Monday, 10 September 2018 00:00

ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  መቐለ በምጽዋ አገልግሎት መጀመሯ “የአዲስ ዓመት ገጸበረከት ነው” - ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ


    ሰሞኑን በአስመራ ተገናኝተው በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ የመከሩት የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ መሪዎች፤ በአካባቢው የፀጥታ ጉዳይ ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን የሶማሊያው ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዚደንት ሙሐመድ ፎርማጆ ስለ ውይይታቸው በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ማስታወሻ፤ሶስቱን ሃገራት በኢኮኖሚ ለማስተሳሰርና በፀጥታ ጉዳይም በጋራ ለመስራት ታሪካዊ ስምምነት ተፈርሟል ብለዋል፡፡
የኤርትራ መንግስት በበኩሉ፤ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን በሙሉ አቅሙ ለመጠቀም እንዲያስችላት በሚል ከወደቡ እስከ ቡሬ ከተማ የሚደርስ የ71 ኪሎ ሜትር ዘመናዊ አስፓልት መንገድ መገንባት መጀመሩን አስታውቋል፡፡ መንገዱ በአንድ ጊዜ አራት ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ዘመናዊ አስፓልት መሆኑን የጠቆመው የኤርትራ መንግስት፤ይህም የሁለቱ ሃገራትን የኢኮኖሚ ትስስር ወደተሻለ ደረጃ ያሻግራል ብሏል፡፡
ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን ለሁለተኛ ጊዜ በኤርትራ ባደረጉት ጉብኝትም “መቐለ” የተሰኘችው የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ፣ ከ20 ዓመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ከምፅዋ ወደብ የኤርትራን የወጪ ንግድ እቃ በመጫን፣ ወደ ቻይና ያደረገችውን ጉዞ አስጀምረዋል፡፡ መርከቧ በምጽዋ አገልግሎት መስጠት መጀመሯ በእጅጉ ያስደሰታቸው ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፤ ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ “የአዲስ ዓመት ገጸበረከት ነው” ሲሉም ገልጸውታል፡፡
በቀጣዩ ሳምንት ኢትዮጵያ፤ የአሰብና የምፅዋ ወደቦችን መጠቀም እንደምትጀምር የተገለጸ ሲሆን ይህን ተከትሎም ጅቡቲ በወደብ አገልግሎት ዋጋ ላይ ቅናሽ ማድረጓን ትራንስፖርት  ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም በጀቡቲ ወደብ 120 ዶላር ይከፈልበት የነበረ አገልግሎት ወደ 20 ዶላር ዝቅ ማለቱ ተጠቁሟል፡፡ ኢትዮጵያ የአሰብና የምፅዋ ወደቦችን የምትጠቀመው በኪራይ ሲሆን የኪራይ ዋጋው ሃገራቱ በሚያደርጉት ስምምነት ይወሰናል ተብሏል፡፡ 

Read 7424 times