Saturday, 15 September 2018 00:00

“በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ውይይት ያስፈልጋል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

• ተቃዋሚዎች ሁሉ የንጉስነትን ሚና መጫወት ይፈልጋሉ
 • ኢህአዴግ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? - ለጊዜው በችግር ላይ
 • አገሪቱ የሚያስፈልጋት ከ5 ያልበለጡ ፓርቲዎች ናቸው
 • በአሰብና ምፅዋ ወደቦች መጠቀም የለብንም - ለምን?
 • ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ምን ዓይነት መሪ ናቸው?


    የቀድሞው የፓርላማ አባልና የኢዴፓ አመራር አቶ አብዱራህማን አህመድ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሚዛናዊና በሳል የፖለቲካ ትንተናዎችን በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ የለውጥ ሂደቱን ተከትሎ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚታዩ “የደቦ ፍርድ” እና ሌሎች አስጊ ሁኔታዎች መፍትሄው የተገደበ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ነው የሚሉት አቶ አብዱራህማን፤ ምርጫ ቦርድ እንዴት ይደራጅ? ተቃዋሚዎች የሚጠብቃቸው የቤት ስራ? የኢህአዴግ እጣ ፈንታ? በሚሉና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡


    ትግሉ የተጀመረው የዛሬ 27 አመት ነው፡፡ ኢህኢዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ከአንድ በኋላ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር፡፡ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም የተካሄደ ጉባኤ ነው፡፡ በዚያ ጉባኤ ላይ ኘ/ር አስራት ወልደየስ፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበርን ወክለው ተገኝተው  ነበር፡፡ እሳቸው በኤርትራ ጉዳይ ህብረተሰቡ የነበረውን አቋም በጉባኤው ባንጸባረቁበት ወቅት ነው፣ትግሉ በይፋ የተጀመረው፡፡ እሳቸውና ሌሎች 42 መምህራን ከዩኒቨርሲቲ የተባረሩትም አቋማቸውን ካንጸባረቁ በኋላ ነው፡፡ ትግሉ የተጀመረው ያኔ ነው፡፡ አሁን ቅርብ ጊዜ የተጋጋለውን ትግል እንደ ዱላ ቅብብል ብናየው፣ የመጨረሻውን ዱላ ተቀብሎ እንደ መሮጥ ነው የሚታየኝ፡፡ ፍጥነትም ነበረው፡፡ ጐልቶ የታየውም ይሄ ፍጥነቱ ነው፡፡ አሁን የመጣው ለውጥ፣ ባለፉት 27 አመታት የተደረገ አጠቃላይ ትግል ውጤት ነው፡፡
አሁን ያለንበትን ሁኔታ ስንመለከት፣ አገሪቱ በምን አይነት ርዕዮተ አለም እየተመራች እንደሆነ ግራ አጋቢ ነው፡፡ ኢህአዴግ ነው እየመራት ያለው፤ የሽግግር መንግስት አልተቋቋመም፣ አዲስ መንግስት አልተመሰረተም፣ በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ የመሪዎች መለዋወጥ ነው የሚታየው፣ ርዕዮተ አለማቸው አብዮታዊ ዲሞክራሲ የተለወጠ ስለመሆኑ አልተነገረንም፡፡ ርዕዮተ አለም የሌለው አብዮት ወይም ለውጥ ደግም ቀጣይነቱ አስቸጋሪ የሚሆን ይመስለኛል። የሆነው ሆኖ፣ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች ከውጪ እንዲመጡ መድረጉ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሚዲያው  ቀደም ሲል ከነበረበት ማነቆ ትንሽ ፈታ ብሎ መንቀሳቀሱ፣ ህብረተሰቡ ሃሳቡን በነፃነት እየገለጸ መሆኑ ጥሩ ነገር ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ለዘመን ያጣናቸው ናቸው፡፡ አሁን ማግኘታችን መልካም ነው። ይሄ እንደተጠበቀ  ሆኖ ትልቅ -- የሆነው የለውጡን ሂደት ሲመት የነበሩ ብዙዎች ወጣተፐች ናቸው እነዚህ ወጣተቶች አሁን ያገኛቸውን ነፃነቶች  የመሸ ኮም አቅማችው ----- እያንደንዱ ነገር መሸኮምን ሰፈ --- ትጠየቃልች ስልጣን መሸከምን ይጠይቃል፡፡ ሃብት ማግኘት፣ እወቀት ማግኘት ሰፊ ትከሻን ይጠይቃል፡፡ አለበለዚያ  ያገኘነውን ነገር እንዴት እንደምንጠቀም ላናውቅ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ፡-በየጐዳናው የደቦ ፍርድ እየተሰጠ ሰዎች እየተገደሉ ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች መቆም አለባቸው፡፡ ሊቆሙ የሚችሉት  ደግሞ በመንግስት መደበኛ አሰራር አይደለም። ፖሊስን የሚሰማው የለም፡፡ የመንግስት መቅሮች ተሽመድምደዋል፡፡ የለውጡ አመራር ደግም ያለው አናቱ ላይ ብቻ ነው፡፡ ወደ ታች አልወረደም፡፡ በዚህም ታች ያለው መዋቅር የማስፈጸም አቅም አንሶታል፡፡ ይሄ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ የደቦ እንቅስቃሴው ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች የለውጡን ቀጣይነት አደጋ ውስጥ ይከታሉ የሚል ስጋት አለኝ፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን ያለንበት ሁኔታ መፈተሽ አለበት፡፡ መንግስት የተለያዩ አማራጮችን መውሰድ ይገባዋል፡፡
ለምሳሌ ምን አይነት አማራጮች?
