Saturday, 15 September 2018 00:00

“ኢትዮጵያ መላውን ዓለም ያስደመመ ለውጥ ላይ ነች” አርበኞች ግንቦት 7

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

 ኢትዮጵያ መላውን ዓለም ያስደመመ ፖለቲካዊ ለውጥ እያደረገች መሆኑን ሰሞኑን አመራሮቹ ወደ አገር ውስጥ የገቡት “አርበኞች ግንቦት 7” ባወጣው የአቋም መግለጫው አስታወቀ፡፡
የንቅናቄው አመራሮች ወደ ሃገር ቤት ከገቡ በኋላ ባወጣው በዚህ የመጀመሪያው የአቋም መግለጫው፤ ዛሬ በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴና የለውጡ ሂደት ቀጥተኛ ባለቤት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ብሏል፡፡
“በሃገሪቱ የተካሄደው ለውጥም የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት የናፈቀውን መላውን የዓለመ ህዝብ ያስደመመ ነው” ብሏል - ንቅናቄው፡፡
ባለፉት ሁለትና ሦስት ወራት ውስጥ ለውጡን በመደገፍ፣ ለውጡን ወደፊት ለማራመድ የሚፈልጉ የሰብአዊ መብት ታጋዮች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሃይማኖት አባቶች ለብዙ ዓመታት በስደት ከኖሩባቸው ሃገሮች ወደ ሃገራቸው መመለሳቸውን ያስታወሰው የንቅናቄው መግለጫ፤ ለተመለሱት ሁሉ እኩል ክብር እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
በዜግነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካን አራምዳለሁ ያለው አርበኞች ግንቦት 7፤ “ለወደፊት የምንገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከሚፈልጋቸው ቅድመ ሁኔታዎች አንዱና ትልቁ የፖለቲካ አካሄዳቸው ከማይገጥመንና በሃሳብ ከምንለያያቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር ተከባብሮና ተቻችሎ መኖር መቻል ነው” ሲል አስገንዝቧል፡፡
ህዝቡ ለአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ፣ በመከባበርና በፍቅር ላይ የተመሰረተ አቀባበል እንዳደረገው ሁሉ፣ ሌሎች ድርጅቶችም ወደ ሃገር ውስጥ ሲገቡ ተመሳሳዩን እንዲፈፅም ጠይቋል - ንቅናቄው፡፡
“ንቅናቄው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በፅናት እየታገለ ያለው ዜጐች ድጋፋቸውንም ሆነ ተቃውሟቸውን በነፃነት መግለፅ የሚችሉበት ሥርዓት በሃገሪቱ እንዲሰፍን እንጂ አንዱ የሌላውን መብት በጉልበትና በኃይል መጨፍለቅ እንዲችል አይደለም” ብሏል፡፡
ሰሞኑን ከአርማና ሰንደቅ ዓላማ መስቀል ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ የተፈጠረው ውዝግብም ያልተገባ መሆኑንና ማንኛውም ድርጅት የየራሱን አርማ የማውለብለብ እኩል መብት እንዳለው ገለፃ፤ ሌላኛውም የሌላውን የመንካት መብት እንደሌለው ማወቅ ያስፈልጋል ብሏል ግንቦት 7፡፡  

Read 9066 times