Print this page
Saturday, 12 May 2012 10:31

የቀ.ኃ.ሥ የሐረር ጦር አካዳሚ ፍሬ

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሰማ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ በሳንድኸርስት ወታደራዊ አካዳሚ

ፋሺስት ኢጣሊያ ተባርሮ ነጻነት ከተመለሰ ወዲህ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያ ትኩረት ካደረገችባቸው የአገር ግንባታ መሠረቶች መካከል የዘመናዊ መከላከያ ግንባታ አንዱ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ከኢጣሊያ ወረራ በፊት የዘመናዊ መከላከያ ኃይል ውጥኖች የነበሩ ቢሆንም የተስፋፉ እና የተደራጁ ባለመሆናቸው ወረራውን ለመመከት ያስቻሉ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም ነጻነት እንደተመለሰ ዘመናዊ የጦር ኃይል ግንባታ የመንግሥት ቅድሚያ ተግባር ሆኖ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ከወረራ ገና ተላቃ በሁለት እግሯ በቅጡ ላልቆመችው አገር፤ የሠራዊት ምሥረታና ሥልጠና የሚፈልገው ብዙ ገንዘብና የሠለጠነ የሰው ኃይል እጦት ከፍተኛ ችግር መሆኑ አልቀረም፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት የተቻለው በዲፕሎማሲው መስመር በተደረገው ታላቅ ተጋድሎ አማካኝነት የወዳጅ መንግሥታት እርዳታ ሊገኝ በቻሉ ነበር፡፡

ይህን ቁልፍ እርዳታ በማበርከት ረገድ ምዕራባውያን የነበራቸው ተሳትፎ ግንባር ቀደም የነበረ ሲሆን ያተኮረውም የኢትዮጵያን ሠራዊት በማሠልጠንና በማስታጠቅ ላይ ነበር፡፡

በመሆኑም በመጀመሪያዎቹ አመታት እንግሊዝ የጦር ሠራዊትንና ፖሊስን በመመስረት እርዳታዋን ያበረከተች ሲሆን በኋለኞቹ አመታት ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በነበራት የወታደራዊ እርዳታ ስምምነቶች መሠረት ሁሉን አቀፍ የሆነ የወታደራዊ ስልጠና እና ትጥቅ ድጋፍ በማድረግ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የመከላከያ ኃይል ግንባታ ቁልፍ አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር ኃይልን በመመስረትና በማቋቋም የስዊድን መንግሥት የማይዘነጋ እርዳታውን የሰጠ ሲሆን፤ የኖርዌይ መንግሥት ደግሞ  የኢትዮጵያን የባሕር ኃይል በማቋቋም ኢትዮጵያን የባህር መከላከያ ኃይል ከገነቡ አገራት ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓል፡፡ ህንድ እና እሥራኤል ደግሞ በትምህርትና በሥልጠና እርዳታቸውን በማበርከታቸው፣ አገሪቱ ዓለምአቀፍ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ሠራዊት እንድትገነባ አስችለዋታል፡፡

ትምህርት ለዘመናዊ የመከላከያ ኃይል ግንባታ ቁልፍ መሆኑን የተገነዘበው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት፤ በሀገር ውስጥ ከፍተኛ የወታደራዊና የፖሊስ መኮንኖች ማሰልጠኛ አካዳሚዎችን አቋቁሟል፡፡

በዚህም መሠረት ለጦር ሠራዊቱ የቀ.ኃ.ሥ የሐረር ወታደራዊ አካዳሚ እና የሆለታ ገነት ጦር ት/ቤት፤ የአየር ኃይል የበረራና የሜካኒኮች ት/ቤት፤ የፖሊስ ኮሌጅ፤ የባህር ኃይል አካዳሚ ተመስርተው በውጭ ሀገር እና በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ብቃት ያለው ስልጠና በመስጠት፣ በየተሰማሩበት የሙያ መስክ አንቱ የተባሉ መኮንኖችን ለማፍራት ችለዋል፡፡

እንዲሁም ትምህርቱ ከላይ በተገለጹት ወታደራዊ አካዳሚዎች ብቻ ሳይወሰን በርካታ መኮንኖች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መደበኛ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ከመደረጉም በላይ ብዙ መኮንኖች ወደ አውሮፓና አሜሪካ እየተላኩ ዝነኛ በሆኑ ወታደራዊ አካዳሚዎች የላቀ ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ በመደረጉ፣ የሠራዊቱን የብቃት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ተችሏል፡፡

