Saturday, 15 September 2018 00:00

የኦፌኮ እና ኦነግ ውይይትና ቀጣይ ግንኙነት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በነገው ዕለት አመራሩ ወደ አዲስ አበባ ከሚገባው የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ጋር በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡ በዚህ ዙሪያ ድርጅቶቹ ምን ዓይነት ግንኙነት ለመፍጠር ነው ያሰቡት? በምን ጉዳዮች ላይ በጋራ ሊሰሩ አቅደዋል? የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በማቅረብ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የኦፌኮ ዋና ፀሐፊ አቶ ጥሩነህ ገሞታ’ን በአጭሩ አነጋግሯቸዋል፡፡


    ከኦነግ ጋር በምን አግባብ ነው በጋራ ለመስራት የወሰናችሁት?
ይሄን ያህል ጊዜ የወሰደ ውይይት አላካሄድንም። የተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው ተገናኝተን የተወያየነው። ውይይታችንም በቀጣይ የኦሮሞ ህዝብ የፖለቲካ ትግል ጉዳይ ላይ  ነበር፡፡ ሰፊ ጊዜ የወሰደ ውይይት አላደረግንም፡፡ በሰላማዊ መንገድ እንዴት መታገል እንደምንችል ነው የተወያየነው፡፡ ይሄን አቅጣጫ ለማስያዝ ነው የተነጋገርነው፡፡
በውይይታችሁ የተነሱ አንኳር ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
እውነተኛ ፌዴራሊዝም ስለሚገነባበት ሁኔታ፣ የሕግ የበላይነት ስለሚከበርበት፣ እውነተኛ ዴሞክራሲ ስለሚገነባበትና ቀጣይነት ያለው ሰላም በኢትዮጵያ ማስፈን ስለሚቻልበት ሁኔታ ነው የተነጋገርነው። ከዚህ የተለየ ነገር አልተወያየንም፡፡ በአጠቃላይ የኦሮሞም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሚፈልጉት ሁኔታ እንዴት መሄድ እንችላለን በሚለው ዙሪያ ነው የተነጋገርነው፡፡
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በምን መልኩ ነው የተወያያችሁት?
እንደሚታወቀው ኦነግ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የነበረ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ከመንግስት ጋር ባደረገው ስምምነት፤ ወደ ሰላማዊ ትግል መመለሱን ተገንዝበናል። በዚህም እውነተኛ ፌደራሊዝምና ዴሞክራሲ ግንባታ ላይ እንዴት እንደሚሳተፍ፣ እውነተኛ ፌደራሊዝም ኢትዮጵያ ውስጥ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመነጋገር እንዴት መገንባት እንደሚቻል ተነጋግረናል፡፡ ቀጣይነት ያለው ሠላምና ዴሞክራሲ በሃገሪቱ እንዲሰፍን ቀና ፍላጐት አለ፡፡ ይህን ፍላጐት በተግባር በመተርጐም ለመስራት ነው ንግግራችን፡፡ ውይይታችን አልተቋጨም፡፡ በቀጣይነት የምንወያይባቸው ጉዳዮችም አሉ፡፡ ተከታታይነት ያለው ውይይት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ገና እናደርጋለን፡፡
በጋራ ለመስራት ተስማምተናል የሚል መገለጫ ሰጥታችኋል፡፡ በጋራ መስራት ሲባል ምን ማለት ነው? እንዴት ነው በጋራ የምትሰሩት?
የደረስንበት ስምምነት በመግለጫችን በግልጽ ተቀምጧል፡፡ አንደኛው፤ የኦሮሞና የኦሮሚያ ጥቅም በዘላቂነት በሚከበርበት ሁኔታ ላይ ሃሳብ በመለዋወጥ የጋራ ግንዛቤ ላይ ደርሠናል፡፡ በዚህ የጋራ ግንዛቤ መሠረት፤ አብረን የምንሠራቸው ስራዎች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ ስምምነት ተፈራርመናል አይደለም ያልነው፡፡ በኦሮሞ ጉዳይ ላይ የጋራ ግንዛቤ ፈጥረናል፡፡ ይሄ ነው ጉዳዩ፤ ሌላ የተለየ ነገር የለውም፡፡
ኦነግ እስከ መገንጠል የሚደርስ የፖለቲካ ጥያቄ ያለው ድርጅት እንደሆነ ከኘሮግራሙ መረዳት ይቻላል፡፡ እናንተ ደግም ፌደራሊዝሙን ማጠናከር እንጂ መገንጠል አይጠቅምም  የሚል አጀንዳ ነው የምታራምዱት፡፡ በጋራ ለመስራት ስትስማሙ እነዚህ ልዩነቶቻችሁ እንቅፋት አይሆኑም?
