Saturday, 15 September 2018 00:00

የጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን የአሜሪካ መንግስት አደነቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታን ለመቀየር የወሰዷቸውን እርምጃዎችና ለውጡን ለማምጣት የሄዱበትን ርቀት የአሜሪካ መንግስት አደነቀ፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ ቲቦር ናጋይ፤ በዶ/ር ዐቢይ አህመድ አመራር በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች አድናቆት የሚቸራቸው ናቸው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የሃገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ የሚያደርጉ እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆኑን የጠቆሙት ቲቦር ናጋይ፤ በዚህም ለበርካታ ችግሮች መፍትሄ ማምጣት ተችሏል ብለዋል፡፡
በሃገሪቱ የተጠራቀሙ ፖለቲካዊ ችግሮችም እልባት እያገኙ መሆኑን መረዳታቸውን የጠቆሙት ኃላፊው ፤ ለመጣው ለውጥም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የአመራር ሚና አድናቆት የሚቸረው ነው ብለዋል፡፡ መንግስታቸውም በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተደረጉ ያሉ ለውጦችን በአድናቆት እንደሚመለከተው ጠቁመው፤ ለዘላቂነቱም ድጋፍ  ይቸረዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵና በኤርትራ መካከል ላለፉት 20 ዓመታት የዘለቁ  ችግሮን በሰላም ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያከናወኑት የዲፕሎማሲ ሥራ የሚደነቅና ያልተለመደ መሆኑን የጠቀሱት  ኃላፊው፤ በቀጣይ አፋኝ የሚባሉ አዋጆችን በማሻሻል የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፋ ተጨማሪ እርምጃዎች እንዲወስዱም ጠይቀዋል፡፡

Read 5083 times