ከተመሠረቱት ኢትዮጵያዊ ወታደራዊ አካዳሚዎች መካከል በሚሰጠው የትምህርት ጥራት ደረጃ በቀዳሚነት የተመሰገነው ሐረር የሚገኘው የቀዳሚዊ ኃይለሥላሴ የጦር አካዳሚ ነው፡፡

የቀ.ኃ.ሥ ሐረር ጦር አካዳሚ ሥራ የጀመረው በ1950 ዓ.ም ከህንድ በመጡ ምርጥ መኮንኖችና ምርጥ መምህራን ሲሆን፤ ለተቋሙ የተቀረፀው ሥርዓተ ትምህርትና ወታደራዊ ሳይንስ በዓለም ከታወቁ ስመ ጥር የአሜሪካን፣ የእንግሊዝና የፈረንሳይ አካዳሚዎች ጋር አቻ ወይም ተመጣጣኝ በሆነ ደረጃ ላይ ነበር፡፡

መጀመሪያ ወደ ሐረር ጦር አካዳሚ የገቡት ወጣቶች የተመለመሉት በንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ትዕዛዝ መሠረት፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በተለያዩ ፋከልቲዎች ተመድበው በመማር ላይ ከነበሩት ተማሪዎች ውስጥ ነበር፡፡

ሰልጣኞቹ በአካዳሚው ወታደራዊና የአካዳሚ ትምህርታቸውን ለሶስት ዓመታት የሚከታተሉ ሲሆን፤ ሲመረቁም ዲፕሎማ ይቀበላሉ፡፡ የሚሰጣቸው ማዕረግም የምክትል የመቶ አለቅነት ማዕረግ ነበር፡፡

የመጨረሻው ህንዳዊ የአካዳሚው አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ሺዎዳን ሲንግ በ1959 ዓ.ም ስለ ሐረር ጦር አካዳሚ ሲናገረ “በዘመናዊ መንገድ የተዋቀረ የላቀ ደረጃ ያለው በአፍሪካ የመጀመሪያው ወታደራዊ አካዳሚ ነው፡፡ የትምህርት ጥራት ደረጃው በአለም ላይ ካሉት ከማንኛውም ወታደራዊ አካዳሚ ጋር መወዳደር ይችላል፡፡ ከእጩ መኮንኖቻችን አንዱ ወደ ሳንድኸርስት ወታደራዊ አካዳሚ ተልኮ ስልጠናውን በአንደኝነት አጠናቆ ተመልሷል” በማለት ተናግረው ነበር፡፡

ደረጃ በደረጃ መምህራኑን በራሱ በአካዳሚውና በውጪ በተማሩ ኢትዮጵያውያን መኮንኖች ሲተካ የቆየው የሐረር አካዳሚ፤ በመጨረሻ ጀነራል ኃይሌ ባይከዳኝ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የአካዳሚው አዛዥ ሆነው በ1959 ዓ.ም ተሾሙለት፡

ከዚህ አካዳሚ ተመርቀው የወጡት መኮንኖች በመላው የሠራዊቱ መዋቅር ውስጥ እየተመደቡ ችሎታቸውን በማስመስከር የእውነተኛ ወታደራዊ መኮንን ተግባራቸውን ፈጽመው ሰራዊቱንና አገራቸውን አኩርተዋል፡፡ አካዳሚው ኢትዮጵያውያንን ብቻ በማሰልጠን ሳይወሰን በወቅቱ ገና ነጻነታቸውን ከተጐናፀፉ የአፍሪካ አገራት የመጡ ምልምሎችን አሰልጥኖ በማስመረቅ፣ የአፍሪካዊ ወንድማማችነት ግዴታውን ተወጥቷል፡፡

የዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነች በቀ.ኃ.ሥ ሐረር ጦር አካዳሚ መምህር የነበረ እና ለተጨማሪ ስልጠና እንግሊዝ ወደሚገኘው ሳንድኸርስት ወታራዊ አካዳሚ የገባ አንድ ኢትዮጵያዊ ሊማር በሄደበት አካዳሚ፣ አሰልጣኝ ሆኖ ማገልገሉን ቆየት ያሉ ሰነዶችን ሳገላብጥ ያገኘሁት መረጃ ነው፡፡ ለዚህ መንደርደሪያ እንዲሆነን የሳንድኸርስት ወታደራዊ አካዳሚን ታሪክ እንቃኝ፡፡

እ.ኤ.አ በ1941 ዓ.ም ለንደን ውስጥ የተመሰረተው ሮያል ሚሊታሪ አካዳሚ እና እ.ኤ.አ በ1802 ዓ.ም የተመሰረተው የሮያል ሚሊታሪ ኮሌጅ ተዋህደው የሮያል ሳንደኸርስት ወታደራዊ አካዳሚን በ1947 ዓ.ም መሠረቱ፡፡