እኔ መፍትሄ የምለው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው። እስከ ዛሬ በነበረው ሂደት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የምንጠላው የአፋኝነት ባህሪ ስለነበረው ነው፡፡ አሁን ግን ለውጥ ያመጣልን  የመንግስት አካል ነው ያለው፡፡ ይሄን የመንግስት አካል የመደገፍ ሁኔታ ይኖራል፡፡ በሱ ላይ የምናሴረው ሴራ አይኖርም፤ ስለዚህ የሚያስፈራ ነገር አይደለም፡፡ በዚያ ላይ  ደግሞ አዋጁን በተለያዩ ገደቦች አድርጐ ማወጅ ይችላል፡፡ የአስቸኳይ አዋጅ አስፈጻሚ ኮማንድ ፖስት፣ የሚሰራቸውን ሥራዎች ውስን አድርጎ ማወጅ ይቻላል፡፡ ይሄ አይነቱ አሰራር በተለያዩ አገሮች የሚሠራበት ነው፡፡ ፈረንሳይ ለሁለት አመታት ትጠቀምበት ነበር፡፡ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ አሁንም ድረስ አለ፡፡ ቱርክ ለሶስት አመታት ተጠቅመውበታል፡፡ ስለዚህ  መንግስትንም ህዝብንም የሚያስፈራው አይደለም፡፡ እንደውም ለውጡን የበለጠ ተቋማዊ  ለማድረግ ይረዳናል፡፡ ለውጡን እስከ መጨረሻው ለማስፈ.ጸም ጥሩ መሳርያችን ይሆናል ብዬ ነው የማምነው፡፡ አሁን ግን በየቦታው ሰው ይገደላል፡፡ በእርግጥ በለውጥ ሂደት ላይ እንዲህ ያሉ ክስተቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ግን ለውጥ ከመጣ በኋላ ተጨማሪ መስዋዕትነት አያስፈልግም፡፡ ለለውጡ ቀጣይነት ሲባል፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በውስን አካባቢዎች ሊደረግ ይችላል፣ በውስን ተግባራት ላይ የተወሰነ ይሆናል፡፡ ግን ተግባራዊ መደረጉ ከተለያዩ ችግሮች ሊያወጣን ይችላል፡፡
በመንግስትና በህዝቡ መካከል አለመተማመንን አይፈጥርም?
አዋጁ የሚዘጋጀው እኮ የፖሊስ፣ የፍትህ፣ የመንግስት ተቋማትን የሚያግዝ ሆኖ ነው የሚደራጀው፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ላይ መተማመን ከሌለ አወቃቀሩን ከኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ከተቃዋሚ ፓርቲዎችም መርጦ እንዲመሩት ማድረግ ይቻላል፡፡ በኮማንድ ፖስቱ ውስጥ ተቃዋሚዎች ድምፅ እንዲኖራቸው ከተደረገ መተማመን ይፈጠራል፡፡ እነሱን ሳያገል የሚሰራ ከሆነ ጠቃሚ ነው፡፡ ዋናው በቅን መንፈስ ጉዳዩን መመልከት ነው፡፡ በድሮው መንፈስ ካየነው ልክ ነው መተማመን ላይፈጥር ይችላል፤ነገር ግን አሁን ለውጥ እያመጣ ነው በምንለው አካል ነው ሂደቱ የሚመራው፡፡
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመለስ ለውጡ መሰረት እንዲይዝ በእርስዎ እምነት ምን አይነት ፖለቲካዊ ተግባራት በቀጣይ ሊሠሩ የሚገባቸው?
