Saturday, 15 September 2018 00:00

‘አሳይቶ የማይነሳ’ ዓመት

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

  እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
‘አሳይቶ የሚሰጥ’ እንጂ ‘አሳይቶ የሚነሳ’ ዓመት እንዳይሆን አንድዬ ይርዳን! መልካም ልቦናውንም አትርፎ፣ አትረፍርፎ ይስጠንማ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ!  አንድዬ!
አንድዬ፡— ማነህ አንተ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምስኪኑ ሀበሻ ነኝ፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡— አንተው ነህ!...እንኳን አብሮ አደረሰን፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምን እያልከኝ ነው?
አንድዬ፡— እንኳን አደረሰህ ስለምትለኝ አስቀድሜ በምላሹ አዲስ ዓመት ልመኝልህ ብዬ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣  አሁን እኔ ሽቅብ ተንጠራርቼ አንተን እንኳን አደረሰህ እልሀለሁ! እንደ እሱ ስትል ሆዳችን ይባባል…
አንድዬ፡— መባባትን ምን አመጣው…
ምስኪን ሀበሻ፡— ተቀይመኸናል ብለን ነዋ! እንዲህ የሚለን ቢቀየመን ነው ብለን ነዋ!
አንድዬ፡— ለነገሩ የእናንተ ሆድ ምን የማይሆነው ነገር አለ! እኔ ትዝ የሚለኝ ለእናንተ ከሌላው የተለየ ሆድ አልሰጠኋችሁ…ጎደል ሲል መከራ፣ ሞላ ሲል መከራ፣ የሆነ መለኪያ ነገር ልግጠምላችሁ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ይሄን ያህል ታዝበኻናል?
አንድዬ፡— ስማኝ እስቲ፣ ሁሉም ነገር ልክ አለው አይደለም እንዴ! ገደብ አለው አይደለም እንዴ! እናንተ ዘላለማችሁን ብሶታችሁም፣ ደስታችሁም ልክ የሚያጣው ለምንድነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ የእውነት በጣም ነው የታዘብከን፡፡
አንድዬ፡— በነገራችን ላይ…እንኳን አብሮ አደረሰን ብዬህ፣ ምነው እስካሁን እንኳን አደረሰህ አላልከኝም?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንተው ባደረስከን፣ አንተው ከዘመን ዘመን ባሸጋገርከን ተንጠራርቼ ‘እንኳን አደረሰህ’ ልል!
አንድዬ፡— እንግዲያው ምን እግር ጣለህ?  ምን ጎደለ ልትለኝ ነው! መቼም ጎደለ እንጂ በቂ ነው የሚባል ነገር ከአፋችሁ አይወጣም፡፡ ለእናንተ ሞልቶ የሚፈሰው የባድሊ ውሀ እንኳን ጎደሎ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደው ከመጣሁ ከረም ስላልኩ ብቅ ብዬ ደጅህን ልሳለም ብዬ ነው፡፡
አንድዬ፡— ጎሽ፣ አቤቱታ ይዘህ አለመምጣትህም ጥሩ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱማ አንድዬ፣ እሱማ… አቤቱታ መች ይጠፋል ብለህ ነው፡፡
አንድዬ፡— እንግዲያ ሞኙ እኔ እንደዛ ያሰበኩት ነኝ፡፡ የሆነስ ሆነና…በነገራችን ላይ አዲሱ ዓመት እንዴት ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ያው እንግዲህ አንተ ይሁን እንዳልከው እየሆነ ነው፡፡
አንድዬ፡— ቆይ፣ ቆይ…አንተ ይሁን እንዳልከው ማለት ምን ማለት ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— ያው አንድዬ ከስቃዩ ትንሽ ልቀንስላቸው ብለህ ደግ፣ ደጉን ነገር እያሳየኸን አይደል…
አንድዬ፡— እናንተ ሰዎች… እናንተ ሰዎች… መቼ ነው ነገር የሚገባችሁ! በትንሽ፣ ትልቁ ስሜን ወዲህ፣ ወዲያ የምታንገላቱት ለምንድነው! እንዴ ለስሜም እዘኑለታ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አልገባኝም…
አንድዬ፡— እናንተ ባስነጠሳችሁም፣ ባደናቀፋችሁም፣ ትን ባላችሁም  ቁጥር ጣልቃ የምገባው አንደኛውን ሥራ ፈት አደረጋችሁኝ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ተው እንደሱ አትበል…
አንድዬ፡— እየው… አንዳንዴ  ምስጋና ካለ ለራሳችሁ ስጡት እንጂ…ስህተት ካለ ራሳችሁንም ውቀሱ እንጂ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ቢሆንም ያላንተ እርዳታ የሚሆን ነገር የለም፡፡