ይህ ዝነኛ የወታደራዊ አካዳሚ ስመ ጥር የጦር መሪዎችንና ወታደራዊ ስትራቴጂስቶችን አፍርቷል፡፡ የተቋሙ የትምህርት ጥራት በአሜሪካ ከታወቀው (United States Military Academy at West Point እና ከፈረንሳዩ (Saint Cyr) የሳን ሲር ልዩ ወታደራዊ አካዳሚ ጋር እኩያ ነው፡፡ አካዳሚው ከመላው ዓለም የሚመጡ ምርጥ ዕጩዎችን በፈተና የሚቀበል ሲሆን፤ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ወታደራዊ መኮንኖች እዚህ አካዳሚ የመግባት ዕድል ገጥሟቸዋል፡፡

ልክ የዛሬ አርባ ዓመት በሰኔ ወር 1964 ዓ.ም ከዚሁ ከሳንድኸርስት ወታደራዊ አካዳሚ አንድ አስገራሚ ዜና ተሰማ፡፡ ይኸውም አንድ ጥቁር አፍሪካዊ ለመጀመሪያ ጊዜ በትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን በማሰልጠን ላይ መሆኑን የሚገልጽ ነበር፡፡ በእርግጥ ሳንድኸርስት አፍሪካውያንን ሲያሰለጥን ለመጀመሪያ ጊዜ አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ ጥቁር አፍሪካዊን በአሰልጣኝነት ተቀብሎ ወደ ቅጥሩ ሲያስገባ ግን በታሪኩ የአሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ ነው ይላል - የዚያን ዘመኑ ዜና፡፡

ዜናው እ.ኤ.አ የ1972 ዓ.ም የሳንድኸርስት ወታደራዊ አካዳሚ ካዴቶች ከፊሉን የትምህርት አመቱን ስልጠና የሚወስዱት ከአንድ አፍሪካዊ ወታደር ይሆናል፣ የአካዳሚው ካዴቶችም ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ጥቁር አፍሪካዊ ወታደራዊ ትዕዛዝ ይቀበላሉ ካለ በኋላ አፍሪካዊው የ26 ዓመት ዕድሜ ያለውና የተስተካከለ ቁመና የተቸረው ለግላጋ ወጣት ወታደር ነው ብሏል፡፡

ወጣቱ አፍሪካዊ የሳንድኸርስት አሰልጣኝ ኢትዮጵያዊ ሲሆን ሻምበል ተስፋዬ ትርፌ የተባለ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ጦር ሠራዊት አባል ነው፡፡ ወደ ሳንድኸርስት ወታደራዊ አካዳሚ በጥር ወር 1964 ዓ.ም የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ አሠልጣኝ ሆኖ ከመምጣቱ በፊት፣ ሐረር በሚገኘው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወታደራዊ አካዳሚ መምህር በመሆን አገልግሏል፡፡ ሻምበል ተስፋዬ በሐረር አካዳሚ የሚያስተምረው ወታደራዊ ታክቲክ በመባል የሚታወቅ ትምህርት ነበር፡፡

ስለዚሁ ጉዳይ በወቅቱ ሻምበል ተስፋዬ ሲያስረዳ እ.ኤ.አ ከ1966 እስከ 1967 ዓ.ም የሳንድኸርስት እጩ መኮንን ነበርኩ፤ ወደ አካዳሚው እንደገና ስመለስ በጣም ደስ እያለኝ ነው፡፡

በዚህ የተከበረ አካዳሚ የራሴ የትምህርት ዘርፍ የሆነውን ወታደራዊ ታክቲክ በማስተማር ላይ ነኝ፡፡ እዚህ በማስተማር ያካበትኩት እውቀት ለሐረር አካዳሚ ሥራዬ በጣም ጠቃሚ ይሆናል በማለት ይገልጻል፡፡

ሻምበል ተስፋዬ በመቀጠልም፤ “የምትመለከቱትን ሠራዊት እወደዋለሁ፤ ውትድርና የማፈቅረው ሥራዬ ነው፤ ሌላ ምንም ሙያን መንካት አልፈልግም” ያለ ሲሆን ቢሳንድኸርስት ወታራዊ አካዳሚ ማስተማርን በሐረር አካዳሚ ከማስተማር የተለየ ሆኖ እንዳላገኘው ከገለፀ በኋላ፤ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት በአፍሪካ የታወቀ የሆነው በምንሠጠው የረቀቀ ሥልጠና የተነሳ ነው ሲል አክሏል፡፡

