Monday, 10 September 2018 00:00

በአዲስ ዓመት ለውጡን የሚያጠናክሩ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 በቀጣዩ አዲስ ዓመት የተጀመረውን ፖለቲካዊ ለውጥ የሚያጠናክሩና ተቋማዊ ቅርፅ የሚያሲዙ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠየቁ፡፡
ያለፈውን ዓመት የሃገሪቱን የፖለቲካ፤ እንቅስቃሴ ገምግመው፣ የቀጣዩን ዓመት ተስፋቸውን በተመለከተ ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የገለፁ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፤ አዲሱ ዓመት በ2010 የተጀመረውን ፖለቲካዊ ለውጥ የሚያጠናክሩ ከሕገ መንግስቱ ጀምሮ አዋጅ፣ ሕጐችና ፖሊሲዎች የሚሻሻሉበት እንዲሁም ለቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ሰፊ ዝግጅት የሚደረግበት መሆን አለበት ብለዋል፡፡
የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ “በቀጣዩ አመት አሁን የተጀመረው ለውጥ ወደ መሬት ወርዶ፣ አስተማማኝ መሠረት እንዲይዝ፣ የህዝብ ምሬት ምንጭ የሆኑ ፖሊሲዎች፣ አዋጆችና ሕጐች መሻሻል አለባቸው” ብለዋል፡፡
የለውጥ አስተሳሰቡም ከጠ/ሚሩና በዙሪያቸው ካሉ አመራሮች ተሻግሮ፣ ተቋማዊ የማድረግ ሰፊ ስራ መሠራት እንዳለበትም ዶ/ር ጫኔ አሳስበዋል፡፡
አዲሱ ዓመት ነፃ የዴሞክራሲ ተቋማት የማቋቋም ሥራ መሠራት እንዳለበት ያስገነዘቡት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ የሸዋስ አሠፋ በበኩላቸው፤ በ2010 የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ አስተማማኝ መሠረት የማስያዝ ስራ መሠራት አለበት ብለዋል፡፡
ለውጡን በአዲስ ሥርዓት መቋጨት የሚያስችል ሥራ የሚተገበርበት ዓመት ሊሆን ይገባል ያሉት የኢራፓ ሊቀ መንበር አቶ ተሻለ ሠብሮ፤ በዋናነት ምርጫ ቦርድንና የምርጫ ሥርዓቱን የማሻሻል ሥራ ተሠርቶ፣ ለ2012 ምርጫ ሰፊ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የመኢአድ ፕሬዝዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሌም የአቶ ተሻለን ሃሳብን ይጋራሉ፡፡
የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ ቀጣዩ ዓመት ህዝባዊ መንግስት ለማቋቋም ሰፊ ቅድመ ዝግጅት የሚደረግበት መሆን አለበት ብለዋል፡፡ ለዚህም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ አጋዥ የሆኑ ተቋማዊ ማሻሻያዎች መደረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡


Read 6961 times