Monday, 10 September 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(3 votes)

 እንቁጣጣሽ!!
   
    አዲስ ዘመን ብለሽ፣
እንቁጣጣሽ ብለሽ፣
ነይብኝ ነይብኝ፣
እኔም አበባ ነኝ፤
አበባ ሁኚልኝ!!
***
ወድሃለሁ ያልከኝ
    የት አለ?... የት አለ?
አንድ አበባ መላክ
    ማንን ሰው ገደለ?
***
አገሬ አበባዬ፣
አደዬ ፀሃዬ፣
አበባዬ አንቺ ነሽ፣
ሌላ አበባም የለኝ፣
ላንቺ የምቀጥፈው-
    እኔው እራሴ ነኝ!!
***
እንቁጣጣሽ ብለሽ፣
አዲስ ዘመን ብለሽ፣
ነይብኝ ነይልኝ፣
እኔም አበባ ነኝ -
    አበባ ሁኚልኝ!!
በአንዲት ጥንታዊት ሃገር እንዲህ ሆነ፡፡ የአንድ ታላቅ ንጉሥ ልጅ፣ የአባቷ ባላንጣ ከሆነ አገርመስፍን ጋር ተዋደደች፡፡ ፍቅረኛሞቹ በድብቅ መልዕክት ይለዋወጣሉ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሚስጢራቸው በአባቷ ባለሟል ታወቀ፡፡… ወሬውም ከአባቷ ጆሮ ደረሰ። ንጉሱም የሰጠውን ለማረጋገጥ አድብቶ ሲጠባበቅ በአዲስ ዓመት መባቻ ላይ ልዕልቲቷ በመናፈሻዋ ቦታ እንዳለች፣ አንዲት እርግብ መጥታ ጉልበቷ ላይ አረፈች። ልዕልቲቱም በርግቧ እግር ላይ የታሰረውን መልዕክት እየፈታች ሳለ አባቷ ደረሰባት፡፡ እየተቆጣ ተቀብሎ ሲመለከተው ደነገጠ፡፡ … ወዲያውም ተንበርክኮ እጆቹን ወደ አማልክቶቹ ዘረጋ፡፡… ለምን ይሆን?
***
ወዳጄ፡- መጪው ዘመን የፍቅር አበባ የሚፈካበት፣ የሰብል አበባ የሚያሸትበት፣ ወጣትነት የሚደምቅበት፣ ዴሞክራሲ ‘ሚያብብበት፣ የአንድነት ደመራ ሚለኮስበት፣ ድህነት ሚቀንስበት፣ ዘረኝነት የሚሞትበት፣ ውሸት የሚጋለጥበት፣ ፍትህ የሚነግስበት፣ ጤና የሚለመልምበት፣ ጭቆና የሚወገድበት፣ ምኞት የሚሳካበት፣ ሁሉም እንደ ወግና እንደ ልማዱ የሚከበርበት፣ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ድልድይ የሚዘረጋበት፣ የተፈናቀሉ የሚመለሱበት፣ የተጐዱ የሚጠገኑበት… ሌላም… ሌላም ብዙ መልካም ነገር ሆኖ… አገራችን እንድትስቅ ምኞቴ ነው፡፡… በነገራችን ላይ የእስራኤላውያንም አዲስ ዓመት ‘Rosh Hashanah’ የሚከበረው በዚሁ በመስከረም ወር ነው።… በአበባና በእሸት!!፡፡
ዘመኑ፡- መስኮቶቻችንን ከፍተን በተለያየ አቅጣጫ እንድንመለከት ይጋብዘናል፡፡ በእግረ መንገድም የበሰበሰው ሥርዓት ክርፋት ወጥቶ፣ ንጹህ የዴሞክራሲ አየር፣ የአደይ አበባ ሽታ ይገባልናል፡፡ ወዳጄ፤ እዚህ ጋ አንድ ነገር ልብ በልልኝ፡፡ በከፈትካቸው መስኮቶች አሻግረህ ለማየት የምትችለው… መጀመሪያ ራስህን ስትመለከት፣ ውስጥህን መመርመር ስትችል ነው፡፡ አለበለዚያ እንደ ዴዎጋን በጠራራ ፀሐይ ፋኖስህን ይዘህ በገበያው መሃል ብትመላለስም እንኳ የምትፈልገውን አታገኝም፡፡ የሚፈልገውን የሚያገኝ የሚፈልገውን የሚያውቅ ነው፡፡… የሚፈልገውን የሚያውቅ ጠቢብ ነው፡፡ ዴዎጋን የሚፈልገውን ያውቅ ነበር፡፡…
“ምን እንደምትፈልግ ንገረኝና ላድርግልህ” ቢለው… ወዳጁና የዘመኑ ዓለም ገዢ የነበረው ታላቁ እስክንድር…
“ከፊቴ ዞር በል፣ የምፈልገው ፀሐይዋን ነው”… ብሎ ነው የመለሰለት፡፡ በዚያን ሰዓት ለሱ ከፀሐይ ብርሃን የሚበልጥበት ምንም ነገር አልነበረም፡፡
