Saturday, 15 September 2018 00:00

ለቀጣዩ ብሔራዊ ምርጫ ሁሉን አሳታፊ ቅድመ ዝግጅት እንዲጀመር ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)


    በመጪው ዓመት 2012 ለሚደረገው ብሔራዊ ምርጫ አጋዥ የሆኑ ተቋማትን የመመስረትና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል አስቸኳይ ድርድር ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር እንዲጀመር በፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው “የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ” ጠየቀ፡፡
ፓርቲው በወቅታዊ መግለጫው፤ የተጀመረው ለውጥ ህዝቡ የሚፈልገውን መቋጫ እንዲያገኝ፣ በቀጣዩ ምርጫ ዙሪያ ከወዲሁ ድርድር መጀመር አለበት ብሏል፡፡
“በምርጫ ጉዳይ ለሚደረገው ድርድር ጊዜ ሊሰጠው አይገባም” ያለው ፓርቲው፤ “በገዥው ፓርቲ እየተደረገ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ ጊዜያዊ ማስታገሻ ከመሆን የዘለለ አይደለም፤ ሁሉን አሳታፊና ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥር ሥርዓት በምርጫ መመስረት ያስፈልጋል” ብሏል።
በሃገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እጅግ የተራራቁ ሃሳቦችን የሚያራምዱ ኃይሎችን የሃሳብ ልዩነቶቻቸውን ለማቀራረብና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችሉ ውይይቶች መካሄድ አለባቸው ብሏል - ፓርቲው።
በሃገሪቱ መሠረታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ድርድሮች ተካሂደው ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግ ያስታወቀው ኢሶዴፓ፤ የተጀመረውን የለውጥ ሂደትም በገዥው ፓርቲ አመራርነት ብቻ ማሳካት አይቻልም ብሏል። ለዚህም የሃገሪቱን ፖለቲካዊ ለውጥ ወደፊት ሊያሸጋግር የሚችል የብሔራዊ አንድነት መንግስት በአስቸኳይ ተመስርቶ፣ የለውጡን ሂደት መምራት አለበት ሲል አሳስቧል፡፡
ፓርቲው በዚሁ መግለጫው፤ በዋናነት ቀጣዩ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ስለ ምርጫው አስተዳደር፣ ስለ ምርጫ ውድድር ሂደቶችና ስለ ታዛቢዎች ድርድር ተደርጐ፣ ከወዲሁ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት ብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የለውጡን አላማዎች በስውር የሚቃወሙና ለውጡን ዋጋ ለማሳጣት የሚሹ ኃይሎች፣ ተጨማሪና አዳዲስ ግጭቶችን ለመፍጠር እየተዘጋጁ ነው ያለው ፓርቲው፤ በመንግስት በኩል ለህዝቡ ዘላቂ ሠላም፣ ደህንነትና አንድነት መጠበቅ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል ብሏል።

Read 4158 times