በነገራቸን ላይ ኦነግ በኢትዮጵያ መንግስት ጋር በፈጠረው ስምምነት፤ አሁን ባለው ህገ መንግስትና የሃገሪቱ ሁኔታ በሚፈቅደው መሠረት ሃገር ውስጥ መስራት እችላለሁ፤  መስራትም አለብኝ ብሎ ነው የመጣው፡፡ ስለዚህ ቀደም ብሎ ይዞ የነበረውን ፕሮግራም በሃሣብ ደረጃ ያሻሻለ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በተረፈ አሁን ኦነግ ስለሚያራምደው አላማ የኦነግ አመራሮች ቢያብራሩ የተሻለ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አንድ ሊታሰብ የሚገባው ነገር፤ ኦነግ በ1983 በኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት በሚመሰረትበት ወቅት የሽግግር መንግስቱ አካል ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በ2010 ይሄ መንግስት ባደረገው ጥሪ መሠረት፤ ከህዝቡ ተቀላቅሎ አብሮ ለመስራት የመጣ መሆኑን ነው የምንረዳው፡፡
ስለዚህ እናንተ በኦነግ አላማዎች ትተማመናላችሁ ማለት ነው?
አንደኛ ማንም አካል በአምባገነናዊ ስርአት ስር መኖር አይፈልግም፡፡ የኦነግ ታሪክም የዚሁ አይነት ነው፡፡ አምባገነናዊ ስርአትን ነው የተቃወመው፡፡ አሁን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተስማምተው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውም ለኢትዮጵያ ህዝብ ያላቸውን ፍቅር ነው የሚያመለክተው፡፡ ከእኛ ጋርም ስንወያይ፣ ይሄን ግንዛቤ የሚያረጋግጥ ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡ ምናልባት ሠዎች ዝም ብለው በራሳቸው ጊዜና ሁኔታ ስጋት ቢፈጥሩ፣ ያ ስጋት እውነተኛ ስጋት ነው ወይ ብሎ ራስን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሰዎች ክፉ ክፉውን ከማሠብ፣ የተሻለውን ቢያስቡ የተሻለ ይመስለኛል፡፡
ኦነግ ዛሬ ወደ ሃገር ቤት ሲገባ፣ አቀባበል ታደርጋላችሁ?
እኛ ሁሉንም የተመለሡትን በደስታ ነው እየተቀበልን ያለነው፡፡ ኦነግንም በዚህ መንፈስ ነው እንኳን ደህና መጣችሁ የምንለው፡፡ በሃሣብ ልዩነት ወይም በአመለካከታቸው ተገፍተው የነበሩ ወደ ሃገራቸው ሲመለሡ በደስታ ነው የምንቀበለው፡፡
አርማን በየመንገዱ ከማቅለምና ባንዲራ ከመስቀል ጋር ተያይዞ የተነሣውን ውዝግብ በተመለከተ ኦፌኮ ምን ይላል?
ሁሉም የፖለቲካ ድርጅት የየራሱን አርማ ይጠቀማል፡፡ ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ሌላውም የራሣቸውን አርማዎች ይጠቀማሉ፡፡ የኦነግም አርማ መታየት ያለበት እንዲሁ ነው፡፡ ፎቢያ ሊሆን አይገባም፡፡ እንደ’ኔ አርማው ለሃገራችንም ለአዲስ አበባም ስጋት ሊሆን አይችልም፡፡ ምናልባት ታሪካዊ ሁኔታውን ወደ ኋላ ዞር ብሎ መመርመር ግድ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዱን ድርጅት ያልሆነ ስም ሰጥቶ አግልሎ በቆየ ሥርአት ውስጥ፣ ያ ድርጅት ወደ ሃገር ቤት ሲመለስ፣ የማይሆን ስሜት ሊፈጥር ይችላል፤ ይሄ ነገር ግን ጊዜያዊ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለየ ነገር የሚፈጥር አይመስለኝም፡፡ በተረጋጋ ሁኔታ ነገሩን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ እኔ የምሠጋው፤ እየወደቀ ያለው ቡድን፣ ከበስተጀርባ ሆኖ እየፈጠረ ያለው ሁኔታ እንዳይኖር ነው እንጂ አርማ የግጭት ሰበብ ሊሆን አይችልም፡፡
ኦፌኮ በኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ጉዳይ አቋሙ ምንድን ነው?  
ከዚህ ቀደምም ገለፀናል፡፡ ሠንደቅ ዓላማን በተመለከት፣ በአሁን ወቅት የህዝብን  ይሁንታ  የሚፈልጉ ነገሮች አሉ፤ ስለዚህ ጉዳዩን ለህዝብ ውሣኔ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ነው የተሻለው መንገድ፡፡
ኦፌኮ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅትች ጋር የሚፈጥረው ግንኙነት በምን መርህ ላይ የተመሰረተ ነው?
ኦፌኮ ከኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋርም ሆነ ከመድረክ ጋር ያለው ግንኙነት፤ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር በመፍታት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በአንድ ወይም በሁለት የፖለቲካ ድርጅቶች የሃገሪቱ ችግር አይፈታም የሚል እምነት አለን፡፡ ስለዚህ ሁሉም ተባብሮ ነው የዚህችን ሃገር ፖለቲካዊ ችግር መፍታት የሚቻለው፡፡ ኦፌኮና ኦነግ በቀጣይ የሚኖራቸው ግንኙነትም፤ በዚሁ መርህ ላይ የተመሠረተ ይሆናል፡፡

Read 1801 times