Saturday, 15 September 2018 00:00

በግጭት ምክንያት በተፈናቀሉ ሰዎች ብዛት ኢትዮጵያ ከዓለም የመሪነት ደረጃን ይዛለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 በሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ኢትዮጵያ ከዓለም በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ሰሞኑን ይፋ በሆነው በዚህ ሪፖርት በ2018 እ.ኤ.አ. ግማሽ ዓመት በእርስ በርስ ግጭት ምክንያት ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ዜጐች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን፣ ይህም በዓለም ሃገራት ያልተለመደ መሆኑን ጠቁሟል - ሪፖርቱ፡፡
ዜጐች የተፈናቀሉባቸው ግጭቶችም በደቡብና በኦሮሚያ ድንበር አዋሳኝ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ፣ በቤኒሻንጉልና በአማራ ክልል እንዲሁም በደቡብ ክልል የወረዳ ለወረዳ ግጭቶች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
ለግጭቶቹ መበራከትና መስፋፋት በኢህአዴግ መካከል የተፈጠረው አለመግባባትና የመንግስቱን ድክመት በምክንያትነት የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ለተፈጠሩት ግጭቶችና መፈናቀሎች የመንግስትን ስልጣን የያዘው ኢህአዴግ ቀዳሚ ተጠያቂና ተወቃሽ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የተፈናቃዮች ጉዳይ አስቸኳይ እልባት ካላገኘ የከፋ ሰብአዊ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል ያለው ሪፖርቱ፤ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በተፈጠረ ግጭት 1.4 ሚሊዮን ሰዎች ከቀዬአቸው የመፈናቀላቸውን ጉዳይ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በቸልታ መመልከታቸው አግባብ አይደለም ሲልም ወቅሷል፡፡
በአሁን ወቅት ውስን የእርዳታ ድርጅቶችና መንግስት ለተፈናቃዮች እርዳታ ለማቅረብ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት አሳስቧል፡፡  

Read 5159 times