አንዱ የፀጥታ ስራ ነው፡፡ ሰዎች ዛሬ በሙሉ ነፃነት መንቀሳቀስ እየቻሉ አይደለም፡፡ በየክልሉ ያሉ ኢንቨስትመንቶች ተሽመድምደዋል፡፡ እንደ ጋዜጠኛ ወደተለያዩ አካባቢዎች ዞር ዞር ብላችሁ ብትመለከቱ፣ መሬቶች በሕገ ወጦች ተወርረዋል። በህጋዊ መንገድ በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች ትልቅ ስጋት ውስጥ ነው ያሉት፡፡ የእርሻ ኢንቨስትመንቶች ተሽመድምደዋል፡፡ መሬቱን አርሶ አደሮች ከብቶቻቸውን ለቀውባቸዋል፡፡ አዝመራቸው እየወደመ ነው ያለው፡፡ ይሄን ሥርዓትና መስመር ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል፤ ከፊታችን ሃገር አቀፍ ምርጫ አለ፡፡ ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲፈፀም፣ የመንግስት መዋቅሮች ፓርቲዎች ሲቀያየሩ መሽመድመድ የለባቸውም፡፡ የመንግስት የፀጥታና አስተዳደር ተቋማትም ስራቸውን በተገቢ መልኩ እየሰሩ መሄድ አለባቸው፡፡ ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ቢቋቋም፣ እነዚህን ነገሮች የማስቀጠል ስራ ይመራል ማለት ነው፡፡ በሰከነ መንገድ እነዚህን ተቋማት ውጤታማ አድርጐ የማደራጀት ስራ በዚህ ሂደት መከወን ይገባል፡፡ በተመሳሳይ የምርጫ ዝግጅትም መደረግ አለበት፡፡ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ መካሄድ አለበት፡፡ ስለዚህ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ለሂደቱ ራሳቸውን ከወዲሁ ዝግጁ ማድረግ አለባቸው። በሕገ መንግስቱ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን ለምርጫው ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ምርጫ ለማስፈፀም ደግሞ አሁን ያለው የምርጫ ማስፈፀሚያ አዋጅ በቂ አይደለም፡፡ አዋጁ ጉድለት አለበት፣ የምርጫ ሕጉ መስተካከል አለበት፣ የምርጫ ቦርዱ አደረጃጀት መፈተሽ አለበት፡፡ እነዚህ በ2011 በቀዳሚነት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሌሎች እንደ በጐ አድራጐት ተቋማት አዋጅ፣ የፕሬስ ሕግ፣ የፀረ-ሽብር ሕግም ጐን ለጐን መሻሻል አለባቸው፡፡ አፋኝ የነበሩ ሕጐች በሙሉ እየተፈተሹ መስተካከል አለባቸው፡፡ እነዚህ ሳይስተካከሉ ወደ ምርጫ ብንገባ ትርጉም የለውም፡፡ ከዚህ ውጪ የዜጐች ከክልል ክልል ተንቀሳቅሶ ሠርቶ የመብላት ሁኔታን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ሞያሌ ላይ ዳር ድንበርህን አስከብር ተብሎ የሚሞት ሰው፣ ጋምቤላ ላይ ለዳር ድንበርህ ተዋጋ ተብሎ የሚሞት ሰው፣ ቤንሻንጉል ላይ ለሚበራው መብራት አዋጣ ተብሎ የሚያዋጣ ሰው፤ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ተዘዋውሮ፣ ሠርቶ የመኖር መብቱ መረጋገጥ አለበት፡፡ የሚቋቋመው ኮማንድ ፖስትም በዋናነት ይሄን የማረጋገጥ ኃላፊነት ይኖረዋል ማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይን የለውጥ እንቅስቃሴ እርስዎ እንዴት ይገመግሙታል?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻቸውን ነው እየተንቀሳቀሱ ያሉት፡፡ ካቢኔያቸው አብሯቸው ያለ አይመስለኝም። ከካቢኔ ሚኒስትሮቻቸው የተወሰኑትን ብቻ ከጐናቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ ይመስለኛል። ለምሳሌ ከኤርትራ ጋር ያደረግነው ግንኙነት ብዙ የተመከረበት አይመስለኝም፡፡ እሳቸው ከአቶ ኢሳያስ ጋር ባላቸው የቅርብ ግንኙነት ወይም ወዳጅነት ብቻ ጥሩ ነገር ይመጣል ብሎ በማሰብ እየተሰሩ ያሉ ነገሮች ይመስለኛል፡፡ ሁለቱን ወደቦች አሰብና ምፅዋን ተጠቀሙ ስንባል በአዎንታ መቀበል አልነበረብንም፡፡ በአሰብና ምፅዋ ወደቦች መጠቀም የለብንም፡፡ የኢትዮ-ኤርትራዊያን ሃብት በእነዚህ ወደቦች መምጣት የለባቸውም፡፡
ለምን? ለዓመታት ስናልመው የነበረ አይደለም እንዴ?
