Monday, 10 September 2018 00:00

“የእዚህ አገር ሰው ካልገጩለት አርዶ አይበላም!”

Written by 
Rate this item
(11 votes)

 አንዳንድ እውነት ተረት ይመስላል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ነጋዴ - አጐበር አከፋፋይ ነበሩ፡፡ ወቅቱ፤ ወባ በአገራችን ብዙውን አካባቢ ያጠቃበት፣ ኮሌራ ስሙን ለውጦ አተት (አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት) የሚል የብዕር ስም ያገኘበት ጊዜ ነበር፡፡ (ዘመን አይለውጠው ነገር የለምና ሁሉን ተቀብሎ ተመስጌን ማለት ደግ ነው!)
አጐበር አከፋፋዩ ነጋዴ፣ ሶስት መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት (NGO/ አንዳንዶች “Nothing Goes On” ይሉታል ሲተረጉሙት) ሠራተኞች ጭነው ወደ ዋናው የሥራ ቦታቸው (እናት-ክፍላቸው) እየሄዱ ነው፡፡ መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት ተጠሪ ከመኪናው ጋቢና ተቀምጠዋል፡፡
“ሥራ እንዴት ነው?” ይሏቸዋል ነጋዴውን፡፡
“መልካም ነው… መቼም እንፍጨረጨራለን!” አሉ፡፡
መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት (መያድ) ተጠሪ በሆዳቸው፤ “ቅቤ ነጋዴ ድርቅ ያወራል” አሉና ተረቱ፡፡
“አጐበራችንን በጥሩ ሁኔታ የምናከፋፍል ይመስልዎታል?”
“አይጠራጠሩ! ሆኖም ይሄ ህዝብ አይታመንም”
“ለምን?”
“መግዛቱን ይገዛል - ግን ደግሞ አጐበሩን ከወሰደ በኋላ፤ ግማሹ የዝናብ ልብስ ያደርገዋል፡፡ ግማሹ የእህል መቋጠሪያ ያደርገዋል፡፡ ከፊሉ ደግሞ አንገት ልብስ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ እናንተ የማስተማር ኃላፊነት አለባችሁ!” ይህንንና ሌላ ሥራውን የሚመለከቱ ጉዳዮች እያወጉ ሲጓዙ፤ በድንገት አንድ ወይፈን መንገዱ ውስጥ ገባ፡፡ ነጋዴው መኪናውን አቁመው ወይፈኑን ለማዳን አልቻሉም፡፡ ገጩት፡፡ ወደቀ፡፡ እሳቸው መኪናውን ከተገጨው ወይፈን አቅጣጫ ቀየስ አድርገው መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት ተጠሪ ተደናገጡ፡፡ ወይፈኑ አሳዘናቸው፡፡ ወይፈኑን “ነገ አሳድጌ አርስበታለሁ” ብሎ በመከራ ተስፋውን ያቆየው ገበሬ ታሰባቸው፡፡ ስለዚህ፤
“ምነው? ወዴት ነው የሚሄዱት? አንድ እንስሳ ገጭተናልኮ’፤ ዝም ብለን መሄድ አንችለም፡፡ የወይፈኑን ባለቤት አግኝተን ማነጋገርና ይቅርታ መጠየቅ፣ ካሣም እፈልጋለሁ ካለ መክፈል አለብን!” አሉ፡፡
ነጋዴውም፤
“ዝም ብለን እንቀጥል! የእዚህ አገር ሰው ካልገጩለት አርዶ አይበላም!” አሉ፡፡
*   *   *
የሀገራችን ሰው መስዋዕትነት ካልከፈሉለት አይነቃቃም፤ እንደማለት ነው!
ሌላው ካልሞተለት አይነሳም! ልብ ካልሰጡት ልብ አይገዛም! ይሄ ዕውነት ሊሆን ይችላል፡፡ (ይሄ ግን ወይፈኑን እየገጩ አይደለም) በተጀመረ መንገድ ለመሄድ ግን አንደኛ ነው! መፍሰስ ከጀመረ ወንዝ ጋር መፍሰስ ይወዳል! በዚያ መንገድ ከሄደ በኋላ ደግሞ ሹሙኝ… ሸልሙኝ ካሱኝ… “ማን አለ እንደ እኔ ላገሩ የሞተ” ለማለት ቀዳሚ ነው! ይሄም ባልከፋ፤ … ግን ችግሩ ፈጦ እሚመጣው “ካሣው የዕድሜ ልክ ይሁንልኝ” ሲል ነው፡፡ “ሁሌ ተጠቃሚ ልሁን” ሲል ነው፡፡ ዛሬም የሚከተለውን ዕውነት መድገም ተገቢ ስለሆነ ደግመን እንበለው፡- He mistakes longevity for eternity (‘ረዥም ዕድሜን ከዘለዓለማዊነት ያምታታል’ እንደማለት ነው)