አንድዬ፡— እኔ እኮ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ገባኝ፣ መቼም እንደገና ጠፍጥፌ አልፈጥራችሁ ነገር…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አስቆጣሁህ እንዴ?
አንድዬ፡— ምን ያስቆጣኛል… ስማ፣ ጥሩ ነገር ሲሆን እሱ ነው ለዚህ ያበቃን ትላላችሁ፣ ክፉ ነገር ሲሆን የእሱ ቁጣ፣ የእሱ ቅጣት ነው ትላላችሁ…እስቲ ለአንድ ሰሞን ነገሮችን ሁሉ እኔ ላይ ማላከክ ይብቃችሁ…
ምስኪን ሀበሻ፡— ግን አንድዬ፣ መቼም ካነሳኸው አይቀር፣ አክራሞታችንን ስታይ ምን ታሰበህ?
አንድዬ፡— ምን ታሰበህ ማለት…
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደው አያያዛችን ምን ይመስላል…
አንድዬ፡— እናንተው ንገሩኝ እንጂ…አያያዛችሁ ምን ይመስላችኋል?
ምስኪን ሀበሻ፡— ያው እንግዲህ ምን መሰለህ አንድዬ፣ ብዙ መልካም ነገሮች እያየን ነው፣ መልካም ነገሮች እየሰማን ነው፣ መልካም ነገሮች እየተመኘን ነው…
አንድዬ፡— ይሄ ሁሉ መልካም ነገር አለ ካልክ፣ ምነው ድምጽህ ደከመብኝ…
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን መሰለህ አንድዬ…ክብድ ይለኛል፤ የሆነ ክፉ ነገር እላዬ ላይ ሊከመርብኝ የደረሰ ይመስለኛል፡፡
አንድዬ፡— ለምን እንደዛ አሰብክ!
ምስኪን ሀበሻ፡— በቃ መልካም ነገሮች ሲሆኑ፣ እንኳን በእኔ እድሜ በልጆቼም እድሜ ይሆናል ያላልኩት ነገር ስመለከት፣ የሆነ ክፉ ነገር ተከትሎ ይመጣል ብዬ ስጋት ይገባኛል፡፡
አንድዬ፡— ደስታውን ያጠፋብኛል ብለህ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አዎ አንድዬ… እንደው ደስታችን ከልክ በላይ ሆኖ አንተንም ረስተን እናስቀይምሀለን ብዬ እሰጋለሁ፡፡
አንድዬ፡— አሁንም ዞረህ እኔው ዘንድ መጣህ…ደስታችንን ታጠፋብናለህ እያልከኝ ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— ኸረ ምን ቆርጦኝ፣ አንድዬ! ኸረ ምን ቆርጦኝ!
አንድዬ፡— ታዲያ እኔን ማስቀየምን ምን አመጣው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ምን መሰለህ፣ አንዳንዶቻችን ነገረ ሥራችን ትንሽ መስመር እያለፈ፣ ድንበር እየጣሰ ሀሳብ ሆኖብናል፡፡ ለሁሉም ነገር ልክ እንዳለው የጠፋን መሰለኝ፡፡
አንድዬ፡— እኮ፣ አስተካክሉታ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ያለ አንተ እርዳታ?
አንድዬ፡— ያለ እኔ እርዳታ…እንደውም ሳስብበት የቆየሁትን ነገር አስታወስከኝ፡፡ ምን እናደርግ መሰለህ…እስከ አዲሱ ዓመት መጨረሻ ከእናንተ ጋር ያለኝን ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ አቋርጣለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን፣ አንድዬ! ምን እያልከኝ ነው?
አንድዬ፡— በቃ፣ ነገሮችን ሳያቸው ከዚህ የተሻለ አማራጭ የለም፡፡ ጭቅጭቃችሁ ሰለቸኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ሜዳ ላይ ልትተወን!  ያለንበትን ሁኔታ እያየህ ሜዳ ላይ ትተህ የአውሬ እራት ልታደርገን!
አንድዬ፡— አዎ፣ ሜዳ ላይ ልተዋችሁ፡ የአውሬ ምሳም ከሆናችሁ፣ እራትም ከሆናችሁ በራሳችሁ ምክንያት እንጂ የእኔ እጅ አይኖርበትም። ሜዳውን ምን እንደምታደርጉት የእናንተ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲሁ በሰበብ አስባቡ ትጨፍሩበት እንደሁ፣ ዘር ዘርታችሁ ታመርቱበት እንደሁ ጉዳችሁን አያለሁ።
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በቃ ወሰንክ ማለት ነው!
አንድዬ፡— እስቲ በሚቀጥሉት ሳምንታትና ወራት የምትሆኑትን አይና  እወስናለሁ፡፡ በል ደህና ሁን፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አመሰግናለሁ አንድዬ፣ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
 ‘አሳይቶ የሚሰጥ’ እንጂ ‘አሳይቶ የሚነሳ’ ዓመት እንዳይሆን አንድዬ ይርዳን! መልካም ልቦናውንም አትርፎ፣ አትረፍርፎ ይስጠን! እንደገናም…‘አሳይቶ የማይነሳ’ ዓመት ይሁንልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4202 times