ውል የታለን!? ከኤርትራ ጋር ውል ሳናደርግ፣ ባለሃብቶችን ገንዘባችሁን በዚያ በኩል አፍስሱ ማለት አስተማማኝ አይደለም፡፡ ሻዕቢያ’ኮ በድንገት ነው ጦርነት ቀስቅሶ በቢሊዮን የሚቆጠር የኢትዮጵያውያንን ሃብት ወደቡ ላይ የወረሰው፡፡ የመብራት ኃይል፣ የቴሌኮሙኒኬሽን የተለያዩ የመንግስት ሃብቶች ተወርሰዋል፡፡ ለእነዚያ የተወረሱ ሃብቶቻችን እልባት ሳናገኝ እንደገና አሁንም ውል ሳይኖር፣በወደቦቹ ተጠቀሙ ማለት አቶ ኢሳያስን አለማወቅ ነው፡፡
ምን አይነት ውል ነው የሚያስፈልገው? የተፈራረሙት ስምምነትስ?
የተፈራረሙት ነገር የመግባቢያ ሰነድ ከመሆን ባሻገር ዝርዝር የወደቡን አጠቃቀም የሚያሳይ እንዳልሆነ በወቅቱ ተነግሮናል፡፡ የወደብ አጠቃቀሙ ዝርዝር መታወቅ አለበት፡፡ ወደቡን ስንጠቀም ክፍያ የምንፈፅመው እንዴት ነው? ስንት ነው የምንከፍለው? በሊዝ ነው ወደቡ የሚሰጠን? እነዚህ ነገሮች በዝርዝር መቅረብ አለባቸው፡፡ ውሉን ያፈረሰ እንዴት ይዳኛል? ይሄም መታየት አለበት፡፡ እነዚህ መረጃዎች፣ ለህዝብም መገለፅ አለባቸው፡፡ እነዚህን ውሎች ሳንፈራረም ዝም ብለን በወደቦቹ መጠቀም ከጀመርን፣ ሌላ አዙሪት ውስጥ ነው የምንገባው፡፡ የኤርትራ መንግስት ደግሞ ታክቲካል እንጂ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ከሃገሮች ጋር ኖሮት አያውቅም፡፡ ከህወኃት ጋር የነበረውን ግንኙነት ብንመለከት፣ ወጥ አቋም ላይ የተመሠረተ አልነበረም። ቋሚ በሆነ ዘላቂነት ባለው ጉዳይ ላይ ወዳጅ ሆኖ አያውቅም፡፡ አንዲት ትንሽ ወንዝን ለመሻገር ሲፈልግ ነው ታክቲክ የሚጠቀመው፡፡ አሁን የገንዘብ ችግር አለበት፣ ወጣቶች ብዙ ጥያቄ እያነሱበት ነው፡፡ እነዚያን መስመር ለማስያዝ ሲል ነው፣ አሁን ወዳጅነት እየመሰረተ ያለው፡፡ እስቲ የትኛውን እስረኛ ነው የፈታልን? የጐረቤት ሃገራት ኬንያ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ---ኢትዮጵያውያን እስረኞችን ሲፈቱ፣ እሱ አንድም ሰው አልለቀቀም፡፡
በኤርትራ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን እርስዎ ያውቃሉ--?
