Tuesday, 04 September 2018 09:29

በየአመቱ ከሩብ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጦር መሳሪያ ይሞታሉ ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአለማችን በየአመቱ ሩብ ሚሊዮን ያህል የተለያዩ አገራት ዜጎች በጦር መሳሪያ አማካይነት ለሚከሰት ሞት እንደሚዳረጉ አንድ አለማቀፍ ሪፖርት ማስታወቁን ደች ዌሌ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ ሚዲካል አሶሴሽን በ195 የአለማችን አገራት ላይ የሰራውን ጥናት መሰረት በማድረግ ያወጣውን አለማቀፍ ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ በአለማችን በየአመቱ ከ250 ሺህ በላይ ሰዎች በጦር መሳሪያዎች አማካይነት ለሞት የሚዳረጉ ሲሆን፣ 70 በመቶ ያህሉም በሌሎች ሰዎች በሚደርስባቸው ጥቃት የሚገደሉ፣ 27 በመቶው ራሳቸውን የሚያጠፉ፣ 9 በመቶው በአደጋ ለሞት የሚዳረጉ ናቸው፡፡
ተቋሙ በአገራቱ እ.ኤ.አ ከ1990 እስከ 2016 በነበሩት አመታት በጦር መሳሪያዎች አማካይነት ለሞት የተዳረጉ ሰዎችን በተመለከተ በሰራው በዚህ ጥናት፤ የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንና በ2016 የፈረንጆች አመት ብቻ በአለማችን 251 ሺህ ሰዎች በጦር መሳሪያዎች ለሞት መዳረጋቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ኤልሳልቫዶር ከአጠቃላይ የህዝብ ብዛቷ አንጻር ብዙ ሰዎች በጦር መሳሪያዎች አማካይነት ለሞት የሚዳረጉባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ናት ያለው ሪፖርቱ፣ በአለማችን በጦር መሳሪያ ለሞት ከሚዳረጉት ሰዎች መካከል ግማሽ ያህሉ የብራዚል፣ ኮሎምቢያ፣ ጓቲማላ፣ ሜክሲኮ፣ ቬንዙዌላ እና የአሜሪካ ዜጎች እንደሆኑም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1368 times