም አስተሳስሮ የሚይዝ ማህበራዊ ገመድ ፍትሕ ነው፡፡ የአንድ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ሰላምና መረጋጋት የሚረጋገጠው በፍትሕ መስፈን ነው፡፡ ሆኖም ሰዎች በእውር ፍላጎትና በአልጠግብ ባይነት እየተመሩ ሰዎችን በሰላም አስተሳስሮ የሚይዘውን ማህበራዊ ገመድ ወይም ፍትሕን በመጉዳት፤ የሰዎችን ሰላምና ህብረትን ያጠፉታል፡፡ መደመር ይህን የተፈጥሮ መሠረት ያለው ማህበራዊ ህግን እንድናስታውስ ጥሪ የሚያቀርብ ፍልስፍና ነው፡፡
የሰው ልጆች ህብረት መሠረቱ ፍቅር ነው። ዝቅተኛ የሰዎች ህብረት ደግሞ ቤተሰብ ነው፡፡ የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት ፍላጎት ለማሟላት፤ የተፈጥሮ ህግን ተከትሎ የተመሠረተው፤ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ የሚያፈራ ህብረት ነው፡፡ ከደም፣ ከባህል፣ ከቋንቋ ከሚፈጠር ትስስር ከፍ ብሎ፤ በሲቪክ አስተሳሰብ የሚመሰረት ህብረትም አለ፡፡ ይህ ህብረት መሠረቱ መደመር ወይም ፍቅር ነው። መሠረቱ፤ የሌሎችን ነጻነት ማክበር፣ ለመሰል ሌሎች ፍጡራን ወይም ሰዎች (እንስሳትና ዕጽዋትን ጨምሮ) ማሰብና ፍትሕን ማክበር ነው፡፡
ጠ/ሚ ዐቢይ ‹‹መደመር›› ሲሉ የህይወትን መሠረታዊ ህግ እያስታወሱን ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት በተጓዝንበት ጎዳና የታዩ አንዳንድ አጥፊ የሆኑ ነገሮችን አስተውለው፤ ይህን ስህተት ለማረም ‹‹እንደመር›› አሉ። መደመር ቀላል የፍቅር ህግ ማስታወሻ ቃል ነው፡፡ የህይወትና የህብረተሰብን ቋሚና ዘላለማዊ ህግ መዘከሪያ ዘይቤ ነው። ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች መድህን የሚሆን ፍልስፍና ነው፡፡


Read 5966 times