አዎ፤ ለምሳሌ የፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ወንድም፣ ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ እዚያ ታስረዋል ይባላል። ካልታሰሩም አልታሰሩም ይበሉን፡፡ በተለያየ ሁኔታ የሄዱ ኢትዮጵያውያን መታሰራቸውን እንሰማለን፡፡ የሻዕቢያ እስር ቤት ውስጥ አንድ ኢትዮጵያዊ ይጠፋል? አይመስለኝም፡፡ መፍታት ስላልፈለገ ነው፡፡ ሻዕቢያ የሚፈልገው አንዳች ነገር ስላለ ነው አሁን ወዳጅነቱን የፈለገው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለህወኃት ያልሆነ ሻዕቢያ ግን ለማንም ሊሆን አይችልም፡፡
እንዴት? “ለህወኃት ያልሆነ ሻዕቢያ ለማንም ሊሆን አይችልም”--ሲሉ ምን ማለትዎ ነው-?
ሻዕቢያ ህወኃት ስትመሰረት ጀምሮ ድጋፍ ሲያደርግላት፣ እሷም ድጋፍ ስታደርግለት የነበረ ነው። ባለ ብዙ ባለውለታዋ ነች፡፡ ግን ከህወኃት ጋር ዘላቂነት ያለው ግንኙነቱን ማጠናከር አልፈለገም። አሁን ከሌሎች ክልል መሪዎች ወይም የኦሮሚያና የአማራ ክልል አመራሮችን አስመራ ላይ ሲያነጋግር፣ ጐረቤቱ የሆነችውን የትግራይ ክልል መሪን ለማነጋገር ፍላጎት አላሳየም፡፡ ይሄ የሚያመለክተው፣ ለህወኃት ጥላቻ እንዳላቸው ነው፡፡ አንድ አይነት ቋንቋ የሚናገሩ ማኅበረሰቦችን የሚመሩ ሁለቱ ድርጅቶች መግባባት አልቻሉም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ቅርቡ ላለው ህወኃት ያልሆነው ሻዕቢያ፤ ለሌላውም ይበጃል ማለት አይቻልም፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን በመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቀዳጁትን ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ እንዴት ያዩታል?
ለእሳቸው እየተሰጠ ያለው ድጋፍ ለኔ የሚያመለክተኝ፣ “ህዝበኝነታቸውን” ነው፡፡ እሳቸው ህዝበኛ (Populist) መሪ ናቸው፡፡ የህዝብን ስሜት ተከትለው ነው የሚጓዙት፡፡ ስለዚህ ድጋፉ ከዚህ የመነጨ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንደ አንድ የፖለቲካ መሪ፣ህዝበኝነት የሚያስፈልግበት ጊዜ አለ፡፡ በምርጫ ወቅት ህዝበኛ የሆኑ ሃሳቦችን ይዞ፣ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ በየትም ሃገር የተለመደ ነው። የአሜሪካው ትራምፕም በህዝባቸው የተወደዱት “አሜሪካ ትቅደም!” ስላሉ ነው፡፡ መደበኛ በሆነው የፖለቲካ ህይወት ግን የህዝብን ጥያቄዎች ትሰማለህ እንጂ የህዝብን ስሜት ተከትለህ አትነጉድም፡፡ መሪ እንደመሆንህ፣ የህዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ የራስህን ስትራቴጂዎች ነድፈህ፣ ከስሜት የጸዱ ስራዎችን ነው መስራት ያለብህ፡፡ አሁን ዶ/ር ዐቢይ እየሄዱ ያሉት የህዝብን ስሜት ተከትለው ነው። በተቃራኒው ከድርጅታቸው ከኢህአዴግ ደግሞ ትንሽ የመነጠል ሁኔታ ይስተዋልባቸዋል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ከምናውቀው ወግ አጥባቂው  ኢህአዴግ ከሚከተለው መርህ፣ በጣም ያፈነገጡ ቋንቋዎች ሁሉ ነው የሚጠቀሙት፡፡ ይሄ መርገብ አለበት፡፡ ህዝበኝነት ሁልጊዜ ይዘውት የሚሄዱት ነገር አይደለም፡፡ እሳቸው ረግበው፣ የህዝቡን ስሜትም ማርገብ አለባቸው፡፡
ባለፉት ወራት በተወሰዱ የፖለቲካዊ ማሻሻያ እርምጃዎች በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሃገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ የተለያየ ርዕዮተ ዓለምና አመለካከት ያላቸው ድርጅቶች ወደ ፖለቲካ ምህዳሩ መምጣታቸው፣ ምን አንደምታ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?