ወዳጄ፡- አሁን ባለህበት ሁኔታ ውስጥ የሚያስፈልግህን ነገር ስታውቅ ራስህን አውቅህ… ኖርህ ማለት ነው… ይላሉ ሊቃውንት፡፡… ፀሃይህን አታስነጥቅ፣ አትከለል ነው ነገሩ፡፡… እንደ ዴዎጋን “ከላያችን ዞር በሉ” በላቸው… እንደ ማለት፡፡ ሶቀራጥስም Gnothi Seauton (Know Yourself) ሲል ይህንኑ ይመስለኛል፡፡ ወደዚህ ሰብዕና የሚያመጣው መንገድ ደግሞ በመጀመሪያ ራስን ኮትኩቶ፣ አርሞና አቃንቶ (Self Cultivation, self made) መገኘት መቻል ነው ይላል፡፡  
ታላቁ ኮንፊዩሸስ፡-
“እያንዳንዱ ሰው እውነትን ካወቀ፣ ምኞቱና ፍላጐቱ ትክክለኛ ይሆናል፣ ፍላጐቱ ትክክለኛ ሲሆን ልቡ በትክክል ይመታል፣ ልቡ በትክክል ከመታ፣ ግላዊ ህይወቱ ጤነኛና በልክ የታነፀ ሲሆን፤ ሰውየው ጤነኛና በልክ የታነፀ ነው፡፡ ቤተሰቡ ጤነኛና በልክ የታነፀ ሲሆን፤ ማኅበረሰቡም ጤነኛና በልክ የታነፀ ይሆናል… ሁሉም እንዲህ ሲሆን ሰላም በአገር፣ ሰላም በምድር ይፈጠራል” በማለት ይመክረና፡፡… ‘The Great learning’… በተሰኘ መጽሐፉ ላይ፡፡… እናም ወዳጄ፤ የጤነኛ ማኅበረሰብ መሠረት የእያንዳንዱ ሰው ሰብዕና ነው፡፡ በምትከፍታቸው መስኮቶች አሻግረህ ማየት ትችል ዘንድ አንተም የልቦናህን ዓይን ክፈት!!
***
ወደ አፈ ታሪካችን እንመለስ፡- ንጉሱ ለልጁ የተላከውን መልዕክት ሲመለከት ደነገጠ ብለናል። ወዲያውም ከመሬት ላይ ተንበርክኮ፣ አማልክቶቹ ምህረት እንዲያደርጉለት መለመን ጀመረ፡፡ ልዕልቲቱ ከወዳጅዋ የተላከው ያልተጠበቀ ነገርና የአባቷ ስሜት መለወጥ ግራ ስለገባት በቆመችበት በላብ ተዘፈቀች። በዚህን ጊዜ ነው ግሪኮች አፍሮዳይት፣ ሮማውያን ቬነስ፣ ሶሪያውያን አታርጋቲስ፣ ባቢሎናውያን ኢሽታር የሚሏትና በመጽሐፍ ቅዱስ አሽቶሬት ተብላ የምትጠቀሰው የፍቅር አምላክ ወደ ልዕልቷ ጆሮ በስውር ተጠግታ… “አይዞሽ የተላከልሽን ነገር ወደ አበባነት የቀየርኩት እኔ ነኝ”… ያለቻት፡፡ በዚያን ዘመን፣ ከጥፋት ውሃ በኋላ አበባ የአዲስ ዘመን ብስራት፣ የልምላሜና የፍቅር ምልክት ተደርጐ ይቆጠር ነበር፡፡… አበባ ባለበት ደስታ አለ፣ አበባ ባለበት ሰላም አለ፣ አበባ የአማልክቶቹ ስጦታ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡… ለዚህ ነው የልጁን አንገት በሰይፍ ሊመታ የተዘጋጀው ንጉሥ፤ ልጁ ‘የመጣላትን’ የአበባ በረከት ሲያይ ትልቅ ሲሳይ የወረደለት የመሰለው፡፡ ለጥፋቱም አማልክቶቹ ቁጣን እንዳይልኩበት ነበር ተንበርክኮ የተለማመነው። የወረወረውን ሰይፍ አንስቶም በልጁ ፈንታ ወሬውን የነገረውን ባለሟል መታበት፡፡ ባለሟሉ ሲቀበር አበባውን ከላዩ ላይ አስቀመጠ፡፡ ለዚህ ነው… አበባ የአዲስ ዘመን መገለጫ፣ የፍቅር የበረከትና የልምላሜ ምልክት እንዲሁም የሙታን መታሰቢያ ሆኖ የዘለቀው ይባላል፡፡
እንቁጣጣሽ ብለሽ፣
ነይልኝ ነይልኝ፣
አበባየሁ ብለሽ
    ነይልኝ ነይልኝ፣
ደግሞ ባዲስ ፀሃይ
ባዲስ ዘመን አደይ፣
    ሁሉን ነገር ትተን
    እንሁን አንድ ላይ፣
እንቁጣጣሽ ብለሽ፣
ነይልኝ ነይልኝ፣
ላንቺ የምቀጥፈው
አበባሽ እኔ ነኝ፡፡

መልካም በዓል!!
ሠላም!!

Read 1499 times