ይኸው የዚያን ዘመን ዜና ሻምበል ተስፋዬ፤ በሳንድኸርስት አካዳሚ አንድ ዙር አሰልጥኖ መጨረሱን አትቶ፣ በነሐሴ ወር 1964 ዓ.ም ወደ አገሩ ወደ ኢትዮጵያ እስከሚመለስ ድረስ ሻምበሉ ራሱ British Army Junior Division Staff Course ሥልጠና ይከታተላል ብሏል፡፡ በመስከረም ወር 1965 ዓ.ም ሻምበል ተስፋዬ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ለተመሳሳይ ፕሮግራም ሌላ ኢትዮጵያዊ መኮንን ወደ ሳንድኸርስት ወታደራዊ አካዳሚ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሳንድኸርስት ወታደራዊ አካዳሚ ከዝነኞቹ መምህራን ጋር ያስተማረው ሻምበል ተስፋዬ፤ ወደ ሐገሩ ሲመለስ እርሱን የሚተካው እና ገና ስሙ ያልታወቀው ኢትዮጵያዊ መኮንን ምን እንደሚመስል ለማወቅ የሳንድኸርስት መምህራን በጉጉት ላይ ናቸው ሲል የዘመኑ ዜና አትቶ ነበር፡፡

የሳንድኸርስት ወታደራዊ አካዳሚ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ማይክ ቴይለር፤ አካዳሚው ሌላ መምህር ከአፍሪካ አገር ያስመጣ እንደሆን ተይቀው ሲመልሱ፤ “እኔ እስከማውቀው ድረስ ከየትም ከሌላ አፍሪካዊ አገር አሰልጣኞችን የማምጣት ሃሳብ የለንም በእርግጥ ይህንን ወደፊት የምንመለከተው ይሆናል፡፡ የሆነው ሆኖ ከኢትዮጵያ ጋር ያለን የልውውጥ ፕሮግራም ግን ይቀጥላል” ማለታቸው በወቅቱ ተዘግቧል፡፡

አንድ የሳንድኸርስት እጩ መኮንን ስለ ሁኔታው ሲናገር፤ ብዙዎቹ የውጪ ሀገር የሳንድኸርስት ሰልጣኞች ሻምበል ተስፋዬን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመለከቱ ግር እንዳላቸው ጠቅሶ፤ ይህም የሆነው መምህራኑ ሁሉ እንግሊዛውያን ይሆናሉ የሚል ግምት ስለነበራቸው ነው፤ በመጨረሻም ከዚህ ኢትዮጵያዊ መኮንን ጋር በመግባባት ሊዘልቁ ችለዋል ብሏል፡፡

ይህ የያኔው ወጣት መኮንን በስተኋላ በደርጉ ዘመን እስከ ከፍተኛው የሠራዊቱ አመራር ደረጃ የደረሱት ብርጋዴር ጀነራል ተስፋዬ ትርፌ ናቸው፡፡ ጀነራል ተስፋዬ ተርፌ ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ወታደራዊ አገዛዝ ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድርገዋል ተብለው፣ በአዲስ አበባ ለአንድ ዓመት ከታሰሩት በኋላም የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ግንቦት 12 ቀን 1982 ዓ.ም ከተገደሉት 12 ከፍተኛ ጀነራል መኮንኖች አንዱ ነበሩ፡፡ ጀነራል ተስፋዬ ትርፌ፤ በመፈንቅለ መንግስቱ ጦስ እስከታሰሩበት ጊዜ ድረስ የመከላከያ ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ነበሩ፡፡ በ1966 ዓ.ም ከፈነዳው ህዝባዊ አብዮት ወዲህ አገሪቱ በብዙ አቅጣጫዎች ያሳየችው የኋሊት ጉዞ ባስከተለው ውድቀት የተነሳ፣ ስመ ጥር ወታደራዊ መኮንኖችን ያፈሩት እነዚያ አካዳሚዎች ዛሬ የሉም፡፡ በተለይ በ17ቱ የደርግ ዘመን እንደታየው የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ይዘት በዓይነትም በጥራትም ሲያሽቆለቁል ቆይቶ በኋላ፣ ለመበተን ቢበቃም ቀደምት መሠረቱ ለዛሬውም ሠራዊት ቢሆን እርሾ እንደሆነ አይጠረጠርም፡፡ አገሪቱ ቀደምት ጀግኖቿን ለመዘከር ባትታደልም ሰራዊቱን በመምራት፣ በማስተማርና በማዘመን ረገድ የተሳተፉ ወታደራዊ ልሂቃንን ግን ታሪክ ሲያስታውሳቸው ይኖራል፡፡

 

 

Read 2740 times Last modified on Saturday, 12 May 2012 10:36