ዶ/ር ዐቢይና እሳቸው የሚመሩት መንግስት በዚህ ረገድ ያመጡት ማሻሻያ፤ ተቃዋሚዎችን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከታቸው ይመስለኛል፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ተቃዋሚዎች፤ ኢህአዴግ አፈረሰን፣ ኢህአዴግ እንዳንቀሳቀስ አደረገን-- በማለት በለቅሶ ውስጥ ነው ያሳለፉት፡፡ አሁን ያ ሁሉ ቀረ፡፡ እስቲ አሁን ራሳቸውን ያደራጁ፡፡ በሃሳብ ዙሪያ ይሰባሰቡ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ተቃዋሚዎች ሁላችንም፤ የንጉስነትን ሚና መጫወት ነው የምንፈልገው፡፡ ይሄ መቅረት አለበት፡፡ አፄ ቴዎድሮስን ያነገሷቸው እነ ገብርዬ፣ እነ ጋልሞ ናቸው፡፡ የእነ ጋልሞን ሚና የሚጫወት ሰው በየፓርቲዎቹ ውስጥ መፈጠር አለበት፡፡ ሁላችንም ንጉስ መሆን የለብንም፤ ልንሆንም አንችልም፡፡ ፓርቲዎች መሪያቸውን ከመረጡ በኋላ በዚያ መሪ ዙሪያ ተሰባስበው፣ ያንን መሪ እየደገፉ መስራት ነው ያለባቸው፡፡ ፓርቲዎች ሲከፋፈሉ የምንመለከተው፣ ሁሉም መሪ መሆን ስለሚፈልግ ነው፡፡ ሁሉም የሊቀ መንበርነትን ቦታ ስለሚፈልግ ነው፡፡ ይሄ መቅረት አለበት፡፡ ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ ጋር ለብሔራዊ እርቅ ከመቀመጣቸው በፊት ከራሳቸው ጋር እርቅ መፈፀም አለባቸው፡፡ እዚያ ውስጥ ያለው ሽኩቻ ቀላል አይደለም፡፡ ፓርቲዎች በሃሳብ ዙሪያ ይሰባሰቡ። ከዚህ አንፃር ወደ ሃገር ቤት የገቡትም ሆነ ነባሮቹ ፓርቲዎች፤ ብዙ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡
እንዴት ቢሰባሰቡ ወይም ቢደራጁ ነው ለራሳቸውም ሆነ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱት ትላለህ?
እኔ እንደሚታየኝ፤ ኢትዮጵያ እንደሰለጠኑት ሃገሮች፣ ኮንሰርቫቲቭ (ወግ አጥባቂ) ፓርቲዎች ሊኖሯት ይገባል። ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲዎች፤ በተለይ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች፤ በስፋት ባህላችን፣ ማህበራዊ መሠረታችን፣ ቅርሶቻችን -- እንዲጠበቁ እያሉ የሚጮሁ መሆን አለባቸው፡፡ በሌላ ወገን ዴሞክራቲክ ፓርቲዎች ደግሞ ያስፈልጉናል፡፡ ሊበራል ዴሞክራት ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ። ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲዎችም ሊኖሩን ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች ሊኖሩን ይገባል፡፡ በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች፤ አንድ ላይ ሰብሰብ ብለው፣ አስተሳሰባቸውን የሚጠብቅ አንድ ግዙፍ ፓርቲ ማቋቋም ይችላሉ። አስር የኦሮሞ፣ አስር የአማራ፣ አስር የትግሬ፣ አስር የጉራጌ፣ አስር ወዘተ ፓርቲዎች ከሚኖሩ፣ አንድ ግዙፍ የህብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ቅርፅ ያለው፣ ነገር ግን ለብሄራቸው ጥያቄ የቆሙ ፓርቲዎች የተሰባሰቡበት፣ የብሄሮችን ጥያቄ የሚያስመልስ ፓርቲ መቋቋም አለበት፡፡ ህዝቡም የአመለካከቱን ባለቤትና ጥቅሙን የሚያስከብሩለትን ፈልጐ ለመደገፍ አይቸገርም። ማኅበራዊ መሠረታቸው የጠነከረ ፓርቲዎች ሊፈጠሩ የሚችሉት በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል የፓርቲ ምስረታ አዋጅም መፈተሽ አለበት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየቀኑ የማይፈለፈሉበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል። ከአምስት ያልበለጡ፣ ከሁለት ያላነሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው ሃገሪቱ የሚያስፈልጋት። ለዚህ እውን መሆን ደግሞ ፖለቲከኞች መወያየት አለባቸው፡፡
በእርስዎ ምልከታ፣ አሁን ኢህአዴግ የሚገኝበት ፖለቲካዊ ቁመና ምን ይመስላል?