ዛሬ በርካታ የውጪ አገር ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ነው፡፡ እየተመሙ ነው፡፡ እንግዳ ተቀባዩ የኢትዮጵያ ህዝብም አስፋልት ሙሉ እየጐረፈ እየተቀበላቸው፤ እያስተናገዳቸውም ነው፡፡ ይሄ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የናፍቆት፣ የስስት ፍሬ ነው፡፡ ያም ሆኖ እዚህ ጋ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮችን ወይም ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡
1ኛ) የሞቀ አቀባበል ማድረጉ (ለስንቱ አቀባበል ማድረግ እንደሚቻል፣ ባንረዳም) ለሞቀ ጥያቄው መልስ የሚሰጡ ተቆርቋሪዎች አገኘሁ የሚል ተስፋ ሰንቆ መሆኑን አለመዘንጋት ነው፡፡ ስለዚህም “እጃችሁ ከምን?” ብሎ የልቡን እንደሚጠይቅ አለመርሳት ነው!
2ኛ) ሰው ሆኖ ሲያወድሱት ደስና ሞቅ የማይለው የለምና፣ ደስታው ወደ አረፋዊ መነፋፋት (Infatuation)፣ አልፎ ተርፎም ወደ ተዓብዮ እና እኔ ብቻ ነኝ ቁልፉ (Ego-Centerism) እንዳይለወጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡
አንድ የማይታወቅ ገጣሚ የፃፈው ስለ“ዝና” የሚያወሳ ግጥም እንዲህ ይላል፡-
Fame
Fame is a bee
It has a song
It has a sting
O God! It also sah a wing!
(ዝና ንብኮ ነው
ይዘፍናል ዜማ አለው
መዋጊያ እሾህ አለው
እግዜር ይሰውረን! - ይበርራል
ክንፍ አለው!!)
ልብ ያለው ልብ ይበል!!
“ነይ ነይ ክብረት - ዓለም
ነይ ነይ ክብረት - ዓለም
የጀመረሽ እንጂ የጨረሰሽ የለም!”
…የሚለውን የዘፈን ግጥምም አንርሳ!
አዲስ ዘመን ዋዜማ ላይ ነን! አገራችን፤ አዲስ ሰው፣ አዲስ ባለ ራዕይ፣ አዲስ ተጓዥ ትሻለች፡፡ ጥያቄዎቿን እንመልስላት! ከድህነቷ እንታደጋት! ብንታደል የጥንቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ መንፈስ ቢፈጠር፣ ከዚያም ቢረቅና ቢራቀቅ መልካም ነው! ሁላችንም አገሬ! አገሬ! የምንልበት፣ ተቀራርቦና ተሳስቦ በአንድነት የመጓዝ ትግል ሊፈጠር የግድ ይላል፡፡ አይቀሬ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ሆኖም ጊዜውን አሳጥሮ በኅብር (in harmony) መራመድ እጅግ አስፈላጊ ነው!
ሁሉም ነገር መስዋዕትነት ይጠይቃል፡፡ ሰው ጠያቂ ይፈልጋል፡፡ ሀቀኛ ተሟጋች ይፈልጋል፡፡ “የሀገሬ ዋና ዋና ችግሮች የቶቹ ናቸው?” ብሎ የሚጠይቅ ልባም ልጅ ይፈልጋል፡፡ ያ ማለት ግን መስዋዕትነቱ ሌላ ጥፋት በመፈፀም የሚመጣ መሆን የለበትም፡፡ ህዝብን የመናቅና የትም አይደርስም ከሚል ንቀትም የሚመነጭ መሆን የለበትም፡፡ “እኔ አውቅለታለሁ” ማለት የተዓብዮ ሁለ ተዓብዮ (The Peak of arrogance) ይሆናል። ከላይ የተረክናቸው ሹፌር፤ “የእዚህ አገር ሰው ካልገጩለት አርዶ አይበላም” ማለት ይሄን ሁሉ ያካተታል፡፡
መልካም አዲስ ዓመት! 

Read 8184 times