ኢህአዴግ አሁን ችግር አጋጥሞታል፡፡ ይሄ የማይካድ ነው፡፡ ነገርግን ኢህአዴጐች ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት ውስጥ እንዴት ራሳቸውን አክመው ማዳን እንደሚችሉ ያውቁበታል፡፡ አሁንም ያጋጠማቸውን ስንጥቅ ይደፍኑታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይሄን ስንጥቅ በዘላቂነት ለመድፈን ግን ከግንባር ወደ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲ፣ ሽግግር ማድረግ አለባቸው፡፡ አንድ የብሔር ጥያቄዎችን የሚመልስ ህብረ ብሄራዊ ተራማጅ ፓርቲ ራሱን አድርጐ ቢያወጣ ውጤታማ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ከዚህ በመለስ ግን ኢህአዴግ ይሰነጣጠቃል ብሎ ማሰብ ትንሽ አስቸጋሪ ነው። ሁሉን አቀፍ ፓርቲ ሆኖ፣ዋና ትኩረቱ ግን የብሔሮችን ጥያቄ የሚመልስ አድርገው ሊያዋቅሩት ይችላሉ፡፡
በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ ብሔራዊ መግባባት ላይ ደርሰናል ብለው ያስባሉ?
አልደረስንም፡፡ ምክንያቱም በሠንደቅ ዓላማ፣ በመንግስት አርማ ላይ፣ ኢትዮጵያን እንዴት ነው የምናያት በሚለው፣ በፌዴራሊዝም አወቃቀሩ ላይ ገና አልተስማማንም፡፡ ነገር ግን ይሄን መስራት ያለበት ህዝቡ አይደለም፡፡ ፖለቲከኞቹ ናቸው በጓዳ መስራት ያለባቸው። ውይይቶችን የሚያቀላጥፉ ተቋማት መፈጠር አለባቸው። ለምሳሌ ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ፣ በምርጫ 97 ወቅት ጥሩ ነገር ሠርቷል፡፡ አሁንም እንዲህ ያሉ ተቋማት ያስፈልጋሉ። ከተነጋገርን በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ መግባባት ላይ እንደርሳለን፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ጉዳዮች በጓዳ ነው መሠራት ያለባቸው፡፡ ፖለቲከኞች ጉዳዩን መክረው ነው ወደ ህዝቡ መውጣት ያለባቸው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን እንደገና ቁጭ ብለን መፈተሽ ይኖርብናል፡፡ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ መወያየት ይገባናል። አለመነጋገራችን ነው ብዙ ችግር እየፈጠረ ያለው። ገመድ ጉተታ ውስጥ ከመግባት ይልቅ በመነጋገር ያለብንን ልዩነቶች መፍታት እንችላለን፡፡  
እርስዎ ምን አይነት የፖለቲካ ስልት ነው ለዚህች ሃገር ጠቃሚ ነው ብለው የሚያምኑት?
በመጀመሪያ ደረጃ አሁን አብዛኛው ሰው እንደሚፈልገው፣ በብሔር መደራጀት እንፈልጋለን የሚሉ ሰዎች ሃሳባቸው ሊከበር ይገባል፡፡ መብታቸው ነው። መብት መሆኑን ማወቅና እውቅና መስጠት አለብን። ይሄ አደረጃጀት ግን አይጠቅምም ብለን መከራከር እንችላለን። ይሄን ስናደርግ በመበሻሸቅ መልኩ መሆን የለበትም። እኔ የምደግፈው ህብረ ብሔራዊ አደረጃጀትን ነው፡፡ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪ እንደመሆኔ መጠን ሰው በአመለካከት ዙሪያ ነው መሰባሰብ ያለበት የሚል አቋም ነው ያለኝ፡፡ አመለካከት ብሔር አይጠይቅም፡፡ ሊበራል፣ ሶሻል ዴሞክራት የሚል አስተሳሰብ ነው እንጂ ያለው ብሔር አይደለም መለኪያው፡፡ የትኛውን ሃሳብ ትመርጣለህ ነው ጉዳዩ፡፡ የብሔር ጥያቄዎች በሰለጠኑት ዓለምም አለ፡፡ ነገር ግን እነዚያን የብሔር መብት ጥያቄዎች የሚያስመልሱት፣ በአመለካከት ዙሪያ በተሰባሰቡት ፓርቲዎች በኩል ነው። ለምሳሌ ቤልጂየም ውስጥ “ፍሌሚሽ” የሚባሉ ጐሳዎች አሉ፡፡ እነዚህ ጐሳዎች፣ ጥያቄዎቻቸው በሊበራል ፓርቲዎች በኩል ነው እንዲነሳላቸው የሚያደርጉት እንጂ በብሔር ተደራጅተው አይደለም። ጣሊያን ሃገርም ተመሳሳይ ነገር እንዳለ አውቃለሁ። ለኢትዮጵያ ህዝብም በዚህ መልኩ መደራጀት ነው የሚጠቅመው የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ እኔ በዜግነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካን ነው የማራምደው፡፡
እንደ አገር ተስፋና ስጋቶቻችን ምንድን ናቸው ይላሉ?
በዚህ ወቅት ለሃገሪቱ ደጀን፤ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች አይደሉም፡፡ ደጀኗ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱ እንዳይፈርስ የመጠበቅ ኃላፊነት የተጣለባቸው መከላከያ ሠራዊት፣ ፖሊስ፣ የፍትህ ሥርዓቱ ናቸው። እነዚህ ተቋማት ጠንክረው መስራት አለባቸው፡፡ ሁላችንም ልናግዛቸው ይገባል፡፡ ኃላፊነቱ በእነዚህ ተቋማት ላይ ያለ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ሌላው ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ግንቦት 2012 መካሄድ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ያንን ማስፈፀም ካልቻለች ወድቃለች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እንዳንወድቅ ጠንክረን መስራት አለብን፡፡ ስጋቴ የውጭ ኃይሎች በመንግስታችን ላይ የተለያዩ ተፅዕኖዎችን እንዳያሳድሩ ነው፡፡ እነዚያን ተፅዕኖዎች አሁን ያለው መንግስት መመከት አለበት፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካልታወጀ፣ አሁን የተጀመሩ ጠቦችና ግጭቶች አይለው መገዳደል ውስጥ ሊከቱን ይችላሉ፡፡ ይሄ በሚገባ ሊጤን ይገባዋል፡፡ ቤተሰብ፣ ሚዲያዎች፣ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች ---ወጣቶችን አቅጣጫ ማሳየት ማስተማር፣ መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው አሁን ሁላችንም አደባባይ ላይ ነው ያለነው፡፡ ፌስ ቡክ አደባባይ ላይ በሞቅታ ውስጥ ነን፡፡ ከዚህ አደባባይ ወደ ቤታችን ስንመለስ ጓዳችን ባዶ ሆኖ ነው የሚጠብቀን። የኢኮኖሚ ጥያቄ በየቤታችን አለ፡፡ ፋብሪካዎች በተለያዩ ምክንያቶች እየተስተጓጐሉ ናቸው፡፡ በቂ ምርት የለንም፤ ግብርናችን እየሰራ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሰው ከአደባባይ ወደ ቤቱ ሲመለስ፣ የኢኮኖሚ ጥያቄ ይጠብቀዋል፡፡ ይሄን የኢኮኖሚ ጥያቄ ለማስመለስ ደግሞ መልሰን ወደ አደባባይ እንዳንወጣ ስጋት አለኝ። ስራ ስጡን፣ ወደሚል ውትወታ መግባታችን የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ መንግስት ሥራ ፈጠራ ላይ መትጋት አለበት፡፡ አንደኛው የስራ ፈጠራ መንገድ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሰፊው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ነው፡፡ ለመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሩ መከፈት አለበት፡፡ በሌላ በኩል፤ ዜጐቻችን በባህር እየሄዱ ከሚሞቱ በህጋዊ መንገድ  ወደ ውጪ አገራት ሄደው፣ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ሸጠው ገንዘብ እንዲያገኙ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ ኤምባሲዎቻችን በዚህ ረገድ የዜጐችን ሰብአዊ መብት እንዲያስከብሩ ማድረግ አለብን፡፡ አለበለዚያ የኢኮኖሚ ጥያቄው አፍንጫችን ስር ቆሞ እየጠበቀን ነው፡፡ 

Read 3925 times